Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔራዊ መግባባት ቅድመ ድርድር መቋጫ አላገኘም

  የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔራዊ መግባባት ቅድመ ድርድር መቋጫ አላገኘም

  ቀን:

  በብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ላይ ቅድመ ድርድር በማድረግ ላይ የሚገኙት ኢሕአዴግና 15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በአጀንዳው ላይ እንዴት ድርድር መደረግ አለበት በሚለው ሳይስማሙ ቀሩ፡፡ የአጀንዳው አካሄድ ምን መሆን ይኖርበታል የሚለውን ለመወሰን ለመጪው ማክሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡

  ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው ቅድመ ድርድር ላይ ኢሕአዴግ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረቡትን የመደራደሪያ ሐሳቦች እንደሚቀበል የገለጸ ቢሆንም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን እርስ በርስ ጉዳዩ እንዴት መሄድ ይኖርበታል በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን በማንፀባረቃቸው፣ ቅድመ ድርድሩ እንደገና በቀጠሮ እንዲበተን ሆኗል፡፡

  በዕለቱ ከ11 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ብሔራዊ መግባባት የሚለው አጀንዳ አካሄድ ምን መምሰል ይኖርበታል የሚለውን ለመወሰን ሁለት ከኢሕአዴግ፣ አምስት ደግሞ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተውጣጡ ግለሰቦችን የያዘ ኮሚቴ ይቋቋም የሚል አቋም ተንፀባርቋል፡፡

  ከ11 ፓርቲዎች ስብስብ ውጪ ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ ለአደራዳሪዎች ያቀረቡትን ሐሳብ የሚያደራጁ ባለሙያዎች መርምረውትና ሐሳብ ሰጥተውበት ለቤቱ አቅርበው፣ በእሱ ላይ በሚደረግ ውይይት አካሄዱን እንለይ በማለት አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡

  በዚህም መሠረት የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄን የመሰሉ ፓርቲዎች ኮሚቴ የሚባል ነገር መቋቋም የለበትም ብለዋል፡፡ የራሳቸውን ሐሳብ ኮሚቴ ለሚባለው አካል የሚሰጠው ለምንድነው? በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

  ኢሕአዴግን ወክለው በድርድሩ የሚሳተፉት አቶ ደግፌ ቡላ ኢሕአዴግ ፓርቲዎቹ ቀደም ብለው ባስገቡት አጀንዳ ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም፣ ባለፈው ቅድመ ድርድር ወቅት እንደገለጹት፣ ‹‹ፓርቲዎቹ ለመነሻ ያቀረቡት የድርድር ሐሳብ የተለያዩና የተበታተኑ በመሆናቸው በባለሙያ መቅረብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

  ይቋቋማል የተባለው ኮሚቴን አስመልክቶ ግን ኢሕአዴግ አባል እንደማይሆን አቶ ደግፌ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ይቋቋማል የሚባለው ኮሚቴ አባል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩን ያነሳችሁ እናንተ በመሆናችሁ የእናንተን ሐሳብ ለማደራጀት ስለሚቸግር ነው፡፡ ነገር ግን ለኮሚቴው የሚያስፈልግ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፤›› በማለት የፓርቲያቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡

  ኮሚቴ የማቋቋም፣ ባለሙያ የመሰየምና በቀደመው የድርድር አካሄድ ይሂድ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ሲወያዩ የቆዩት ፓርቲዎቹ ወደ አንድ የስምምነት ነጥብ ባለመድረሳቸው፣ ቅድመ ድርድሩ እንደገና ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ በቀጠሮ እንዲያድር ተደርጓል፡፡

  ‹‹በኢሕአዴግ በኩል ሦስቱም አማራጮች ክፍት ናቸው፡፡ ዋናው ችግር ያለው በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ምንም ችግር የለም፡፡ ሌላ ቀጠሮ መያዝም ይቻላል፡፡ ነገር ግን ስትግባቡ ብትጠሩን ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ሌላ ቀጠሮ ብንይዝም ቀኑን ሙሉ ተጨቃጭቀን የምንለያይበት ሁኔታ ነው የሆነው፤›› በማለት አቶ ደግፌ ተቃዋሚዎች ሐሳባቸውን አደራጅተው እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  በመጨረሻም አደራዳሪዎቹ ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ ቀጠሮ የያዘ ሲሆን፣ በቀረቡት አማራጮች ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ግን ድርድሩ እስካሁን በሄደበት መንገድ እንደሚቀጥል አስታውቀው ቅድመ ድርድሩ ተጠናቋል፡፡    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...