Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንቡ ክፍተቶች የሥርዓተ አልበኝነት ምንጭ እንዳይሆኑ!

  በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም. ፀድቆ ከአምስት ዓመታት በኋላ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ፣ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ቢይዝም ክፍተቶች ስላሉበት ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው፡፡ በአገሪቱ ከሚታየው አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ አንፃር ሲታይ ሥርዓት የሚያሲዝ ደንብ መውጣቱ ተቀባይነት አለው፡፡ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተካከል ደንቡ ጠቃሚ ቢሆንም፣ በውስጡ የያዛቸው ግልጽነት የጎደላቸው፣ ለመረዳት አዳጋች የሆኑና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማይጣጣሙ የቅጣት እርከኖች ተሰግስገውበታል፡፡ እነዚህ ክፍተቶች ለትራፊክ ፖሊሶች ገደብ አልባ ሥልጣን በመስጠት የበለጠ ትርምስ እንዳይፈጠርም ሥጋት ያጭራሉ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን እያነሳን ችግሩን እናመላክታለን፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ይህ ደንብ በአጠቃላይ በስድስት የጥፋት እርከኖች ተከፋፍሏል፡፡ ለጥፋቶቹ የሚመዘገበው ነጥብና የሚወሰደው ዕርምጃ (የገንዘብ ቅጣት) ሰፍሯል፡፡ በስድስቱም የቅጣት እርከኖች ውስጥ በአሽከርካሪዎች ቸልተኝነት፣ ብቃት ማነስና ሕግ አለማክበር ምክንያት የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች የተዘረዘሩትን ያህል፣ ግልጽነት የጎደላቸውና ለመረዳት አዳጋች የሆኑም አሉ፡፡ በአንደኛ እርከን የጥፋት ዝርዝር ውስጥ ውኃ በእግረኛ ላይ የረጨ አሽከርካሪ ሁለት ነጥብ ተመዝግቦበት 60 ብር  ይቀጣል፡፡ ሆን ብለው ከሚያጠፉት ውጪ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በዝናብ ወቅት ጎርፍ አስፓልት መንገድ ላይ እየጋለበ፣ በርካታ መንገዶች ተቆፍረው ውኃ እያቆሩና ችግሩ እየታወቀ ካቅም በላይ የሆነባቸውን ለመቅጣት መነሳት አዳጋች ነው፡፡ የወደፊቷን አዲስ አበባ ታሳቢ ያደረገ ቢሆን እንኳ በዚህ ሁኔታ ተፈጻሚ መሆኑ ግራ ያጋባል፡፡

  በሁለተኛ እርከን የጥፋት ዝርዝር ውስጥ ከመጠን በላይ ድምፅ ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? የመኪና ሞተር፣ ጥሩንባ ወይስ ሌላ ምን? በፍጹም ግልጽ አይደለም፡፡ በሦስተኛ የጥፋት እርከን ዝርዝር ላይ የመቀመጫ ቀበቶ ሳያስር ወይም ተሳፋሪዎች የመቀመጫ ቀበቶ ማሰራቸውን ሳያረጋግጥ ያሽከረከረ የሚል ከነቅጣቱ ሰፍሯል፡፡ አሽከርካሪው የመቀመጫ ቀበቶ የማሰር ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን ምን ያህሎቹ የቤት አውቶሞቢሎችና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ናቸው ይኼንን መጠይቅ የሚያሟሉት? የነገን መሻሻል እያሰቡ ዛሬ ቅጣት መጀመርስ ምን ይባላል? ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ የጠገነም ይቀጣል ይላል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? የመጠገን ፈቃድ ሰጪውንና የጊዜ መጠኑን የሚያውቅ ማን ነው? ግራ ያጋባል፡፡ ያልተፈቀደ ጭነት ከሕዝብ ጋር የጫነም ይቀጣል ይላል ደንቡ፡፡ ያልተፈቀደ ጭነት ምንድነው? ማብራሪያ ያስፈልጋል፡፡ ለተሽከርካሪው እንቅስቃሴ ካላስፈለገ በስተቀር ሁለት እጅን መሪ ላይ ሳያደርግ ያሽከረከረ ይቀጣል፡፡ በማን ነው ሁለት እጅን መሪ ላይ ማድረግና አለማድረግ የሚመዘነው? አይገባም፡፡ ለትርጉም የተጋለጠ ነው፡፡

  ይህ ሥራ ላይ የዋለ ደንብ ለዓመታት በገንዘብ ላይ ብቻ የተመሠረተን ቅጣት አስተማሪ በሆነ መንገድና እግረ መንገዱንም የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ፣ አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ ጠቀሜታ እንዳለው ተነግሮለታል፡፡ በቅጣት እርከኖቹ መሠረት የጥፋት ነጥብ ከ14 እስከ 16 ሲደርስ ለስድስት ወራት የማሽከርከር ፈቃድ ላይ ዕገዳ ይደረጋል፡፡ የተሐድሶ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ የጥፋት ነጥቡ ከ17 እስከ 19 ሲደርስ ለአንድ ዓመት የማሽከርከር ፈቃድ ዕገዳና ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ከ20 እስከ 21 ሲደርስ ግን የማሽከርከር ፈቃዱ ይሰረዛል፡፡ ባለፈቃዱ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደ አዲስ ሌላ ፈቃድ ለማውጣት ይገደዳል፡፡ ይህ የቅጣት ዕርምጃ በተደጋጋሚ ጥፋት በሚፈጽሙ ላይ ተግባራዊ መደረጉ እንዳለ ሆኖ ግን፣ በዚህ ደንብ ውስጥ ባሉ ክፍተቶች ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ሥልጣን የተሰጣቸው የትራፊክ ፖሊሶች ሥልጣናቸውን ያላግባብ እንደማይጠቀሙበት ምን ማስተማመኛ አለ? አንድ ጥፋት ያጠፋ ሰው ሬኮርድ ለሁለት ዓመት ሲያዝበት፣ ከቅጣት ለማምለጥ ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ላለመፍጠሩ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? በርካታ የጎንዮሽ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

  የዚህ ደንብ ሌላው አስቸጋሪነት ከከተማው መንገዶች ባህሪ፣ ከትራፊክ ፍሰቱ፣ ከተሽከርካሪዎች ይዞታ፣ ከእግረኞችና ከእንስሳት እንቅስቃሴና ከመሳሰሉት ጋር ለመናበብ አዳጋች መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ደንቡ አሽከርካሪዎች ላይ ጫና ለመፍጠር ብቻ ትኩረት ማድረጉ ከአስተማሪነት በላይ ቅጣት ላይ ያነጣጠረ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት መኖሩ በደንቡ ውስጥ ቢሰፍርም፣ ያልተጤኑ ችግሮችን ዓይቶ የሚሻሻሉ ነገሮችን ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ በርካታ አሽከርካሪዎች ደንቡን እንደማያውቁ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዳልተሰጣቸው፣ ደንቡ ተግባራዊ ሲደረግም በሥራቸው ላይ የሚያመጣውን ጫና በስሚ ስሚ መስማታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ ከሆነ የማስተካከሉ ሥራ ቅድሚያ ይሰጠው፡፡

  ማንኛውም ተግባር በሕግና በሥርዓት መመራት አለበት፡፡ በተለይ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ እየሆነ የመጣው የትራፊክ አደጋ ቀንሶ የስው ሕይወት እንዳይቀጠፍ፣ የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ደንቡ ሲወጣ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ያካተተ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ግልጽነት የጎደላቸውና ለመረዳት አዳጋች የሆኑ ነገሮች ውስጡ አሉ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችን ሥልጣን ገደብ የለሽ የሚያደርጉ ክፍተቶች ታይተውበታል፡፡ በተደጋጋሚ ጥፋት የፈጸሙ አሽከርካሪዎች ከማሽከርከር ፈቃድ ዕገዳና ከስረዛ ለመዳን ሲሉ ደንቡን የሚጥሱ በርካታ ችግሮች እንዳይፈጥሩ፣ ሙስናን ለማስፋፋት በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮች እንዳያስፋፉና ለበለጠ መተረማመስ ምክንያት እንዳይሆኑ የታሰበ አይመስልም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ ምልክቶች፣ በሚገባ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በዘመን አፈራሽ ቁሳቁሶች ሳይደራጅ ይህንን ደንብ እንደወረደ ተግባራዊ ማድረጉ በራሱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

  በአጠቃላይ ሕግና ሥርዓት ለማስፈን ተብለው የሚወጡ ሕጎች፣ መመርያዎችና ደንቦች ሙሉ በሙሉ ከስህተት የፀዱ እንዲሆኑ መጠበቅ ባይቻልም፣ በተቻለ መጠን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ መሆን አለባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የባለድርሻ አካላትን ይሁንታ ሳያገኙና ተገቢው ግንዛቤ ሳይፈጠር ደንብ አውጥቶ፣ በችግር ላይ ችግር መደራረብ ተገቢ አይደለም፡፡ ሥርዓት ለማስያዝ ተብሎ ሥርዓት አልበኝነት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማደረግ መሞከር ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ ይብሳል፡፡ ይህ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በርካታ ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን ይዞ፣ በተወሰኑ የቅጣት ዝርዝሮቹ ምክንያት ለክፍተት ከተጋለጠ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ከችግር ያልፀዳ ደንብ ዞሮ ዞሮ ተገልጋዩን ከመጉዳት የዘለለ ፋይዳ ስለማይኖረው፣ በባለድርሻ አካላት ተቃውሞ ቢቀርብበት ሊገርም አይገባም፡፡ ክፍተቶቹ መላ ካልተፈለገላቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ለቅጣት በተሠለፉ ሕግ አስከባሪዎችና በአሽከርካሪዎች መካከል በሚደረጉ አለመግባባቶች ሊዘጉ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ዋነኞቹ የጉቦ ማቀባበያ ኮሪደር መሆናቸው አይቀርም፡፡ የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንቡ ክፍተቶች የሥርዓት አልበኝነት ምንጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ይደረግ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት...

  በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

  በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

  ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል የኢትዮጵያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...

  የሴራ ፖለቲካ መረብ ይበጣጠስ!

  ኢትዮጵያ አሁንም ከበርካታ ፈተናዎች ጋር እንደ ተፋጠጠች ነው ያለችው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብፅ በጎረቤት አገሮች አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ፍጥነቷን ጨምራ እየተንቀሳቀሰች...