የኢትዮጵያና የኖርዌይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት በሚሻሻልበት፣ ሴቶች የበለጠ የትምህርት ዕድል በሚያገኙበት እንዲሁም የሁለቱም አገሮች ትብብር ወደላቀ ደረጃ ከፍ በሚልበት መንገድ ላይ መከሩ፡፡
‹‹የኖርዌይና የኢትዮጵያ የጋራ የትምህርት ጉባኤ›› በሚል ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን በተካሄደው ፕሮግራም፣ ከሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡና በተለያዩ ምሁራን የተሠሩ የምርምር ውጤቶች ቀርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርትን ለማስፋፋት የኖርዌይ መንግሥትና የኖርዌይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ ጉባኤውም የሁለቱም አገሮችና የትምህርት ተቋሞቻቸው ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው ትብብራቸው ምን እንደሚመስልና ወደፊት በስፋትና በጥልቀት እንዴት መቀጠል እንደሚችል መክረዋል፡፡ እንዲሁም ጉባዔተኞች በቀረቡት ጥናትና ምርምሮች መሠረት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ይሻሻል ዘንድ የኖርዌይ መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በሚረዳበት መንገድ ላይም ተወያይተዋል፡፡
ጉባኤው በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድርያስ ጋአርደር የመክፈቻ ንግግር በይፋ የተከፈተ ነበር፡፡
አምባሳደር አንድርያስ በመክፈቻ ንግግራቸው ‹‹ጉባኤው የትምህርት ትብብሩ ምን እንደሚመስል የሚፈተሽበት ማዕቀፍ ይከፍታል›› ያሉ ሲሆን፣ ኖርዌይ በስፋትና በጥልቀት ትብብር ከምታደርግባቸው አራት የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎረቤት አገሮች የመጡ ስደተኞች ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርገው ጥረት፣ በኖርዌይ መንግሥት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑንም አክለዋል፡፡ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ዕድል ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ካባ በንግግራቸው፣ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር ወደ 36 ከፍ ማለቱና በቅርቡ 11 አዳዲስ እንደሚከፈቱ የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ መቐለ፣ ጅማ፣ አዲስ አበባና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች የኖርዌይ አዲሱ የትምህርት ኢንሼቲቭ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም አገሮች በቀጣይነት የትምህርት መስፋፋትና ጥራት ላይ በጥልቀት ለመተባበር የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት የፈረሙ ሲሆን፣ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ፣ በኢትዮጵያ ትምህርት በማዳረስና በማስፋፋት በኩል ከፍተኛ እመርታ ቢያሳይም፣ በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓትና የትምህርትን ጥራት በመጠበቅ ዙርያ የሚታዩ ያሉዋቸው አንዳንድ ችግሮችን ለመቅረፍ የኖርዌይ መንግሥትና ከፍተኛ የአገሪቱ የትምህርት ተቋማት ልምድና ዕውቀት መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የትምህርት ተቋማት ተቋማዊ አቅምና የምርምር ብቃት ከፍ ለማድረግ የኖርዌይ መንግሥት ድጋፍ የላቀ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የኖርዌይ መንግሥት ባለፈው ዓመት አዲስ ኢኒሼቲቭ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የትምህርት ተደራሽነትን፣ የትምህርት ጥራትን፤ ለሴቶች የተለየ የትምህርት ዕድል ማስገኘትና በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች የትምህርት የሚያገኙበት ላይ ያተኮረ እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡
በጉባኤው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ150 በላይ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የዓለም ባንክና የዩኤስኤአይዲ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ከሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርመር ጥናት የቀረቡ ሲሆን፣ ከመካከላቸው፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ይገኙባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን የተካሄደው ፕሮግራም የተዘጋጀው በስማርት ኤቨንትስ ነው፡፡