Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ከፖለቲካዊ ውይይቶች መሻገር ያልቻለው ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ መግባባት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. የሸራተን ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በምሁሩን፣ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ በአገር ሽማግሌዎችና በተለያዩ ግለሰቦች ተሞልቷል፡፡ በዕለቱ ያተሰበሰቡት እነዚህ ታዳሚዎች የሰባሰባቸው ዓላማ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኘው ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከልና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) በጋራ ባዘጋጁት ‹‹ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነት›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሕዝባዊ የምክክር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ነው፡፡

  የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲሆኑ፣ የእሳቸውን መክፈቻ ንግግር ተከትሎም ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይት ቀርበው ነበር፡፡

  በዕለቱ የመወያያ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ደግሞ ታዋቂው የፌዴራሊዝም ምሁር አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል ኃላፊ ዘመላክ አይተነው (ዶ/ር) ናቸው፡፡

  የሁለቱን ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፍ ተከትሎ ከተወያዮች የተለያዩ ሐሳብ የተሰነዘሩ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ያተኮሩት መድረኩ ከሀልዮታዊ ትንታኔ ይልቅ፣ መሠረታዊ የአገሪቱን ቅራኔዎች ከሕገ መንግሥቱ አንፃር በመገምገም አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በቅጡ የሚያመላክት ቢሆን ምርጫቸው እንደነበር ነው፡፡

  የውይይቱ ዓላማን በተመለከተ የሕግና ፍትሕ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ደግፌ ቡላ አጠር ያለ ገለጻ አድርገው ነበር፡፡ እንደ አቶ ደግፌ ገለጻ ከሆነ የምክክር መድረኩ ዓላማ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ፣ ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነትን አስተሳስሮ መገንባት በሚቻልበት መንገዶች ውይይት ማድረግ ነው፡፡

  ‹‹በፌዴራል ሥርዓቱ ግንባታ ሒደት እስካሁን ድረስ የተገኙ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ልንደርስበት ከምናስበውና ከሚገባን ግቦቻችን አንፃር ስንመለከት፣ ገና ያልተሻገርናቸውና ያላከናወንናቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ካለው ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ በሚደረገው ሽግግር ልናራግፋቸው ሲገቡ፣ አሁንም የተሸከምናቸው በርካታ አሉታዊ ጉዳዮች አሉ፤›› በማለት፣ እንዲህ ያሉ መድረኮች የሚታዩትን አሉታዊ ጉዳዮች ከመጠቆምና ከመቅረፍ አንፃር ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት በመሆን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  የአቶ ደግፌ ቡላን አጠር ያለ የፕሮግራሙን ዓላማ ከተመለከተው ገለጻ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የአገር ግንባታ ሒደት በአንድ ወቅት ተጀምሮ በሌላ ወቅት ደግሞ የሚቋረጥ ሳይሆን፣ ዘለዓለማዊ ጥረት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራንን በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡

  የአገር ግንባታ ሥራ በርካታ ተግባራትን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀላል ወደ ከባድና ውስብስብ ምዕራፍ የሚሸጋገር የዕድሜ ልክ ተግባር እንደሆነም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹በአንድ ወቅት ከባድና ውስብሰብ የነበረው ሥራ ቀጣዩ ምዕራፍ በተሻለ ሁኔታ በሚሳካበት ጊዜ ተመልሶ ሲታይ ቀላል እየመሰለ የሚታይ፣ ቀጣዩ ምዕራፍ ከተዳናቀፈ ደግሞ የመጀመርው ምዕራፍ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር በዘመን መነጽር ለመመልከት ዕድል የሚሰጥ ነው፤›› በማለት፣ ውስብስቡን የአገር ግንባታ ሒደት ለማስቃኘት ሙከራ አድርገዋል፡፡

