Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመንግሥት ውሳኔዎች ምክንያታዊ ይሁኑ!

  መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይወስናል፡፡ ከብሔራዊ ጉዳዮች ጀምሮ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በርካታ ውሳኔዎች ላይ ይደርሳል፡፡ ሁሉም ውሳኔዎች የሕዝብን መብትና ጥቅም፣ የአገርን ክብርና ብሔራዊ ደኅንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ውሳኔዎች እነዚህን መሠረታዊ ፍላጎቶች መነሻ አድርገው ሲተላለፉ፣ በዜጎች ዘንድ ይሁንታና ከበሬታ ያገኛሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ ውሳኔ ላይ ሲደረስ ደግሞ፣ በተቻለ መጠን ጉዳት እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ ሊኖር የሚችለው ግን ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ መንግሥትን የሚመራው አካል (አስፈጻሚ) የሕዝብ ውክልና ባለው ፓርላማ አማካይነት ተጠያቂነት እንዳለበት ሲረጋገጥ የዘፈቀደ ውሳኔዎች አይኖሩም፡፡ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለውሳኔዎች ትክክለኛነትና ፍትሐዊነት ጥያቄ ሲያነሳ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት የሚቻለው፣ የአስፈጻሚው አካል እንቅስቃሴ ተጠያቂነት ሲኖርበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ባለመሆኑና ተጠያቂነት ባለመኖሩ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ በአግባቡ ምላሽ የሚሰጥ ስለሌለ ችግሮች እየተደራረቡ ቀውስ መፍጠራቸው ይታወቃል፡፡ ከምክንያታዊነት ይልቅ ግብታዊነትና ስሜታዊነት እየበረቱ መደማመጥ ጠፍቶ፣ የኢትዮጵያ ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ነው የከረመው፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር እየተፈቱ ነው፡፡ በአገር መሪ ደረጃ ከሕዝብ ጋር የቀጥታ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ውይይቶች ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋርም እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ ቢያንስ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ዓውድ ለመፍጠር የሚያስችሉ በጎ ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ ገና የሚታዩ ነገር ግን በሒደት ሊከናወኑ የሚችሉ በርካታ ገንቢ ጉዳዮች እንደሚኖሩም ይታሰባል፡፡ መንግሥት በአንድ ልብና ሐሳብ በጅምሮች ላይ ጠንክሮ ከገፋ፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚሆን መሠረት ለመጣል ይቻላል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ አልፎ አልፎ ስህተቶች ቢፈጠሩ እንኳን፣ ለብሔራዊ መግባባት ሲባል በመተራረም አብሮ ለመሥራት መደጋገፍ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አንዳንድ የሚተላለፉ ውሳኔዎች አሉታዊ መልዕክት እንዳያስተላልፉ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ሰዎች ክሳቸው ሲቋረጥ ወይም በይቅርታ ሲፈቱ አንድምታው ግልጽ ነው፡፡ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች በዚህ መንገድ ሲስተናገዱ ደግሞ ውዥንብር ይፈጠራል፡፡ ይኼንን ውዥንብር የማጥራት ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ሲቀጥል ጥያቄው እየጨመረ ስለሚመጣ ምክንያዊ ሆኖ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ምላሽም ተቋማዊ እንዲሆን አገር በሲስተም እንድትመራ መደረግ አለበት፡፡

  የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄ የሚያቀርበው ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ግልጽነት ሲጠፋ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳልነው የመንግሥት አሳታፊነት በጣም ከመጥበቡ የተነሳ፣ የአገሪቱን ውሎና አዳር ለማወቅ ሕዝብ ባዕድ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ከፍተኛ መቃቃር ተፈጥሯል፡፡ ይህ መቃቃር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለቅራኔ በር ከፍቷል፡፡ የቅራኔው ከመጠን በላይ መጦዝ ደግሞ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ የነበረውን እንጥፍጣፊ አመኔታ የበለጠ አጥፍቶታል፡፡ በዚህም ሳቢያ አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በነውጥ ውስጥ ከርማለች፡፡ መንግሥት ይኼንን ነባራዊ እውነታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በዚህ ወቅት እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን በየቀኑ መመርመር አለበት፡፡ በየመሥሪያ ቤቱም ሆነ በአገር ደረጃ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በማስተዋልና በጥንቃቄ መተላለፍ አለባቸው፡፡ ሕዝብን የሚያግባቡና ለብሔራዊ አንድነት የሚረዱ ጉዳዮች ይሁንታ ሲሰጣቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግር የሚያሰኙ ውሳኔዎች ደግሞ ለምን የሚል ጥያቄ ማስነሳታቸው የግድ ነው፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ የማስረዳት ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ለዚህም ተቋማዊ አሠራር ያስፈልጋል፡፡

  ሰሞኑን በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ከተፈቱት ውስጥ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ በርካታ ግለሰቦች ተፈተዋል፡፡ ፀረ ሙስና ትግሉ በጥናትና በረቀቀ ሥልት የሚመራ ከሆነ ከመነሻው ተጠርጣሪዎች ሲያዙም ሆነ ሲከሰሱ ሒደቱ ግልጽ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዘመቻ የሚከናወን ሲሆን ደግሞ ንፁኃን ጭምር ተጎጂ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲመሠርት ሥራውን በአግባቡ አከናውኖ ካልሆነ ተጠያቂነቱ የመንግሥት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ግን በአገር ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶ በሚዲያ ጭምር ብዙ መግለጫዎች ከተሰሙ በኋላ፣ መንግሥት የተጠርጣሪዎችን ክስ ሲያቋርጥ መሥፈርቱ ምን እንደሆነ ለሕዝብ ግልጽ መደረግ አለበት፡፡ ክስ ተቋረጠ ማለትስ ካሁን በኋላ ‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን› ነው? ወይስ የተዘረፈ የአገር ሀብት ለማስመለስና አጥፊዎችን ለመቅጣት ሌላ ዝግጅት ይደረጋል? ይኼንን በአግባቡ መመለስ ካልተቻለ፣ ነገና ተነገ ወዲያ ከተማ ውስጥ ኪስ ሲያወልቁ የነበሩ ወይም በገጠር በረት ሰብረው የዘረፉ፣ ወይም በተለያዩ ደረቅ ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው ‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ› እያሉ አቤት ማለታቸው አይቀርም፡፡ ከመንግሥት የሚሰጠው ምላሽና የሕዝብ አስተያየት በግልጽ ቢደመጥ ከመላምት ይገላግላል፡፡

  መላምት ሲባል በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጉላሉ የተለያዩ በጥያቄ የተሞሉ አስተያየቶችን ነው፡፡ መንግሥት በሙስና ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን ሲፈታ የተፅዕኖው መበርታት አስገድዶት ነው ወይ የሚል መላምት አለ፡፡ ይኼውም በሙስና ተጠርጥረው ከተያዙ ሰዎች ውስጥም ከፖለቲካ ጋር ስማቸው የሚነሳ ስላለ ነው? ወይስ የቤተሰቦች አቤቱታ የፈጠረው ጫና ነው? በሌላ በኩል ከመነሻው የክሱ አመሠራረት በራሱ ችግር አለበት? ወይስ ታሳሪዎቹ ከመልካም አጋጣሚ ጋር ተገናኙ? ካልሆነም የመንግሥት ውሳኔ እስረኞችን በሙሉ ፈቶ እፎይ ለማለት ያሰበ ነው? ይህ እንዳይባል ደግሞ ከእስረኞች መካከል አሁንም ያልተፈቱ ስላሉ እኛስ የሚል አቤቱታ እየቀረበ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ አስተያየቶች በመላምት የታጀቡ ስለሆኑ፣ መላምቱ ደግሞ ለምናነሳው ጉዳይ ምላሽ ስለሌለው የመንግሥት ማብራሪያ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳቱ ለምን ይጠቅማል የሚል አስተያየት ካለም፣ ወደፊት ችግሮች እንዳይፈጠሩና ከወዲሁ ለመተራረም ስለሚጠቅም ነው፡፡ በአንድ ወቅት መስመሩን የሳተ ጉዳይ አሁን ማስተካከያ ካልተደረገለት ስህተትን ለመድገም ይዳርጋል፡፡ በጨዋ አነጋገር ‹አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሰባት ጊዜ ለካ› ማለት ነው፡፡

  በአጠቃላይ መሳሳት ችግር የለውም፡፡ ስህተት የሚኖረውም የሚሠራ ሰው ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ስህተትን ላለመድገም መጠንቀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ በጣም በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ብትሆንም፣ በምንም ዓይነት መመዘኛ ከችግሮቿ ይልቅ ተስፋዎቿ ይበልጣሉ፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ይህች ታሪካዊት አገር ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ባለቤት ናት፡፡ ይህ ወጣት ትውልድ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ የሆነው ወጣት ትውልድ በጠቃሚ መንገድ የሚኮተኮተው ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ትልቅ ሥፍራ ሲሰጥ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ምክንያታዊ ሆኖ ለቁምነገር እንዲበቃ ከኋላ ቀር አመለካከቶች መራቅ አለበት፡፡ ስሜታዊነትና ግብታዊነት ከተፀናወተው አስተሳሰብ ፀድቶ ለማኅበራዊ ፍትሕ ዘብ መቆም መቻል ይገባዋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትመሠረት ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት የሚቻለው፣ ፍትሕዊነት ኢፍትሐዊነትን ሰያሸንፍ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ አገር በሲስተም (ሥርዓት) እንድትመራ እንጂ፣ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለች እንዳትሆን መሠረት ይጣል፡፡ ለዚህም የሁሉም ዜጎች ዕገዛ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን መንግሥት ውሳኔዎቹ ምክንያታዊ እንዲሆኑ ሲተጋ ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

  ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው በኢትዮጵያ...

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...