Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደ መንግሥት ተሿሚዎችና የፓርላማ አባላት ጥቅማቸውን...

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደ መንግሥት ተሿሚዎችና የፓርላማ አባላት ጥቅማቸውን የሚያስከብር ማሻሻያ ቀረበ

  ቀን:

  የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የፓርላማ አባላትና ዳኞች ብቻ ከኃላፊነት ሲነሱ ከጉስቁልና የራቀ ኑሮ እንዲኖሩና ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከለላ በሚሰጠው አዋጅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲካተቱ የሚያደርግ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

  አዋጅ ቁጥር 653/2001 ጥቅማ ጥቅሙ እንዲሰጥ የሚፈቅደው ከኃላፊነት ለተነሱ የአገር መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች ብቻ ነው፡፡

  የምክር ቤት አባላት የዚህ ጥቅማ ጥቅም መብት ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ግን በአዋጁ ላይ አልተካተቱም ነበር፡፡ ‹‹የምክር ቤት አባላት የሚለው የአዋጅ ትርጓሜ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚነት በመሥራት ላይ የነበሩትን የምክር ቤት አባላት ባለማካተቱ የአፈጻጸም ችግር አጋጥሟል፤›› በማለት አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡

  እስካሁን የሚሠራባቸው ሕጐችና ተግባራዊ አፈጻጸሞች የሚያሳዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ እንዲሁም የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው በቋሚነት የሚሠሩ አባላት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንደሚያገኙ በየራሳቸው የውስጥ ደንቦችና መመርያዎች መቀመጡን የማሻሻያው ማብራሪያ ይጠቁማል፡፡

  የሁለቱም ምክር ቤት አባላት የደመወዝና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች ክፍያ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት እኩልና ተመሳሳይ መሆናቸውን ደግሞ፣ የቀድሞው ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በጥር ወር 2003 ዓ.ም. ለመንግሥት ተሿሚዎች ያደረገው 35 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ የምክር ቤት አባላትንም የሚያካትት መሆኑ በማብራሪያው እንደ ምክንያትነት ቀርቧል፡፡ በመሆኑም ከሦስተኛው ዙር የምርጫ ዘመን ጀምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚ አባልነት የሠሩ የምክር ቤት አባላት የጥቅማ ጥቅሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማሻሻያውን አቅርቧል፡፡

  ፓርላማው በተላከለት አዋጅ ላይ ሰሞኑን ይወያያል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በምክር ቤቱ የሚፀድቅ ከሆነም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ በቋሚ አባልነት የሚሠሩ አባላት ኃላፊነታቸውን በሚያጠናቅቁበት ወቅት የጥቅማ ጥቅሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች አዋጁ ከአምስት ዓመት በላይ ወደኋላ ሄዶ እንዲሠራ በረቂቅ ደረጃ የቀረበበት ሕጋዊ አግባብን ፓርላማው ሊያጤነው እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡

  ይህ የጥቅማ ጥቅም መብት በአዋጅ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዲኤታዎችና ከላይ በተገለጹት ማዕረጐች የሚሠሩ የመንግሥት ተሿሚዎችን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አካላትና ዳኞች ይገኙበታል፡፡

  ዓላማውም ከላይ የተዘረዘሩት ኃላፊዎችና ዳኞች ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚሠሩ በመሆናቸው፣ ከኃላፊነት ሲነሱ ከጉስቁልና የራቀ ኑሮ እንደኖሩ ማድረግና ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥበቃና ከለላ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ የአዋጁ ዓላማ ያስረዳል፡፡

  በ2001 ዓ.ም. የፀደቀው አዋጅ ለፓርላማ አባላት የሚፈቅደው ጥቅማ ጥቅም የጡረታ አበል፣ ከአንድ ዓመት ደመወዝ ያልበለጠ የሥራ ስንብት አበል፣ ከ18 ወራት ደመወዝ ያልበለጠ የመቋቋሚያ አበል ነው፡፡ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ እንዲሁም ለፓርቲ ተጠሪዎችና የመንግሥት ተጠሪዎች ግን መኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪ፣ ደመወዝና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ይደነግጋል፡፡     

   

     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...