  ‹‹የአገር ግንባታ ሥራ መቼም ቢሆን የማይቋጭ የዘለዓለም ተግባር ነው ከሚባልበት መነሻ አንዱ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚከናወንና የአንዱ ትውልድ በጎም ሆነ መጥፎ ሥራ ለቀጣዩ ትውልድ በመነሻነት ይወሰድ እንደሆነ እንጂ፣ ያለቀለት ስኬት ተደርጎ የመወሰድ ዕድሉ ሙሉ መሆን አይችልም፤›› ሲሉ፣ የአገር ግንባታ ሒደት የበርካታ ትውልዶች ቅብብሎሽና ጥረት ውጤት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  ይህ አገርን የመገንባት ቅብብሎሽ በአንድ ወቅት የማይቆምና በመሠረቱ ከሰው ልጅ ድንበር የለሽ ፍላጎና ጥማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ አዲስ ትውልድ መፍጠር የአዲስ ጥያቄና ፍላጎት መፈጠር እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ማኅበረሰቡ በዘመኑ ዕይታ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ደርሷል ቢባል እንኳ አዲሱ ትውልድ አዳዲስ ነገሮችን መፈለጉን አያቋርጥም፡፡ ይህም የሰው ልጅ እስካለ ድረስ የሚቀጥል ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ሕግ ነው፤›› በማለት፣ የኢትዮጵያም የአገር ግንባታ ሥራና ሒደት በዚህ ሒደት መቃኘት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  የእሳቸውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የውይይት ጽሑፍ ያቀረቡት ዘመላክ አይተነው (ዶ/ር)፣ ከፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ኅብረት ያለፈ ብሔራዊ አንድነት መገንባት በሚቻልባቸውና በሚያስፈልጉባቸው መንገዶች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

  የመወያያ ጽሑን ባቀረቡበት ወቅት የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት በተመለከተ የሚነሱ ተፃራሪ ሐሳቦችን በመቃኘት ጀምረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራል ሥርዓቱ በአንድ ወገን የአንድነት ዋልታና ማገር ነው የሚሉ ወገኖችን ሐተታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ አገሪቱን የሚበታትንና ለአንድነት የቆመ ሳይሆን አንድነት ላይ የቆመ ነው የሚሉ ሐሳቦች እንደሚታዩ በመጠቆም ነው፡፡

  የፌዴራል ሥርዓቱን የሚደግፉ ሰዎች ሥርዓቱን እስከ ዛሬ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በባህልና በማኅበራዊ ጉዳዮች ተገልለው የቆዩ ብሔሮችን አቅፏል፣ መገለላቸውንም አስቁሟል፡፡ ሕዝቦች የሚወከሉባቸው ምክር ቤቶችና በፌዴራል በክልልና በአካባቢ ደረጃ በመመሥረት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎአቸውን ለማጠናከር አስችሏል ብለው እንደሚከራከሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብሔሮች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩባቸው የክልልና የአካባቢ አስተዳደሮችን ለመመሥረት፣ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን የሚያረጋግጡበትን፣ እንዲሁም ቋንቋና ባህላቸውን የሚያሳድጉበትን መንገድ እንደከተፈ ከመከራከር ባለፈ ሥርዓቱ ይህን በማድረጉ በራሱ በሕዝቦች መካከል ያለውን ብሔራዊ አንድነት እንዳጠናከረው፣ በመሆኑም ብሔራዊ አንድነት መገንባት የሚለው ላይ መነጋገር አያስፈልገንም በማለት እንደሚከራከሩ አውስተዋል፡፡

  ከዚህ ሐሳብ በተፃራሪ የተሠለፉት ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ ሰዎች ካላቸው ብዙ ማንነቶች መካከል አንዱን የብሔር ማንነታቸውን መርጦ ሕገ መንግሥታዊ ሹመት መስጠቱ፣ እንደ ትልቅ ችግር እንደሚመለከቱት ጠቅሰዋል፡፡

