Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ድርቁን በብቃት መቋቋምና ዘለቄታዊ መፍትሔ ላይ ይተኮር!

  በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት የተነፈገው የአሁኑ ድርቅ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም ዙሪያ ጫጫታ እየተሰማበት ነው፡፡ መንግሥትና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በቅርቡ ባወጡት ሰነድ 10.2 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የድርቁ አድማስ ከሰፋም መጠኑ ሊጨምር ይችላል፡፡ የድርቁ መከሰትና አሳሳቢነት ይፋ ከተደረገ ወዲህ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ መንግሥት ከራሱ ካዝና በማውጣት ችግሩን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በዝናብ መጥፋት ምክንያት ባለፈው ዓመት የበልግና የመኸር ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡ መንግሥትም በዚህ ችግር ምክንያት የሚጠበቅበትን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊቱን መለስ እያደረገ ስለሆነ ለዘለቄታዊ መፍትሔ መነሳት የግድ ነው፡፡

  ኤልኒኖ በሚባለው የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ምክንያት የደረሰውን ድርቅ ለየት የሚያደርገው፣ የዝናብ እጥረቱ ለረጂም ጊዜ መቆየቱ ነው፡፡ ይህም የዘንድሮውን ኤልኒኖ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንካራ አድርጎታል፡፡ ድርቁ ሲራዘም ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይጋለጣሉ፡፡ በቶሎ ወደ እርሻ ሥራቸው ስለማይመለሱ ጫናውን ያበረታዋል፡፡ ከሰዎች በተጨማሪ እንስሳት ለግጦሽና ለውኃ ችግር ስለሚጋለጡ የድርቁን አስከፊነት ያሳያል፡፡ ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ ዕርዳታ ሲያቀርብ የቆየው መንግሥት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የችግሩን መጠን በግልጽ ማሳየት አለበት፡፡ ድርቁን ከመቋቋም በላይ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡

  በተለይ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ከሚታያቸው ሥጋት አንፃር ችግሮችን እያጋነኑ ያቀርባሉ ቢባል እንኳ፣ ዕርዳታው የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከተረጂነት ወጥተው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ጥሪት ያገኙ ዘንድ አስፈላጊው ሁሉ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ድርቅ ሲከሰት የሚያስከትለው ጥፋት ከፍተኛ ነው፡፡ በሰው ሕይወት፣ ጤናና ሥነ ልቦና ላይ ከሚያደርሰው አደጋ በተጨማሪ አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ያሳጣል፡፡ ይህ ጥቅም በገንዘብ ሲመነዘር መጠኑ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ድርቅ አውዳሚ ኃይል በመባል ይታወቃል፡፡ ለዚህም የድርቁ ቆይታ ካበቃ በኋላ የሚታዩ ድኅረ ድርቅ ክስተቶች የዘላቂ መፍትሔን አስፈላጊነት በሚገባ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡

  በሚቲዎሮሎጂ ባለሥልጣን ትንበያ መሠረት በቅርቡ ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ በተለይ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከተረጂነት ወጥተው የእርሻ ሥራ መጀመር አለባቸው፡፡ ዘር፣ ማዳበሪያና የተለያዩ የእርሻ ግብዓቶችን እንዲያገኙ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ መገኘት አለበት፡፡ በአንድ በኩል ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ የተጋለጡ ወገኖችን መመገብ፣ የጤና እንክብካቤ ማድረግና ከቀዬአቸው እንዳይፈናቀሉ መርዳት ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዝናብ የሚመጣ ከሆነ እነዚህ ወገኖች ወደ መደበኛ ተግባራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተገቢውን ድጋፍ ማቅረብ ደግሞ ወሳኝ ነው፡፡

  በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በአጠቃላይ 1.4 ቢለዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ አገሪቱም ከዚህ በፊት ከነበራት ጊዜያት በበለጠ ደረጃ ድርቅን ለመቋቋም ዝግጁነትና አቅም መገንባቷም ተወድሷል፡፡ የአሁኑ ድርቅ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከታዩት ሁሉ በጣም አደገኛ ነው ቢባልም፣ እስካሁን ድረስ በድርቁ ምክንያት የአንድም ሰው ሕይወት እንዳላለፈ መነገሩም ያፅናናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁንም መዘናጋት አያስፈልግም፡፡ የአየር ንብረቱ ተለውጦ መዝነብ ሲጀምር አብረው ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው የእነሱም ጤንነት ያሳስባል፡፡ ለዚህም ሲባል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጥረቶች ጎን እንዲሠለፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን በትኩረት መከታተል ተገቢ ነው፡፡

        የሕፃናት፣ የአጥቢ እናቶችና የእርጉዞች ጉዳይም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ሕፃናት በአልሚ ምግቦች እጥረት ምክንያት ይጎዳሉ፡፡ የሚያጠቡ እናቶች በቂ ምግብ ስለማያገኙ እናትና ልጅ እንዲሁ የችግሩ ተጋላጭ ናቸው፡፡ እርጉዝ እናቶችም በቂ ምግብ ካላገኙ ለፅንሳቸውም ሆነ ለራሳቸው ጤና አሥጊ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው ሴቭ ዘ ችልድረን በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በመጪው ነሐሴ ወር ብቻ 350 ሺሕ ያህል ሕፃናት በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ይወለዳሉ፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ሕፃናት በቂ ምግብና ምቹ ሁኔታ ሳይኖር መወለዳቸው በራሱ ከፍተኛ ፈተና ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለድርቁ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ልዩ ትኩረትና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡

        አገሪቱ በአካባቢው ከሚገኙ አገሮች በላቀ ደረጃ ስደተኞችን ታስተናግዳለች፡፡ የኤርትራ፣ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ከአገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በዚህ ድርቅ ወቅት ማስተናገድ ፈተናው ከባድ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ቀለብ የሚሠፈርላቸው ከአገር ውስጥ ገበያዎች በመሆኑ፣ በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፡፡ በተጨማሪም ስደተኞቹ በአገራቸው አንፃራዊ ሰላም ተፈጥሮ የሚመለሱበት ጊዜ ስለማይታወቅ፣ ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ ጫና ይኖራል፡፡ ይህም ዘለቄታዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡

  በአጠቃላይ የድርቁ ፈተና ቀላል ባለመሆኑ አሁንም ያላሰለሰ ትግል ይጠይቃል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊቱን መለስ ሲያደርግም መግደርደር አያስፈልግም፡፡ የድርቁ ገጽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢለዋወጥም፣ ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ በዜጎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ቀን ከሌት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ዝናቡ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ከዕርዳታው ጎን ለጎን መከናወን ያለባቸው ተግባራት ትኩረት ይሻሉ፡፡ ሕይወትን ከመታደግ በተጨማሪ ለዘለቄታ ጉዳዮች ርብርቡ መቀጠል አለበት፡፡ በአገር አቀፍ፣ በክልልና በማኅበረሰብ ደረጃ የተጠናከረ የመረጃ ፍሰት በመፍጠር ይህንን አሳሳቢ ጊዜ በጥበብ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በየጊዜው እየተመላሰ ሕዝቡንና አገሪቱን መከራ የሚያበላው ድርቅ ካሁን በኋላ እንዳይከሰት መሠራት አለበት፡፡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ከመከለስ ጀምሮ ለዘለቄታው የሚበጅ መፍትሔ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ድርቁን በብቃት መቋቋምና ዘለቄታዊ መፍትሔ ላይ ይተኮር!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...