Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርኢትዮጵያዊነት ለምን ኃይል ሆነ?

  ኢትዮጵያዊነት ለምን ኃይል ሆነ?

  ቀን:

  በወልደ አማኑኤል ጉዲሶ

  ‹‹ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው›› በሚል ርዕስ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. አንድ አስተያየት አዘል መጣጥፍ ባለፈው ሳምንት ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ በርካታ አንባቢያን አዎንታዊ አስተያየቶችን በመስጠት ሰፋ አድርጌ እንዳቀርብ ስላበረታቱኝ፣ ቀጣይ ጽሑፍ እንዳዘጋጅ አነሳስቶኛልና እነሆ በፍቅር እንድታነቡ ጋብዣለሁ!

  ስለኢትዮጵያዊነት ኃይልነት፣ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ክቡርነት፣ ስለኢትዮጵያችን ድንቅ አገርነት ብዙ ተብሏል፣ ብዙም ተጽፏል፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች ወደፊትም በርካታ መልካምና አስተማሪ ጭብጦችን ለእኛም ሆነ ለተከታዩ ትውልድ ሊጽፉ እንደሚችሉም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት ውበት፣ ስለኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ ባለቤትነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ብዝኃነት በአገር ውስጥ ሆነን ብዙም ላይሰማን፣ ብዙም ትርጉም ላንሰጥ እንችል ይሆናል፡፡ በሌሎች አገሮች ዜጋ አለመሆን የሚያስከፍለው ዋጋ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን የአካል መጉደል፣ የአዕምሮ ጉዳትና የሕይወት መስዋዕትነትን እስከ ማስከፈል የሚመነዘሩ ትዝታዎች መኖራቸውን ብዙዎቻችን እንረዳለን፡፡ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በዜጎቻችን ላይ ይደርሱ የነበሩ ልዩ ልዩ ዓይነት በደሎች አሁንም አሉ፡፡ ለአንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ገር ማለት የደም ሥርን ዋኝቶና አጥንትን ሰርስሮ የሚገባ ኃያል የፍቅር ማዕበል ነው፡፡ የሕይወት ስንቅ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈልገንም ሆነ ሳንፈልግ በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ‹‹ሁኔታዎች›› ሲከሰቱ፣ አንዳንዶቻችን ፈጥነን ለሁላችንም የማይጠቅም ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡

  የራሱ ፋንታ ነው፣ ካልደፈረሰ አይጠራም፣ እንደገቡበት ይወጡበት፣ ምን እንዲህ አንጠራራቸው. . . ወዘተ ወደሚሉ ማጠቃለያዎች እንደርሳለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደዚያ ሜዳ የሚያደርሱ አስገዳጅ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ አገራዊ ሁኔታው ሰላማችንንና ልማታችንን የሚያደናቅፍ እንዳይሆን ሰከን ብሎ ማሰቡ ነገ ለመድረስ ላሰብንበት የጋራ ግብ ዋጋው ትልቅ መሆኑን እንዘነጋለን፡፡ ግቡም ሁሉንም ዜጋ የሚጠቅም መሆኑን እንረሳለን፡፡ አገር የመውደድ ስሜት ከሌሎች አመለካከቶች ሁሉ ይለያል፡፡ አገራዊ ስሜት ከፖለቲካዊ ስሜት የገዘፈ ነው፡፡ በፖለቲካዊ አመለካከቶች ዙሪያ ልዩነቶች መኖራቸው ምንጊዜም አይቀሬ ነው፡፡

  የፖለቲካ ልዩነት የሌለው አገርና ሕዝብ መውጫና መግቢያ የሌለው የረጋ ውኃ ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ ተካረረ የእርስ በርስ ግጭቶች ከመድረሳቸው በፊት እልህ አስጨራሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች መደረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውይይቶች ሲካሄዱ የይስሙላ ሳይሆኑ ልባዊና በአገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባትን የሚፈጥር ኃይል ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ እየተሻሻለ የሚሄድ ጉዞ ሳይሆን እየተሸራረፈ የሚደናቀፍ መንገድ ይሆናል፡፡

  ሥልጣን የያዘው ኃይልም ሆነ ለሥልጣን ትግል የሚያደርጉ አካላት አገር የጋራ መሆኑን በሚገባ መገንዘባቸው የጋራ ጠቀሜታ አለው፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማመንም አለባቸው፡፡ ማመን ብቻ ሳይሆን ወደ መሬት ማውረድ አለባቸው፡፡ ሥልጣን የያዘው አካል በሥልጠን ዘመኑ ሕዝብ የሚወደውንና ሕዝባዊ ከበሬታ የሚያገኝበትን ልማት ከሠራ በሕዝብ ዘንድ በባለውለታነቱ ዘወትር እንደተወደሰ ይኖራል፡፡ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በታሪካዊ ወቅት ሳይጫወት ዘመኑ ካለፈበት ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል፡፡ ታሪካዊ ተወቃሽ እንዳይሆን የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና ምክር የሚፈልግ እንጂ፣ ሥልጣንን መጠቀሚያ አድርጎ ዛፍ ላይ የተንጠለጠለና የማይወርድ የሚመስል መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለሕዝቡ የገቡትን ቃል ማክበር አለባቸው፡፡ ማክበር ባይችሉ ደግሞ ምክንያቱ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ማለት በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ያለፉ ሥርዓቶች ደካማ ጎኖች እንደ ከበሮ እያስጮሁና ያላግባብ ሥልጣን ላይ ያለውን አካል እንደ እንቧይ ካብ እየካብን መኖር (መካብ በሚገባን ቦታ መካብ እንዳለ ሆኖ) ይቅርብን፡፡

  ካቡ በፈረሰ ጊዜ የራሱ ጉዳይ ማለት ይመጣል፡፡ የራሱ ጉዳይ ማለት ብቻ ሳይሆን አብሮ መናድም አለና፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ በአገራችንም በርካታ መንግሥታትና የመንግሥታት መሪዎች ሥልጣን ላይ ወጥተዋል፡፡ እነዚህ መንግሥታትም ሆኑ መሪዎች በዘመናቸው የየራሳቸው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አሻራዎች አሏቸው፡፡ ብዙዎቻችን ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ አሻራዎችን አግዝፈን በማየት ገንቢ ላልሆኑ ትችቶች፣ ብሎም መበቃቀል ወደሚያደርሱ ድርጊቶች በፍጥነት እንጋበዛለን፡፡ የሁሉንም አገር መሪዎች የአመራር ዘመን ስንመለከት ከላይ ከተጠቀሱት ድርጊቶች በአንዱ ወይም በሁለቱ ታጅበው ያለፉና ያሉም እንዳሉ በተጨባጭ እንገነዘባለን፡፡

  አንድ ታሪካዊ ክንዋኔ አልፎ ሁለተኛው ቦታውን ሲረከብ ሰላማዊ መሆኑን ብዙዎች የሚደግፉት ሲሆን፣ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚመጡ ለውጦች ሁሉ ውጤታቸው ይብዛም ይነስ ጉዳት አላቸውና ጠንቀቅ ማለት ነው፡፡ አስከፊና አስነዋሪ የታሪክ ጠባሳ ጥለው ያልፉና የሚቀጥለውን ትውልድ እርስ በርስ ያነታርካሉ፣ ያቆስላሉ፣ ያፋጃሉ፡፡ እንደ ወረርሽኝ በሽታ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብረው ይሄዳሉ፡፡ አብሮ እየኖረ ያለውንና ወደፊትም አብሮ የሚኖረውን ሕዝብና የሁሉም እናት የሆነችውን ወርቃማ አገር ለትርምስ ያበቃሉ፡፡

  ወደ አንድ ወይም በርካታ አገሮች ሲሄዱ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ኩሩ ዜጎች እንደሆንን (የሌሎች አገሮችን ማንነት ማሳነስ አይሁንብኝና) ከብዙዎች ባዕዳን ይሰማሉ፣ ያነባሉ፣ ያስተውላሉ፣ ይመለከታሉም፡፡ ከዚያም በእርግጥም ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ ኃይል መሆኑን አውቀው ተጨማሪ ኃይል ያገኛሉ፡፡ ስለኢትዮጵያችን ከጥንት ጀምሮ ይነገሩ ከነበሩና ከተጻፉ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ጥቂቶቹን ብቻ ለግንዛቤ ብናነሳ፣ አገራችን  የምትታወቀው በምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ፏፏቴነት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የዳቦ ቅርጫትነት፣ ለጥቁሮችና በቅኝ ግዛት ሥር ሲማቅቁ ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች የአሸናፊነትና የአይበገሬነት አርዓያ በመሆን፣ ከቅኝ ተገዥነትና ከባርነት ለመላቀቅ መራር ትግል ለሚያደርጉ ጭቁን ሕዝቦች የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፈለ ድጋፍ በማድረግ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሳትነካ ሊነኩዋት የመጡባትን የዘመናት ጠላቶች አምበርክካና አሳፍራ የመለሰች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር መሆን ነው፡፡

  የጦረኝነትን ታሪክ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡ ይህ የጦረኝነት ታሪክ ወደ ፀረ ድህነት ውጊያ ሜዳነት በዘላቂነትና በአስተማማኝነት መቀየር አለበት፡፡ አይመስላችሁም? ስለኢትዮጵያችን በውጭ አገር ድርሳናትና ቋንቋዎች የተሰጡ ትርጉሞችን በአጭሩ ስንመለከትም ‹‹ፊታቸው የተቃጠሉ ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር (ሩሲያዎች፣ ግሪኮችም ይህንኑ ትርጉም ይጋራሉ)፣ ሐሐሐሀሐሀሀሀሀበበበሀበሻ (ዓረቦች፣ ኢትዮጵያ (ግሪኮች)፣ አቢሲኒያ (አቢሲኒያ የሚለው ስያሜ መነሻው የት እንደሆነ አይታወቅም አከራካሪ ነው የሚሉ ጸሐፊዎች እንዳሉ ሆኖ፣ አንዳንዶቹ ትርጉሙን ድብልቅ ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ይላሉ)፣ አትያብ (በዓረብኛ ቅመሞች፣ ሽቶዎች እንደ ማለት ነው)፣ በተራራ ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች፣. . . የሚሉ ትርጉሞች እንዳሉ ሆኖ ለማንኛውም ግን አጠራሩ ከዓረብ ባህረ ሰላጤ እስከ አፍሪካ ቀንድ ድረስ ያሉ አካባቢዎችን የሚያካልል እንደ ነበረ እንገነዘባለን፡፡ ዓረቦቹ እንዳሉት በእርግጥም ቅመሞችና ሽቶዎች ነን፡፡ (ከዚህ ሰፋ ያሉ ትርጉሞችን ለታሪክ ምሁራን እንዲተው ይፈቀድልኝ፡፡)

  እነዚህን መንደርደሪያዎች ለክፍል ሁለት ጽሑፌ የተጠቀምኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለኢትዮጵያ ከተሰጡት ትርጉሞች መካከል በአንዱ በተለይም ጥቁር ሕዝቦች የሚኖሩበት ወይም ፊታቸው የተቃጠሉ ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር በሚለው ላይ አጭር ‹‹ማብራሪያ›› መስጠት ፈልጌ ነው፡፡ አንባቢያን ፊታቸው የተቃጠሉ ሕዝቦች ማለት ጥቁሮች የሚኖሩበት ለማለት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ይህ ትርጉም በተሰጠበት ዘመን በአፍሪካ ወይም በሌላ ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ስለመኖራቸው የሚያውቁ ነጮች ወይም ሌሎች ሕዝቦች መኖራቸውን ጥርጣሬ ያሳድርብኛል፡፡ (በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አኅጉሮች ከሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች መካከል ፊታቸው በጣም ጥቁር የሆኑ ሕዝቦች በአገራችን እንዳሉን ያውቃሉ? ጥቁር ቆንጆ ነው ሲባልስ?) አይገረሙ ነገሩ እውነት ነው፡፡ ጥቁር ውበት ነው፡፡ ይህ ውበትና ቆንጅና ደግሞ የእኛ የኢትዮጵያውያን መለያ መሆኑ ከማንም ከምንም በላይ እኛኑ ኢትዮጵያውያንን ያኮራናል፣ ያስደስተናል፣ እያኮራንና እያስደሰተንም እንኖራለን፡፡

  ከላይ የተገለጹት አገሮች በየቋንቋዎቻቸው ወይም በሥነ ልሳኖቻቸው ሕዝባችንን ወይም አገራችንን ጥቁሮች ወይም ፊታቸው የተቃጠለባቸው ሕዝቦች የሚኖሩበት አገር ያሉት ያለ ምክንያት አይመስለኝም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ይጋራሉ ብዬ በማስበው ዕይታዬ ኢትዮጵያውያን በእርግጥም ጥቁሮች ነን፡፡ ያውም የውበት ኅብረ ቀለም ያለን ሕዝቦች፡፡ በዚህም ጥቁርነታችን እንኮራለን፣ እንመካለንም፣ ለዚህ ትርጉም ያነሳሳቸው የሚመስለኝ እኛ ኢትዮጵያውን ስንታወቅ ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች አይታወቁም ነበር ማለት አያስችለንም ይሆን? እኛ ከውጭው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስንመሠርት ሌሎቹ ጥቁሮች በቅኝ ግዛት ሥር ስለነበሩ ይህ ይፋዊ ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ ዛሬም ቢሆን የእኛን ያህል የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የሌላቸው አሉ፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ማዕከል ሆና መቆየቷ ነው፡፡ ለአፍሪካ አንድነትና ነፃነት በኢትዮጵያዊነት ስሜት በቁርጠኝነት በመሥራታችን ነው፡፡ ነገም ወደ ፊትም ኢትዮጵያዊ ባህላችንን የጠበቀ መስተንግዷችንንና ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችንን አጠናክረን ከቀጠልን፣ ይህ ከኒውዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛ እንደሆነ የሚጠቀሰው አገልግሎታችን ክብሩን እንደጠበቀ ይዘልቃል፡፡ ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው ወደሚለው ርሴ እንዲመለስ ይፈቀድልኝ፡፡

  እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለኢትዮጵያዊነት የሚመስለኝን አስተያየት ሳቀርብ ከብዙዎቹ ኢትየጵውያን የተለየ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ኖሮኝ ባይሆንም፣ ወይም ስለሌሎቹ መናገር ግዴታ ባይሆንብኝም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንድን አስተሳስብ አጉልቶ አንዱን አሳንሶ ለማሳየት፣ ብሎም ለማደብዘዝ ለዓመታት ሲሠሩ የነበሩ አስተሳሰቦችን ትተን ለአገራችን ልዕልናና ከፍታ ስንል ወደ አንድ የሰገነት ጫፍ ማድረስ የጋራ ግዴታችን ይመስለኛልና ነው፡፡ ወደ ሰገነት ጫፍ ማድረስ ይገባል ሲባል ወደ ጫፍ በማድረሱ ሒደት በኢትዮጵያችን ምንም ዓይነት የሚዳሰሱ ተግባራት አልተሠሩም የሚል ጨለምተኛ አስተሳሰብ የለብኝም፡፡ ወደ ፊትም አይኖርብኝም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መሰንዘር መነሻ የሆኑኝ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን አስተሳሰቦች ደግሞ በእኔ አዕምሮ አግዝፌ አሳይቼ በሌሎች ላይ ይህንኑ ለማራገፍ አይደለም፡፡ ይህንን የሚለው በተለያዩ አከባቢዎች ስሜታዊ መገለጫዎች እየተንፀባረቁ የሚታዩበትን ሁኔታ ስለሚስተዋል ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ኃይል ሆኖ መቀጠል አለበት እላለሁ፡፡ የማይስማማ አስተሳስብ ካለም እንወያይ፡፡

  ዶ/ር ዓብይ ሁልጊዜ ስማቸውን ሲያወድሱ የምሰማቸው የህንዳውያን አባት ማህተመ ጋንዲ (በእርግጥም መወደሳቸው አግባብ ነው) ከተናገሯቸው አብነቶች አንዱ፣ ‹‹አንድ ዓይን ከጠፋ ሌላውን ዓይን ማጥፋት ብቻ መላ ዓለምን ዓይነ ሥውር ያደርጋል፤›› የሚለው አባባላቸው ነው፡፡ ማህተመ ጋንዲ አክለውም፣ ‹‹ከበቀል ቅጣት ይልቅ ይቅርታ መደራረግ ሰዋዊነት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግም ‹‹ለፍቅር ጥንካሬ›› በሚለው ጽሑፉ ይቅርታ የመደራረግን አስፈላጊነትን አጉልቶ ሲያሳይ፣ ‹‹ይቅርታ መደራረግ ወደ አዲስ መሻሻልና አዲስ ጅማሮ ያበቃል፣ ይቅር መባባል የአንድ ወቅት ተግባር ሳይሆን፣ የዘወትር ባህል ሊሆን ይገባል፤›› ብሏል፡፡ ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ዴዝመንድ ቱቱ በበኩላቸው እ.ኤ.አ. በ1999 ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ያለ ይቅርታ መደራረግ ይቅርታ የለም፤›› ብለዋል፡፡

  ይቅርታ መደራረግ ራስን (መንግሥትም ቢሆን) ነፃ ለማውጣትም ሆነ ከአዕምሮ እስረኝነት ለማውጣት ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለሌሎች የዓለም ሕዝቦች ሞዴል የሆነችው ከማንዴላ እስር መፈታት በኋላ ከ500 ዓመታት በላይ ሲያስሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲጨቁኑና ሌሎችን ሰብዓዊ ጥሰቶች ሲፈጽሙባቸው ለነበሩ ነጮች ልባዊ ይቅርታ በማድረግ ነው፡፡ በወቅቱ የማንዴላን የይቅርታ አስተሳሰብ የተቀበሉት ጥቁሮች ብቻ አልነበሩም፡፡ አስተሳሰቡን የተቀበሉት ጥቁሮችም ሆኑ ነጮች ዝናና ክብር አግኝተዋል፡፡ ጥቁሮቹ ነጮቹን እንበቀል ካሉ ሁለቱም ወገኖች መጨረሻቸው ወዴት እንደሚያደርስ በደንብ ተወያይተዋል፣ ተማምነዋል፡፡ በዚህም ቅሬታዎችንና ቂም በቀሎችን በመተው ወንድማማችነትንና ሰብዓዊነትን ማስታረቅ ችለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቁሮች የተሟላ የኢኮኖሚ የበላይነት ባይኖራቸውም የፖለቲካ የበላይነት አላቸው፡፡ የፖለቲካ የበላይነት ብቻውን መፍትሔ ባይሆንም ‹‹በሥልጣናቸው›› ለአገራዊ ጉዳይ እጅ የመጠምዘዝ አቅም አግኝተዋል፡፡ እነሆ በሰላምና በመቻቻል እየኖሩ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ከሚያለያየን ይልቅ የሚያመሳስለን፣ ከጠላትነት ይልቅ ቤተሰባዊነታችንና ወዳጅነታችን፣ ከሥጋት ይልቅ አብሮነታችን፣ በዚህም ሆነ በዚያ የሚያከባብረንና የሚያዋድደን ታሪክ እንጂ በጠላትነት የምንፈራረጅበት ታሪክ የለንም፡፡ እነዚህ መልካም ባህሎችና የመልካም ሕዝቦች እሴቶች ጎልተው መውጣት አለባቸው፡፡ የእኛን መልካም ነገራችንን ለሌላው የዓለም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለልጅና ለልጅ ልጆቻችን ካላሳየን ማን ሊመጣልን ነው፡፡

   አገራችን የበለጠ ተሰሚነት ያላትና ያደገች እንድትሆን እያንዳንዳችን ኃላፊነት አለብን፡፡ የተበታተነች አገርና የተበታተንን ሕዝቦች እንዳንሆን ነቅተን ዘብ መቆም አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን የዛሬው ዓለም ሰላም እንደ ብርጭቆ ተሰባሪ መሆኑን ለራሳችን ስንል ማወቅ አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ በአንድ በኩል አገሩን የሚወድና የሚጠብቅ ትውልድ መፍጠር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አንድነታችን በቀላሉ የማይናወጥ ሕዝብ መሆናችንን ለዓለም በተለይም ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የእኛን መውደቅ ለሚመኙ ወገኖች ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የአገሩን ታሪክ የሚያውቅና የሚንከባከብ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡

  አገራችን የጀመረችው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለጦር ጀግንነት አያወራም፡፡ አንገታችንን እያስደፋ ያለውን ድህነት እንድንዋጋ ለመላው ሐዝባችን አገራዊ ጥሪ ተደርጎልናል፡፡ እርስ በርስ አሸናፊና ተሸናፊ በመባባል ከምንሸነጋገል የልማት አርበኛ ለመሆን እንሽቀዳደም፡፡ እያስመዘገብን ያለው ውጤት ለዚህ የሚያበቃን ስለመሆኑ እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከዚህ የበለጠ ማደግ የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው በጉልበት ስንመካ ሳይሆን፣ በአዕምሮ እያሰብንና ቴክኖሎጂ እየተጠቀምን ስንሠራ ነው፡፡ ድሮስ ቢሆን የሀብት ድህነት እንጂ የአዕምሮ ድህነት እንዳልነበረብን እናውቅ የለ? የሀብት ድህነትን ጠንክረን በመሥራት ልንሻገር እንችላለን፡፡ የተሻለ ለመማርና በተሻለ ቦታ ለመሥራት በውጭ አገሮች ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያውያን ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ስንገነዘብ አገራችንን ወደ ቀድሞ ገናና ክብሯ መመለስ አያስችለንም? ያንን ድንቅ ክብርና ሞገስ ያቆዩልን በሁሉም ኢትዮጵያ የነበሩ ጀግና አባቶቻችን ናቸው፡፡ በተናጠል የሚወደስና አንሶ የሚታይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፣ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ይህ ሀቅ መሆኑን አንዱን አሳንሰው ሌላውን ደግሞ ላቅ አድርገው የሚያዩ አካላት መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሰላም ለእኛም ለአገራችንም ይሁን፡፡ ለዛሬው በዚህ ላብቃ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wgudissoa@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...