Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜና​የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ኃላፊ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

  ​የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ኃላፊ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

  ቀን:

  • አቶ ኤርሚያስ አመልጋ እየሰጡት ያለው ቃል 50 ገጽ ደረሰ

  ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ እስር ጋር በተገናኘ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ኃላፊ፣ ሕገ መንግሥቱን ጥሰዋል በሚል አቤቱታ ታስረው እንዲቀርቡ ተጠየቀ፡፡

  ኃላፊው ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠየቁት፣ የአቶ ኤርሚያስ የሕግ አማካሪና ጠበቆች ናቸው፡፡

  ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. አቶ ኤርሚያስን ፖሊስ በመከልከሉ ምክንያት የሕግ አማካሪዎቻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ለችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን በመጠቆም ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማለት ያስተላለፈው ትዕዛዝ አለመፈጸሙን በመናገር ነው፡፡

  ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ፍርድ ቤቱ ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጠርጣሪው ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው መከበር እንዳለባቸው በመጠቆም በቤተሰብ የመጎብኘት፣ የሃይማኖት አባት የማግኘትና የሕግ ባለሙያ የማነጋገር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር ያስተላለፈው ትዕዛዝ አልተፈጸመም፡፡ ጠበቆቹ በተደጋጋሚ ወደ ተቋሙ በመሄድ እንዲያገናኟቸው ቢጠይቁም እንዳልሆነላቸው አስረድተዋል፡፡

  አቶ ኤርሚያስ ተጠርጥረው ስለታሰሩበት ምክንያት ‹‹ቃል አልሰጥም›› የማለት ሕጋዊ መሠረት ያለው መብት እንዳላቸው የገለጹት ጠበቆቹ፣ ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመነጋገርና የመመካከር ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ታልፎ ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ሳይነጋገሩና ሳይመካከሩ ቃል እንዲሰጡ መደረጉ ሕገ መንግሥቱን መጣስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ተግባር የተፈጸመው ለዜጎች ምሳሌ መሆን በሚገባው ተቋም በመሆኑ፣ የወንጀል ምርመራ ኃላፊው ታስረው እንዲቀርቡና ለምን ሕገ መንግሥቱን እንደጣሱ እንዲጠይቁላቸው አመልክተዋል፡፡

  ላለፉት 31 ቀናት (እስከ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ) በእስር ላይ በሚገኙት አቶ ኤርሚያስ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ እንዳልጨረሰ ለፍርድ ቤቱ የገለጸው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ቡድን፣ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ባለፉት የምርመራ ቀናት የአቶ ኤርሚያስን ቃል እየተቀበለ መሆኑን፣ ከአቶ ኤርሚያስ ጋር ግንኙነት አላቸው ለተባሉ የተለያዩ ተቋማት ሰነድ እንዲልኩለት ደብዳቤ መበተኑንና የተለያዩ የምርመራ ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድቷል፡፡ መርማሪ በድኑ የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ አቶ ኤርሚያስ በራሳቸው ሥልጣን ከአክሲዮን ባለድርሻዎችና ከቤት ገዢዎች ያገኙትን ገንዘብ በማውጣት ለእነማን እንደሰጡት አድኖ መያዝ፣ የገዟቸውን ቤቶችና መሬቶች ማሳገድ፣ ሽርክና በመግባት በጋራ ለማልማት ውል የተፈራረሟቸውን ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበል፣ አክሲዮን ማኅበሩ ኦዲት እየተደረገ በመሆኑ የኦዲተሮችን የምርመራ ውጤት መቀበልና ሌሎች ምርመራዎች እንደሚቀሩት በማስረዳት የጠየቀው ተጨማሪ ጊዝ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

  የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ የተቃወሙት የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ ከታሰሩ 31 ቀናት ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ቡድኑ ማስረጃውን አሰባስቦ ለመጨረስ በቂ ጊዜ ነበረው፡፡ በዚህ ጊዜ አለማጠናቀቁ ሥራውን በተገቢው ሁኔታ አለመሥራቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪውን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ለፍርድ ቤቱ እያቀረበው ያለው ማስረጃ ተመሳሳይ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን በማስታወቅ ተቃውመዋል፡፡

  የአቶ ኤርሚያስ ንብረቶችም ሆኑ የሰነድ ማስረጃዎች እሳቸው የመፍትሔ አካል ለመሆን ጠይቀውና ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የታገዱ መሆኑን ጠበቆቹ ጠቁመው፣ አሁን የሚታገድ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ለማረጋገጥ ከተፈለገም አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ሠራተኞች ያሉት ሕጋዊ ተቋም በመሆኑ ከዚያ ማሰባሰብ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ የቤት ገዢዎች ኮሚቴና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ፣ የንግድ ሚኒስትሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ ዳይሬክተርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተካተቱበት ዓብይ ኮሚቴ ጭምር የአቶ ኤርሚያስ ንብረት መታገዱን የሚያውቁ በመሆናቸው፣ በድጋሚ ንብረት ላሳግድ የሚባልበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

  አክሲዮን ማኅበሩ ሕጋዊ ማኅበር በመሆኑ በየዓመቱ ኦዲት ስለሚያሠራ ያንን ሰነድ በቀላሉ መሰብሰብ እንደሚቻል የገለጹት ጠበቆቹ፣ አቶ ኤርሚያስ በዋስ ቢፈቱ ምንም ዓይነት ጫና ሊያሳድሩ ስለማይችሉ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

  ቤት ገዢዎች የውል ረቂቅ ቀርቦላቸው፣ አንብበውና ተረድተው ውል በመፈራረም ክፍያ የፈጸሙት ቫት፣ ታክስና ማንኛውንም የመንግሥትን ክፍያ እየፈጸመ ከሚገኘው አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ጋር መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ የመርማሪ ቡድኑን ጊዜ ከማጥፋትና የመንግሥትን የጽሕፈት መሣሪያዎች ከማባከን ባለፈ ምንም ነገር ሊገኝ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስም ምንም የፈጸሙት ማታለል እንደሌለ አክለዋል፡፡ ቤት ገዢዎችም እየተናገሩ ያሉት በውሉ መሠረት ቤታቸውን እንዳላስረከቡዋቸው እንጂ እንደተታለሉ እየገለጹ ባለመሆኑ፣ ‹‹ውሉ አልተፈጸመም›› ከተባለም መክሰስ የሚቻለው በፍትሐ ብሔር እንጂ ምንም የወንጀል ፍሬ ነገር በሌለበት የማታለል ክስ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

  በመጀመሪያ ዕይታ ሚዛን የሚደፋ ማስረጃ (Prima Facie Evidence) ሳይኖርና ገና እየተጣራ ባለ ሒደት ‹‹ማታለል ነው›› ብሎ መደምደም የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ምርመራ ሒደትን ያልተከተለና ሕገወጥ የምርመራ ሒደት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ከተጠየቀም መጠየቅ ያለበት ማኅበሩ እንጂ አቶ ኤርሚያስ በግላቸው የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ እንደሌለ የተከራከሩት ጠበቆቹ፣ የተለያየ ወሬ ስለተናፈሰ ሰው በወሬ እንደማይታሰርና ሕጉም እንደሚከለክል አክለዋል፡፡

  ሁሉ ነገር ባለቀበት ሁኔታ ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቅ ምን ሊሠራ እንደሆነ እንዳልገባቸው የገለጹት ጠበቆቹ፣ የቤት ገዢዎች ኮሚቴና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉበት ኮሚቴ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቁት እነሱን ጠርቶ መጠየቅ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ያላቸው አካላት ወሬ በማስወራት ነገሩ እንዲወሳሰብ እያደረጉት እንጂ ቤት ገዢዎች እየጠየቁት ያለው ‹‹ቤታችንን ወይም ገንዘባችንን ስጡን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ለመፈጸም ደግሞ አቶ ኤርሚያስን የመፍትሔው አካል አድርጎ እየሠራ የሚገኘው በቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትሩ በአቶ መኩሪያ ኃይሌ እየተመራው ያለው ኮሚቴ ጠንቅቆ የሚያውቀው በመሆኑ፣ የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ጥያቄው ውድቅ ሆኖ አቶ ኤርሚያስ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

  መርማሪ ቡድኑ ይቀረኛል ያለውን የምርመራ ሒደት በድጋሚ ገልጾ በማኅበሩና በአቶ ኤርሚያስ በግላቸው ያለው የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ ደብዳቤ መበተኑን፣ 40 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ብረት ጂቡቲ ስላለና በርካታ ንብረታቸው በአየር ላይ በመሆኑ እሱን በመከታተል ለማሰባሰብ እየሠራ መሆኑን አስረድቷል፡፡

  ፖሊስ ራሱን ችሎ በራሱ የምርመራ ሒደትና የምርመራ ኤክስፐርቶች የሚሠራ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ምርመራውን እያካሄደ መሆኑን የጠቆመው መርማሪ ቡድኑ፣ ዓብይ ኮሚቴውንም ሆነ ንዑስ ኮሚቴውን በመጠየቅ ሥራውን የሚሠራ ጥገኛ ተቋም አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ በጉዳዩ 630 ባለአክሲዮኖችና 2,500 ቤት ገዢዎች ያሉበት በመሆኑ፣ በጥንቃቄ መመርመር እንዳለበት ጠቁሞ የተወሰኑትን ለምስክርነት ቃል እንደሚቀበል ገልጿል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በአግባቡ ቃላቸውን እየሰጡና ለምርመራ እየተባበሩ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ አስረድቶ፣ ከጠበቃ ጋር እየተገናኙ እንደሆነ እምነት ቢኖረውም ካልሆነ ግን ጠይቆ የሚስተካከልበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁም ‹‹ቃሌን አልሰጥም ወይም ቃልህን አትስጥ ተብያለሁ›› አለማለታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጾ፣ ቃላቸውን እየሰጡ ያሉት በፈቃዳቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ የጠየቀውም ተጨማሪ የምርመራ ጊዝ እንዲፀድቅለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

  አቶ ኤርሚያስ እንዲናገሩ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው፣ ‹‹ምርመራ በመካሄዱ ችግር የለብኝም፡፡ 31 ቀናት የታሰርኩበት ምክንያት ግን ምን ይጎዳል ተብሎ ነው?›› ካሉ በኋላ፣ ግብረ አበር እንደሌላቸውና የኦዲት ሥራውም ዘንድ እንደማይደርሱ ተናግረዋል፡፡ እስከ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ 50 ገጽ የደረሰ ቃል መስጠታቸውንና ቀሪ መስጠት ያለባቸው ቃል ካለ ሌላ 50 ገጽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

  ‹‹በግልጽ ጥፋትህ ይህ ነው ተብሎ ለምን አይነገረኝም?›› በማለት ጠይቀው፣ ምርመራ እንዲሰናከል እንደማይፈልጉ ነገር ግን በጥቅል ሳይሆን እሳቸው የሠሩትን በተናጠል እንዲጠየቁ አመልክተዋል፡፡ የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት መከበር ጥያቄን በሚመለከት እንዳስረዳው ጉዳዩ ዋስትና የማያስከለክል ቢሆንም፣ የተጠረጠሩበት ገንዘብ መጠን 1.4 ቢሊዮን ብር ከመሆኑ አንፃር ዋስትና መፍቀድ ከባድ ስለሚሆን እንደማይፈቅድ አስታውቋል፡፡ ፖሊስ ከጠየቀው ተጨማሪ 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለየካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...