Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሥር ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች እየተጠበቁ ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ከአሜሪካ ሦስት ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል አንዱ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

  በሐዋሳ 300 ሔክታር መሬት ላይ ተገንብቶ በጥቂት ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር በሚጠበቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከሚጠበቁ አሥር ትልልቅ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራችና ገዥ የውጭ ኩባንያዎች ጋር መንግሥት ድርድር እያካሄደ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡

  ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀላል ኢንዱስትሪ መስክ የበላይ ለማድረግ ያለመው መንግሥት ለዚህ ህልሙ በጨርቃ ጨርቅና በስፌት ዘርፍ ለሚያያደርገው መስፋፋት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገቡት ውስጥ ከአሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከኢንዶኔዥያና ከሆንግ ኮንግ ከተውጣጡ አሥር ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎችን እንደመረጠ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  እነዚሁ ምንጮች እንዳብራሩት ከሆነ ከአሥሩ ውስጥ ሦስቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የእነ ቶሚ ሒልፊገርና ካልቪን ክሌን ብራንዶችን ጨምሮ የበርካታ ምርቶች ባለቤት የሆነው ፊሊፕስ-ቫን ሒውሰን (ፒቪኤች) ኮርፖሬሽን አንደኛው የአሜሪካ ኩባንያ ሲሆን፣ የማምረቻ ሼድ በሊዝ ገዝቶ ለመግባት ድርድር ላይ መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የህንዶቹ ሬይመንድ ግሩፕና አርቪንድ ኩባንያም ድርድር እያካሄዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቃና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፒቪኤች በተጨማሪ ራልፍ ላውረን (አርኤል) ኮርፖሬሽንና ቫኒቲ ፌር (ቪአር) ኮርፖሬሽኖች በአሜሪካ ትልልቅ ኩባንያዎች ከመሆናቸው በላይ፣ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ እንደ አቶ ፋሲል ማብራሪያ፣ ፒቪኤች ትልቁና ምናልባትም በአፍሪካ ጭምር የማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ በመክፈት ቀዳሚ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ኩባንያው በአብዛኛው ምርት በማስመረትና በመግዛት እንጂ በአምራችነት ብዙም ተሳትፎ ሲያደርግ እንደማይታወቅ አቶ ፋሲል ይገልጻሉ፡፡

  ይሁንና ፒቪኤች የመንግሥት ኃላፊዎችንና ማኅበሩን ማነጋገር ከጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ማስቆጠሩን አቶ ፋሲል ጠቅሰው፣ ኩባንያው ወደ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት አምራች ሆኖ እንዲሠማራ በማሳመን እንዲመጣ ትልቁን ሥራ የተወጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ እንደሆኑ መስክረውላቸዋል፡፡

  ምንጮች ከፒቪኤች በተጨማሪ አርኤልና ቪኤፍ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል ይመጣሉ ከተባሉት ውስጥ እንደሚካተቱ ቢገልጹም፣ አቶ ፋሲል ግን እነዚህ ኩባንያዎች በደንበኞቻቸው በኩል ከኢትዮጵያ የአልባሳት ምርቶችን ለመግዛት የሚመጡና በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲደረግ የሚገፋፉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

  ከፒቪኤች ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ኩባንያው ባለፈው ዓመት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት የቻለ ነው፡፡ ከካልቪን ክሌንና ከቶሚ ሒልፊገር በተጨማሪ፣  ቫን ሒውሰን፣ ኣሮው፣ ስፒዶ፣ ዋርነርስ ኤንድ ኦልጋ የተባሉትንና ሌሎችንም ብራንዶች በባለቤትነት የሚያስተዳድር ትልቅ የአሜሪካ ኩባንያ ነው፡፡

  117 ዓመታት ያስቆጠው ሌላው የአሜሪካ ኩባንያ ቫኒቲ ፌር በበኩሉ 12.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ራንግለርና ሊ የተባሉትን ታዋቂ የጅንስ አልባሳትና ሌሎችንም በባለቤትነት የሚያስተዳድር ኩባንያ ነው፡፡ የፖሎ ምርቶችን በባለቤትነት የያዘው ራልፍ ላውረንም በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በትልቁ ከሚጠበቁት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

  በሌላ በኩል ከሰባቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ የሆነውና በመንግሥት የሚገነባው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በፍጥነት ከተገነቡት መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ሐምሌ የመሠረት ድንጋይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀመጥ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት ዶ/ር አርከበ እንዳስታወቁት፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በታኅሳስ ወር መጨረሻ  እንደሚጠናቀቅ ይጠበቅ ነበር፡፡

  በ246 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ግንባታው እየተገባደደ የሚገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 37 የማምረቻ ሼዶች ይኖሩታል፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት የተገነባው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 250 ሚሊዮን ዶላር ከመፍጀቱም በላይ፣ ከስድስት ዓመት በላይ ከመፍጀቱም ባሻገር 20 ሼዶች ያሉት ነው፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች