Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አያት አክሲዮን ማኅበርና ዋና ሥራ አስኪያጁ ከአራጣ ማበደር ክስ ነፃ ሆኑ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – 17 ክሶች ውድቅ በመደረጋቸው ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳም ይሰረዛል

  በሪል ስቴት ልማት ፈር ቀዳጅ የሆነው አያት አክሲዮን ማኅበርና የአክሲዮኑ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑት አቶ አያሌው ተሰማ፣ ተመሥርቶባቸው ከነበረው አራጣ የማበደር ወንጀል ክስ ጥር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በነፃ ተሰናበቱ፡፡

  የአክሲዮን ትርፍ በመውሰዳቸው ብቻ ብድር ሳይኖር አራጣ አበድረዋል ሊባሉ እንደማይገባ፣ ሌሎች ባለድርሻዎችም ድርሻቸውን ወስደው ሳለ አራጣ አበድረዋል መባል እንደማይችል፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡

  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ በነበሩትና በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው አቶ መርክነህ ዓለማየሁና ባልደረቦቻቸው 23 ክሶች ተመሥርቶባቸው ላለፉት ስድስት ዓመታት በእስር ላይ የከረሙት አቶ አያሌው ተሰማ፣ ዶ/ር መሐሪ መኮንና አቶ ጌታቸው አጎናፍር መሆናቸውን መዘገባቸውን ይታወሳል፡፡

  የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ በአያት አክሲዮን ማኅበር፣ በአቶ አያሌው፣ በዶ/ር መሐሪና በአቶ ጌታቸው ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት መሥርቶት የነበረው ክስ ቤት በዱቤ በመሸጥ የባንክ ሥራ ተክቶ መሥራት፣ ቤቱን በዱቤ ሲሸጡ ቫት ከራሳቸው ላለመክፈል ለገዥ ማስተላለፍ፣ ሐሰተኛ ሰነድ ማቅረብ፣ ያለቫት ደረሰኝ ግብይት መፈጸም፣ ወጪን በማናር የገቢ ግብር መሰወር፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ለሦስተኛ አካል አሳልፎ መስጠት፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የውጭ አገር ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ይዞ መገኘት የሚሉ ዋና ዋናዎቹ ክሶች ነበሩ፡፡

  ክሱን የመረመረው የሥር ፍርድ ቤት ማኅበሩንና ግለሰቦቹን በ21 ክሶች ጥፋተኛ በማለት አቶ አያሌውን በ12 ዓመታት ጽኑ እስራትና ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ፣ ዶ/ር መሐሪን በ12 ዓመታት ጽኑ እስራትና 436 ሺሕ ብር፣ አቶ ጌታቸውን በአሥር ዓመታት ጽኑ እስራትና ከ400 ሺሕ ብር በላይ ቅጣት ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ወስኖባቸው ነበር፡፡ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያሉት እነ አያት አክሲዮን ማኅበር ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየ የይግባኝ አቤቱታ ጥር 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ አግኝተዋል፡፡

  ማኅበሩና አቶ አያሌው (ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው) የባንክ ሥራን ተክቶ በመሥራት ወንጀል በሥር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለበት ውሳኔ (አራት ተመሳሳይ ክሶች) ተሽሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዱቤ ሽያጭ በየትኛውም ዓለም የሚደረግ በመሆኑ የባንክ ሥራን ተክቶ ሠርቷል ሊያስብል እንደማይቻልና ወንጀልም አለመሆኑን አስረድቷል፡፡

  ማኅበሩ በዱቤ ቤት ሲሸጥ ቫቱን ከራሱ መክፈል ሲገባው ለገዥዎች ማስተላለፉ ጥፋት መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም አፅንቶታል፡፡ አቶ አያሌውም የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው በእሳቸውም ላይ ፀንቷል፡፡ ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ ተነጣጥለው የቀረቡ ክሶች ተጣምረው ታይተዋል፡፡

  የተጭበረበረ ሐሰተኛ ሰነድ ማቅረብ ወንጀል ዓቃቤ ሕግ የከሰሰ ቢሆንም፣ የሰነድም ሆነ የሰው ምስክር ማቅረብ ባለመቻሉ ክሱ ውድቅ መሆኑንና ከዚሁ ክስ ጋር ቀርበው የነበሩ ሁለት ክሶች ውድቅ መደረጋቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

  አያት አክሲዮን ማኅበር ቤት ያለቫት ደረሰኝ መሸጡ ተገልጾ የወንጀል ክስ የቀረበበት ቢሆንም፣ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

  አያት አክሲዮን ማኅበር (በ14ኛ፣ 15ኛ እና 17ኛ ክሶች) ወጪን በማናር ገቢን ማሳነስ ወንጀል በቀረበበት ክስ የሥር ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ማለቱ ትክክል መሆኑን ጠቁሞ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም አፅድቆታል፡፡

  ሐሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ ሒሳብ እንደሚያሠሩ የተገለጸው የወንጀል ክስን በሚመለከት (17ኛ፣18ኛ እና 19ኛ ክሶች)፣ ማኅበሩ ያቀረበው ሐሰተኛ ሰነድ እንደሌለ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎችን ለሦስተኛ ሰው ማከራየት ቀድሞውኑ ወንጀል አለመሆኑን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ገልጾ፣ በአስተዳደር የሚያልቅ በመሆኑ ቀረጥና ታክሱ ታስቦ 50 በመቶውን እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡

  ወጪ በማናርና ሕገወጥ ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል መጠቀም ወንጀል መጠየቅ ያለበት አያት እንጂ አቶ አያሌው አለመሆናቸውን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ገልጾ፣ የሥር ፍርድ ቤት አቶ አያሌውን ጥፋተኛ ያላቸው በስህተት በመሆኑ ነፃ በማድረግ ድርጅቱን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ የአቶ አያሌው ቤት ሲበረበር የተገኘ 20 ሺሕ ዶላር ሕገወጥ ገንዘብ መሆኑን ገልጾ ዓቃቤ ሕግ ክስ ቢመሠርትም፣ የሥር ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን ይግባኝ ሰሚውም አረጋግጧል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አቶ አያሌው ለሕክምና ከብሔራዊ ባንክ አስፈቅደው በመውሰድ ከሕክምና ሲመለሉ የተረፋቸውን ማስመዝገባቸው ሕገወጥ ሊያሰኛቸው እንደማይገባ በመግለጽ ነው፡፡

  በአጠቃላይ አያት አክሲዮን ማኅበር በተመሠረተበት ክስ በሥር ፍርድ ቤት ተጥሎበት የነበረው ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ መቀጮ ገንዘብ ቀሪ ተደርጎለታል፡፡ ጥፋተኛ በተባለባቸው ሦስት ክሶች በእያንዳንዳቸው 500,000 ብር በድምሩ 1.5 ሚሊዮን  ብር እንዲከፈል ተወስኖበታል፡፡

  አቶ አያሌው የገንዘብ ቅጣቱ ቀርቶላቸው በስምንት ዓመታት እስራት፣ አቶ ጌታቸውም የገንዘብ ቅጣቱ ቀርቶላቸው በሰባት ዓመታት እስራትና ዶ/ር መሐሪ በአምስት ዓመታት እስራት እንዲቀጡና የገንዘብ ቅጣቱ እንዲቀርላቸው ዳኛ በላቸው አንሺሶና ዳኛ ዳኜ መላኩ የተሰየሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ሦስቱም ፍርደኞች ለስድስት ዓመታት በእስር መቆየታቸው ታውቋል፡፡ በተሰጠው ውሳኔ የተከሳሾቹ ጠበቆች ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ አቶ ታምሩ ወንድም አገኘሁና አቶ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋዬ ደስተኛ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች