Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊ​በሕገወጦች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ያስችላል የተባለ የኮንዶሚንየም ቤቶች ቆጠራ እሑድ ይጀመራል

  ​በሕገወጦች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ያስችላል የተባለ የኮንዶሚንየም ቤቶች ቆጠራ እሑድ ይጀመራል

  ቀን:

  ባለፉት አሥር ዓመታት ለነዋሪዎች የተላለፉ 102 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ፣ እሑድ የካቲት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቆጠራ ሊጀመር ነው፡፡ የቆጠራው ዓላማ በሕገወጦች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ነው ተብሏል፡፡

  በዘጠኝ ዙር ለነዋሪዎች ከተላለፉት መካከል በሕገወጦች የተያዙ ቤቶች በመኖራቸው በቆጠራው በሚሰበሰቡ መረጃዎች መሠረት ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል፡፡

  የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝና የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቴ ቆጠራውን በሚመለከት ማክሰኞ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

  አቶ ይድነቃቸው እንደገለጹት፣ የግል ቤት እያላቸው ኮንዶሚንየም የያዙ፣ የቀበሌ ቤት ውስጥ እየኖሩ ኮንዶሚኒየም ቤት ይዘው የሚያከራዩ፣ የራሳቸውን ይዞታ ለሦስተኛ ወገን አስተላለፈው ኮንዶሚኒየም የያዙ፣ ኮንዶሚንየም ቤቶችን በኃይል ሰብረው በመግባት የያዙና የማይገባቸውን ቤት ቀላቅለው በመሥራት ደብዛውን ያጠፉ አካላት አሉ ተብሏል፡፡

  ‹‹ቆጠራው ተሰብስቦ በሚተነተነው መረጃ አማካይነት በእነዚህ ሕገወጦች ላይ ዕርምጃ ይወስዳል፤›› በማለት አቶ ይድነቃቸው የቆጠራውን ዓላማ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ከባንክ ጋር ያለው ውልና አስተዳደር ዘመናዊ ቅርጽ ባለመያዙ፣ ዕዳቸውን መክፈል ያቆሙ ባለቤቶች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ይድነቃቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘጠኝ ዙር ዕጣ 102 ሺሕ ቤቶች አስተላልፏል፡፡ ባለፈው ዓመት መጋቢት ባወጣው አሥረኛው ዙር ዕጣ፣ 35 ሺሕ ቤቶች ለነዋሪዎች በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ቤቶች ላይ ቆጠራው ተግባራዊ አይሆንም፡፡

  የአሁኑ ቆጠራ የሚካሄደው እስከ ዘጠነኛው ዙር ድረስ በተላለፉ ቤቶች ላይ ነው፡፡ አቶ መስፍን እንደተናገሩት፣ ቆጠራ የሚደረግባቸው 102 ሺሕ ቤቶች በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በ147 ሳይቶች የሚገኙ ናቸው፡፡

  እያንዳንዱ መኖሪያ ቤት በቅድሚያ 65 መጠይቆች ይቀርባሉ፡፡ ከዚህ በኋላም የቤቱ ባለቤት የሆነ ግለሰብ የባለቤትነት መረጃ ያቀርባል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በማዕከል ከሚገኘው ከቀድሞው መረጃ ጋር ተመሳክረው ትክክለኛ መረጃ ላይ ይደርሳል፡፡

  ይህ ሥራ 2,500 የቴክኒክ ቡድኖች ከተለያዩ ማኅበራት ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩት በመሆኑ፣ ምንም ዓይነት የአሠራር ክፍተት እንደማይኖር አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

  ከዚህ ውጪ 8,400 ቤቶች ለልማት ተነሺዎች ተብለው ሳይተላለፉ ቆይተው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 4,137 ቤቶች ውል ተዋዋይ ባለመቅረብ ያለተጠቃሚ ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

  በተለይ በእነዚህ ቤቶች ላይ በርካታ ሕገወጥ ተግባር የተፈጸመ መሆኑን ከነዋሪዎች ቅሬታ ሲቀርብ ስለሆነ፣ በሚካሄደው ቆጠራ እነዚህ ቤቶች ያሉበት ደረጃ በግልጽ እንደሚታወቅ ተጠቁሟል፡፡

  በሁለቱም ባለሥልጣናት ቆጠራው ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቀረት ሁነኛ መሣሪያ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ አቶ መስፍን ጨምረው እንደገለጹት፣ በአጠቃላይ አስተዳደሩ ከፍተኛ ድጎማ አድርጎ ለነዋሪዎች ያቀረባቸው ቤቶች ለታለመላቸው ዓላማ መዋል አለመዋላቸው ይታወቃል፡፡     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...