Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ሰላም የሚያስፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ

  ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ሰላም የሚያስፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ

  ቀን:

  በተሾመ ብርሃኑ ከማል

  የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማች ሕዝቦች በሰላም እንዲኖሩ መወሰኑ፣ እጅግ ከፍተኛ ብልህነት የተሞላበት ዕርምጃ መሆኑ አያጠይቅም፡፡ ይህም ሆኖ በአንዱ ወይም በሌላ የተለያዩ ሕዝቦችን በሰላማዊ መንገድ አንድ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ እጅግ ጠቃሚና ተመራጭ ቢሆንም፣ ሰላማዊው መንገድ የሚያስከፍለው መስዋዕትነት እንዳለ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ላይ የነበሩ ሕዝቦች፣ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተከፋፈሉ ሕዝቦች ወደ አንድነት ሲያመሩ መታየት ያለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ለእኛ ችግር መፍትሔ የሚሆነን ግን ታሪካዊ አንድነታችን ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ አንድነት እንደምን ይገለጣል?

  የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አንድነት ታሪክን ገልጠን ስናየው

  በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ አብዛኞቹ ግብፅ ከኢትዮጵያ ቀድሞ ትልቅ መንግሥት የነበራት ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅን ታስገብር እንደነበረ የሚያውቀውም በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ ዛሬ በግብፅ የሚገኙ ጥንታዊ ኮረብታዎችና ቅርሶች በኢትዮጵያውያን የተሠሩ መሆናቸው ሲነገረው ማመን የሚከብደው ይኖራል፡፡ ኤርትራን የምትጨምረዋ ኢትዮጵያ ከግብፅም ባሻገር እስከ ጥንታዊቷ ፐርሺያ ግዛቷን አስፋፍታ እንደነበር ለማወቅ ሲመራመር ልቡን የሚጠራጠርም ሊኖር ይችላል፡፡

  ነገር ግን ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በመላው ዓለም ስመ ገናና፣ እንዲሁም ሰፊ ግዛት የነበራት መሆኗን ጥንታውያኑ የግሪክ፣ የሮማ፣ የባይዛንታይን፣ የፊንቅ፣ የቻይና፣ የዓረብ ታሪክ ጸሐፊዎች በሰፊው ጽፈውላታል፡፡ በምሥራቅ አፍሪቃ የሥልጣኔ ጮራን የፈነጠቀች አገር መሆኗን አሁንም (በተለይም በአክሱም፣ በአዱሊስ፣ በመጠራ፣ በቋሐይቶ፣ በይሓ፣ በእንደርታ፣ በውቅሮ፣ በላስታ፣ በጎንደር፣ ወዘተ) ያሉ ቅርሶቿ ያረጋግጣሉ፡፡ ወደፊት ተቆፍረው የሚወጡና ታላቅነቷን የሚመሰክሩ መረጃዎችም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ እንደሚወጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የአንዳቸው ታሪክ ያለ አንዳቸው ታሪክ የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡

  ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድነት ጥቅል የማንነት ጥያቄን መፈተሽ ያስፈልጋል

  በመሠረቱ ማንነት በእናት ማኅፀን፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በአካባቢ፣ በቀበሌ፣ በአገር የሚዳብር ሲሆን፣ በአገር ደረጃ የሚገኘው አገራዊ ባህርይ ይባላል፡፡ በአገራዊ ደረጃ ከሚከሰቱት የማንነት መገለጫ ባህሪያት አንዱ ብሔራዊ ኩራት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ 1985 ዓ.ም. እስከ 1988 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በሰሜን ትግራይ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ ለብዙመታት በጦርነት እየታመሰ ፍዳውን ያይ የነበረ ሕዝብፎይታ አግኝቶ ነበር፡፡ ከዛላ አምበሳ ወደ ሰነዓፈ፣ ከዓድዋ ወደ አድቀይህ፣ ከሽሬ ወደ ሰራዬ፣ ከሌሎች ሥፍራዎች እየተነሳ ይንቀሳቀስ የነበረው ሕዝብ ጦርነት ያስከተለውን ችግር በአጭር ጊዜ ረሳ፡፡ በጣሊያን ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ተለያይተው የነበሩ ወንድማማቾችና እህታማቾች፣ አባትና ልጆች፣ ባልና ሚስቶች እየተገናኙ ደስታቸውን ገለጡ፡፡ ለመንግሥታቱም ምሥጋና አቀረቡ፡፡ ድሮውንም የነበረው የጋብቻ ትስስር ቀጠለ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገበያ መጥቶ መነገድም ሆነ ወደ ኤርትራ ድንበር ገበያ ሄዶ ነግዶ መመለስ መዘውተር ጀመረ፡፡ ከጦርነቱ በፊት አንድ የነበረው ሕዝብ ያኔውኑ እንደነበር አንድ ሆነ፡፡

  የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ውጤትን በሚመለከት ሚያዝያ 21 ቀን 1985 ዓ.ም. ከቀኑ 800 እስከ 1200 ባካሄደው አምስተኛ አስቸኳይ ሰብሰባው ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ በከፍተኛ ድምፅ ሲያፀድቅ፣ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በሰጡት የግል አስተያየት እንደሚከተለው ተናግረው ነበር፡፡

  እያንዳንዱ የራሱ የሆነ አመለካከት አለው፡፡ እኔ አሁን የምናገረው የራሴን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ለመግለጽ የምፈልገው በሪፖርቱ ላይ የሪፈረንደሙ ውጤት የአንድ ፖለቲካ ታሪክ ፍፃሜ ነው ስለመባሉ ነው፡፡ በእርግጥም የአንድ ፖለቲካ ታሪክፃሜ ነው፡፡ ነገር ግን የታሪክ መጀመርያም መጨረሻም አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት ታሪክ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ይኖራል . . . 50 ዓመታት በፊትም፣ በኢጣሊያ ጊዜም፣ በፌዴሬሽኑ ወቅትም፣ በዘውዳዊውና በደርግ አገዘዝ ሥርም፣ በሽግግር መንግሥቱ ወቅትም ብዙ የፖለቲካ ክስተቶች ተለዋውጠዋል፡፡ ነገር ግን ከታች ያለው መሠረታዊ የሕዝቦች ግንኙነት ግን አልተለወጠም፡፡ እርግጥ እነዚህ መሠረታዊ ግንኙነቶች በአንዳንድ የፖለቲካ ፍፃሜ ባህርያቸውን ሊቀይሩ ባይችሉም ደግሞ ሊደበዝዙ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ነዚህ መሠረታዊ ግንኙነቶች ላይ በየቀኑ ቦምብ በሚወርድበት ወቅት መደብደባቸው አይቀርም፡፡ በመጀመርያ የሚታየው፣ በመጀመርያ የሚታሰበው የሚወርደው ቦምብ ነው፡፡ አብሮ የሚፈጠር ቁስል ነው፡፡ ቦምብ የሚበጣጥሰው አካል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የጦርነት ግንኙነት በሚኖርበት ጊዜ ከሥር ያሉት ዘላቂ የሆኑት መሠረታዊ የሆኑ ግንኙነቶች ይደፈናሉ፡፡ በደም ይሸፈናሉ፡፡ ይህ የደም ደመና በሚለቅበት ጊዜ ከሥር ያሉት ግንኙነቶች የሚገኙት እዚያው ሆነው ነው . . . አሁን ያለው እውነት በደም ደመና ተሸፍኖ የነበረ፣ ነገር ግን እየተለወጠ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

  አዎን አገር ማለት፣ ታሪክ ማለት፣ ባህል ማለት፣ ማኅበራዊ ሕይወት ማለት ማንነት ነው፡፡ ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ስንል ‹‹እኔ አገሬ ነኝ፣ እኔ ታሪኬ ነኝ፣ እኔ ባህሌ ነኝ›› እንላለን፡፡ ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያውያን ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ብለን እንጠይቅና ‹‹እኔ የኢትዮጵያ ጥንታዊና ዘመናዊ ኅብረተሰብ ማኅበራዊ ሕይወት ቅሪት ነኝ›› የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ እንግሊዝ አገር ቢቀመጥ፣ ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝ ዜግነት ቢሰጠው፣ ስለእንግሊዝ አገር ማወቁና ለእንግሊዝ ሕገ መንግሥት ማደሩ የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ ሰብዕናውና ውስጣዊ እኔነቱ ግን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለብዙ ዓመታት ወደ አሜሪካ የሄዱ፣ ለአሜሪካ የሠሩ፣ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አፍሪካውያን የጥንት ትውልዳቸውን የሚቆጥሩትና ከዚህ ጋር የተያያዘ የሚሠሩት ማንነት በትውልድም የሚወረስ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

   

  ለመሆኑ ‹‹እኔ ማን ነኝ?›› ብሎ መጠየቅና ራስን ማወቅ ምንድነው?

  በመሠረቱ አንድ ሰው በማንነቱ ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሌላ ለመሆን ቢፈልግ እንኳን በውስጡ ያለው ማንነቱ ‹‹አለሁ›› ብሎ ሳያውቀው አፈትልኮ ይመሰክርበታል፡፡ ሌላ የሆንን ቢመስለንም ማንነታችን ይከተለናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ በግል አመለካከታቸው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ›› ‹‹አይደለህም›› ሊባባሉም ይችላሉ፡፡ ሁለቱ በተናጠል ወይም በጋራ ከሌላ ሰው ጋር ሲወያዩ ሌላ ሰው በሁለቱ መካከል በሐሳብ አቀራረብ፣ አገላለጽ፣ በሥነ ምግባር፣ በእንቅስቃሴ ልዩነት ላያይ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር አንድ ምዕራብ አፍሪካዊ ወይም ደቡብ አፍሪካዊ ዘግይቶ ቢመጣና ቢቀላቀል ግን የተለየ መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሱዳን፣ የግብፅ፣ የጂቡቲና የሱማሌ ተወላጆች ቢኖሩ የሱማሌና የጂቡቲዎቹ ሰዎች ከሱዳኖቹና ከግብፆቹ ይበልጥ ተመሳሳይ ባህርይ ይኖራቸዋል፡፡

  ዊልያም ጀምስ የተባሉ የሥነ ባህርይ ሊቅ (1892 ዓ.ም.) እኔነት ሁለት ደረጃዎች አሉት ይላሉ፡፡ አንደኛው ራስን የማወቅ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ራስን በሒደት ማወቅ ነው፡፡ ራስን ማወቅም ቁሳዊ እኔነት፣ ማኅበራዊ እኔነትና መንፈሳዊ እኔነት እንደሆኑ ዊልያም ጀምስ ይተነትናሉ፡፡ ማኅበራዊ እኔነት (ማንነት) ሌሎች ስለእርሱ የሚረዱት ሲሆን፣ ቁሳዊ ማንነት ደግሞ የእኔ ባዩ አካልና የእርሱ ንብረት ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ ማንነት ደግሞ በውስጡ የሚሰማው የእኔነት ስሜቱ ነው፡፡ ‹‹እውነተኛ ማንነት በውጪ ከሚንፀባረቀው ጋር ይወዳደራል (ይመሳሰላል) ማለት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ሮይ ኤፍ ባውመስተርና ማርክ ሙራቬን ‹‹ማንነትን ከማኅበራዊ፣ ባህላዊና ከታሪካዊውድ ጋር ማዋሃድ (ማስማማት) በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ግለሰብ ሊመርጥ፣ ሊለውጥ፣ እንደሚመቸው አድርጎ ለማሻሻል ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚያ የግለሰብ ማንነትልውና እንዲኖረው ታሪክ፣ ባህልና ተቀራራቢ ማኅበራዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

  ነገር ግን ምንም ያህል ተመሳሳይነት ቢኖር የተዘራ ጥላቻ ካለ፣ የእርስ በርስ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ካለ፣ መከዳዳት ካለ፣ ጥላቻ፣ የፈሰሰ ደም፣ ክህደት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሊደበዝዝ ይችላል፡፡ ወይም በአንድ አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሦስት አራት (መቶም፣ ሺም ሊሆን ይችላል) ኢትዮጵያውያን አካባቢያቸውን ትተው  ወደ ሦስትና አራት ቦታዎች (አውሮፓ፣ ቻይና፣ አላስካ፣ ወዘተ) ቢሄዱ ለጊዜው አነጋገራቸው፣ አለባበሳቸው፣ አመጋገባቸው፣ አኗኗራቸው፣ ወዘተ ሊቀየር ይችላል፡፡ ተመልሰው ሲገናኙም ብዙ የተለወጡ ሊመስል ይችላል፡፡ ይህ አዲስ ማንነት ግን እንደ ጭምብል ቢሆን እንጂ ማንነትን የሚያጠፋ አይደለም፡፡

  ስለማንነት ጉዳይ በርካታ ሊቃውንት ከጥንት ጀምሮ አስተያየታቸውን፣ ምክራቸውን፣ ፍልስፍናቸውንና አመለካከታቸውን ሰጥተውናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ግርሃም ግሪን የተባለውውቅ ደራሲ ሲሆን፣ እርሱም ‹‹የጉዳዩ ማለቂያ›› (The End of the Affair) በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ፣ ‹‹የሚያሰኝህን ሁሉ ብትጥል ምን ትሆን ይሆን?›› ማለቱ ይጠቀሳል፡፡ መልሱም ከ‹ሁለት ያጣ ጎመን› የሚል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ የኢጣሊያ ቅኝ ገዥ መንግሥት ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ውጪ የሆነ ሰው ሠራሽ ማንነት ቢሰጠው ማንነት ላይ ላዩን ሊገለጥ በሚችል ባህርይው ሊያንፀባርቅ ቢችል እንጂ፣ በውስጡ ሌላ ሊሆን አይችልም እንደ ማለት ነው፡፡ ወይም በተለምዶ ተዋናይ ቋሚ የሆነ ማንነቱን የማወቅ ችግር አለበት እንደሚባለው ነው፡፡ በእርግጥም አንድ ተዋናይ እንደተላበሰው ገጸ ባህርይ ላዕላዊ ማንነቱ ሊለዋወጥ እንደሚችለው ሁሉ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎችም ያልሆኑትን ልሁን ቢሉ የራሳቸውን ማንነት ሊጠፋባቸው ይችላል፡፡ ግሬይ ፉል የተባሉ የሥነ ባህርይ ሊቅም ይህን በሚለከት ‹‹የትናንቱ እኔ ከዛሬው እኔ ጋር ሥነ ባህሪያዊ ግንኙነት አላቸው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

  በአንድ ታላቅ ሰው የተፈጸመ አንድ ተጨባጭ ምሳሌ እንይ፡፡ ፕሮፌሰር አብርሃም ደሞዝ የተባሉ ዝነኛ ምሁር፣  ‹‹ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት ኤርትራውያንን ቢጨቁንም፣ የደርግ መንግሥት ደግሞ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ቢያካሂድም፣ እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ ልሆን አልችልም፤›› ብለው ሐምሌ 13 ቀን 1986 ዓ.ም. አሸልበዋል፡፡ አስከሬናቸውም ከአሜሪካ (ኖርዝ ካሮላይና) መጥቶ ቅድስትላሴ አርፏል፡፡ ሌሎች ከእርሳቸው ጋር ተመሳሳይ አቋም ያሳዩት አርዓያነት ያለው ተግባር ታላቅ ስለሆነ ክብር ሲሰጣቸውና እንደ አብነት ሊወሰዱ ይገባል፡፡ የማንነት ምንነትን በተጨባጭ ለማሳየት እንዲቻል ቀደም ሲል የቀረቡትሳቦች በምሳሌነት ቀረቡ እንጂ፣ ከዚህ ሰፋ ባለ መንገድም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ማንነት በረዥም የታሪክደት የሚዳብርና ይህም በተለያዩ ባህሎችና አስተሳሰቦች የሚገለጽ መሆኑ ነው፡፡

  ለምሳሌ በአንድ ኑክሌር ፊዚክስ የተራቀቀ ኢትዮጵያዊ ምንም ያህል ለረዥም ጊዜ በውጭ አገር ቢኖር የሳይንስ ክህሎቱ፣ የአካሄዱ፣ የአነጋገሩ፣ የአለባበሱ፣ ወዘተ መገለጫዎች ከሌሎች አገሮች ሳይንቲስቶች ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም፣ የሐዘንም ሆነ የደስታ፣ የፍቅር፣ የጥላቻ፣ ስሜቱን የሚገልጽባቸው ባህሪያቱ ከእርሱ ጋር ናቸውና የሚገለጹት እንደ ሳይንሳዊ ትንተናው አቀራረብ አይደለም፡፡ የሚገለጹትጅብ እንዳገሩ ይጮኻልእንዲሉ በወላጆቻቸው፣ በወገኖቻቸው በአገራቸው መንገድ ነው፡፡  ተመሳሳይ የአንድ ምዕራባዊ ማንነት ራሱን በማስቀደም ወይም ‹‹እኔ፣ ለእኔ›› በሚል ላይ የተመሠረተ ቢሆን፣ የኤርትራውያን ማንነት ግን እንደ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ‹‹እኔ ለቤተሰቤ፣ እኔ ለወገኔ፣ ቤተሰቤም ለእኔ፣ ወገኔም ለእኔ›› በሚል የመደጋገፍ፣ በይሉኝታ፣ በትህትና፣ በመተሳሰብና ለሌላውድሚያ በመስጠት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡

  እርግጥ ነው ማንነት ቀደም ሲል በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንደተጠቀሰው ሁሉ ለጊዜው ሊሸፈን፣ ሊደበዝዝ፣ የሌለ ሊመስል ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ ውስጥ በዘመናዊ ሥልጣኔ ምክንያት በርካታ ዋና ዋና ባህላዊ እሴቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ ለምሳሌ ወላጅ ሲሞት እንደ ኢትዮጵውያንና ኤርትራውያን ማዘን፣ ከዘመድ አዝማድ ጋር ተሰባስቦ በተንጣለለ የመኪና መንገድ ላይ ድንኳን ጥሎ ወይም ዳስ አዘጋጅቶ፣ ለሦስት አራት ቀናት አስተዛዛኝ ሆኖ መቆየት፣ መንገዱ የተዘጋበትም ነግ በእኔ ብሎ በሌላ በኩል ዞሮ መሄድ፣ ወይም እስከ ጭራሹ መኪናውን ሩቅፍራ ትቶ በእግሩ መኳተን ላይኖር ይችላል፡፡ አንዳንዱም የእናቱን አስከሬን ሆስፒታል በሚገኝ በረዶ ቤት አስቀምጦ የዕለት ሥራውን ካከናወነ በኋላ በተመቸው ሰዓት ሊቀብር ይችላል፡፡ እናት ነበረች፣ ዕድሜዋ ሲደርስ መሞቷ አይቀርም ሞተች፡፡ በቃ፡፡ ይህ ለአውሮፓውያን በጣም ቀላል፣ ለኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ደግሞ የሚከብድ ነው፡፡ ይህም ባውሜይሰር እንደሚሉት የእሴት ክፍተትን ፈጥሯል፡፡

  በአውሮፓ ሰዎች ሕግም፣ ደንብም፣ መመርያም፣ መሥፈርትም ሳያስፈልጋቸው ሲያከናውኗቸው የነበሩት ዘመናዊ ቢሮክራሲ ተተክተዋል፡፡ በኮምፒዩተር ውስጥ ገብተው በጣቶች ቁልፎችን በመነካካት ውሳኔ የሚሰጣቸውና የሚከናወኑ ሆነዋል፡፡ መሬት ላይ ሆኖ ወደ ሰማየ ሰማያት የሚተላለፉት መልዕክቶች በጣቶች በመነካካት ሆኗል፡፡ በአውሮፓውያን ዘንድ የወላጅና የልጅ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላላ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ዕድሜው/ዕድሜዋ 18 ዓመት ከደረሰ የራሱን ዕድል በራሱ ይወስናል፡፡ ይህን አድርግ፣ ይህን አታድርግ የሚለውን ምክር ሊቀበለውም ላይቀበለውም ይችላል፡፡ ይህም የባህላዊ እሴት ክፍተትን ፈጥሯል፡፡ የባልና ሚስት ግንኙነት በኢኮኖሚ እኩልነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በቃል ኪዳን ፀንቶ መኖር ወይም አለመኖር የድሮ ወግ ሆኗል፡፡ ልጅ ለመውለድ የምትሻ ሴት ከወንድ ጋር ሳትተኛ፣ ማንነቱም በውል ከማታውቀው ሰው የምታገኘውንምና ማርገዝ ትችላለች፡፡ አዎን የወንድ ዘርሩን ከሆስፒታል ወይም ከሚሸጥ ድርጅት ከገዛች ደግሞ ‹‹የምን ባል ነው! ባል ለራሴ!›› የሚል አስተሳሰብ የእሴት ክፍተትን ፈጥሯል፡፡ ወንድና ወንድ እንዲጋባ ሕጉ ከፈቀደ ሚስት ብሎ ሴት፣ ባል ብሎ ወንድ ነገር ስለማያስፈልግ የባህል ክፍተት ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ክፍተቶች እስካሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን ዘንድ እጅግ የተጠሉ ናቸው፡፡ እንደ መሠልጠንም፣ እንደ ዘመናዊነትም አይታዩም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ ቅር ሊሰኙ ይችላሉ፡፡

  ዋናው ቁም ነገር ስለተለያየው ፖለቲካ ሳይሆን ስለተለያየው አባትና እናት፣ ስለተለያየው ወንድምና እህት፣ ስለተለያየው ዘመድ አዝማድ ማስብና ለዚያ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሰዎች መለያየት ከውስጣችን ሊሰማን ይገባል፡፡ ‹‹እኔ ብለይስ?›› ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ያን አስበን ምን መደረግ እንዳለበት ስናውጠነጥን፣ ከሁሉ አስቀድሞ በሕዝቦች መካከል መርዘኛ ጥላቻ ከመዝራት መቆጠብና በጥላቻ ምትክም የፍቅርንና የአንድነንትን ችግኝ መትከል ነው፡፡

  ለመሆኑ ጥላቻ ምንድነው?

  ጥላቻ የሰው ልጅ የገነባውንሕይወት ድር ከመበጣጠሱም በላይ፣ ማኅበራዊ ይዘትና ቅርፅ ከያዘ መዘዙ በቀላሉ የማይነቀል መርዝ ነው፡፡ በጥላቻ መንፈስ የተመረዘ ኅብረተሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮው ድርና ማግ እየተሸማቀቀ ወደ ድህነት መዘቅዘቁ አይቀሬ ነው፡፡ በሰዎች መካከል ጥላቻን ማስፋፋት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ አንዳንድ ምሳሌዎችን በመጠቃቀስ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በመጀመርያ ጥላቻ ምንድነው? ጥላቻ ከፍርኃት ወይም ከመንፈስ መጎዳት የሚመነጭን ይህንን ሁሉ የሚገልጥ ስሜት ነው፡፡ አንድን ነገር በመረረ ሁኔታ አለመውደድና ነገሩ ሥር ሰዶ ለመበቀል የሚያነሳሳ ድርጊትም ነው፡፡ ጥላቻ በአንድ ነገር ውስጥ ጥሩ ነገር ቢኖር እንኳ ያንን መልካም ገጽታ የሚከልል ጠንካራ የስስት መጋረጃ ነው፡፡ ስሜቱ በጥላቻ የተጋረደም ለጥፋት እንጂ ለልማት ከቶ ሊነሳሳ አይችልም፡፡ አንዱን በመጥላቱ ምክንያት ሌላው ከእሱ (ከዚያ ከሚጠላው) ጋር የተያያዘ መሆኑን ጭምር ይረሳዋል፡፡ ለምሳሌ ወተት የማይወድ ሰው ከወተቱ ጋር የተያያዘውን ጥቅም ሁሉ ሊያስታውሰው እንደማይፈልግ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ይህም በወተት ውስጥ ምን ቢሆን ጥቅም ሊኖረው አይችልም ብሎ እንደ ማሰብ ይሆናል፡፡ ይሁንና አንድ ሰው በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወተትን ቢጠላ ደግሞ ሌሎች እንዲጠሉት ማድረግ ለራሱም ቢሆን አይበጀውም፡፡ በማኅበራዊ ኑሮም ቢሆንም ግለሰብን በግል መጥላት አንድ ነገር ሲሆን፣ ኅብረተሰብን በጅምላ መጥላት ግን ለራስም ቢሆን የሚሰጠው ፋይዳ አይኖርም፡፡ ያለፈን ያረጀንና ያፈጀን በግል መጥላት ይቻላል፡፡ የሚጠሉትን ነገር እየደጋገሙ መጥላት ግን ለመውደድ ሊተው ይችላል፡፡ የነበረውን ጊዜ በከንቱ ማጥፋት ይሆናል፡፡ ከመረረ ጥላቻ ተነስቶ አንዱ ባለ ጊዜ፣ ጊዜ የጣለውን እያወገዘና እየተሳደበ ቢውል ሰሚ ‹‹እንዲህም እባል ነበር›› ማለቱ በፍፁም የማይቀር ይሆናል፡፡ 500 እስከ 250 .ዓ. የነበረው ሱታፒታክ፣ ‹‹ጥላቻን ጥላቻ ባልተከተለ እንጂ በጥላቻ መንገድ ከቶ ማስወገድ አይቻልም፤›› ብሎ ነበር፡፡ ቢቻል የደርግ መንግሥት ለአሥራ ሰባት ዓመታት ያህል ከኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ወደፊት ያለውን ሁሉ እጅግ በመረረ ጥላቻ ዓይቶ ነበር፡፡ እሱ ራሱ ጥላቻን ሲዘራ በሕዝብ የሚያስፈቅር ተግባር ለማከናወን ጊዜ በማግኘቱ ግን አይወድቁ አወዳደቅ ወደቀ፡፡

  ጥላቻ የመረረ ከሆነ በትንሹና በትልቁ መቆጣትና መበሳጨትን ያስከትላል፡፡ ይህም ቀጣይ ባህርይ መርዝ እንደበሉ ሁሉ እያቅበዘበዘ ፈፅሞ ያላሰቡትን መጥፎ ድርጊት ያስፈጽማል፡፡ ከወዳጅ ምክር ይልቅ የጠላትን አሳሳች ምክር እንዲከተሉ ያደርጋሉ፡፡ ሁሉም በጅምላ ተጠራጣሪ በማድረግ ወደር የለውም፡፡ ጥላቻው የፍቅር ግልባጭ ቢሆንም እንኳ ያለፈውን ጥሩ ጥሩ ነገር ለማስታወስ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ኦቴሎ የሚያፈቅራትን ዴዝዲሞና በሁለት እጆቹ ፈርጥቆ እንደ ገደላት ማለት ነው፡፡

  ጦርነት የሚያስከትለው ጥላቻ

  በየትኛውም አገር እንደታየው ድሮውንም የሕዝብ ጥላቻ የሚፈጠረው በጦርነት ነው፡፡ አንዱ ጦረኛ ሌላውን ድል አድርጎ ሲይዝ ሌላ ጥላቻ ይወለዳል፡፡ በተጠቃለለ መልኩ ጥላቻ ያለፈ ስህተት ተብሎ ካልተተው በስተቀር ተሸናፊው ወገን አንገቱን እንዲደፋ የጥላቻ መርዝ መርጨት ሌላ ጥላቻን ከመውለድ በስተቀር ፍቅርን አያመጣም፡፡ የተጣላው ሲያምፅና እንደገና በኃይል ለማንበርከክ ጥረት ሲደረግና የማይቀረው ጦርነት በአዲስ መልክ ይቀጥላል፡፡

  አንቷን ቼኾቭ (1860 እስከ 1904 ..) “ፍቅር፣ ጓደኝነትና መከባበር የጋራ ጥላቻን ያህል ሕዝብን አያስተባብርምእንዳለውም ሆኗል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ያረጀውን መጥፎ ጥላቻ ለታሪክ ማኅደር ሰጥቶ ሕዝብን አረጋግቶና አስማምቶ ማስተዳደር መቻል ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ያለፈውንርዓት ለማስወገድና ዴሞክራሲያዊርዓት ለመዘርጋት ሲባል የተከፈለው መስዋዕትነት፣ ጥላቻን አስወግዶ በሕዝቦች መካከል የፍቅርን ነፍስ የሚዘራ መሆን ይኖርበታል፡፡ የድሮ አገዛዝ መጥፎ ከሆነ የአሁኑ አስተዳደር የሚሻል መሆኑን በተግባር ማሳየት ይገባል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እኮ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጠቀሰው /1517/ ጥል ካለበት ከሰባ ፍሪዳ ይልቅ ጎመንን በፍቅር መመገብ በአያሌው ይመረጣል፡፡ እ.ኤ.አ. 1865 እስከ 1915  የነበረችው ጀርመናዊቷ ኤዲዝ ከቬል፣አርበኝነት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ በማንም ላይ ጥላቻና ምሬት ሊኖረኝ አይገባም›› ያለችውም ለሕይወታችን ታላቅ ምሳሌ ሊሆን ይገባል፡፡

  ጦርነት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች ተካሄዷል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ሥልጣኑን የያዙ በሳል መሪዎች ሲኖሩ ግን የሕዝብ አስተሳሰብ ወደ ልማት ያተኩራል፡፡ ብዙ የባህል፣ የልምድና የመሳሰሉት ልውውጦች ስለሚኖሩ ጋብቻና መዋለድ ስለሚከተልም ሁኔታውን ለፍቅር ያመቻቸዋል፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገር ሰው ያንን ቋንቋ ከሚናገር ብሔረሰብ ጋር፣ አንድን ሃይማኖት የሚከተል ሰው ያንን ሃይማኖትሚከተሉ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊፈጥር ከመቻሉም በላይ፣ ራሱን ከአንዱ ወይም ከሌላው ጋር በማመሳሰል የጥቅምም ሆነ የጉዳት ተካፋይነትሜት ያድርበታል፡፡ በተለዋጩም አንድን ቋንቋ የሚናገር ግለሰብ ጋር አንድን ሃይማኖት የሚከተል ማኅበረሰብ ያንን ሃይማኖት ከሚከተል ግለሰብ ጋር ራሱን በቀላሉ ለማመሳሰልና የጥቅምና የጉዳት ተከፋይነት ስሜት ሊያድርበት ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ኦሮሞ የተነካ እንደሆነ መላ ኦሮሞ እንደተነካ፣ እንዲሁም አንድ አማራ የተነካ እንደሆነ መላ አማራ እንደተነካ አድርጎ በማቅረብ በቀላሉ ትርምስ ለመፍጠር ይቻላል፡፡ ተነካ የተባለው ግለሰብ የብሔረሰብ ወይም የሃይማኖት መሪ በሚሆንበት ጊዜ የሰውን ስሜት ለማነሳሳት ቀላል ነው፡፡ ከግለሰቡም አልፎ ድርጅትን ወይም እምነትን (ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያንን ወይም የክርስትና ሃይማኖት) የሚነካ ከመሰለ ቆም ብሎ ለማሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡

  ይኼንን የመሳሰሉ ነገሮች በመጠቀም በውሸትም ቢሆን የሰውን ስሜት ውጥረት ውስጥ ለማስገባት ይቻላል፡፡ በሰዎች መካከል የሚመሠረት ጥላቻ በማስታወስ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ ተጨባጭ ነገሮች ቢኖሩም ባይኖሩም በብሔረሰቦች ወይም በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ወይም በተለያዩ ሰዎች መካከል ከረዥም ዘመናት በፊት የነበሩ አለመግባባቶች ለአሁኑ ጥላቻ መሠረት ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ ፍራንሲስ ቤከን (1561-1626) እንዳለው መኮሳተርና መቆጣት ፍርኃትን፣ ጭካኔ ግን ጥላቻን እንደሚፈጥር ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ መፍራትም ቢሆን ፊት ለፊት ካልሆነ በስተጀርባ የተፈራራውን ስም በጥላቻ እንደሚያስነሳ የታወቀ ነው፡፡

  የሰዎች ጥላቻ የመጨረሻ ደረጃ

  በመጀመርያ ደረጃ ጥላቻና ቅራኔ እየተስፋፋ በሚሄድበት ሁኔታ የሰው ልጅ መደበኛሜቶች ማለትም መዝናናት፣ ማመዛዘን፣ ማምረት፣ የዕለት ተግባርን ለማከናወን አለመቻል፣ ወዘተ ሲኖር ሥጋት፣ ውጥረት፣ ለጠብ በመዘጋጀትና በውግዘት ይተካል፡፡ ጥላቻ እንደ አሜባ የመስፋፋትና የማደግ ባህርይ ስላው ኅብተረሰብን ወደ ግጭትና ትርምስ ያደርሳል፡፡ ጦርነት ደግሞ በቅድሚያ የሚበላው ወጣቱን ክፍል ስለሆነ የመሻሻልና የማደግ ዕድል አብሮ ያከትማል፡፡ በአንድ በኩል ወጣቱ ትኩስ ኃይል፣ በሌላ በኩል አጥፊ መሣሪያ በግጭት አውድማ ላይ ስለሚገናኙብረተሰብን ገደብ ለሌለው ጥፋት ይዳርጋል፡፡ ልዩነቶችን በጦር ሜዳ ለመፍታት ለመሞከር ለሚቀጥለው ግጭት መሠረት መጣል እንጂ፣ ችግሩን ከመሠረቱ ማስወገድ አይደለም፡፡ የጦርነት ሎጂክ ሌላ ሎጂክ እየወለደ የአምራችነት ሳይሆን የጦረኝነት ባህል ተስፋፍቶብረተሰብን ጉዳት ላይ ይጥላል፡፡ በሰዎችና በሰዎች በብሔረሰብና በብሔረሰብ መካከል ጥላቻ በሚስፋፋበት ሁኔታ ጉዳት የሚደርሰው በሰዎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ዕፅዋት፣ አዝርዕት፣ እንስሳት፣ ከባቢ አየርና ሌሎችም የሰው ሕይወት የተመሠረተባቸው ነገሮች ሁሉ ጉዳት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ መሬት የተፈጥሮ ፀጋውን የተገፈፈው አካባቢው ለብዙ ምዕተ ዓመታት የጦርነት አውድማ በመደረጉ ምክንያት ጭምር መሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ መንግሥትና የውጭ ወራሪ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረጉ ጦርነቶች ምንጮች እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡

  ስለዚህ ወደዝቦች አንድነት ለመጓዝ አስቀድመን የጥላቻን መርዝ ማፅዳት ይገባል፡፡ ይህም ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲገናኙ ነፃ እናድርጋቸው፡፡ ሕዝቦች በነፃ እየተገናኙ መነጋገር፣ መነገድና ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ለመመሥረት በሚበቁበት ወቅት በመጀመርያ ሕዝባዊ ውህደት፣ ቀጥሎም ኢኮኖሚያዊ ውህደት፣ በመጨረሻም ፖለቲካዊ አንድነት መምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህን እያደረግን የሕዝቦችን የአንድነት ታሪክ መሥራት እንጀምር፡፡ ይሳካልናል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...