Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉከኤርትራ ጋር እውነተኛ ሰላም ያስፈልገናል

  ከኤርትራ ጋር እውነተኛ ሰላም ያስፈልገናል

  ቀን:

  በአብዱል መሐመድ

  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚፈጠር ሰላም ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦችና ለጠቅላላው የአፍሪካ ቀንድ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች በሚያዝያ 1990 ዓ.ም. ደም ያፋሰሰ ጦርነት ካካሄዱ ከሃያ ዓመታት በኋላ ዛሬም ሰላም አላሰፈኑም፡፡ ነገር ግን ሰላምን ዕውን የማድረግ መነሻቸው የጋራ ታሪካችንና የጋራ መፃዒ ዕድላችንን ታሳቢ ባደረገ ሰፊ ራዕይ ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ ቀጣናው ከጋራ ደኅንነት መርሆች እያፈነገጠ ባለው የዓለም ሥርዓት ሳቢያ፣ እጅግ በጣም ከባድ በሆኑ ሥጋቶች በተከበበበት በዚህ ወቅት፣ በተጎራባች አገሮች መካከል ያሉ ውዝግቦችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አስፈላጊነት ከምንጊዜውም የላቀ ነው፡፡

  የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግና ኮሚሽኑ ለኤርትራ ከወሰነላት ግዛቶች ለመውጣት ደፈር ያለ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ያለ ጥርጥር የተናጠል ዕርምጃዎች ባለበት የቆመ ግጭትን ወደፊት በበጎ ሁኔታ ለማላወስና መፍትሔ ለማግኘት የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን ለመተለም ያለውን ዕምቅ አቅም እገነዘባለሁ፡፡             

  የኢትዮጵያ ዓላማ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝቦች ጨምሮ የአካባቢውን ጥቅም የሚያስጠብቅ አጠቃላይ ሰላም ማስፈን ሊሆን ይገባል፡፡ ለሰላም እጅን መዘርጋት አንድ ነገር ነው፡፡ የሚፈለገውን ሰላም ዕውን ለማድረግ መሠራት የሚኖርባቸው ሥራዎች ግን ውስብስብ ናቸው፡፡

  የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ የማድረጉ ሒደት የሚጠይቃቸው አንዳንድ እጅግ ቁልፍ ቴክኒካዊና ሕጋዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ጉዳዩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ኮሚሽን የድንበር ወሰንን የመቀበል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡     

  ውሳኔውን [የድንበር ኮሚሽኑ እንዳደረገው] በካርታ ላይ በማመልከትና መሬት ላይ ድንበሩን በችካል በማካለል መካከል እጅግ ቁልፍ ሊባል የሚችል ልዩነት አለ፡፡ የአልጀርሱ ስምምነት አካል በሆነው ግጭትን የማስቀረት ስምምነት መሠረት፣ ጊዜያዊ የሰላም ቀጣናውን ለመቆጣጠር የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያና የኤርትራ ተልዕኮ (UNMEE) ድንበር የማካለሉን ሒደትም እንዲያግዝ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን በ2000 ዓ.ም. ኤርትራ በፈጠረችው መሰናክል ሳቢያ፣ ልዑኩ ሥራውን በአግባቡ መከወን የማይችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የልዑኩ ተልዕኮ እንዲቋረጥ ወስኗል፡፡ ስለዚህም ይህን ቁልፍ ተግባር የማከናወኑ ተግባር በሁለቱ ወገኖች፣ ማለትም በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ወድቋል፡፡ ሆኖም፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ኮሚሽንም እንዳመለከተው፣ ድንበሩን በካርታ ላይ ከማመላከት መሬት ላይ ወደ ማካለሉ ምዕራፍ ለመግባት የማይጣጣሙና ውስብስብ ገጽታ ያላቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የአገሮቹ ድንበር ሜዳዎችን፣ መንደሮችን፣ ተራራዎችንና ወንዞችን እያቆራረጠ የሚያልፍ በዘፈቀደ የተሰመረ ዓይነት ነው፡፡ የድንበር ወሰኑን የሚያመላክቱ የድንጋይ ችካሎች (ጡቦች) በመሬት ላይ መተከል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሥራ ተግባራዊ በሚደረግበት ሒደት ላይ የድንበር መስመሩ መንደርን፣ ባስ ሲልም መኖሪያ ቤትን አቋርጦ የሚያልፍ ከሆነ ምንድነው የሚደረገው? የድንበር ወሰን አመልካቹ ጡብ የት ጋ ሊተከል ይገባዋል በሚለው ላይ ሁለቱ ወገኖች በጥቂት ሜትሮች ልዩነትም እንኳ ቢሆን ካልተስማሙ ምንድነው መደረግ ያለበት? ከሁሉም በላይ አንገብጋቢው ጉዳይ ደግሞ፣ በአካባቢው የሚኖሩት ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው? ተፈላጊው ሰላም ሊመጣ የሚችለው የድንበር ማካለሉን ተግባር በሁለቱም በኩል ያሉት ሕዝቦች ተቀብለውት ትብብር ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡     

  እነዚህን ጉዳዮች በማሰብ የመውጣቱና ድንበር የማካለሉ ተግባር፣ ከመስክ አዛዥ እስከ ከፍተኛው የመንግሥት የሥልጣን አካል ድረስ ባሉት በሁሉም እርከኖች የማይቋረጥ፣ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር በሚያስችል መንገድ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተባበርን የግድ እንደሚል ግልጽ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ከባድ ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡        

  [ይህን ጉዳይ ከአንደኛው ወገን አኳያ ብቻ ማየት ስህተት ነው፡፡] በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ለኢትዮጵያ በሚሰጡትና ራሳቸውን ኤርትራዊ የሚሉ ነዋሪዎች በሚገኙባቸው እንደ ፆረና ያሉ መሬቶች ጉዳይስ ምንድነው መደረግ ያለበት? የድንበር ማካለሉን ሥራ መሬት ላይ ተግባራዊ የማድረጉ ሒደት በድንበሩ አካባቢ ለሚኖሩት ማኅበረሰቦች ትርጉም ሊኖረው የሚችለው፣ በግል ሀብት ባለቤትነት፣ በ[ማኅበረሰቦች] ነፃ እንቅስቃሴና በተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም፣ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ‹ስስ ድንበሮች› ባሉባቸው ሌሎችም የተለመዱ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነቶች ሲኖሩ ነው፡፡    

  በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩት ሕዝቦች ከእነሱ ጋር ምክክር አለመደረጉን በመጥቀስ ባድመ ላይ የተቃውሞ ሠልፍ ያካሄዱት አሳማኝ የሆነ ያሳሰባቸው ጉዳይ በመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ላይ ቅንጣት ያለመግባባት ስሜት ከተፈጠረ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል፡፡     

  በእርግጥም የአልጀርሱ ስምምነት ከሚሸፍናቸው ጉዳዮች ውስጥ የድንበር ወሰን ጉዳይ ብቸኛው ያልተቋጨ ጉዳይ አይደለም፡፡ በስምምነቱ ጦርነቱ እንዴት እንደተጀመረ መመርመርን ጨምሮ፣ ሌሎች ተግባራትንም እንዲያካሂድ የተቋቋመ የቅሬታ ኮሚስዮን አለ፡፡ ኮሚስዮኑ የተሰጠውን ተግባር አከናውኖ የጨረሰ ሲሆን፣ ከጦርነቱ አጀማመር ጋር በተያያዘ ባካሄደው ምርመራ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በሜይ 1998 ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ አራትን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ስለፈጸመች፣ ኢትዮጵያ ልትካስ ይገባታል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በቅሬታ ኮሚስዮኑ ከተባለው ባሻገርና ከዚያም በላቀ ደረጃ ግን፣ ኤርትራ ግጭት የማስቀረት ስምምነትንም በመጣስ ፋይዳ ቢስ አድርጋዋለች፡፡ ስለዚህም በማያወላዳ መንገድ ለአልጀርሱ ስምምነት ተገዢ ሆኛለሁ የሚለው የኤርትራ ንግግር ተዓማኒነት የሌለው ነው፡፡           

  ስምምነቱ በተበጣጠሰ ሳይሆን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ነው መፈጸም ያለበት፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት መንፈስ፣ ቀጣይ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ትብብሮችን የመሳሰሉና በአካባቢው የሰላምና የፀጥታ ፈተናዎች ዙሪያ የጋራ ዕይታ መያዝን ጨምሮ፣ ውይይት ሊደረግባቸው የሚገቡ ሌሎችም ጉዳዮች አሉ፡፡ 

  የአገሮቹ የድንበር ወሰን በትክክል የቱ ጋ ነው በሚለው ጉዳይ እየተወዛገብን ለጋራ ፈተናዎቻችን መልስ ልናገኝ አንችልም፡፡ ይልቁንም የድንበር ማካለሉን ጉዳይ ቴክኒካዊ ብቃትን በተላበሰ መንገድ ዕልባት ልናበጅለት እስካልቻልን ድረስ፣ አንገብጋቢ በሆኑት በእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያማ ለውይይት እንኳ መቀመጥ አይቻለንም፡፡    

  እጅግ ብዙ ሊነጋገሩባቸው የሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች ያሏቸው ሁለቱ አገሮች፣ ድንበሩ በትክክል የትኛው ነጥብ ላይ ያርፋል ወደሚል አናሳ ጉዳይ ላይ ወርደው መወዛገባቸው እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ኤርትራውያን ለነፃነት ያካሄዱት ትግልና ኢትዮጵያውያን ተራማጆችም ከጭቆናና ከኢፍትሐዊነት ጋር ለሚደረግ ትግል ድጋፍ የሰጡበት ምክንያቱ ይህ [የድንበር መስመር ጉዳይ] አልነበረም፡፡

  ኤርትራ የነፃነት ትግል ታካሂድ በነበረበት ወቅት ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ብዙ ጊዜ ተገናኝቻለሁ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኘነው እ.ኤ.አ. በ1990 በአፍአበት ግንባር አቅራቢያ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ሞቅ ባለ መንፈስ ከተቀበለኝ በኋላ፣ በመጀመርያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታችንን ዕውን በማድረግ ለመቶ ዓመታት አወዛጋቢ ታሪካችን ዕልባት እናብጅና ከዚያ በኋላ ለ3,000 ዓመታቱ የጋራ ታሪካችን ዕውቅና ልንሰጥ እንችላለን አለኝ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የተገናኘነው ካርቱም ውስጥ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ኤርትራ ነፃ ከወጣች ኢትዮጵያ የባህር በር ልታጣ እንደምትችል አነሳሁለት፡፡ በአሰብ ጉዳይ ክርክር ማንሳቴ ኢሳያስን አስቆጣው፡፡ የአሰብ ወደብ ትርጉም የሚኖረው ከኢትዮጵያ ጋር ከተሳሰረ ብቻ መሆኑን፣ ከዚያ ውጪ ኤርትራ በወደቡ አንዳችም ጥቅም እንደማይኖራት አስረግጦ ነገረኝ፡፡ አልፎም ወደቡ ለብዙ ዓመታት ለኢትዮጵያ ሊከራይ እንደሚችል ጠቆመኝ፡፡  

  በተጨማሪም የኤርትራ የነፃነት በዓል በተከበረበት እ.ኤ.አ. በግንቦት ወር 1993 ዓ.ም. በወቅቱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ፣ ጦርነቱ ለአያሌ ሕዝብ ምን ያህል አስከፊ እንደነበርና የኤርትራ ነፃ መውጣትን ተከትሎ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ብሩህ መጪ ዘመን ዕውን ሊሆንላቸው እንደሚችል ተስፋ ማድረግ እንደሚችሉ በስሜት እንደተናገሩ አስታውሳለሁ፡፡ በሥፍራው ከነበሩት ኤርትራዊያን ብዙዎቹ ይህን መሰል ንግግር ከኢትዮጵያ መሪ በመስማታቸው ስሜታቸው ተነክቶ አለቀሱ፡፡  

  የኤርትራውያን ትግል ለኢትዮጵያውያን ተራማጆች መነቃቃትን የፈጠረ፣ ብዙዎቻችንን ራስን በራስ ከማስተዳደር መርሆችና ከሕዝባዊ ትግል ጋር ያስተዋወቀ ክስተት ነበር፡፡ በ1980ዎቹ ለኤርትራ እንደ ሉዓላዊ አገር ዕውቅና ለመስጠት ቀዳሚ ለመሆን ፈቃደኛ መንግሥት በአዲስ አበባ ባይኖር ኖሮ የኤርትራ ነፃነት እጅግ፣ እጅግ በጣም ከባድ ሊሆን ይችል ነበር፡፡       

  የነፃነት ጦርነቶቹ ለላቀ ዓላማና ለሁለቱም አገሮች መሠረታዊ ለውጥ ተጋድሎ የተካሄደባቸው ናቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች የተካሄዱት ትግሎች የጋራ ዓላማ አዲስ ግንኙነትን ዕውን ማድረግ እንጂ ድንበሮችን መከላከል አይደለም፡፡ በመላ አፍሪካ ያሉ ሕዝቦችና መንግሥታት ከ100 ዓመታት በፊት ቅኝ ገዢዎች በካርታ ላይ ያሰመሯቸው የድንበር መስመሮች ‹አርቲፊሽያል› መሆናቸውን፣ ከዚያ በበለጠ ሕዝብን ያማከሉ የሕዝብ ድንበሮች መኖራቸው ሊበረታታ እንደሚገባ ተገንዝበዋል፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ እንዳሉት፣ በድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች እንደ ተፈረፈረ እንቁላል ናቸው፣ እነርሱን ድንበር በማስመር መነጣጠል አይቻልም፡፡            

  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደው ጦርነት ከድንበር ጉዳይ ጋር ብቻ የተያያዘ እንደ ነበር አድርጎ በመውሰድ፣ መፍትሔ የሚያገኘውም ድንበሩን በማስመር ነው የሚለው ሐሳብ ወለፈንድ ነው፡፡ የድንበሩ ውዝግብ የአጠቃላይ ችግሩ አንድ ገጽታና ለጦርነቱ መቀስቀስ እንደመነሻ የሚወሰድ ነው፡፡ ነገር ግን በአልጀርሱ ስምምነት ላይ ተመሥርቶ በግጭቱ ላይ የተካሄደው ኦፊሴላዊ ምርመራ ይፋ እንዳወጣው፣ ምክንያቶቹ ከዚያም በላይ ውስብስብ ናቸው፡፡ በድንበሩ ሳቢያ ደም የሚያፋስስ ጦርነት ውስጥ መግባት አስፈላጊ ነበር የሚል ሐሳብም በእውነቱ ግራ ነው፡፡ በአፍሪካ ተጎራባች አገሮች መካከል ካሉት ድንበሮች የተካለሉት ከ30 በመቶ በታች ናቸው፡፡ በዓለማችን ላይ ከ270 የሚበልጡ ገና ያልተፈቱ የአገሮች የድንበር ውዝግቦች አሉ፡፡ የድንበር ጥያቄን በኃይል መፍታት ግን ተቀባይነት የለውም፡፡ የድንበር ውዝግቦች በድርድር ሊፈቱ ይችላሉ፡፡           

  የዚህን አላስፈላጊ ጦርነት መጥፎ ጠባሳ በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ከጠፋው የሰው ሕይወት፣ በአያሌ ሕዝብ ላይ ከተፈጠረው የሕይወት መመሰቃቀል፣ እንዲሁም በሁለት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከተፈጠረው የባይተዋርነት ስሜት ጋር፣ በቅኝ ግዛት ድንበር ላይ ትኩረት ካደረገ እጅግ ጠባብ ዕይታ የመነጨውን የመሪዎቹን ጠባብ ርዕይ ነው የምንመለከተው፡፡ ወደዚህ የድንበር መስመር አባዜ እንድንመለስ ሊያደርገን የሚችል ጉዳይ ቢኖር፣ እጅግ ኋላ ቀር የሆነ ያለመተማመን ደመነፍስ ብቻ ነው፡፡  

  ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እስካሁን የኢትዮጵያን በጎ ጥሪ አልተቀበሉም፡፡ እልባት ያላገኘውን ግጭት ወለፈንዳዊ ሰበዝ እያንጓለሉ ሲሆን፣ ከሐሳበ ግትርነታቸውና ከእብሪተኛ ባህርያቸውም ጋር ጉዳዩ ከድንበሩ ጥያቄ እጅግ የገዘፈ የመሆኑን እውነታ እያሳዩ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላም አንዳችም የተቀየረ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1998 ግጭቱ ሲቀሰቀስ በአሜሪካና በሩዋንዳ የተካሄደው የመጀመርያው ሽምግልና የተሰናከለበት አንዱ ምክንያት የማስማሚያ ሐሳቡ፣ ከድንበር ባሻገር ያሉ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን አላካተተም የሚል ነበር፡፡ በአሜሪካና በሩዋንዳ የቀረበው ማስማሚያ፣ በቅድሚያ ነገሮች ከወረራው በፊት ወደነበሩበት ይመለሱና ከዚያ የድንበር ጥያቄው ወደ ግልግል ፍርድ ቤት ያምራ የሚል ነበር፡፡ ውዝግቡ የድንበር ጉዳይ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ በዚህ የማስማሚያ ሐሳብ መሠረት መፈታት በቻለ ነበር፡፡              

   

  እንደሚገመተው ኢሳያስ የጠንካራ ተደራዳሪ ቁመና ለማሳየት የሚሞክሩት በአዲስ አበባ ያለው አዲስ መንግሥት ደካማ ነው ከሚል እሳቤ በመነሳት፣ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ እሺታን ላገኝ እችላለሁ በሚል ምክንያት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል፣ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም መፍጠር፣ አገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያስተዳደሩ ለመቆየታቸው፣ ሠራዊታቸውንም አጠቃላይ ሥምሪት ላይ ለማዋላቸው፣ ለረዥም ጊዜ ሲሰጡ የቆዩትን ሽፋን ሊያሳጣቸው፣ ይኼንም ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ1997 በጥልቀት የተረቀቀውን፣ ነገር ግን እስካሁን ተፈጻሚ ሆኖ የማያውቀውን ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ ወደማዋሉ ሒደት ለመመለስ የሚጋብዝ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ በማሰብ ተጨንቀው ሊሆንም ይችላል፡፡ በእርግጥም ይህ የሚሆን ከሆነ ለመናገር ነፃነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች መንገድ የሚጠርጉ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ይታሰባል፡፡        

  ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ኢሳያስ ስለኢትዮጵያ ያላቸው ዕይታ አልተቀየረም፡፡ ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን የኤርትራ መሪዎች ኢትዮጵያን ‹‹በአልባሳት የተጀቦነች ዛየር›› ሲሉ ገልጸዋት ነበር፡፡ ኮንጎን ለረዥም ዘመን ሲገዙ የኖሩት ሞቡቱ [ሴሴሴኮ] ‹ከመብረቅ የፈጠነ› በሚባል ወታደራዊ ዘመቻ ከሥልጣን የተወገዱበትና ይህን ተከትሎ መላ አገሪቱ ከባድ ውድቀት ውስጥ የገባችበት ወቅት ነበር፡፡ እነሆ ግን ከሁለት አሠርት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ እንደበሰበሰ ግንድ አልወደቀችም፤ ይልቁንም ከዚያን ጊዜው እጅግ በተሻለ መጠን ወደ ብልፅግና ያመራች ጠንካራ አገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን ለውጦች በማካሄድ ላይ የምትገኝ የታታሪ ማኅበረሰቦች አገር ነች፡፡ በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ በፍጥነት የሚያድግ አገር እንደሚያጋጥመው ሁሉ፣ እንከኖችና ተግዳሮቶችም እንዳሉባት ዕሙን ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ግን በተቃራኒው ኤርትራ ካለችበት ፈቀቅ ማለት አልቻለችም፡፡ የሕዝቧን ትኩስ ኃይል በማያቋርጥ የስደት ፍሰት እያጣች ስትሆን፣ አብዛኛዎቹም ወደ ኢትዮጵያ እየኮበለሉ ነው፡፡ የኤርትራ ዩኒቨርሲቲዎች የተዘጉ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቿም ተመራቂዎቻቸውን በቀጥታ ወደ ጦር ሠራዊቱ ይልካሉ፡፡ ከሕዝቧ ቁጥር አንፃር ሲታይ በስደተኞች ብዛት ከየትኛውም የዓለም አገር ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች፡፡ ከእነዚህ ሁነቶች አኳያ ኢትዮጵያ ከፍና ተለቅ ማለት ይጠበቅባታል፡፡ የሰላም አጀንዳን በመወሰን ረገድ መሪ ሚና መጫወት ትችላለች፣ መጫወትም ይኖርባታል፡፡  

  ኢሕአዴግ የመጀመርያውን ዕርምጃ ተራምዷል፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ በተናጠል ኢትዮጵያ እጇን ለኤርትራ ዘርግታለች፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ይህን ከጥንካሬ ይልቅ የድክመት ምልክት አድርገው ተመልክተውታል፡፡ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ዕርምጃም ዕልባት ሊያገኙ የሚገባቸውን ጉዳዮችን በዝርዝር ለይቶ ለጠረጴዛ ድርድር ማቅረብ፣ ከዚህም ጋር በአልጀርስ ከስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች በሙሉ፣ እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን እንደምን ወደ መደበኛ መልካቸው መመለስ እንደሚቻል የሚያመላክት አጀንዳ መቅረጽ፣ አገሮቹ የሦስት ሺሕ ዓመታት የጋራ ታሪካቸውን ዳግም ይጀምሩ ዘንድ መሪ ሚና መጫወት ይኖርባታል፡፡ የኤርትራ አጀንዳ በሆነው የድንበር ጉዳይ ላይ መቸንከር የለብንም፡፡ ይልቁንስ በሰፊ ርዕይ የተቃኘ ጉዟችንን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ይህን መሰል ግጭቶች ዕልባት የሚያገኙበት ዓለም አቀፍ አሠራር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተገናኝቶ አለኝ የሚሉትን ጥያቄ በሙሉ ለውይይት ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ መሆኑን በአፅንኦት መናገር ይኖርብናል፡፡     

  ኢትዮጵያ የአልጀርሱ ስምምነት በምልዓት ሊተገበር ይገባዋል፣ የድንበር ማካለሉ ዝርዝር ጉዳዮች፣ የወታደሮች ሥርዓት ባለው አኳኋን የመውጣት ጉዳይ፣ በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩት ሕዝቦችን ሥጋቶች ከግምት ባስገባ መንገድ በትክክለኛው መንገድ መከናወን ይኖርበታል የሚል አቋም በፅናት ማራመድ ይኖርባታል፡፡ ይህን ማድረግ ኢትዮጵያ ሁለቱን አገሮች የሚመለከተውን አጀንዳ ሁሉን አቀፍ፣ በመርህ ላይ በተመሠረተና በትክክለኛው መንገድ ቀርፃ መሪ ሚና መጫወት የምትችል፣ ችግሩን አጥብቦ በሚመለከት ብያኔ ሳቢያ ወደ አላስፈላጊ ንትርክ ተጎትታ የማትገባ ጠንካራ አገር መሆኗን ያሳያል፡፡ በዚህም ጫናውን ወደ ኢሳያስ መገልበጥ፣ በኤርትራ አዲስ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈቅድ የሚያስገድድ ሁኔታን መፍጠር፣ በሕዝቡ ላይ ለሚፈጽመው አፈና እንደ ሰበብ የሚጠቀምበትን ‹የኢትዮጵያ ፍራቻ› ካርታ ማስጣል ይቻላል፡፡    

  የአልጀርስ ስምምነት ምስክሮች የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላትም ለሰላም የተከፈተውን ይህን መልካም ዕድል ላለማባከን፣ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ በአዲስ መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከዚህም የላቀ ፋይዳ ያለው አንድ ነገር አለ፡፡ የሰላምን ጉዳይ ለመሪዎቹ ብቻ ልንተውላቸው አይገባም፡፡ ከመንግሥታቱ ባሻገር የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የሚያቀራርቡ በዜጎች የሚካሄዱ የሰላም ንቅናቄዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ግንኙነት የሚመለከቱ ተረኮችን በድንበር ጉዳይ ላይ ከተቸነከረ ጠባብ ጥያቄ አውጥተን፣ ከዚያ ወደ ላቀ ወደ ሁለቱ አገሮች መፃዒ ዘመን ማተለቅ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅና በብዝኃነት የምትገለጽ አገር ናት፡፡ ከኤርትራ ጋር ሰላም የመፍጠር ጉዳይ የመንግሥታችን ብቻ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ለሕዝቦቹም የራሴ የሚሉት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የድርሻቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ ለሰላም ሰፊ ንቅናቄ ማድረግ አለብን፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያውያን ጋር ዳግም መገናኘትን ለረዥም ጊዜ ሲናፍቁ ከኖሩት የኤርትራ ዜጎች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ለመገንባት መንቀሳቀስና የወገናዊ ግንኙነታችንን ፍሬዎች ለማጣጣም መትጋት ይኖርብናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካሬ፣ ለሰላማዊ ውይይትና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ለመኖር ያለን ፍፁም ዝግጁነት ነው ለየአገሮቻችን እውነተኛውን ሰላም ሊያጎናፅፍ የሚችለው፡፡           

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bati101@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...