Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየአልጀርስ ስምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለመፅደቁ በሕግ ፊት ዋጋ ቢስ ነው...

  የአልጀርስ ስምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለመፅደቁ በሕግ ፊት ዋጋ ቢስ ነው ተባለ

  ቀን:

  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደውን ዕልቂት ያስከተለ ጦርነት በማስቆም ቀጣናውን ወደ ሰላም ለመመለስ የተደረገው የአልጀርስ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች፣ በሕግ ፊት ቦታ እንደሌላቸው የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች አስታወቁ፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች ሐሙስ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በጣይቱ ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የመግለጫው ማጠንጠኛ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የያዘውን አቋም በመቃወም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች ተቃውሞ በመግለጫ ብቻ ሳያበቃ፣ እሑድ ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ከስድስት ኪሎ ሰማዕታት ሐውልት እስከ አራት ኪሎ ድላችን ሐውልት ድረስ በሚካሄድ ሰላማዊ ሠልፍ ይታጀባል ብለዋል፡፡

  የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች የተቃውሞ መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ በዓለም አቀፍ ሕግ አንድ ስምምነት የሕግ ፋይዳ ኖሮት አስገዳጅ እንዲሆን በተፈራረሙ አገሮች ሕግ አውጭ አካላት ተመርምሮ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(12) እና 9(4)፣ አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት በኢትዮጵያ የሚፀናው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከተመረመረና የአገሪቱን ጥቅም እንደሚያስጠብቅ ተረጋግጦ ከፀደቀ በኋላ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡

  በዚህ ጉዳይ ላይ አስረግጠው መግለጫ የሰጡት የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጅ የሕግ ባለሙያ አቶ ሥዩም ዮሐንስ እንደገለጹት፣ የአልጀርስ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አልፀደቀም፡፡ ባለመፅደቁም ገዥ ሕግ አይሆንም ብለዋል፡፡

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 29 ቀን 1993 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥት መካከል የተደረገ የሰላም ስምምነት ማፅደቂያ አዋጅ አውጥቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ (2) ላይ የኢፌዴሪ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ስምምነት ከኤርትራ መንግሥት ጋር እንዲፈራረም ተስማምቷል ይላል፡፡

  የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ብዙም ባልተለመደ መንገድ በአዋጁ አንቀጽ (3) ላይ ደግሞ፣ ‹‹ይህ አዋጅ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ከተፈራረሙበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፤›› የሚል ድንጋጌ ሠፍሯል፡፡ መግለጫ ከሰጡት መካከል አቶ ሐይሽ ስባጋዲስ የአንቀጽ ሦስትን ድንጋጌ ቴክኒካዊ ስህተት ብለውታል፡፡

  አንቀጾቹ እርስ በርሳቸው ቢቃረኑም አቶ ሥዩም እንደሚሉት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአልጀርሱ ስምምነት እንዲፈረም ይሁንታ ሰጥቷል፡፡ አንድ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በዓለም አቀፍ ሕግ (በቪዬና ኮንቬንሽን) እንደ ዓለም አቀፍ ስምምነት በተለይ በሁለት አገሮች መካከል የተካሄደ ከሆነ የሚፀናው፣ የሁለቱም አገሮች ሕግ አውጭ አካላት መርምረው ሲያፀድቁት ብቻ ነው፡፡

  ‹‹የአልጀርሱ ስምምነት በረቂቅ ደረጃ ያለ ስምምነት ነው፡፡ ለምን ቢባል የሚፀናው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ብቻ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱም አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚፀናው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል በማለት ሲያፀድቀው ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፤›› ሲሉ አቶ ሥዩም አስታውቀዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ይህ የአልጀርስ ስምምነት በኤርትራ በኩልም ፀድቋል ተብሎ እንደማይታመን፣ በመግለጫው እንደተብራራው የአልጀርስ ስምምነት በኤርትራ ሕግ አውጪ በኩል ስለመፅደቁ ምንም ማስረጃ የለም፡፡

  እንደ አቶ ሥዩም ገለጻ፣ የኤርትራ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የለውም፡፡ በኤርትራ የነበረው ነፃ አውጭ ሠራዊት (ሻዕቢያ) እና ከአካባቢው ነዋሪዎች የተውጣጣ ሸንጎ ነው እንደ ፓርላማ ሆኖ የሚሠራው፡፡ ይህ ሸንጎ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት በተፈጠረው መናጋት ለ15 ዓመታት ተሰብስቦ አያውቅም፡፡ ተሰበሰበ ከተባለም ከሁለት ጊዜ አይበልጥም በማለት አቶ ሥዩም ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት በአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅ ለተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ይደረጋል፡፡ እስካሁን በኤርትራ በኩል ይህ ስምምነት ስለመፅደቁ የተደረገ ሪፖርት የለም፤›› በማለት አቶ ሥዩም ያብራራሉ፡፡

  ይህ በመሆኑ የአልጀርስ ስምምነትም ሆነ በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ፣ በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ሕግ ፊት ዋጋ ቢስ መሆናቸው በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

  በአልጀርስ ስምምነት መሠረት ዘ ሔግ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሁለቱንም አገሮች ሕዝብ በተለይ ደግሞ ስለሁለቱ አገሮች ድንበር ሙሉ ዕውቀት ያላቸውን የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች አስተያየት ከግምት አለማስገባቱን፣ ውሳኔው ደግሞ በባዶ መሬት ላይ ብቻ ያረፈ ሳይሆን በአካባቢው ሕዝብ ላይም ጭምር ነው ይላሉ፡፡ በተለይም የራስ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና እሴት ያለው ሆኖም በቁጥር አናሳ የሆነውን የኢሮብ ብሔረሰብ ለሁለት በመክፈል እንደሚለያይ፣ በመሆኑም ውሳኔው የአናሳ ብሔረሰብ አባላት ቋንቋ፣ ባህል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ትስስር፣ እንዲሁም የጋራ እሴት እንዲያከትም እንደሚያደርግ፣ በተለይም ደግሞ ውሳኔው በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 1(2)፣ በዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ (1) እና የአፍሪካ ሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 20(1) የአንድ አናሳ ሕዝብ የማይገሰስ መብት ተብሎ ዕውቅና የተሰጠውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ሙሉ በሙሉ የሚጥስ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

  መግለጫውን የሰጡት የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች እንደሚያምኑት የጦርነቱ መሠረታዊ መንስዔ አድበስብሶ በማለፍ የብዙ ሺሕ ኢትዮጵያዊን ጀግኖች አፅም ያረፈበትን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ለኤርትራ መንግሥት መሪዎች ገፀ በረከት ማድረግ፣ የኢትዮጵያውያንን ሥነ ልቦና ከመጉዳቱም በላይ ለትውልድ የሚተርፍ ኃፍረትን ይፈጥራል፡፡

  መግለጫውን ከሰጡት አራት የብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል አቶ ሐይሽ ስባጋዲስ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሕገወጥ በሆነው ስምምነት የኢትጵያን ሉዓላዊ መሬቶች በመስጠት ሰላም ይመጣል ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ በመቀጠል የመሬት ስጦታው ወደ መቀሌና አላማጣ የማይሄድበት ምክንያት የለም በማለት፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ የደረሰበትን አቋም በጽኑ ተቃውመዋል፡፡

  ‹‹ጦርነቱ የድንበር አይደለም፡፡ በአግባቡ ያልተያዘ የኢትዮ ኤርትራ ፍቺ ውጤት ነው፡፡ ጦርነቱ የድንበር ካልሆነ ኢሮብንና ሌሎች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬቶችን በመስጠት ይፈታል ወይ?›› በማለት መግለጫው የሰጡት የኢሮብ ተወላጆች ይጠይቃሉ፡፡

  ኢሮብ በሰሜን ምሥራቅ ትግራይ የምትኝ ወረዳ ናት፡፡ የሕዝቡ ቁጥር ከ35 ሺሕ ብዙም የማይበልጥ ሲሆን፣ የድንበር ማካለሉ ተግባራዊ ከተደረገ አካባቢውን ለሁለት ይከፍለዋል፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚረግ ከሆነ የብሔረሰቡ ህልውና አደጋ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ፣ ማንኛውም የብሔረሰቡ ተወላጅ ክስተቱን የማይቀበል መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

  መግለጫውን የሰጡት አቶ ጥዑለይ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ አብርሃ ምሥጋናን ጨምሮ አራቱም የብሔረሰቡ ተወላጆች ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክብር፣ እንዲሁም እነሱን አምነው የወደቁ ጀግኖችን አርበኞች አደራ ማስጠበቅ ስለሆነ የወቅቱን ፈተናዎች በአንድነት በመቆም በጋራ ማስከበር ነው ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት የሁለቱንም አገሮች ሕዝቦች ጥቅም ያማከለ፣ ሁሉንም ለግጭቱ መነሻ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን የማሸነፍ የሰላም ድርድር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማድረግ እንዳለባቸው የኢሮብ ተወላጆች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...