Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ትልልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች የሚገኙበት የንግድ ጉባዔ ይጠበቃል

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሩብ ዓመት ጉዞና የውጭ ኩባንያዎች ምልመላ

  ‹‹ኮርፖሬት ካውንስል ኦን አፍሪካ›› የተሰኘውና ለትርፍ ያልተቋቋመው ተቋም ይፋ ባደረገው መረጀ መሠረት በመጪው ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደው ትልቅ የንግድ ጉባዔ የሁለቱን አገሮች ኢንቨስተሮችና ኩባንያዎች ያገናኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  በቅርቡ ይፋ እንደተደረገውና የአፍሪካ ኩባንያ ምክር ቤት ተቋም እንዳሰራጨው መረጃ ከሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚከፍቱት ይህ ፎረም፣ ትልልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቅ ትዕይንት ነው፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ሲካሄድ ቆይቶ በአዲስ አበባ አሥረኛውን ፎረም፣ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በሚካሄድበት ሳምንት የንግድ ጉባዔው እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ እስካለፈው ወር መጀመርያ ድረስ 30 ያህል ትልልቅ የአሜሪካና የአፍሪካ ኩባንያዎች ስፖንሰር እንደሚያደርጉት ቢገለጽም፣ ፎረሙ በክፍያ የሚካሄድ ነው፡፡ ቦይንግ፣ ማይክሮሶፍት፣ ፎርድ እስካሁን ስማቸው በስፖንሰርነት እየተጠቀሰ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ይገኙበታል፡፡  

  የአሜሪካና የአፍሪካ ንግድ ጉባዔው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች እንደሚገኙ ሲጠበቅ፣ አበዳሪ ባንኮች ብድር ለመስጠት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ይገመግማሉ፣ ብድር ያፀድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና አዳዲስ የንግድ ስምምነቶችም ይፋ እንደሚደረጉ ተስፋ ተጥሏል፡፡

  በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረው የሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ላይ ከዘረዘራቸው ተግባራት መካከል በተለይ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት መስክ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን ካሏቸው አገሮች መካከል ከአሜሪካ ጋር ስላለው ግንኙነት የጠቀሱት አለ፡፡

  በሁለቱ አገሮች መካከል ስምምነት ተደርጎባቸዋል ከተባሉት መካከል በሐምሌ ወር አዲስ አበባን ለሦስት ቀናት የጎበኙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና ልዑካኖቻቸው ጋር የተደረጉት ይታወሳሉ፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ እንደሚገልጹት፣ አቅምና ጥራት ያላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አሜሪካ ስለምትሰጠው ድጋፍ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ስለሚቋቋምበት መንገድ ንግግር መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሦስት ወራት ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

  ዶ/ር ቴድሮስ እንደጠቀሱት፣ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ትሆን ዘንድ አሜሪካ ልትሰጥ ስለምትችላቸው ድጋፎች ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይሁንና ስምምነቱ ምን እንደሆነ አልገለጹም፡፡ በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያ በተጓተተው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ወቅት እንደምንም የአገልግሎት ዘርፍን በተመለከተው ዋናው የድርድር ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

  በዚህ ሒደት ወቅት ለኢትዮጵያ መንግሥት ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎች እያነሱ ካሉት አገሮች መካከል አንዷ አሜሪካ ናት፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ሒደትን የሚመለከተው የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ድርድርና ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጠው ማብራሪያ መሠረት፣ አሜሪካን ጨምሮ ተደራዳሪ አገሮች መንግሥት አይነኬ ባደረጋቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ የባንክ፣ የቴሌኮምና የንግድ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የሚደረጉበትን አግባብ እየጠየቁ በመሆኑ መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ እንዲወስን ይጠበቃል ብሏል፡፡ ይሁንና ዶ/ር ቴድሮስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት የምትሰጠው ድጋፍ ስምምነት እንደተደረገበት ለፓርላማው ቢገልጹም፣ ድጋፉ ምን እንደሆነ ግን ሳይገልጹ አልፈውታል፡፡

  ከዚህ ባሻገር ግን በኢኮኖሚና በቢዝነስ ዲፕሎማሲ መስኮች ሚኒስቴራቸው በዚህ ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል የውጭ ኩባንያዎችንና ባለሀብቶችን በመመልመል ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሰባት የተመረጡ ትልልቅ ኩባንያዎች ቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉ ታቅዶ እንደነበር፣ ሆኖም እስካሁን በስም ያልገለጿቸው 13 ትልልቅ ኩባንያዎች የኢንስትመንት ጥናትና ጉብኝት እንዳደረጉ ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል፡፡ በመካከለኛና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ 148 የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጉብኝትና ጥናት እንዲያደርጉ ታቅዶ እንደነበርና 120ዎቹ መምጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡ 

  በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስክ ስለመከናወናቸው ከተጠቀሱት ውስጥ ከመደበኛ የፋይናንስ ምንጮች እንዲለቀቁ ቃል የተገቡትን ማስለቀቅ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ ምንጮችን ማፈላለግም የሩብ ዓመቱ ሥራዎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከ768 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ለማስለቀቅ ታቅዶ እንደነበር፣ ከዚህ ውስጥ 607.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መለቀቁን ዶ/ር ቴድሮስ ጠቅሰዋል፡፡ 

  ኢንቨስተሮችንና ኩባንያዎችን መልምሎ ማምጣቱ ሚኒስቴራቸው ከሚያከናወናቸው ትልልቅ ሥራዎች መካከል የሚመደብ መሆኑን ገልጸው፣ በቪዛ አሰጣጥ በኩል የሚታዩ አሳሳቢ ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ የቢዝነስ ቪዛ አሰጣጥ ላይ ያለውን መጓተት ለማስተካከል የሚመለከታቸው ተቋማት ሊያስተካክሉ እንደሚገባ መገምገሙን ዶ/ር ቴድሮስ ሳይገልጹ አላላፉም፡፡

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች