Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የአዛውንቱ ሙጋቤ የዘገየው ጩኸት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ለበርካታ የአፍሪካ ታዛቢዎች የአፍሪካ ኅብረት የአምባገነኖች መጠለያ ነው፡፡ ዴሞክራሲን፣ ሰብዓዊ መብትን፣ ሙስናን፣ ሴቶችንና ሌሎች በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ አዋጆችና ሰነዶች ቢያፀድቁም፣ የፈረሙዋቸውን ስምምነቶች ዞር ብለው የሚያዩ በጣም ጥቂቶች ናቸው የሚል ወቀሳም ይቀርባል፡፡ አኅጉሩን በተመለከተ ግን የጋራ ትግል ሲያካሂዱ ይስተዋላል፡፡

  በነፍጥም ሆነ በምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣ ኃይል የሕገ መንግሥትን አንቀጾች በመቀየር ጭምር፣ እሱ ካልተሳካም በይስሙላ ምርጫ፣ በምርጫም ከተሸነፈ በጠመንጃ በሥልጣን ላይ ዕድሜ ልክ መቆየት በአፍሪካ ምድር አዲስ አይደለም፡፡

  ሥልጣን አገርንና ሕዝብን ለማገልገል ሳይሆን፣ ራስን ቤተሰብን እንዲሁም የኢኮኖሚ ሸሪኮችን ፍላጎት የሚያጣጥሙበት ነው፡፡ ሥልጣን አገልጋይነት ሳይሆን፣ የሀብት ማግበስበሻ መሣሪያ ነው፡፡ የራስን ምቾት መጠበቂያ መንገድ ነው ተብሎ በስፋት ይተቻል፡፡ ቦትስዋናን፣ ጋናን፣ ናይጄሪያንና ሌሎች በጣት የሚቆጠሩ በምርጫ መሪዎች ከሥልጣናቸው የወረዱባቸው ጥቂት አገሮች ናቸው፡፡ በተቀረው አፍሪካ ግን ሥልጣንን ሙጥኝ ማለት መርህ ይመስላል በማለትም ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ አገሮች መፈንቅለ መንግሥት መከራዎች ይኬሄዱባቸዋል፡፡ እነሱም በተራቸው ለሌላ መፈንቅለ መንግሥት የሚዘጋጁ መሆናቸው የተለመደ መሆኑ በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

  እንደ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የመሳሰሉ በሕዝባቸው የነፃነት አባቶች ተደርገው የሚታዩ መሪዎችም፣ ተመልሰው ጨቋኞች ሆነው የዕድሜ ልክ ሥልጣን ይጠብቃሉ፡፡ በቱኒዝያ የተነሳው የዓረብ የአብዮት ማዕበልም ከሰሜን አፍሪካ ወደ ሌላው በተለይ ከሰሃራ በታች ወዳሉ የአፍሪካ አገሮች ይዛመታል ተብሎ ሲጠበቅ አልሆነም፡፡

  በአፍሪካ አኅጉር አንድ የአፍሪካ መንግሥት እንዲመሠረት ከሚያቀነቅኑት መሀል የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ቀዳሚ ነበሩ፡፡ የአፍሪካ ቃል አቀባይ እስከመባል ደርሰው የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም፣ በተቃዋሚዎቻቸው በአምባገነንነት የሚጠሩ ነበሩ፡፡

  ብዙዎቹ ስለአፍሪካ ዴሞክራሲ፣ ስለአፍሪካ ጥቅምና ስለሕዝቦቿ ለማውራት ሞራል ያላቸው ተደርገው አይታዩም፡፡ በትግል ፅናታቸው የአፍሪካ አባት ተደርገው ሲታዩ የነበሩት የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላም ቢሆኑ፣ እንኳን ለሰፊው የአፍሪካ ሕዝብ ሊተርፉ ለአገራቸው ጥቁሮችም ከስም በዘለለ ያተረፉላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነፃነት እምብዛም ነው በሚል የሚወቅሷቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ከነጮች ጋር ቢደራደሩም ዓላማቸው ተሰናክሎ ሕይወታቸው እንዳለፈም ይነገራል፡፡ በአፍሪካ ያለው ሙስና፣ አምባገነንነት፣ ድንቁርና፣ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ሰተት ብለው እንዲገቡ ደንበኛ ቀዳዳዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ አፍሪካውያን በስም ነፃ ቢወጡም አሁንም በቅኝ ገዢዎቻቸው የቋንቋ ቱሩፋት ሳይቀር አንግሎፎንና ፍራንክፎን እየተባባሉ መከፋፈላቸው የተለመደ ነው፡፡

  በስመ ሸምጋይነት፤ በአቅም ግንባታ፣ በግንዛቤ መፍጠር፣ በዕርዳታ ስም አፍሪካ ውስጥ የሚፈልጉትን አካል ሥልጣን ላይ ለማቆየት፣ የማይፈልጉትን ለማስወገድ የሚሠሩት ምዕራባውያን ጥቂቶች አለመሆናቸው ለብዙ ጊዜያት የሚተረክ ነው፡፡ ነጮች በአፍሪካ ምድር ሊያዩዋቸው ከማይፈልጉ መሪዎች መካከል የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ አንዱ ናቸው፡፡

  የአዛውንቱ ጩኸት

  በየዓመቱ ከሚካሄዱት የኅብረቱ መሪዎች እምብዛም ትኩስ ዜና የማይጠብቁ በርካታ ታዛቢዎች፣ ዛሬ ዛሬ አመለካከታቸውን የሚለውጡ ዜናዎችን እየሰሙ ነው፡፡ ዶ/ር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡበት መንገድ መጠነኛ ግርግር ፈጥሮ ነበር፡፡

  ከዚሁ ክስተት በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ኅብረቱ ውስጥ የተከሰተው አነጋጋሪ ነገር በነጮች ላይ ቅያሜ ያላቸው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ነበር፡፡

  አዛውንቱ ገና ወንበሩን በተረከቡ ወቅት በምዕራባውያን ላይ ያነጣጠረ ንግግራቸውን ለሰማ፣ ሰው ኅብረቱን ተጠቅመው የሆነ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ ብሎ መጠበቁ አይቀርም፡፡ እምብዛም የተጠበቀውን ያህል አልሆነም፡፡ አልያም በመሪዎቹ ላይ አስፈላጊውን ተፅዕኖ መፍጠር አልቻሉም፡፡

  አቶ መለስ በአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪነታቸው ምክንያት የበለፀጉ አገሮች ለደሃ አገሮች በተለይ ደግሞ ለአፍሪካ ካሳ እንዲከፍሉ ያደረጉት ትግል ዓላማውን ሳይመታ ሕይወታቸው በማለፉ፣ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ሳይመጣ ተንከባልሎ ቀርቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎች በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ላይ ተቃውሞ ያነሱበት ወቅት የነበረ ቢሆንም፣ እሱም ቢሆን የሚታይ ለውጥ ያስገኘ አልነበረም፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር ሆነው እንደ ትልቅ አጀንዳ የያዙት የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቱ የአፍሪካን መሪዎችን እየመረጠ መወንጀሉን እንዲያቆም የተደረገው ጥረት፣ በአሁኑ የኅብረቱ ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ አልተስተዋለም፡፡

  የዚህ ዓመት የኅብረቱ መደበኛ ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ የተስተዋለው ግን፣ ለቻድ ተረኛው ሊቀመንበር ወንበራቸውን ያስረከቡት አዛውንቱ ሙጋቤ ያደረጉት መሳጭ የተባለው ንግግር ነበር፡፡

  በብዙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደ ጥላቻ ንግግር ተደርጎ የተዘገበው የፕሬዚዳንቱ ንግግር፣ የተባሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጥቂት ነጮች መሣሪያ መሆኑን እንዲያቆም የሚጠይቅ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚሁ በከፍተኛ ጭብጨባ ታጅበው ያደረጉት ንግግር፣ ቀደም ሲልም ኅብረቱም እንደ አቋም የያዘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ ያድርግ የሚል ሲሆን፣ በዚህን ያህል ድምፀትና ክብደት ሲነገር ግን የመጀመሪያው ነው፡፡ በተለይ በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው አምስት አገሮች መካከል እኩል ለአፍሪካ ዕድል የማይሰጥ ከሆነ፣ አፍሪካ ከመንግሥታቱ ድርጅት ራሷን ለማግለል ትገደዳለች የሚለው ማሳሰቢያ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ንግግር ነበር፡፡

  ሙጋቤ በንግግራቸው መሀል የኅብረቱን ስብሰባ በመሳተፍ ላይ የነበሩትን የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙንን አሻግረው እያዩ፣ ‹‹የፀጥታው ምክር ቤት እንዲሻሻል ጠይቀናል፣ ጠይቀናል፣ ጠይቀናል፤›› በማለት ባዶ ንግግር ማድረግ እንደሰለቻቸው አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ሚስተር ባን ኪሙን እባክዎን ይንገሩልን፡፡ ይህ የመጨረሻ መልዕክታችን ነው፡፡ በፀጥታው ምክር ቤት ሀቀኛ የሆነ እኩልነት እንዲኖር በየስብሰባዎቹ ተገኝተን ባዶ ንግግር አድርገን ወደቤት እንመለሳለን፡፡ ማንም ጉዳዩን አጥብቆ የያዘው የለም፤›› ካሉ በኋላ፣ አዳራሹ ውስጥ የተገኙ የጉባዔውን ተሳታፊዎች ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ በዓይናቸው ጎብኘት አድርገው ረዘም ላሉ ሰከንዶች ፀጥ ብለው ቆዩ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤትም ቢሆን በተሳሳተ ሥፍራ ላይ ነው የከተመው፤›› ብለው ወደ ግራ እየተመለከቱ፣ ‹‹አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የት ነው ያለው? 1.2 ቢሊዮን በህንድ፣ 1.3 ቢሊዮን በቻይና፣ በአፍሪካም አንድ ቢሊዮን ሕዝብ አለ፡፡ አንድ ላይ ሲደመር ከሦስት ቢሊዮን በላይ ነን፤›› አሉ፡፡ ቀኝ እጃቸው ከፍ አድርገው እየጠቆሙ፣ ‹‹ባለ ቢጫ አፍንጮቹ ነጮች ደግሞ አንድ ላይ ሲደመሩ ተመልከቱ፡፡ እኛን አያክሉም፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ትክክለኛ አባልነት ያላቸው ነጮች መሆናቸው ገልጸው፣ ‹‹ተመድ ህልውናው እንዲቆይ የሚፈልጉ ከሆነ፣ እኛ አፍሪካውያንም እውነተኛ አባላት መሆን ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

  ባን ኪሙንን፣ ‹‹ጥሩ ሰው ነዎት፡፡ ነገር ግን የእኛ ታጋይ እንዲሆኑ አንጠብቅም፣ ዓላማዎም አልነበረም፡፡ እንደ አፍሪካውያን ግን ለማንነታችንና ለሰብዕናችን እኛው እንታገላለን፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ብቻ እኛ ፃዕረ መንፈስ ሳንሆን ሰዎች መሆናችንን ይንገሩልን፡፡ ዓለም የእኛም ነች፤›› ብለዋል፡፡

  አዛውንቱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ላይ ያነጣጠረ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ‹‹ኦባማ ምንድነው? እንደኛ ጥቁር ቢሆንም የእነሱን ቋንቋ የሚናገር ድምፅ ነው፡፡ እኛን ሳይሆን እነሱን እንዲመስል የተቀመጠ ነው፡፡ ነጮች ዛሬም የበላዮች ናቸው፤›› በማለት ወርፈዋቸዋል፡፡ ለጥቁሮች መብት ያደረጉት ተጋድሎ አለመኖሩን ለመግለጽ ከቅኝ ግዛት ዘመን በኋላም ቢሆን፣ ነጮቹ በተለያዩ ገጽታዎች አፍሪካ ውስጥ ረጂዎችና ሸምጋዮች እየመሰሉ ጥቁሮችን እርስ በርስ እያዋጉና እየሰለሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

  የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነት የሥልጣን ሽግግር ፕሮግራሙ የአሥር ደቂቃ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ሲሆን፣ ለአንድ ሰዓት ያህል ረዥም ንግግር ካደረጉ በኋላ ለተረኛው መሪ ለቻዱ ፕሬዚዳንት እድሪስ ዴቢይ ሲያስረክቧቸው ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥተው ነበር፡፡

  ‹‹እስትንፋሴ እስካለ ድረስ ትግሌን አላቋርጥም፡፡ እግዚአብሔር ወደ ራሱ እስኪቀላቅለኝ ድረስ ምቶቼ ይቀጥላሉ፤›› በማለት ንግግራቸውን የቋጩ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችን በሳቅ ፍርስ አድርጓቸዋል፡፡ በንግግራቸው የነፃነት ትግሎች ትውስታና የአገራቸውን የዚምባብዌ ሁኔታ ያስታወሱ ሲሆን፣ ‹‹ነጮች እኔ ሥልጣን ለቅቄ ሌላ ሰው በእኔ ቦታ ላይ ማስቀመጥ ያምራቸዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፣ ይህ ነጮች በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚሆኑ አመራሮችን ለማምረት የሚያደርጉት ሲሉ እስከ ዕለተ ሞታቸው ሥልጣን እንደማይለቁ ተናግረዋል፡፡

  ሙጋቤ ማን ናቸው?

  ዓለም አቀፍ ሚዲያውን ጨምሮ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ማንዴላ አድናቂዎች እንዳሉ ሁሉ፣ የአፍሪካ ተቆርቋሪዎች ደግሞ ‹‹ለነጮች መቼም እጅ የማይሰጥ የአፍሪካ ልጅ፤›› ይሉዋቸዋል የዚምባብዌን መሪ ሮበርት ሙጋቤን፡፡

  የ91 ዓመቱ አዛውንቱ ሙጋቤ የነጮችን አገዛዝ በማሸነፍ እ.ኤ.አ. በ1980 የዚምባብዌ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለሰባት ዓመታት የመሩ ሲሆን፣ በ1987 የመጀመርያው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የነጮችን አገዛዝ በመቃወማቸው ለአሥር ዓመታት የፖለቲካ እስረኛ ሆነው የቆዩት ሙጋቤ፣ በአገሪቱ ከሚገኙት ነጮች ጋር በተደረገው ጦርነት አሸናፊ ሆነው የጋራ መንግሥት ለመመሥረት በበቁበት ጊዜ ነበር በብዙ የአፍሪካ ሕዝቦች እንደ ጀግና መቆጠር የጀመሩት፡፡

  ሙጋቤ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ከአንድ በመቶ የማይበልጠው በነጮች እጅ የነበረው የሚታረስ መሬት ለጥቁሮች ለማከፋፈል ጥረት ሲያደርጉ፣ በመንጠቅ ምትክ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በቂ ካሳ እየተከፈለ ፖሊሲያቸው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አላደረጉም ነበር፡፡

  በተደረገው ድርድር የተወሰነ መረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ከአሥር ዓመታት በላይ የዘለቀ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 ወደ ሥልጣን የመጡት ቶኒ ብሌር፣ የሙጋቤ የመሬት ማሻሻያ ፕሮግራም ስምምነትን ውድቅ አድርገውታል፡፡ ‹‹ከቀድሞ የእንግሊዝ ገዢዎች ጋር ምንም ግንኙነት የለንም፣ የመክፈል ግዴታም የለብንም፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ሙጋቤ በነጮች እጅ የነበረውን መሬት ለጥቁሮች ማከፋፈል ሲያያዙት በተለይ በእንግሊዝና በአሜሪካ ጥርስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ አገራቱ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በመጣሉም ኢኮኖሚው ደቋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱም እየጨመረ መጥቶ መቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ተደርሶም ነበር፡፡  

  እ.ኤ.አ. በ2000 በዚምባብዌ ይኼንን የመሬት ጉዳይ በተመለከተ ለሕዝበ ውሳኔ ቢቀርብም፣ በጥቂት ልዩነት ውድቅ ሆኗል፡፡ ሙጋቤ የሚመሩት የዚምባብዌ አፍሪካ ብሔራዊ አንድነት ድርጅት (ZANU-PF) በፓርላማ ነጮች ከያዙት መሬት እንዲለቁ ተጨማሪ አዋጅ ያፀደቀ ሲሆን፣ በውዴታም በግዴታም ነጮችን ከይዞታቸው በማባረር መሬቱን ለጥቁሮች እንዲከፋፈል አድርገዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይም ቢቢሲን ጨምሮ የምዕራባውያን ሚዲያዎችም ዘምተውባቸዋል፡፡

  በርካታ የግድያ ሙከራ ይደረግባቸው የነበሩት ሙጋቤ ግን ጥቁሮች የኢኮኖሚውና የፖለቲካው የበላይነት እንዲኖራቸው ተጨማሪ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ የነጮች እርኩስ ድርጊት አድርገው የሚቆጥሩት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን (ግብረሰዶም) በማውገዝና በዚህ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ለማጥፋት ዕርምጃዎች በመውሰድ ይታወቃሉ፡፡

  ሙጋቤ ተቃዋሚዎቻቸው በሙሉ ከጀርባቸው ነጮች እንዳሉ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (MDC) የሚመሩት ሞርጋን ሻንጋራይ ግን እ.ኤ.አ. በ2008 ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊነታቸው በአገሪቱ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ በድጋሚ ምርጫ ተደርጎ ግልጽ አሸናፊ ባለመኖሩ የጥምረት መንግሥት ለመመሥረት በቅተዋል፡፡ ቆይቶ ግን የጥምረት መንግሥቱ ፈርሷል፡፡

  የዛሬውን ጨምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች በነጮች ላይ ያላቸውን የከረረ ጥላቻ በግልጽ የሚናገሩ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፣ ቀደም ሲልም በቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት አገሮች ከመሠረቱት የጋራ ማኅበር (ኮመን ዌልዝ) አገራቸው ራሷን እንድታገል ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡ 

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -