Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  በዚህ የ‹‹ኮሜዲ›› ዘመን ብዙ ሰዎች ቀልደኛ የሆኑ ይመስላሉ፡፡ ለዛሬው ገጠመኜ መነሻ የሆኑኝን አንዳንድ ትውስታዎችን አቅርቤ ወደ ጉዳዬ አመራለሁ፡፡ ዘመኑ የቀልድ አይደል? አንድ ጊዜ ጫማዬን የሚያሳምርልኝ ታዳጊ ከሊስትሮ ሳጥኑ አጠገብ ሁለት ደብተሮች አስቀምጧል፡፡ የልጁ ብልህነት አስደስቶኝ፣ ‹‹ጎበዝ ልጅ በርታ፡፡ ማታ ማታ ትማራለህ እንዴ?›› ስለው በመገረም እያየኝ፣ ‹‹ኧረ እኔ አልማርም፤›› አለኝ፡፡ እኔም ደንገጥ ብዬ፣ ‹‹እነዚህ ደብተሮች የማናቸው ታዲያ?›› በማለት ጠቅየኩት፡፡ እሱም ሳቅ እያለ፣ ‹‹እነዚህ? እነዚህማ የቀን ውሎዬን የምጽፍባቸው ናቸው፤›› አለ፡፡

  ልጁ እንደነገረኝ ከሆነ ከአላፊ አግዳሚው የሚሰማውን ቀልድና ተረብ ደብተሮቹ ውስጥ ይከትባል፡፡ ‹‹ምን ያደርግልሃል?›› ለሚለው ጥያቄ የሰጠኝ መልስ ፈገግ ያደርጋል፡፡ ‹‹ቀልዶች ተጠራቅመው አይደል የኮሜዲ ፊልሞች የሚሠሩት? እኔም የምሰማቸውን ቀልዶችና ተረቦች አጠራቅሜ ካቀነባበርኩኝ በኋላ ፊልም ለሚሠሩ ሰዎች በደህና ገንዘብ እሸጣቸዋለሁ፡፡ ከዚያም ድህነትን ደህና ሰንብት እላለሁ፤›› አለኝ፡፡ በጣም ገርሞኝ፤ ‹‹ለመሆኑ ይኼንን ዘዴ የነገረህ ማነው?›› ስለው፣ ‹‹ከኑሮ በላይ ማን አስተማሪ አለ?›› ሲለኝ ሌላ ጥያቄ አልነበረኝም፡፡ ተሰናብቼው መንቀሳቀስ ከጀመርኩ በኋላ ገርሞኝ ዞር ብዬ ሳየው ምላሱን እያወጣ እያሾፈብኝ ነበር፡፡ ለካ በእኔ ላይ እየተለማመደ ነበር፡፡

  አንድ ጊዜ ደግሞ ሥጋ ለመግዛት መኖሪያዬ አካባቢ የሚገኝ ልኳንዳ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ሥጋ ቆራጩ ቢላውን እያፋጨ፣ ‹‹ስንት ኪሎ?›› አለኝ፡፡ ከመጠኑ በፊት ዋጋው ስንት እንደሆነ ስጠይቀው፣ ‹‹ቴክ አዌይ የቁርጥ 250 ብር፣ የክትፎ 250 ብር፣ የወጥ 200 ብር፣ እዚህ ከሆነ ደግሞ 300 ብር …›› ብሎ ዘረዘረልኝ፡፡ በዋጋው ሥሌት መሠረት የኪሴን አቅም ካገናዘብኩ በኋላ አንድ ኪሎ የቁርጥና አንድ ኪሎ የወጥ ሥጋ አዝዤ ሰውየው መቁረጥ ጀመረ፡፡ በዚህ መሀል፣ ‹‹ለመሆኑ በዚህ ውድ ዋጋ እየሸጣችሁ ገበያ አለ እንዴ?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ሥጋ ቆራጩ ዛሬ ገና ሥጋ የምገዛ መስዬው ይሆን ወይም በሌላ ምክንያት አላውቅም ምኑንም ምኑንም ቆርጦ ሚዛን ላይ ካስቀመጠ በኋላ፣ ‹‹ወይ ጊዜ ድንችና ሥጋ የማይለዩ ይመጡብን ጀመር?›› ብሎ ሲያሽሟጥጥ ቴአትር የሚሠራ ይመስል ነበር፡፡

  በጣም ተናድጄ ስለነበር፣ ‹‹ሰማህ እኔ እኮ ለሥጋ እንግዳ ወይም ባዕድ አይደለሁም፡፡ ከፈለግህ ከበሬው ጭንቅላት እስከ ጭራው ድረስ ያለውን የብልት ክፍል እጠራልሀለሁ፡፡ ስለዚህ ከሽንጥ፣ ከዳቢት፣ ከሳልገኝ አመጣጥነህ ስጠኝ፤›› ብዬ ስንጣጣ ሳቀብኝ፡፡ ሳቁን ከጨረሰ በኋላ፣ ‹‹እንዴት አሪፍ ነህ እባክህ? እኔ እኮ ገበያ አላችሁ ወይ ስትለኝ በሆዴ የማነው ፋራ ብዬሃለሁ፡፡ ሥጋ የምታውቅ ከሆነ ለምን ልኳንዳ ቤት አትከፍትም ነበር?›› ብሎ አላገጠብኝ፡፡ የማንም መቀለጃ መሆኔ እያናደደኝ፣ ‹‹በል በቃህ…›› ስል፣ ‹ኧረ ጌታዬ አትቆጣ፡፡ ውስጥ ገባ ብትል እኮ የአንበሳ ልደት የሚያከብሩ አንበሶች አሉ፡፡ ያውም ሦስት ሆነው አምስት ኪሎ ጥሬ ሥጋ ጨርሰው ሁለት ኪሎ የጨመሩ…›› ሲለኝ በአላዋቂነቴ ይሆን በምን እንደሚቀልድ ሳላውቅ ሒሳቤን ከከፈልኩ በኋላ የሰጠኝን ጉላንጆ ተሸክሜ ተለያየን፡፡ ይኼም አንድ ቀን የኮሜዲ ፊልም ስክሪፕት ይጻፍበት ይሆናል፡፡

  ከላይ እንደገለጽኩት በትውስታዎቼ የጀመርኩት ለዛሬው ገጠመኜ እንዲመች ብዬ ነው፡፡ በቀደም ዕለት ከጓደኞቼ ጋር ምሳ በልተን ቡና እየጠጣን ሪፖርተር ጋዜጣ የያዘ አዙዋሪ መጣ፡፡ ከአዙዋሪው ላይ የተቀበልነው የዕለቱ ጋዜጣ የመጀመርያ ገጽ ላይ ከላይ የሰፈረው ዜና ቀልባችንን ሳበው፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2009 ዓ.ም. ሪፖርት ለፓርላማ መቅረቡን የሚተነትነው ዜና በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለውን የገንዘብ ብክነት፣ ሒሳብ አለማወራረድ፣ የተዝረከረኩ አሠራሮችና በርካታ ግድፈቶችን ይዟል፡፡ ይህ የተለመደና አሳሳቢ የተባለ ችግር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ዝም በመባሉ ዋና ኦዲተሩ መሰላቸታቸውን ዜናው ያስረዳል፡፡ ይህ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር አሁንም መፍትሔ አለማግኘቱ እንደ ዜጋ ያበሳጫል፡፡ ለሙስናና ለዘረፋ የተመቻቹ አሠራሮች መኖራቸው ደግሞ ያስደነግጣል፡፡ ደንብና መመርያ እየተጣሰ የሚፈጸሙ ግዥዎችና የግንባታ ሥራዎች መብዛት ራስን ያሳምማል፡፡ እኔና ጓደኞቼ ዜናውን አንብበን ከጨረስን በኋላ የጦፈ ውይይት ይዘናል፡፡ እልህ በተሞላበት ሁኔታ ነበር የምንነጋገረው፡፡

  ውይይታችንን በፅሞና ሲሰማ የነበረው አንድ ጓደኛችን እኛ በኃይለ ቃል የምንነጋገርበትን ጉዳይ ወዲያው ቀየረው፡፡ ጓደኛችን ይኼንን ሁሉ ዓመት እንዲህ ዓይነት ሪፖርት ቀርቦ እንደነበር አስታውሶ፣ በወቅቱ ይሠራበት የነበረው አንድ የዕርዳታ ድርጅት ውስጥ የሥራ ማስኬጃ ሒሳብ የሚያንቀሳቅስ ሰው በአንድ ወር ውስጥ የ60 ሺሕ ብር ጉድለት ተገኘበት አለን፡፡ ሰውየው መሸት ሲል ውስኪ ቤት ጎራ እያለ መጎንጨት በመልመዱ ምክንያት በአንድ ወር 60 ሺሕ ብሩን አጨብጭቦበታል፡፡   ያገኘውን ሁሉ ጠርሙስ እያወረደ እየጋበዘ፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ፣ ‹‹እስካሁን ያልታየብህ የሒሳብ ጉድለት ከየት መጣ?›› ሲሉት እንደ ቀልድ፣ ‹‹ውኃ ወስዶት ነው፤›› ይላቸዋል፡፡ በእሱ ቤት መቀለዱ ነው፡፡ በአነጋገሩ የተናደዱት ኃላፊ፣ ‹‹ዕምነት በማጉደል ወንጀል ከስሼ አስቀጣሃለሁ፤›› በማለት ሲያስፈራሩት፣ ‹‹እንኳን እኔ አንድ ደሃ  ብዙዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን አጥፍተው ማን ጠየቃቸው?›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ‹‹ሰውየው የዋዛ አልነበሩምና ተከሶ እስራት ተፈርዶበት እስር ቤት ተላከ፡፡ አሁንም ከሳሽና ቀጪ ከሌለ ቢሊዮኖች ጠፉ፣ ሒሳብ አይወራረድም፣ ብክነት አለ፣ ዕርምጃ ይወሰድ የሚል ጩኸት ብቻውን ዋጋ የለውም፤›› አለን፡፡

  ጠያቂና ተጠያቂ በጠፉበት ጊዜ አንጀትን ከማሳረር መቀለድ የሚሻል መሰለኝ፡፡ የዘመኑ የኮሜዲ ፊልም ደራሲያን ምነው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ቢደፍሩ? ነው ወይስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለኮሜዲ አይመጥኑም? ‹‹ቢሊዮኖች የት ኮበለሉ?›› በሚል ርዕስ ኮሜዲ ፊልም ቢሠራ እኮ የሚሊዮኖችን ቀልብ መሳብ ይቻላል፡፡ ከዚያም ሚሊዮን ብሮችን ማፈስ ነው፡፡ አደራ አስቡበት፡፡ በሌላ በኩል በቀደም ዕለት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስና እየተሸሞነሞነ መጠራት የለበትም፣ ይልቁንም ሌብነት ወይም ዘረፋ ነው መባል ያለበት ሲሉ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ኮሜዲው ወደ ትራጄዲ ተቀይሮ መረር ያለ ዕርምጃ የሚወሰድ ከሆነ ጥሩ፣ ካልሆነ ግን የቆሰለ አውሬ እየነካኩ እንዳያስፈጁን አደራ እላለሁ፡፡ የዚህን አገር ውስብስብ ችግር ለመፍታት እኮ ስንት መከራ አለ፡፡ እኛስ ባዶ ሆዳችንን ነው የምንጮኸው፡፡ ጠግበው እንደ አንበሳ ማግሳት የለመዱ ‘ዘራፍ!’ እያሉ ያለ የሌለ ጉልበታቸውን ይዘው ቢነሱ ማን ያስጥለናል? ዘረፋ ላይ በአንድ ልብ ታጥቆ መነሳት ካልተቻለ እኮ አገር እንደሚናጋ ማሰብ ይገባል፡፡ የጠገበና የራበው ጉልበታቸው እኩል አይደለምና፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

  (አባቡ ሥዩም፣ ከቄራ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...