[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ የቀጠሩት ደላላ ስላረፈደባቸው ደወሉለት]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የት ደርሰሃል?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ታስሬያለሁ፡፡
- ማን አሰረህ?
- ማለቴ መንገዱ ተዘጋግቶ አንድ ቦታ ታስሬያለሁ፡፡
- ለምንድን ነው መንገድ የተዘጋው?
- ስብሰባ አለ ነው የሚሉት፡፡
- የምን ስብሰባ?
- የአፍሪካ ኅብረት ነው ምናምን አሉ፡፡
- ታዲያ ሌላ አማራጭ መንገድ አትጠቀምም?
- ወይ አማራጭ መንገድ?
- ምነው?
- ሁሉም መንገድ ተዘጋግቷል ስልዎት፡፡
- ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ልበል?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ምንም መንገድ የለም ትላለህ?
- የለማ ታዲያ ምን ላድርግ?
- ለዚህ እኮ ነው ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ያልኩት፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰፈር ውስጥ ሳይቀረን አይደል እንዴ መንገድ የሠራነው?
- ምን አሉኝ?
- እንደ ሠንሠለት የተያያዘ መንገድ አይደል እንዴ የሠራነው፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና አልደርስም እያልከኝ ነው?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ዓይነት ጣጣ ነው?
- ለምንድን ነበር የፈለጉኝ?
- ለጥብቅ ጉዳይ ነዋ፡፡
- በስልክ አይነግሩኝም?
- በስልክ የሚነገር አይደለም፡፡
- ለዛሬ ቢነግሩኝም ግን ችግር የለውም፡፡
- ለምንድን ነው ችግር የሌለው?
- ያው ቢግ ብራዘሮች በከተማዋ ትልቅ ስብሰባ ስላለ በዛ ስለሚጠመዱ እኛ ትዝ አንላቸውም ብዬ ነው፡፡
- ፈልጌ ነበር፡፡
- ምንድን ነው የፈለጉት?
- ዶላር ነዋ፡፡
- ይጠይቁዋ ታዲያ?
- የት ነው የምጠይቀው?
- ባንክ ነዋ፡፡
- ቀልዱን ለምን አትተውም?
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን እኮ ቅጥል ነው ያደረጋችሁን፡፡
- ለምንድን ነው የተቃጠላችሁት?
- በቃ ዶላር ሰውን አንበሽብሻችሁት እኛ ጋ እኮ ወደቀ፡፡
- ያጋጥማል እንግዲህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ክፉኛ እኮ ነው የከሰርኩት፡፡
- ስንት ከሰርክ?
- ኧረ አልጠራው ቁጥሩን፡፡
- ለምን?
- ስጠራው ያመኛል፡፡
- አስፕሪን መዋጥ ነዋ፡፡
- አስፕሪን የሚያሽለው ቁጥር አይደለም፡፡
- ለማንኛውም በአስቸኳይ ፈልግልኝ፡፡
- ምን ያህል?
- የቻልከውን ያህል፡፡
- መቼም እኔ ለእርስዎ የማልሆነው ነገር የለም?
- እኔስ ለአንተ የማልሆነው ምን አለ?
- ድር ቢያብር …
- ዶላር ያስር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- እኔ የምልሽ?
- ምንድን ነው?
- የአንቺ ቢዝነሶች መቼ ነው የሚያተርፉት?
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- ባለፈው ማተሚያ ቤት ክፈትልኝ አልሽ ከፈትኩልሽ፡፡
- እናሳ?
- ከዛም በኋላ ሞባይል ቤት አልሽ እሱም ተከፈተ፡፡
- ልክ ነው፡፡
- ትርፍ ግን ሲያመጡ አላይም፡፡
- እንዴት ማለት?
- ቢያተርፉ ኖሮማ እስኪብርቶ እንኳን ትገዥልኝ ነበር፡፡
- እኔ እኮ ከእስኪብርቶ ፋብሪካው ይሻላል ብዬ ነው፡፡
- የምን ፋብሪካ?
- የእስኪብርቶ ፋብሪካ ነዋ፡፡
- ትቀልጃለሽ?
- የምን ቀልድ ነው፤ መንግሥት ራሱ ወደ ኢንዱስትሪ ግቡ እያለ አይደል?
- እሺ የእኛ የኢኮኖሚ ተንታኝ፡፡
- ተሳሳትኩ እንዴ?
- ስሚ መቼም በከፈትኩልሽ ቢዝነሶች ከብዙ ሰዎች ጋር ትገናኛለሽ ብዬ አስባለሁ?
- አዎን ምነው?
- እስኪ አፈላልጊልኝ፡፡
- ምንድን ነው የማፈላልግልህ?
- ዶላር ነዋ፡፡
- ምን ያህል?
- ቁጥሩን ቴክስት አደርግልሻለሁ፡፡
- ዶላር ስትል እኔንም አስታወስከኝ፡፡
- ምንድን ነው ያስታወስኩሽ?
- እኔም እፈልጋለሁ፡፡
- ምን?
- ዶላር ነዋ፡፡
- ለምን?
- አሜሪካ ያለችው ልጃችን ምርቃት እኮ ደርሷል፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ሲሆን አንተም መምጣት አለብህ፡፡
- አገሪቷን ለማን ትቼ?
- ስለዚህ እኔ ከእህቴ ጋር እሄዳለሁ፡፡
- ስለዚህ?
- ያው ለሁለታችንም የሚበቃ ዶላር ፈልግልና፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ከዛም ልጅህን ትንሽ ማዝናናት አለብኝ፡፡
- ምን ዓይነት ነገር ነው?
- እንድታስብበት ብዬ ነው፡፡
- ምኑን?
- ዶላሩን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደወለላቸው]
- ሄሎ!
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- የተበሳጩ ይመስላሉ፡፡
- ምን ባክህ አስቸጋሪ ሆነ እኮ?
- ምኑ?
- ዶላር ማግኘት፡፡
- ይኸው ሰሞኑን እንዳንበሻበሻችሁት ሰምቼ አይደል እንዴ!
- እኛ አልተንበሻበሽንማ፡፡
- ለራስዎት ነው እንዴ የፈለጉት?
- አዎን፡፡
- ለምን አልክልዎትም እኔ ታዲያ?
- አንተ ብትልክልኝም እዚህ የሚደርሰኝ በብር ነው፡፡
- እሱስ ልክ ነው፡፡
- ሲቀጥል የምፈልገው መጠን ደግሞ አንተ የምትችለው አይደለም፡፡
- ይኼን ያህል?
- አገሪቷ እኮ አድጋለች፡፡
- እርስዎም አድገዋል እንጂ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- መቼም የግል ሚዲያ ትከታተላለህ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎም ቢከታተሉ ጥሩ ነው፡፡
- አንተን የቀጠርኩህ ተከታትለህ ሪፖርት እንድታደርግ መስሎኝ?
- አይ እንዲሁ ነገሩን ነው፡፡
- ለመሆኑ ሰው ዶላር ከየት ነው የሚያገኘው?
- ያው ከባንክ ነዋ፡፡
- ከዚያ ሌላ?
- ከብላክ ማርኬት ነዋ፡፡
- ከእሱ ሌላ?
- ከሰሞኑ ስብሰባ ነዋ፡፡
- ቀልዱን ተው እስቲ፡፡
- ማለቴ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ከሚመጡት ተሰብሳቢዎች ማለቴ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ያው ተሳታፊዎቹ ዶላር ይዘው ስለሚመጡ ከእነሱ ሊገኝ ይችላል፡፡
- የት ነው የሚገኙት እነሱ?
- ሆቴላቸው ነዋ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሆቴል ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ባክህ?
- ዛሬ ከየት ተገኙ?
- ሁሌም እኔ ነኝ እንጂ አንተ መቼ ትፈልገኛለህ?
- አይ ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ጉዳይ ሲኖርዎት ነው የሚፈልጉኝ፡፡
- እ…
- ምን ልታዘዝ ታዲያ?
- ሥራ እንዴት ነው?
- ያው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡
- የሆቴል ሥራውን ማለቴ ነው፡፡
- ምንም አይል፡፡
- ሰሞኑን እንግዶቹ እየመጡ ነው?
- አዎ ሰሞኑን እንኳን ቢዚ ሆነናል፡፡
- አንድ ነገር ላስቸግርህ ነበር፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ለአክስቴ ልጅ እናንተ ሪሰፕሽን ጋ ትንሽ ሱቅ ፈልጌ ነበር፡፡
- የምን ሱቅ?
- የዶላር መመንዘሪያ፡፡
- እሱ ሥራ እኮ የመንግሥት ፈቃድ ያለው ባንክ ብቻ ነው የሚሠራው፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
- እንዴት አላስብ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ሁሉን ነገር እጨርሰዋለሁ፡፡
- ይጠንቀቁ ግን፡፡
- ምኑን?
- እጨርሳለሁ ብለው እንዳይጨረሱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- እኔ የምልህ?
- ምንድን ነው?
- ዶላሩን የምትፈልገው ለምንድን ነው?
- ለጨረታ፡፡
- የምን ጨረታ?
- ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ልሠራው ያሰብኩት ሥራ አለ፡፡
- ሥራ ቀየርክ እንዴ?
- የምን ሥራ?
- ሚኒስትርነትህን፡፡
- ወደ ምንድን ነው የምቀይረው?
- ወደ ኢንቨስተርነት፡፡
- ምን?
- ጡረታዬ እየደረሰ እንደሆነ አትርሺ፡፡
- ለመሆኑ ተሳካልህ?
- ምኑ?
- የዶላሩ ፍለጋ፡፡
- ኧረ ተይኝ እስቲ፡፡
- ምነው?
- ምንም የሚያበረታታ ነገር አይደለም፡፡
- ለመሆኑ የት ነው የፈለግከው?
- ያልፈለግኩበትን ጠይቂኝ፡፡
- እኮ የት የት ፈልገሃል?
- ከአባ ኮራን ሰፈር …
- እ…
- እስከ አባ ኮራፕት ሰፈር!