– ምርጫው ተቃውሞ ቀርቦበታል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመወከል ለፓን አፍሪካ ፓርላማ እንዲሳተፉ በአፈ ጉባዔው የቀረቡ አምስት አባላትን የያዘ ቡድን በሁለት የተቃውሞ ድምፅ ፀደቀ፡፡
በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት፣ ለእንደዚህ ዓይነት ፓርላሜንታዊ የዲፕሎማሲ መድረክ አባላትን በዕጩነት የሚያቀርቡት አፈ ጉባዔው ናቸው፡፡
በዚሁ መሠረት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የፓርላማውን ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በሰብሳቢነት፣ አቶ አፅብሃ አረጋዊ፣ አቶ ሆርዶፋ በቀለ፣ ወ/ሮ ሰሃርላ አብዱላሂና አቶ ተክሌ ተሰማን በአባልነት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) እና የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋብዴፓ) የሚወክሉ ሦስት የምክር ቤቱ አባላት ግን የአፈ ጉባዔውን ዕጩዎች አቀራረብ ተቃውመዋል፡፡
አፈ ጉባዔው ያቀረቧቸው አራት ዕጩዎች ብአዴንን፣ ሕወሓትን፣ ኦሕዴድንና ደቡብን የሚወክሉ ሲሆን፣ አንድ አባል ደግሞ ከሶሕዴፓ ተወክለዋል፡፡
ውክልናው አግባብነት የለውም ያሉት ሦስቱ የፓርላማው አባላት ከአጋር ፓርቲዎች አንድ ሰው ብቻ እንዴት ይወከላል ሲሉ ምክንያታቸውን አቅርበዋል፡፡ አጋር ፓርቲዎችን የሚወክሉት አምስት ክልሎች በመሆናቸው እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ አባላቱን የመረጡት ከየፓርቲዎቹ ተወካዮች ጋር ተወያይተው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለውክልናው የታጩት የፓርላማ አባላት የተመረጡት መሠረታዊ ፓርቲያቸው በሚወክለው ሕዝብ ብዛት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹የቁጥሩ ጉዳይ ጥሩ አይደለም፡፡ በቁጥር ቢሆን በዚህ ፓርላማ 187 መቀመጫ ያለው ኦሕዴድ ነው፡፡ ስለዚህ ከኦሕዴድ በየኮሚቴው የሚወከሉ አባላት ቁጥር ሊበዛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውስጣዊ ማንነታችንን ያፈርሰዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከእሳቸው ምላሽ በኋላ ድምፅ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ፣ በሁለት ተቃውሞ አባላቱ ፓርላማውን ወክለው በፓን አፍሪካ ፓርላማ እንዲሳተፉ ፀድቋል፡፡