[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ቀጠሮ ቢኖራቸውም ሾፌራቸው አርፍዶባቸው በጣም ተበሳጭተዋል]
- ጤነኛ ነህ ሰውዬ?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መጀመሪያ የጠየቅኩህን መልስልኝ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ጤነኛ ነህ ወይ?
- ይቅርታ አልኩ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በጠዋት ቀጠሮ እንዳለኝ ነግሬህ አልነበር?
- ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
- ከአቅምህ በላይ አትጠጣ ብዬ አልነገርኩህም?
- ኧረ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞኝ ነው ያልኩት፡፡
- ባለፈው በመሥሪያ ቤታችን የተሰጠውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ወስደሃል አይደል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ አቅምህ ከተገነባ እንዴት ሆኖ ነው ከአቅምህ በላይ ችግር የሚገጥምህ?
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ሊገባኝ ይችላል?
- የእናንተ ችግር እኮ ይኼ ነው፡፡
- ምኑ ነው የእኛ ችግር?
- አለማዳመጥ፡፡
- እሺ ላዳምጥህ ምን ሆነህ ነው ያረፈድከው?
- ታክሲ የለም፡፡
- ምን ታክሲዎቹ በአሸባሪዎች ታፍነው ተወሰዱ?
- አይደለም፣ አድማ መትተዋል፡፡
- አድማ?
- አዎን አድማ፡፡
- የት ነው አድማ የመቱት?
- እዚህ አዲስ አበባ ነዋ፡፡
- ይኼ ነገር እዚህም ገባ እንዴ?
- ምኑ?
- አድማው፡፡
- ያው አሁን አድማ የመቱት ታክሲዎቹ ናቸው፡፡
- ምን ሆነን ብለው ነው?
- አዲሱን የትራፊክ ደንብ ተቃውመው፡፡
- ለምንድነው የሚቃወሙት?
- ሥራ አጥ ያደርገናል ብለው ነዋ፡፡
- ለምንድነው ሥራ አጥ የሚሆኑት?
- ቅጣቱ ከፍተኛ ነዋ፡፡
- አለማጥፋት ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሚሠራ ሰው እኮ መሳሳቱ አይቀርም፡፡
- የተሳሳተማ ይቀጣል፡፡
- እንደዚያማ ከሆነ የእርስዎም ቢሮ ቂሊንጦ ነበር የሚሆነው፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ይተውት በቃ፡፡
- ለመሆኑ ታክሲ ቢጠፋ ለምን በባቡር አልመጣህም?
- በየትኛው ባቡር?
- ይኸው የከተማ ባቡር ዘርግተናል አይደል እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር የከተማው ባቡር እኮ ለተወሰኑ ሰዎች ነው የሚያገለግለው፣ አብዛኛው ሕዝብ በታክሲ ነው የሚጠቀመው፡፡
- እኮ አሁን አንተ ለምን በባቡር አትጠቀምም?
- ባቡሩ በእኛ ሠፈር አያልፍማ፡፡
- አየህ ኪራይ ሰብሳቢ ውስጥ ነው የምትኖረው ማለት ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ባቡሩ የሚያልፍበት ሠፈር ልማታዊ ሠፈር ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ደመወዝ ከጨመሩልኝ እኮ እኔም ባቡሩ በሚያልፍበት መንገድ ቤት መከራየት እችላለሁ፡፡
- ለማንኛውም የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት እንዳለህ ለመረዳት ችያለሁ፡፡
- ይኼ ነው እኮ ከሕዝቡም ጋር እያጋጫችሁ ያለው ነገር፡፡
- ምኑ?
- አለማዳመጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ጸሐፊያቸው ገባች]
- ክቡር ሚኒስትር ባለጉዳይ ይፈልግዎታል፡፡
- የምን ባለጉዳይ?
- ሰሞኑን በተደጋጋሚ ሲመላለስ ነበር፡፡
- ቢመላለስስ?
- ለዛሬ ቀጥረውት ነበር፡፡
- ሌላ ሥራ አለኝ አልችልም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዛሬ ከዚህ ሌላ ቀጠሮ የለዎትም፡፡
- እኔ ጠፋሁ እየተቆጣጠርሽኝ ነው?
- ልቆጣጠርዎት ፈልጌ ሳይሆን…
- ታዲያ ምን ፈልገሽ ነው?
- ቴሌቪዥን ይመለከታሉ?
- ሰሞኑን የአሜሪካ ምርጫ እከታተላለሁ፡፡
- ኧረ የአገር ውስጥ ሚዲያ አይከታተሉም?
- ሥራም አላጣሁ፡፡
- ታዲያ እኛን ለምንድነው የምታደናቁሩን?
- በምን?
- በየጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግር ምናምን እያላችሁ ነዋ፡፡
- እንዴት ማለት?
- አንደኛው የመልካም አስተዳደር ችግር እኮ አሁን እርስዎ የሚያደርጉት ነው፡፡
- የመልካም አስተዳደር ችግር ያለውማ ሕዝቡ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ይኸው ዛሬ ታክሲ ባለመኖሩ ምክንያት ነው ከሥራ ያረፈድኩት፡፡
- ታክሲ መጠቀም ጀመሩ እንዴ?
- ኧረ ምን በወጣኝ? ሾፌሬ ታክሲ አጥቶ ግን እኔንም አስረፈደኝ፡፡
- ለዚያ ነው የመልካም አስተዳደር ችግር ያለው ሕዝቡ ጋ ነው ያሉት?
- በሚገባ፡፡
- ኧረ እኔ እንደሰማሁዎት ሌላ ሰው እንዳይሰማዎት፡፡
- ቢሰማ ምን ያመጣል?
- ለማንኛውም አንድ ነገር ልጠይቅዎት፡፡
- ምን?
- በሚዲያ የምትደሰኩሩትን አቁሙ፡፡
- የቱን?
- ውሸቱን!
[አንድ ደላላ የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሮ ገባ]
- አሉ እንዴ?
- ቀጠሮ አለህ?
- የለኝም ግን አሁን ደውዬላቸው ነበር፡፡
- ሥራ አላቸው፡፡
- ኧረ ሴትዮ አሁን ደውዬላቸዋለሁ፣ ገብተሽ ንገሪያቸው፡፡
[ጸሐፊያቸው ቢሯቸው ገባች]
- አንድ ሰውዬ ቢሮ አለ፡፡
- ማን ነው?
- አሁን ደውዬላቸው ነበር ብሎኛል፡፡
- አስገቢልኝ ቶሎ፡፡
- ምን?
- ሰምተሽኛል፡፡
[ደላላው ቢሯቸው ገባ]
- እሺ ምን ይዘህ መጣህ?
- ጮማ የሆነ ነገር ይዣለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ጮማ?
- ያው ፆም ሊገባ ነው ብዬ ነዋ፡፡
- እኮ ምንድነው?
- ጠቀም ያለ ዶላር፡፡
- ስሙ ሲጠራ ራሱ ያስደስተኛል፡፡
- በቃ ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ የሚፈለገው ያው የተለመደው ነው፡፡
- የተለመደው ምን?
- መሬት ነዋ፡፡
- አታስብ ስለሱ፡፡
- እርስዎም ስለዶላሩ አያስቡ፡፡
- መቼ ይደርሳል ታዲያ?
- ከፆሙ በፊት!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ደወሉላቸው]
- በአስቸኳይ ናልኝ፡፡
- ምን ሆነሻል?
- መኪናዬ ቆመችብኝ፡፡
- ጎማ ፈንድቶ ከሆነ እዚያው አካባቢ ሰው ፈልገሽ አስቀይሪ፡፡
- እሱ ቢሆንማ መቼ ጠፋኝ? አሁን ብቻ ናልኝ፡፡
- ሥራ ላይ ነኝ እኮ?
- ነዳጅ አልቆብኝ ነው የቆምኩት፡፡
- ኩፖን ሰጥቼሽ አልነበር እንዴ? ለምን አልቀዳሽም?
- ነዳጅ በኩፖን ብቻ አይቀዳማ፡፡
- ለምን አይቀዳም?
- ነዳጅ የለም፡፡
- ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከኒዮሊብራሎች ጋር መዋል ተይ አላልኩሽም?
- ምንድነው የምታወራው?
- ለመሆኑ ሚዲያ ትከታተያለሽ?
- በደንብ፡፡
- ዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ ምን ያህል እያሽቆለቆለ እንደሆነ አታውቂም?
- እና ቢቀንስስ?
- ስሚ እኛ እኮ ከዚህ ተነስተን ነዳጅ በየቤቱ በቧንቧ ለማስገባት እያሰብን ነው፡፡
- ‘ሽቶ ቀርቶብኝ ፈስሽን ባቆምሽልኝ’ አለ ሰውዬው፡፡
- ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
- ነዳጅ የለም ነው እኮ የምልህ?
- እኮ ለምን?
- አልተዋሃደም፡፡
- የአራቱ ፓርቲ ውህደትማ ይቆይ ብለናል እኮ፡፡
- ሰውዬ እኔ የአንተን ፖለቲካ አይደለም የማወራው፡፡
- አልተዋሃደም ስትይኝ ነዋ?
- ነዳጁን ነው የማወራህ፡፡
- ነዳጅ ይዋሀዳል እንዴ?
- ይኼን ነው እኮ የምልህ?
- ምንድን ነው የምትይኝ?
- ልትግባቡ አልቻላችሁም፡፡
- ከማን ጋር?
- ከሕዝቡ ጋር!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ባለፈው ባዘዙኝ መሠረት ጥናቱን ጨርሻለሁ፡፡
- እሺ፡፡
- የችግሮቹ መንስዔዎችም ታውቀዋል፡፡
- እነሱማ ግልጽ ናቸው፡፡
- ሊነግሩኝ ይችላሉ?
- ኪራይ ሰብሳቢነት፡፡
- እሺ፡፡
- ሙሰኝነት፡፡
- ይቀጥሉ፡፡
- ማናአለብኝነት፡፡
- ሌላስ?
- የመልካም አስተዳደር ችግር፡፡
- ትክክል ነዎት ክቡር ሚኒስትር ግን አንድ ነገር ረሱ፡፡
- ምን ረሳሁ?
- የውስጥ የምትል ቃል፡፡
- እንዴት?
- እነዚህ ሁሉ ችግሮች ያሉት በውስጣችን ነው፡፡
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ እኮ ተማሮብናል፡፡
- እንዴት?
- ባለፈው ኦሮሚያ ላይ ሕግ አውጥተን ነበር፡፡
- ልክ ነው፡፡
- ሕዝብ በሚገባ አልተወያየበትም ተብሎ ግን ወዲያ ተቀለበሰ፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- አሁን ደግሞ የትራፊክ ደንብ ወጥቶ ነበር፡፡
- አዎን፡፡
- እሱም ለሦስት ወራት ተግባራዊ እንዳይደረግ ተደርጓል፡፡
- ሕዝቡ አልቀበልም አለ?
- ችግሩ እኮ ይኼ ነው፡፡
- ምንድነው ችግሩ?
- ከሕዝቡ ጋር ሳንወያይ ነው ሕግ የምናወጣው፡፡
- ሕዝቡማ መርጦናል እኮ፡፡
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር፣ ሕጐች ሲወጡ በጥናትና በምርምር የተደገፉ መሆን አለባቸው፡፡
- የጥናትና የምርምር ተቋማት አሉን አይደል እንዴ?
- ቢኖሩንም ግን ችግሮቹ በደንብ እየታዩ አይደሉም፡፡
- ችግር የለውም እኔ መፍትሔ አለኝ፡፡
- ምን ዓይነት መፍትሔ ክቡር ሚኒስትር?
- አንድ ዳይሬክቶሬት ማቋቋም አለብን፡፡
- ምን የሚሉት?
- ትራያል ኤንድ ኢረር!