  የፌዴራል ሥርዓቱ አቀራረፅም እንደ አንዱና ትልቁ እንከን አድርገው እንደሚወስዱት በማውሳት፣ ‹‹አንድ ክልል ለአንድ ብሔር የሚለው መርህ ሙሉ ለሙሉ ባይተገበርም የፌዴራል ሥርዓቱ የቆመበት በስፋት፣ በሕዝብ ብዛት፣ በተፈጥሮ ፀጋ በእጅጉ የተለያዩ ክልሎችን በመፍጠር ብሔራዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ ጥሎታል በማለት ይተቹታል፤›› በማለት የተቃርኖውን ፅንፍ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

  ከዚህ አንፃር ከፌዴራል ሥርዓቱ አድናቂዎች በተቃራኒ፣ ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱ የብሔራዊ አንድነትን ከመጠበቅ አንፃር መሠረታዊ የአቀራረፅ ችግር ስላለው፣ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ከሥር ከመሠረቱ መጀመር አለበት ይላሉ፤›› በማለት፣ ከአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ፣ እንዲሁም ብሔራዊ ማንነትን ከመገንባት አንፃር ያሉትን ሁለት ተገዳዳሪ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡

  እነዚህ ሁለት ተገዳዳሪ ሐሳቦች እንዳሉ አውስተው በእርሳቸው አተያይ ግን ሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ለብሔራዊ አንድነት ግንባታ ቦታ አልሰጠም የሚለው እንደማያስኬድ፣ የሕገ መንግሥቱን ሐረጎች በመምዘዝ ተከራክረዋል፡፡

  የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ፍላጎት እንዳለ እንደሚጠቀስ ገልጸው፣ ‹‹አንድ ፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት ጋር መገናኘቱ ግልጽ ነው፤›› በማለት፣  የሕገ መንግሥቱ ሐረጎች ለብሔራዊ አንድነት ግንባታም ሥፍራ እንዳላቸው ይሞግታሉ፡፡  

  ከዚህ በተጨማሪም ስለብሔራዊ መዝሙር፣ እንዲሁም ስለሰንደቅ ዓላማው የሚጠቅሰውን አንቀጽ በመጥቀስ ሕገ መንግሥቱ ብሔራዊ አንድነትን ከመገንባት አኳያ ያለውን አተያይ አብራርተዋል፡፡

  እነዚህን ተፃራሪ ሐሳቦች ለማስታረቅና አገራዊ አንድነትን ለመገንባት ይቻል ዘንድ መልካም ነው ያሉትን የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ‹‹ያለፉ ታሪካችን ላይ መገንባት፣ እንዲሁም ሁለትና ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን የሚናገር ትውልድና ኅብረተሰብ መፍጠር፤›› የሚሉት ናቸው፡፡

  ሌላው ጽሑፍ አቅራቢ አሰፋ ፍስሐ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለፌዴራል መንግሥትና ለክልል በተሰጡ ሥልጣኖች ላይ በአፈጻጸም ደረጃ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የመጡትን ችግሮች አብራርተዋል፡፡

  የፌዴራል መንግሥቱ በሕገ መንግሥት የተሰጡትን ሥልጣኖች በሚያስፈጽምበት ጊዜ አንድነቱን አብሮ ስለሚያራምድ፣ በዚህ ሒደት የፌዴራል መንግሥት የተሰጡትን ሥልጣኖች በአገሪቱ በጠቅላላ የሚያስፈጽምበት መዋቅር ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

  ‹‹እስካሁን ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች ልዩነት እንዳለ ሆኖ በፓርቲው ሥርዓት ይፈጸም የነበረ ነገር ነው እንጂ፣ ተቋማዊ ይዘት ያለው ዓይነት ነገር አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥት የክልሎችን ሥልጣን መውሰድ የለበትም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ስለማይፈቅድ የራሱን ሥልጣን ግን በክልሎች ደረጃ ማስፈጸም የሚችልበት ሙሉ መዋቅር ሊኖረው እንደሚገባ፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የክልሎችን ተቋማትን፣ ክልሎችም የፌዴራል ተቋማትን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው አብሮ ማሰብ ያስፈልጋል፤›› በማለት፣ የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት የፌዴራል ሥርዓቱን ከማስቀጠል አንፃር እጅግ ወሳኝ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  ከዚህም አንፃር የትምህርት ፖሊሲ፣ ሚዲያ፣ የባህል ፖሊሲ፣ ታሪክ፣ የቋንቋ ፖሊሲ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚየም፣ ጀግኖችን፣ የመንገድ ስያሜዎችን፣ ወዘተ በጋራ የተካበቱ መስተጋብሮችና እሴቶችን ለማራመድ መጠቀም የግድ እንደሚል አሳስበዋል፡፡

  ከሁለቱ ምሁራን ጽሑፍ ቀጥሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ ጽሑፉ የአገሪቱን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ቢሆን እንደሚመርጡ ያመላከቱት በርከት ያሉ ነበሩ፡፡

  ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ የሺዋስ አሰፋ አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ቁስልን ፕላስተር መሸፈን አያድነውም፡፡ ይደብቀዋል እንጂ፡፡ ከመድረኩ የተነሱት ነገሮች እንደዚያ ስለመሰሉኝ ነው፡፡ በደንብ ችግሩን ፍርጥ አድርጎ ወደ መፍትሔ መሄድ የሚሻል ይመስለኛል፤›› በማለት፣ ከመድረኩ የቀረቡት ጽሑፎች በጎ ጎን ቢኖራቸውም አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በግልጽ እንደማያመላክቱ ገልጸዋል፡፡  

  ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹አገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ውስጥ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ግን መጀመርያ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ መግባባት ምን ላይ ነው?›› በማለት ጠይቀው፣ ‹‹በብሔራዊ መዝሙሩና በሰንደቅ ዓላማው ላይ እኮ መግባባት የለንም፡፡ በሕገ መንግሥቱም እንዲሁ፤›› በማለት፣ ለአገራዊ መግባባት ግብዓት ይሆናሉ ተብለው የተጠቀሱት ነገሮች ራሳቸው የልዩነት ምንጭ ሆነው እንዴት ስለብሔራዊ አንድነት እናወራለን በማለት በመሞገት፣ ‹‹የችግሮችን መነሻ እየዘለልናቸው አንሂድ፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

  በተመሳሳይ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የአቶ ይልቃልንም ሆነ የሌሎች ግለሰቦችን ሐሳብ እንደሚጋሩ በመግለጽ፣ ‹‹የዛሬው ውይይት ትንሽ ከፍ ቢል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መተንተን እንችላለን፣ መነጋገርም እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ የደረስንበትን ደረጃ አንስተን ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ደግሞ መግፋት አለብን፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡

  አያይዘውም፣ ‹‹የፌዴራል አደረጃጀቱ ድክመቱና ጥንካሬው እንዳለ ሆኖ ትልቁና ወደ ብዙ ችግር የመራን ዴሞክራሲ መገንባት አለመቻላችን ነው፡፡ ዴሞክራሲ መገንባት ስላልቻልን የሕግ አስፈጻሚ፣ የሕግ አውጪና የሕግ ተርጓሚ አካላትን የሥራ ሚናቸውን ለይተው አንዱ አንዱን እየተቆጣጠሩ መጓዝ ስላላቻልን፣ ትልቁ የፌዴራል ሥርዓታችን ላይ የመጣው ችግር ከዚህ የመነጨ ነው የሚለውን እንሰማለን ብዬ አስቤ ነበር፤›› በማለት፣ ያሰቡትና ከመድረክ የሰሙት እንደተለያየባቸው አውስተዋል፡፡

  በመጨረሻም በዕለቱ የቀረቡትን ሐሳቦች ወደፊት ለሚዘጋጁ የፖሊሲ ሰነዶች እንደ ግብዓት እንደሚወስዷቸው አቶ ደግፌ ገልጸው ውይይቱ መቋጫውን አግኝቷል፡፡ 

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -