Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ​አገር በቀሉ ኩባንያ ለቤቶች ግንባታ ከወጣው የብረት ጨረታ ራሱን አገለለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጨረታው በሁለት የቱርክ ኩባንያዎች መካከል ሆኗል

  ለቤቶች ግንባታ የሚውል 14 ሚሊ ሜትር ብረት ለመግዛት፣ ለየመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ያወጣው ጨረታ፣ ፍትሐዊ አይደለም በማለት አገር በቀሉ ኩባንያ ስቲሊ አርኤምአይ ራሱን አገለለ፡፡ ሁለቱ የቱርክ ኩባንያዎች ቪልሜክስማና ሜታል ማርኬት ብቻቸውን መወዳደራቸው ታውቋል፡፡

  ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውን 44,075 ቶን አርማታ ብረት ግዢ ጨረታ ሰኞ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከፍቷል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ተከፍቶ ኮንትራቱ ሊፈረም ባልቻለው በዚህ ጨረታ ሲቲሊ ራሱን በማግለሉ ሁለት የቱርክ ኩባንያዎች ብቻቸውን ለውድድር ቀርበዋል፡፡

  ስቲሊ አርኤምአይ ራሱን ያገለለው ከአንድ ወር በፊት ይህንኑ ጨረታ ተወዳድሮ አሸናፊ በመሆኑ ኮንትራት ለመፈረም በሚዘጋጅበት ወቅት፣ ጨረታው ተዘርዞ በድጋሚ  እንዲወጣ በመደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስቲሊ ባቀረበው አቤቱታ ይህ ጨረታ ለሁለተኛ ጊዜ እንደተሰረዘበት በማስታወቅ፣ በአገር በቀል ኩባንያዎች ላይ ትልቅ ችግር የሚፈጥር አካሄድ በመሆኑ ውሳኔው በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

  ቀደም ብሎ በወጣው ጨረታ አገር በቀሉ ስቲሊና ሁለቱ የቱርክ ኩባንያዎች ተወዳድረው ነበር፡፡ በዚህ ጨረታ ስቲሊ  አርኤምአይ በቴክኒክና በፋይናንስ አሸናፊ መሆኑ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኅዳር 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አስታውቆ ነበር፡፡

   ነገር ግን በወቅቱ ሦስተኛ ወጥቶ የነበረው የቱርኩ ሜታል ማርኬት፣ ለመንግሥት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ በጨረታ ሒደቱ ላይ ያለውን ቅሬታ አቅርቧል፡፡

  በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የሚመራው ሥራ አመራር ቦርድ የቱርኩን ኩባንያ ቅሬታ በመቀበል፣ ስቲሊ አሸናፊ የሆነበትን ጨረታ ሰርዟል፡፡ በወቅቱ የቀረበው ቅሬታ ማጠንጠኛ መንግሥት ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች 15 በመቶ የዋጋ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚሆነው ግን አገር በቀል ድርጅቶች በሚያቀርቡት ምርት ላይ 35 በመቶ እሴት ሲጨምሩ ነው፡፡ የቱርኩ ኩባንያ ቅሬታ ስቲሊ 35 በመቶ እሴት ባለመጨመሩ 15 በመቶ የዋጋ ተጠቃሚነት ሊሰጠው አይገባም የሚል ነው፡፡

  ይህንን የቱርክ ኩባንያ ቅሬታ ቦርዱ በመቀበሉ የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ታኅሳስ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የስቲሊን አሸናፊነት ሰርዟል፡፡

  ነገር ግን ስቲሊ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመንግሥት ግዢ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ ባቀረበው አቤቱታ፣ በሕግ የተቀመጠውን 35 በመቶ እሴት እንደሚያሟላ በመተንተን ጨረታው ሊሰረዝ እንደማይገባ አሳስቧል፡፡

  የግዢና ንብረት  አስተዳዳር አዋጅ 649/2001 ለማስፈጸም የወጣው የግዥ አፈጻጸም መመርያ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን እሴት አጨማመር በተመለከተ የተቀመጠውን አሠራር ተግባራዊ ያደረገ መሆኑን በማስረዳት፣ ቦርዱ ያሳለፈውን ውሳኔ በድጋሚ ሊያጤን እንደሚገባ ስቲሊ አርኤምአይ ጠይቋል፡፡

  ነገር ግን ቦርዱ ጨረታው እንዲሰረዝና ሦስቱም የቀድሞ ተወዳዳሪዎች የቴክኒክ መወዳደሪያቸው እንዳለ ሆኖ ዋጋ ከልሰው እንዲያቀርቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

  የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የግዢ ሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ሰለሞን በትረ ጨረታው ሰኞ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከፈተበት ወቅት እንደገለጹት፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋም የዓለም የብረት ዋጋም በመቀነሱ የቀድሞ ተወዳዳሪዎች ዋጋ ከልሰው እንዲያቀርቡ በደብዳቤ ተገልጾላቸዋል፡፡ ‹‹በዚህ መሠረት ሦስቱ ኩባንያዎች ቢጋበዙም፣ ስቲሊ ራሱን አግልሏል፤›› በማለት አቶ ሰለሞን የሁለቱን የቱርክ ኩባንያዎች የፋይናንስ መወዳደርያ ሰነድ ከፍተዋል፡፡

  በጨረታ ቪልሜክስ በአንድ ቶን 308 ዶላር፣ ሜታል ማርኬት ደግሞ 349.50 ዶላር በቶን አቅርቧል፡፡ ስቲሊ ቀደም ሲል በተወዳደረበት ጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ በቶን 18,262 ብር በማቅረብ ነበር፡፡

  ስቲሊ አርኤምአይ በቢሾፍቱ ከተማ በ1.2 ቢሊዮን ብር የብረት ማምረቻ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡ ፋብሪካው በዓመት ከ360,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ብረት የማምረት አቅም እንዳለው ይነገራል፡፡

    

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች