የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት፣ በጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሕይወትና ሥራ ላይ ባተኮረው ዲቪዲ ዶኪሜንታሪ (ዘጋቢ) ዙርያ ሚዪዚክ ሜይ ዴይ ኢትዮጵያ ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በወመዘክር አዳራሽ ውይይት ያካሂዳል፡፡ በዕለቱ ከ8 እስከ 11 ሰዓት በሚዘልቀው መሰናዶ ለውይይቱ የጥናት ወረቀት የሚያቀርበው ዶኪሜንታሪውን ያዘጋጀው እዝራ እጅጉ ሲሆን፣ የታሪክ ባለሙያው ሰለሞን ተሰማ ጂ ውይይቱን ይመራዋል፡፡
ዘጋቢ ፊልሙን ያሳተመው ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን እንዳስታወቀው፣ በዕለቱ የአክሊሉ ሀብተ ወልድ የወንድም ልጅ የሆኑት አቶ አምዴ አካለወርቅ የሚገኙ ሲሆን ከታዳሚያን ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ፡፡ ዶክመንታሪው የአክሊሉ ሀብተወልድን ያልተነገሩ ታሪኮች፣ እንዲሁም ታሪካዊ ንግግራቸውን፣ አብረዋቸው ከሠሩ ሰዎችና ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጋር የተደረገውን ቆይታ አካቶአል፡፡