Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ከመጣ ደላላ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

  [ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን ቢሯቸው ያስጠሩታል]

  • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • አሁን አንድ ወሳኝ ጉዞ አለኝ፡፡
  • ወደ ፊልድ ሊወጡ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የምን ፊልድ ነው ወደ ውጭ ነው እንጂ?
  • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ውጭ አገር ልሄድ ነው፡፡
  • የምን ውጭ አገር ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ስማ ዓለም ሁሉ የሚሰበሰብበት ቦታ ላይ ኢትዮጵያን ወክዬ ነው የምገኘው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር አንድ ሚኒስትር እንዴት ነው አገር ወክሎ ውጭ የሚሄደው?
  • ምን ዓይነት ንቀት ነው ያለብህ?
  • ኧረ እኔ ምንም ንቀት የለብኝም፡፡
  • እኔ ኢትዮጵያን ወክዬ ስንት ዓለም እንደዞርኩ አታውቅም?
  • አይ እኔማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ወክለው መጓዝ ያለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ብዬ ነው፡፡
  • እኔ እኮ ስለማታውቀው ነገር ለምን እንደምትዘባርቅ ነው የሚገርመኝ፡፡
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ካላወቅክ ደግሞ መጠየቅ ይሻላል፡፡
  • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ወድጄ አይደለም እንደዚህ የምሆነው፡፡
  • የማዝህን ነገር ብቻ ለምን አትፈጽምም?
  • ቢያዙኝም እኔንም ያስጠይቀኛል፡፡
  • ማን ነው የሚጠይቅህ?
  • መመርያ የወጣበት ጉዳይ እኮ ነው፡፡
  • ስማ እኔ ሳዝህ አትሰማም ማለት ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር ስለሚያስጠይቀኝ እኮ ነው?
  • ስለምን መመርያ ነው የምታወራው?
  • ውጭ አገር ዝም ብሎ መሄድ አይቻልም፡፡
  • ታዲያ እየጮህኩ ልሂድ?
  • ጉዞ ለአገሪቷ አስፈላጊነቱ በሚገባ መጣራት አለበት፡፡
  • ለአገሪቷማ በጣም አስፈላጊ ጉዞ ነው ስልህ?
  • ስለዚህ ከበላይ ትዕዛዝ ሊመጣልኝ ይገባል፡፡
  • የምን ትዕዛዝ?
  • ለእርስዎ አበል በዶላር እንድሰጥ ትዕዛዝ ሊሰጠኝ ይገባል፡፡
  • በቃ አንተም በእኔ ላይ አለቃ እየሆንክ ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር እኔ እዚህ ያለሁት ላስፈጽም ነው፡፡
  • ምኑን?
  • መመርያውን!

  [ክቡር ሚኒስትር ሌላ ሚኒስትር ጋ ይደውላሉ]

  • እንዴት ነው አገሪቷን እየመራን ያለነው?
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • እኛን እየተበቀላችሁን ነው እንዴ?
  • የምን በቀል ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ስንቱን አይደል እንዴ እየፈታችሁ ያላችሁት?
  • ጥሩ አይደል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ታዲያ እኛን ግን የቁም እስረኛ አደረጋችሁን፡፡
  • ምን ሆነው ነው ክቡር ሚኒስትር? ተረጋግተው ያስረዱኝ እስቲ?
  • ሰሞኑን አንድ ወሳኝ የሆነ የውጭ ጉዞ አለብኝ፡፡
  • ምን ዓይነት ጉዞ?
  • በቃ አገሪቷን በመላው ዓለም የሚያስተዋውቅ መድረክ ነው፡፡
  • ይኼማ ጥሩ ነው፡፡ ካቢኔ ላይ ያቅርቡትና ይወሰንበታ?
  • ይኼ ቢሮክራሲ እኮ ነው ያሰለቸኝ፡፡
  • የምን ቢሮክራሲ?
  • እኔ እንደ ሚኒስትርነቴ በዚህ ጉዞ ላይ እንኳን መወሰን አልችልም?
  • ክቡር ሚኒስትር ያኔ መመርያው ሲወጣ ዝም ብለው አሁን እንደዚህ የሚሆኑት ለምንድነው?
  • ለአንድ የውጭ ጉዞ መወሰን የማልችል ከሆነ ብለቅ ይሻለኛል፡፡
  • ምኑን ነው የሚለቁት?
  • ሚኒስትርነቱን፡፡
  • እሱማ ግልግል ነበር፡፡
  • እኔ እንኳን ልብህን ልየው ብዬ ነው እንጂ መቼም አለቅም፡፡
  • የት ለመጓዝ ነው ግን ይኼ ሁሉ ግርግር?
  • ዓለም የተሰበሰበበትና ኢትዮጵያን ላሳይ የምችልበት ቦታ ነው፡፡
  • እኮ የት ነው?
  • የዓለም ዋንጫ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ፊታቸው ላይ በጣም የድካም ገጽታ ይታያል፡፡ ቢሯቸው ውስጥ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር ፊትዎ ላይ በጣም የድካም ስሜት ይነበባል፡፡
  • ትናንትና እንቅልፍ አልተኛሁም ነበር፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የድሮ የአርሴናል ጨዋታዎችን በቲቪ ሳይ ነበር፡፡
  • ምን ተገኝቶ ክቡር ሚኒስትር?
  • አይ አሠልጣኙ ባለራዕይ ስለሆነ ታሪኩ ስለሚመስጠኝ ነው፡፡
  • ለነገሩ ጥሩ አሠልጣኝ ነበር፡፡
  • የሚገርምህ ምንም የማይታወቁ ተጫዋቾችን በዓለማችን ታዋቂ አድርጓቸዋል፡፡
  • ግን ለክለቡ ውድቀትም ተጠያቂ ነው ይባላል፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ማለት አርሴናል በፊት ከነበረው ዝናና አቋም አሁን ወርዷል፡፡
  • የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ሁልጊዜ ልማታዊ ስትሆን በየመንገዱ የተለያዩ እንቅፋቶች ሊገጥሙህ ይችላሉ፡፡
  • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ቬንገር ልማታዊ አሠልጣኝ ነው፡፡
  • ቡድኑን ለዚህ ውድቀት የዳረጉት ቬንገር ናቸው የሚሉም አሉ እኮ?
  • እነሱ አፍራሽ ኃይሎች ናቸው፡፡
  • ሰውዬው ጡረታ መውጣት በነበረባቸው ጊዜ አልወጣም ብለው ነበር፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • ጓደኛቸው አሌክስ ፈርጉሰን በቃኝ ብለው ሲወጡ፣ ይኸው እሳቸው የሙጥኝ ብለው ነበር፡፡
  • እንደ እሱ ዓይነት የኳስ መሐንዲስ ጡረታ አልወጣም ቢል ምን ችግር አለው?
  • ለነገሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያስቸገረው ብዙ ቬንገሮች በመኖራቸው ነው፡፡
  • እንዴት?
  • ይኸው ብዙዎች ሥልጣን ላይ ለ20 ዓመታት የሙጥኝ ብለው አለቅም ብለዋል፡፡
  • በአሽሙር እኔን ለመናገር ፈልገህ ነው?
  • ይቅርታ አድርጉልኝና እርስዎም አንደኛው ቬንገር ነዎት፡፡
  • እ…
  • ይኸው ዴስክዎ ላይ እያንቀላፉ ለወጣቱ ሥልጣኑን ማሳለፍ አይፈልጉም፡፡
  • ምን?
  • ያደለውማ እንደ ቬንገር ሳይሆን እንደ ዚዳን በአጭር ቆይታው ሦስት ዋንጫ በልቶ ሥልጣኑን ይለቃል፡፡
  • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
  • ጡረታ ቢወጡ ጥሩ ነው፡፡
  • እኔማ ጡረታ መውጣት አልፈልግም፡፡
  • በፍላጎት ካላደረጉት በግዴታም ቢሆን ይወጣሉዋ፡፡
  • ስማ ከመንግሥት ፔሮል ብወጣም ከእንትኑ ግን አልወጣም፡፡
  • ከምኑ?
  • ከትግሉ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር ከተፈታ ባለሀብት ጋር ተገናኙ]

  • እንኳን ለቤትህ አበቃህ ወዳጄ፡፡
  • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሰላም ነህ ግን ወዳጄ?
  • ሰውን ማመን ቀብሮ ነው አሉ፡፡
  • ምነው?
  • እንዲያው አንድ ቀን እንኳን መጥተው አይጠይቁኝም?
  • አሁን እኔ ቂሊንጦ አካባቢ ብትይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እያወቅክ?
  • ሌላው ቢቀር እንዴት ቤተሰቤን አይጠይቁም?
  • አገሪቷ በደኅንነት የተሞላች አይደለች እንዴ?
  • ለማንኛውም ግን ቅር ብሎኛል፡፡
  • ምንም ቅር እንዳይልህ፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ለዚህ እንድትበቃ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ የለም፡፡
  • ማለት?
  • በየጊዜው ዓቃቤ ሕጎቹንና ዳኞቹን ሳገኝ እንደተሟገትኩልህ ነው፡፡
  • ምን ብለው?
  • ፍጹም ንፁህ መሆንህን ነዋ፡፡
  • እሱን እንኳን ተውት፡፡
  • ስማ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ብትል፣ ሁሉም ሲያነጋግሩኝ አንተ በፖለቲካ እንደታሰርክ ነበር የምነግራቸው፡፡
  • እኔ እኮ ጋዜጠኛ አይደለሁም፡፡
  • ያው ነው ኤንጂኦ ኤንጂኦ ነው፡፡
  • እና ከጎንህ ነበርኩ እያሉኝ ነው?
  • ይኼንን ማንንም መጠየቅ ትችላለህ?
  • ለማንኛውም ላደረጉልኝ ነገር በጣም አመሰግናለሁ፡፡
  • አንተም ግን ከእስር ቤት የወጣህ አትመስልም፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • በጣም ነዋ ያማረብህ፡፡
  • እሱን እንኳን ተውት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እስር ቤት ራሱ ጥሩ ቦታ እንዲያስሩህ ለኃላፊዎቹ በተደጋጋሚ አስረድቻቸዋለሁ፡፡
  • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ እኮ አመጣጤም ላደረኩልህ ነገር ትክሰኛለህ ብዬ ነው፡፡
  • ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
  • ኧረ እባክህ?
  • በደስታ ነው እርስዎን የምክስዎት፡፡
  • ምን ልታደርግልኝ?
  • የምሰጥዎትን እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
  • ምንድነው የምትሰጠኝ?
  • የነዳጅ!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ከመጣ ደላላ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት እያደረገው ያለው ለውጥ በጣም ያስደስታል፡፡
  • ማለት?
  • አገሪቷ ላይ እየነፈሰ ያለው የተስፋ ንፋስ ያስደስታል፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • እስረኞች እየተለቀቁ ነው፣ ፖለቲከኞች እየተፈቱ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከመንግሥት ጋር የሚቃረኑ ፓርቲዎች ራሳቸው ጥሪ እየተደረገላቸው ነው፡፡
  • ከዚህ በኋላ እኛ ሰላምና ልማት ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው፡፡
  • እኔም አገሬ የገባሁት ይህንን ተረድቼ ነው፡፡
  • ለመሆኑ ምንድነው የምትሠራው?
  • እኔ ፈረንጆቹ አገር የታወቅኩኝ ደላላ ነኝ፡፡
  • ኒዮሊብራል ነህ ማለት ነው?
  • እኔ አገር ወዳድ ሰው ነኝ፡፡
  • ለምንድነው የመጣሁት አልከኝ?
  • መጀመርያ ራሴን ለማሳደግ፣ ቀጥሎ ደግሞ አገሬን ለማሳደግ ነው፡፡
  • እሱስ ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ ጋር ብዙ ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡
  • ምን ዓይነት ሥራ?
  • እኔ ብዙ ኢንቨስተሮች ማምጣት እችላለሁ፣ እርስዎ ደግሞ እዚህ መሬቱንም ሆነ ሌላውን ማመቻቸት ይችላሉ፡፡
  • እኔ ምን እጠቀማለሁ?
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር በኮሚሽን እንጠቃቀማለን፡፡
  • ችግሩ እኮ አንተ ኒዮሊብራል መሆንህ ነው፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ኒዮሊብራል ሳይ ሰውነቴን ይወረዋል፡፡
  • እኔም እኮ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለውን ነገር ሳስበው ሰውነቴን ይወረዋል፡፡
  • ምን እያልከኝ ነው?
  • እርስዎም አብዮታዊ ዴሞክራት እንደሆኑ፣ እኔም ኒዮሊብራል እንደሆንኩኝ መቀጠል እንችላለን፡፡
  • ለነገሩ አሁን በምትለው መንገድ መሥራት የምንችልበት ዕድል አለ፡፡
  • እንዴት?
  • ያው መንግሥታችንም አቅጣጫ አስቀምጦልናላ፡፡
  • የምን አቅጣጫ?
  • ከእኛ ጋር ከሚቃረኑ ፖለቲከኞች ጋር አብረን እንድንሠራ አቅጣጫ ስለሰጠን በዚያ መንገድ ማስኬድ እንችላለን፡፡
  • ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • እኔና አንተም በዚህ መንገድ ነው የምንሠራው፡፡
  • በምን?
  • በጥምረት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት...

  በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

  በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

  ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል የኢትዮጵያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዎና መንገሣቸውን እያነሱ ደስታቸውን ሲገልጹ አገኟቸው]

  እሰይ አገሬ... እሰይ አገሬ እልልል ምን ተገኘ ደግሞ ዛሬ? የአትሌቶቻችንን ድል ነዋ! በክፉ ሲነሳ የቆየውን የአገራቸውን ስም በወርቅ እያደሱ እኮ ነው?  አየሽ፣ መንግሥት የአገራችን ችግር ያልፋል ስሟም...