Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትየኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ምን ይሻለዋል?

  የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ምን ይሻለዋል?

  ቀን:

  በገነት ዓለሙ

  የኤርትራ መንግሥት/ሻዕቢያ ባድመንና አካባቢውን የወረረው በ1990 ዓ.ም. ግንቦት ወር መጀመርያ ላይ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ የካቲት 21 ቀን 1991 ዓ.ም. ከተጠናቀቀው ከዘመቻ ፀሐይ ግባት ከግንቦት 1992 ዓ.ም. ሌላው ግዙፍ ጦርነት ወዲህ ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. (ዴሴምበር 12 ቀን 2000) የአልጀርሱ ስምምነት ከተፈረመ፣ በዚህ ስምምነት መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን ሚያዝያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም. ውሳኔውን ካስታወቀ በኋላ . . . ከዚያም የድንበር ኮሚሽኑ ብሎ ብሎ ቢሰለቸው የአንድ ዓመት ‹‹ቀጠሮ›› ሰጥቶ፣ ይህ የአንድ ዓመት ገደብ ሲያልቅ ራሱን ያሰናበተበትን የኅዳር 18 (ኖቬምበር 27 ቀን 2006) 1999 ዓ.ም. ውሳኔ ወዲህ፣ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኗ እንደ አዲስ የተሰማው ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ላይ ነበር፡፡ ይህንን ውሳኔና ጥሪ ‹‹ልዩ›› የሚያደርገው የኢትዮ ኤርትራን ጉዳይና ነገር በኅዳር 1997 ዓ.ም. በፓርላማ ጭምር ቀርቦ ከፀደቀው የመንግሥት ውሳኔ ወዲህ የመጣ አዲስ ነገር በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ የ1997 ዓ.ም. የሰላም ሐሳብ ዝርዝር፣ የአሁኑ ደግሞ ደምሰሳ በመሆኑም አይደለም፡፡ የ1997 ዓ.ም. የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ የተቀበለው በመርህ ደረጃ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆኑም ዋናው ልዩነት አይደለም፡፡ የዘንድሮውን ‹‹ውሳኔ›› ልዩ የሚያደርገው የኢሕአዴግ ውሳኔ፣ ለዚያውም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሆኑ ነው፡፡

  ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ችግሮች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው በፓርቲና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ተፈልቅቆና ጠርቶ አለመውጣቱ ቢሆንም፣ የፓርቲው ድምፅና ውሳኔ የመንግሥት ድምፅና ውሳኔ ለመሆን ምንም ከልካይና ገላጋይ ባይኖረውም፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚም ሆነ የፓርቲው (የኢሕአዴግ) ምክር ቤት ካስፈለገ አንድም ሁለትም መሆን የሚከለክላቸው ፍጥርጥርም ሆነ ሕግ ኖሮ ባያውቅም፣ የግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ግን ይህንን ‹‹ማስመሰል›› እንኳን ማለፍ ያልቻለ ‹‹አስደንጋጭ›› ሆኗል፡፡ ውሳኔውን ‹‹አስደንጋጭ›› እና አወዛጋቢ ያደረገው ያልተለመደ ግልጽ ተቃውሞ ያጋጠመው፣ ግን የገዥው ፓርቲ ለዚያውም የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ የመንግሥት ውሳኔና ፖሊሲ ሆኖ ‹‹ያለ ኃፍረት›› በመቅረቡ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ራሱ ውስጥና በአባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው የግራ/ቀኝና የትግል አዝማሚያ ልዩነት መኖር፣ የፓርቲውም ሆነ የፓርቲው የሥልጣን አካላትና አባላት የገደል ማሚቶነት መናጋት፣ የተለመደውና የሰፈነው ‹‹አድራጊ ፈጣሪነት›› ምቾት እያጣ መምጣት ነው፡፡

  በዚህ ምክንያት ለወትሮ ውስጥ ለውስጥ ብቻ እየተብሰለሰለና እየተንተከተከ ግፋ ቢል ደግሞ የውጭ አገር የሾርት ዌቭ ሬዲዮና የሳተላይት ቴሌቪዥን ዜና ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችል የነበረው ብሶትና ቅዋሜ፣ የአገር ውስጥ የመንግሥትና የፓርቲ ሚዲያዎች ጭምር ዘገባና ትንታኔ ሆኖ ሲቀርብ አየን፡፡ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍና የዚህም ድጋፍ አስተጋቢና አብራሪ ፕሮግራሞችን ማየት ወግ ሆነ፡፡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ እኩል ውክልና ያለው ሕወሓት በማዕከላዊው ኮሚቴ አማካይነት ባልተለመደ ሁኔታ አስቸኳይ ስብሰባ ሲጠራ፣ አስቸኳይ ስብሰባም አድርጎ ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የአቋም መግለጫ ሲያወጣ፣ በአቋም መግለጫውም የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የግንቦት 28 ውሳኔን በሾርኒ ሳይሆን በግልጽ እያገላበጠ ‹‹ሲጠርብ››፣ እንዲሁም በዚሁ ምክንያት የኢሕአዴግ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ሲጠይቅ ሰማን፡፡

  የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁን አነጋጋሪ የሆነውን ውሳኔ እንኳንስ የመንግሥትና የአገር፣ የራሱ የፓርቲው ውሳኔ አድርጎ ለብቻውና በዚህ ብቻ መወሰን እንደማይችል በመርህ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በገዛ ራሱ የመተዳደርያ ደንብ የተወሰነና የታወቀ ነው፡፡ ኢሕአዴግን በበላይነት የሚመራው (ከአንድ ጉባዔ እስከ ተከታዩ ጉባዔ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ)፣ ለዚያውም የፓርቲውን ጉባዔ ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ አገር አቀፍ ሚናና ትርጉም ባላቸው ጉዳዮች ላይ ፖሊሲዎች ማውጣት የሚችለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ቢሆንም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አሁን ውሳኔ የሰጠበትን ጉዳይ ለምክር ቤቱ የማቅረብ ሥልጣን ጭምር ቢኖረውም፣ አሁን ሲሆን እንደሰማነው የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ የአገር ጥሪ፣ የመንግሥት አቋም፣ የሌላውን ወገን ወይም አገር በጎ ምላሽ ብቻ የሚጠይቅ ፖሊሲ ሲሆን ማየት ግን እንደተባለው ብዙ ችኮላና ጥድፊያ የበዛበት፣ በራሱ በፓርቲው ውስጥም ያለ ብልኃትና መላ የተገለጸ ውሳኔ ነው፡፡

  በግለሰብ ደረጃ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰነው ጉዳይ የመንግሥትና የኢትዮጵያ አቋም ቢሆን፣ የ1997 ዓ.ም. ውሳኔን ቢሽርና በዝርዝር አዲስ የሰላም ሐሳብ ቢተካ፣ ኢትዮጵያም ወዳ የገባችበትን የአልጀርስ ስምምነትና ስምምነቱ የወለደው ኮሚሽን የሰጠው ውሳኔ ተፈጻሚነት የሚቋጭበትን ሕጋዊና ሰላማዊ መላ ይዛ የምትቀርብበት ሥርዓት ውስጥ ብትገባ ደስተኛ ነኝ፡፡ አዲሱ ሐሳብም ይህንን ያመላክታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› መንገዱ አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ይዘት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ውሳኔው በተደረሰበት አሠራርና አግባብ ላይ ጭምር ሐሳብን ማንሸራሸርና ማሰማት፣ ተቃውሞንም ማስተጋባት ማንም የሚሰጠውና የሚከለክለው መብትና ነፃነት አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ችግራችን የተለያዩ ሐሳቦች የተቃረኑ መንገዶች መኖራቸውና መገለጻቸው ሳይሆን፣ አሸናፊ የሆነው ሐሳብና መንገድ ራሱ በሕግና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ሊደረስበት የሚገባ መሆኑ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

  በችኮላም ይሁን በተለመደውና ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው መንገድ ነጉዶ ኢሕአዴግ ሐሳቡን እንዲህ ፖሊሲና ሕግ ሲያደርግ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ወይም አዲስ የኢትዮ ኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመንደፍ ‹‹ድረሴ›› መፍትሔ ማውጣት የአዲሱ ዓብይ አህመድ ኢሕአዴግ ‹‹ችኩል›› አሠራር ሆኖም አይመስለኝም፡፡ በአንድ ፓርቲና በመስመሩ የመመራት ጉዳይ ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ የማረጋገጥ ነገር ነው ብሎ መጠየቅ ያለፉት 27 ዓመታት፣ በተለይም ያለፉት 23 ዓመታት የፌዴራላዊት ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ዋና ጎደሎ ሆኖ ኖሯል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ረገድ ያሻውን ሲያደርግ፣ የፈቀደውን ሕግ አድርጎ ሲያወጣ፣ ሲሽር 27 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የአሁኑን የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ ውሳኔ እንኳንስ የአገር ሕግና ፖሊሲ የራሱ የኢሕአዴግ የድርጅቱ ከመሆን የከለከለው፣ ወይም ከመሆን የተገዳደረው፣ ምናልባትም ያጋለጠው 27 ዓመታት ሙሉ ሠርተን ያዋቀርነው ዴሞክራሲ ሳይሆን ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት የተፈጠረው የሕዝብ እንቅስቃሴ ያስከተለው ግፊትና የፈጠረው መነቃቃት ነው፡፡ የሕወሓት የሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫም ምንጭ የኢሕአዴግ ‹‹ውስጠ ዴሞክራሲ›› ሳይሆን ተከድኖ የበሰለ ፀረ ዴሞክራሲ ውስጥ የተነሳው ማዕበል የከፈተው ማስተንፈሻ የፈጠረው ነው፡፡

  እውነቱን ለመናገር የኤርትራን የሥር የመሠረት የነፃነት ትግልና የኋለኛውን አርነት ያመጣው፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ እምነትና እብሪት ሕግ ሆኖ በስንት ትግል የተገኘውን ፌዴሬሽንና ለሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአርዓያነቱ ሊተርፍ ይችል የነበረውን የራስ አስተዳደር በመሻራቸው ነው፡፡ ሥልጣንን መሬት ላይ ወድቆ ያገኘው ወታደራዊ መንግሥትም ጉዳዩን አባባሰው፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ትግል ውስጥ መፈታት ይገባውና ይቻል የነበረውን የኤርትን የነፃነት ትግልም የኢሕአዴግ እኔ ብቻ ልክ ዳፍንት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውጭ አድርጎ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ አይደለም ብሎ ፈረደበት፡፡ አማራጭ የሌለው ሪፈረንደም ተካሄደ፡፡ ኤርትራ የብቻ አገር እንድትሆን የሚያደርገው ውሳኔ ‹‹አማራጭ›› ካጣ በኋላም ለብዙ የሕዝብ ወገኖች ሌላው ቢቀር ለውዝግብና ጦርነት መንገድ በማይከፍት አኳኃን ለመለያየት አለመቻሉና አለመፈቀዱ ሌላው የእኛው መንግሥት ጭምር ተባባሪ የሆነበት አሳዛኝ ድርጊት ነበር፡፡

  እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከነፃነት በኋላም የተፈጠረው ችግር በገዛ ራሳችን መንግሥት ማናለብኝነት፣ ከእኔ ሌላ አዋቂ የለም ባይነትና በዚህ ላይ በተመሠረተ ጥፋት የመጣ ነበር፡፡ የተገነጠለችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ አልነጠልም አለች፡፡ መሪዎቿ ኤርትራ የግላችን ኢትዮጵያ የጋራችን ብለው ኢትዮጵያ ላይ ተተከሉ፡፡ የእኛውም መንግሥት ይህንን የሚቃወሙትን እየተዋጋና እያሳጣ ተመቻቸው፡፡ ሻዕቢያ ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር የተፈራረማቸውን ውሎችና ነባርና አዳዲስ ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ተተግኖ፣ በአገሪቱ ሁለገብ ሕይወት (በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ በፋይናንስ፣ በወታደራዊ አውታሮች ሁሉ) ያሉትን ደጋፊዎቹንና አባላቱን የሥልጣን፣ የሻጥር፣ የመረጃና የጥቅም ማቀነባበሪያ አድርጎ በተለይም ከወደብ ጥቅምና ከኦነግ ጋር በተበጀ ልጓም ወያኔን እየተቆጣጠረ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የጋራችን ኤርትራ የብቻዬ›› በመባል የተገለጸ ምጥመጣውን ተያያዘው፡፡ የኤርትራ ግንባታና የወታደራዊ ትግግዝ አገር እስከመሆን የውጭ ብድር በኤርትራ ስም እስከመበደር የሄደው የኢሕአዴግ መንግሥት ግን፣ ይህንን አንጋዳ ግንኙነት አቃንቶ የጋራ ጥቅም ፈር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ አልቻልም፡፡ ኤርትራዊውና ኢትዮጵያዊውም በአግባቡ እንዲለይ ማድረግ አልሆንለት አለ፡፡ የተዛነፈውና የተዛባው ግንኙነት የተቃውሞ መፍለቂያ ሆነ፡፡ ይህም በራሱ በኢሕአዴግ ድርጅትና በሠራዊቱ ውስጥ የልዩነት መብቀያ ከመሆን አንስቶ ከመላ የአገሪቱ ሕዝብ ጋር መቃረኛ እስከመሆን የሰፋ አድማስ ነበረው፡፡

  የሻዕቢያ መንግሥት ግን ኢትዮጵያን የጋራ ማድረጉን ቀጠለ፡፡ የኢትዮጵያም መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ተቃውሞ ‹‹ለ እልህህ . . ›› ብሎ ለሻዕቢያ ተመቸው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በመላ አገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከንግድና ከፋይናንስ አውታሮች አንስቶ እስከ ላይ የመንግሥት ቢሮክራሲ ድረስ ባለው መረብ አማካይነት የማይሠራው የማፍያ ሥራ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ስም ከውጭ ይበደራል፡፡ ከኢትዮጵያ ባንኮች ሕግ የጣሰና ከዋስትና ጋር የማይመጣጠን ከፍተኛ ብድር ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ወኪሎቹ አማካይነት ይወስዳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከጭነት መኪና ንግድ እስከ ፋይናንስ ድረስ በእጅ አዙር የንግድ ሥራ ይሠራል፡፡ ሽፋን ሆነው በሚሠሩ የንግድ ተቋማቱና በዜጎቹ በኩል የሚያሰባስበው ትርፍ ሳይበቃው የአሻጥር ንግድም ያጣጡፋል፡፡ የውጭ ሸቀጥ በትራንዚት ስምና በሌላ የኮንትሮባንድ ሥልት እያስገባ፣ የኤርትራ ምርቶችንም እያሰረገ ዋጋ ሰብሮ ትርፍ ያጋብሳል፡፡ የገበያ ቀውስ ይፈጥራል፡፡ ምልክት/ታግ እየቀየረ የኤርትራን ምርቶች የውስጥ ምርቶች አስመስሎ ይሸጣል፡፡ የከተማ ቦታ እየተረከቡ መቸብቸብ፣ የቅርስ ስርቆትና የዕፅ ንግድ ሌሎች የሀብት ማሰባሰቢና ማካበቻ መንገዶች ነበሩ፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማትና በብዙኃን ማኅበራት ውስጥ ደጋፊዎቹ ሹም ሆነው የሚዘርፉበት፣ አልሆን ሲል ደግሞ የቻሉትን ያህል ቋጥረው ሽው የሚሉበት አሠራር ነበር፡፡ ከኤርትራ ወደቦች አገልግሎት ገቢዎች ባሻገር በዕቃዎች ትልልፍ ላይ ካለ ጉቦ አንዲት ጋት የማያላውስ ቢሮክራሲያዊ ጭምልቅልቆሽም ሀብት መምጠጫ (በጉቦና በትርፍ ጊዜ ሥራ ክፍያ) አድርጎ ይጠቀማል፡፡ የጭነት ማቆያ ኪራይ እየተከመረበት የኢትዮጵያ አስመጪ ዕቃውን ለመተው የሚገደድበት ሁኔታ ሁሉ ያጋጥመው ገባ፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

  የኢሕአዴግ መንግሥት እስከ 1990 ዓ.ም. በነበረው የሰባት ዓመት ቆይታው ኢኮኖሚው ላይ ነፍስ በመዝራት ውስጣዊ የፖለቲካ ሰላም በመፍጠርና የሕዝብ ተቀባይነትን በማግኘት ረገድ ገና አልተሳካለትም ነበር፡፡ የናደውን የመከላከያ ኃይል እንኳን በወጉ መልሶ አልገነባውም፡፡ እንዲያውም የመከላከያን ግንባታ ያስታወሰው በግብፅ መሪ ላይ በተሰነዘረ የግድያ ሙከራ ምክንያት ከሱዳን ጋር በተጣመደ ጊዜ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ የፖሊስና የፍትሕ አስተዳደሩ መታደስ ይቅርና ቀውሱ አልተገታም፡፡ የጊዜው ትልቅና ግዙፍ እንቆቅልሽ ደግሞ አገሪቱ መዝጊያ የሌለው ቤት እስክትመስል ድረስ የሻዕቢያንና የውስጥ አርበኞች የማፍያ፣ የዝርፍያ፣ የስለላና የአፈና ሥራ (ለራሱ ደኅንነት ሲል እንኳ) መቆጣጠር የተሳነው መሆኑ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ብቻ ሳይሆን የሻዕቢያን ተቃዋሚዎች ጭምር መተናነቅ ያዘ፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ወያኔ የሻዕቢያ ወኪልና ፍጡር ነው፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ መንግሥት የላትም፤›› ተባለ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያሰኘው የሻዕቢያ ጉድና መዥገርነት ብዙ ነው፡፡ ጦርቱንም የወለደው ድንበር ወይም ባድመ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ‹‹አልነጠልም›› ባይነት ነው፡፡

  ኢሕአዴግም ይህን ሁሉ ያውቅ ነበር፡፡ ባለ ብዙ ጆሮ ነውና አይጠፋውም፡፡ ግን ለምን? የበለጠ ጥናት የሚጠይቅና ለሙያተኞች የሚተው ቢሆንም፣ አንደኛውና ዋነኛው የራሱ የኢሕአዴግ የሥልጣን ስስት ነው፡፡ ተቀናቃኞችን ላለማስቀረብ ሲል በተለያየ መልክ የሚገለጹ ተቃውሞዎችን በመተናነቅ ተጠምዶ ጊዜውንና አቅሙን ሲፈጅ ኖረ፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ ያለው ጆኦ ፖለቲካዊ ውስብስብ ግንኙነት አስተማማኝ የመከላከያ ኃይል መያዝን የሚጠይቅ መሆኑን ያለመረዳትም እንጭጭነት ነበረበት፡፡

  በሌላ በኩል በኢሕአዴግ ሥር የገባችውን ኢትዮጵያን ሻዕቢያ የሚመለከታት እንደ ግዳይ፣ ማለትም እንደ ዕዳ ከፋይ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ራሱም ይህንን ዓይነቱን አተያይ ከእነ ተግባራዊ መገለጫዎቹ ለመታገል የሚያስችል ንፅህና አልነበረውም፡፡ በሻዕቢያ አድራጎቶች ኢሕአዴግ ቅሬታ ቢኖረው እንኳን የጋራ ሉዓላዊ ጥቅምን ሻዕቢያ እንዲያከብር ገፍቶ መጫን ‹‹ጠላተ ብዙ›› ሆኖ እያለ አንድ አለኝ የሚለውን አጋር ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ ያሸለበውንና የሚያውቀውን የሻዕቢያን ሸረኝነት በራሱ ላይ ማነሳሳት ይሆንበት ነበር፡፡ ማለትም የባህር በር ተከልክሎ በቀውስና በእጅ አዙር ጥቃት ተመትቶ የመወገድ አደጋን መጋበዝ ይሆንበታል፡፡ በተቃውሞ እየተለበለበ የሻዕቢያን መዘባነን ታግሶ የቆየው ለዚህ ይመስላል፡፡

  ከጦርነቱም በኋላ ከ1991 እና ከ1992 ዓ.ም. ድል በኋላ ኢሕአዴግ የሰላም ስምምነቱን ያከናወነበት አሠራር ጥፋት በጥፋት የተሞላ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለው፣ በውስጡ የሚያምነውና ፈርሞ የሚከራከርበት ጉዳይ ለየቅል ናቸው፡፡ ባድመን የሚያስተዳድረው ዕድሜ ልኩን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው እያለ ለሕዝብም ይህንን እያሰማ የመከራከሪያውን ፊርማ ያኖረው ግን፣ በቅኝ ግዛት ውሎች መሠረት ባድመ የማናት የሚለው ጭብጥ እንዲወሰንለት ነው፡፡ የ1994 ዓ.ም. የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ እንኳን ባድመን ለማን እንደወሰነ የ‹‹ማወቅ›› ችሎታው ጨርሶ የጠፋበት መንግሥት ነው የኢትዮጵያን ጉዳይ ሲመራው የቆየው፡፡ ለደም መፋሰስ፣ ለዚያውም ለሚዘገነንን ፍጅት ሰበብ የሆነው የድንበርና የባድመ ጉዳይ ለሁለቱም አገሮች የሚፋጅ እሳት ሆኖ አሁንም ተገሽሯል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንዳለ የማስፈጸምና በድርድር የማረቅ የሁለቱ መንግሥታት ተቃራኒ ፍላጎቶች፣ ይህ ቢፈታ እንኳን ከመንግሥታቱ ውጪ ያሉ የሁለት ሕዝቦች የተዳፈኑ ፍላጎቶች እንደተፋጠጡ ናቸው፡፡

  ቀውስ ሳይመጣ የድንበር ወዝግቡ ‹‹ተፈታ›› ቢባል እንኳ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ምን ያህል ከንቁሪያ ይገላገላሉ? ዋናው የፀብ ምንጭ ድንበር ባለመሆኑ የድንበር መፍትሔ ፀብን አያካትምም፡፡ ከ1983 እስከ 1990 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ የሻቢያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰበ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዳያዳብር ጠንቅ የሆነውና “የመቶ ዓመት የቤት ሥራ” ለተባለለት ደባ ምንጭ የሆነው ግለሰባዊ ክፋት ሳይሆን፣ ከጣሊያንና ከእንግሊዝ በመቀበል ኢትዮጵያ በቅኝነት ገዝታናለች የሚለው ህሊናን ሲመርዝ የኖረ የፈጠራ ታሪክ ያፈራው ቁጭትና ተበቃይነት ነው፡፡

  የየአገራቸውን መንግሥት የተጠጉትም ሆኑ ከሁለቱም ጉያ ውጪ ያሉት ተቃዋሚዎች ከነባር ዕይታና ፍላጎት የተላቀቁ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ፊት ለፊት ተነገረም፣ ዙሪያ ተዞረም ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያበቃ አቅምን አዳብሮ ካለመገኘት የተነሳም ሆነ በተለያየ ጊዜ በተፈጸሙ የፖለቲካ ስህተቶች ምክንያት ሳይሟላ የቀረ የወደብ መብት ጥያቄ አለ፡፡ የኤርትራውያኑ ትኩረት ደግሞ የአገርን ጥቅም አሳልፈው ሰጡ ሳይባሉ የድንበር ውሳኔውን መጨረስና የተቋረጠ የወደብንና የሸቀጥ ነክ ንግድን መመለስ ነው፡፡ ‹‹አሰብ ለኢትዮጵያ ይገባል›› እያሉ እሷን እንደምንም ለማግኘት የሚደረግ ማድባት፣ “አሰብን የግመል መጠጫ አድርጎ” ከመበቀል ፍላጎት ብዙም የማይለይ ወይም ከእንግዲህ አፍንጫህን ላስ ለሚል ደንታ ቢስነት የተመቸ፣ በኤርትራ በኩል ተቀባይነት የማያገኝና በሰላም ለመኖር የማያስችል አካሄድ ነው፡፡ የድንበር ውዝግብን መፍትሔ ሰጥቶ መውጫ ለሌላት ኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎትን ‹‹በሰላም›› የመሸጥ ዓላማም እንዳለፈው የበሩ ጌታ እኔ ሆኜ ላሽቆጥቁጥ ከማለት የማይለይ፣ ከኢትዮጵያ በኩል የሚመጣውን ተጠቃሁ ባይነትና የባህር በር መብት ጥያቄ፣ ከዚህም የሚመነጨውን የሁለት አገሮች ቁርቁስና በወደቡ ያለመጠቀም በቀልንም ሆነ የጦርነት አደጋን የማያስቀር ነው፡፡ ሁለቱም የፀና ሰላምና መደጋገፍን ከማስገኘት አኳያ ሲመዘኑ ምኞታዊ ወይም ራስ ወዳድ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡

   ዓይነ ደረቅነትንና የተሸፋፈነ ብልጠትን ተሻግረን ለእውነትና ለፍትሕ የቆመ አዕምሮ የማይክዳቸውን ሀቆች እናስቀምጥ፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል የሚሰማው የባህር በር ጥያቄ ረዥም የባለይዞታነትና ይዞታ የማስመለስ ትግል ታሪክ ያለው፣ አሁንም ከሕዝብ መብት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ ትክክለኛ መፍትሔ እስካለገኘ ድረስ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ቢያለባብሰው እንኳ የማይጠፋ ጥያቄ ነው፡፡ የኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይቶ የመውጣት ፍላጎትና መብት በኢትዮጵያ የወደብ ጥቅም ምክንያት መሰረዝ እንዳልነበረበት ሁሉ፣ የኢትዮጵያም ታሪካዊና ሕዝባዊ የወደብ መብት እንደሌለ ተደርጎ በቅኝ ግዛታዊ መሥፈሪያ መሰረዙ አግባብ አልነበረም፡፡ ከታች ጀምሮ ወጥ የሆነው የአፋር ሕዝብ የባህር መዳረሻ ላይ በቅኝ ግዛት መመዘኛ ተቆርጦ በግድ የሌላ አገር አካል የተደረገበትን ሴራ ፍትሐዊ የሚያደርግ ምንም መከራከሪያ የለም፡፡

  አንዱ ችግር አልበቃ ብሎ ቀሪውን ድንበርም በቅኝ ግዛታዊ ስምምነት መሠረት መፋረድ መፍትሔ የማይሆን ጥፋት ነበር፡፡ ከድንበር አካባቢ ሕዝቦች ፍላጎት የኮሚሽኑ ውሳኔ አይበልጥም፡፡ ከሕዝቦች ፍላጎት ጋር ሳይገናዘብ ተግባራዊ ሊደረግ ቢሞከርም ቁጣ ማስነሳቱ እንደማይቀር እየታየ ያለ ነው፡፡ የቅኝ ካርታው ላይ የወሰን አካባቢ ሕዝቦች ፍላጎት ቦታ ተሰጥቶት የወሰኑን ጣጣ ለመፍታት ቢሞከር፣ የሕዝብ ፍላጎት መንገድ ካገኘ ላይ ድረስ መነሳሳቱ የማይቀር ነው፡፡ የሁለቱን አገሮች ዘላቂ ሰላም የሚያስገኝ መፍትሔ መገኘቱም እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡ እንዲያውም ሁለቱም አገሮች ያልጠበቁት ቀውስ እንዳይከሰት ያስፈራል፡፡ የወፈፌነት አጭር ጊዜ ባመጣው ጦስ በመታወር፣ ወደብን ለብቻ ተቆጣጥሮ በመግፈፍም ሆነ ያመለጠ ወደብን ባለመጠቀም ረዥም ታሪካዊ አመጣጥና ተጋድሎን በሚጋራ ወንድማማች ሕዝብ ላይ በቀል መፈጻጸም፣ ከአንድ በቀል ሌላ በቀል እያረቡ ራስን በራስ መቅጣት መሆኑ ሲበዛ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአሰብ ወደብ ገንዘብ እየከፈሉ መጠቀምን ለሌላ አገር ወደብ እየከፈሉ እንደመጠቀም አድርገው ሊቆጥሩት እንደማይችሉ ሁሉ፣ ኤርትራውያንም የኢትዮጵያን በአሰብ ወደብ ከመገልገል መቆጠብ እንደ ጥቃት እንጂ እንደ ተራ መብት ሊያዩት አይችሉም፡፡

    ከተጠቀሱት ነጥቦች መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮ ኤርትራ ችግሮች መፍትሔ  ከቅኝ ግዛት አመጣሽ የዕይታ ግቢ ወጥቶ ቤተሰባዊ ግቢ ውስጥ መግባትን፣ የሁለቱንም የወደብ ጥቅም አንድ ላይ ከማድረግና ከመበልፀግ ጋር ማጣጣምን ይጠይቃል፡፡ ከኢትዮጵያ በሕዝቦች ጥንቅሩ የተለየና አንድ ኤርትራዊ ብሔርነት ያለው ሕዝብ ተፈጥሯል የሚለው ልብ ወለድ ከእነ አገር ስያሜው እስከ ጂቡቲ የተዘረጋ ጠፍር የመሰለ (መውጫ ከልካይ አጥርን የሚወክል) ካርታ፣ በዚሁም መሠረት ወጥ ሕዝቦች ላይ የተደረገ አንድ አይደላችሁም የሚል ቆረጣ፣ ጦርነቱ፣ የድንበርና የወደብ ውዝግቡ ሁሉ እንዳለ ከቅኝ ገዥዎች በተወረሰ ወጥመድ ተይዞ የተካሄደና የሚካሄድ መናጨት ነው፡፡ ሁለት የሆኑት አገሮች ነፃ የሚወጡትና ሰላም የሚያገኙትም የተሰነጉበትን የቅኝ ግዛት ካቴና ሰብረው የላቀ ጥቅማቸውንና ቤተሰብነታቸው አጥብቀው መያዝ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ለኤርትራ ልጆች ከወደብ አገልግሎት ኪራይ የሚለቀም ገቢና የዜግነት አጥር በሌለበት ሰፊ ኢኮኖሚ ውስጥ የመዋኘት ጥቅም ፈጽሞ በአንድ ሚዛን ላይ ለንፅፅር ሊቀመጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ሁለቱ አገሮች በዴሞክራሲያዊ ኅብረት ገበያቸውን የመቀላቀል ትንሹን ዕርምጃ እንኳ ቢራመዱ፣ ባሉበት ጂኦፖለቲካ ውስጥ የሚጎናፀፉት የታፋሪነትና የተሰሚነት ቦታ፣ የሰላምና የብልፅግና ዕድል፣ በአካባቢያቸው ላይ የሚያሳድሩት የመረጋጋትና የአቅጣጫ ለውጥ እኛንም ከማኅበራችሁ ጨምሩን ባይ ሌላ ጎረቤትንም የሚያመጣ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት በጠባቸው ሰንገው የያዙት (ተቃዋሚዎቻቸውም ያልፈለቀቁት) ይህንን ተጨባጭ ዕድል ነው፡፡ ለሁለቱም የሚያዋጣው ይህ አማራጭ የዚህ ጽሑፍ ባለቤትም ሆነ ሌላ ሰው ከጉጉቱ ያፈለቀው ሳይሆን፣ ሁለቱ አገሮች ያሉበት የዛሬ እውነታ (ጠብና መጠፋፋትን አምክኖ ለማደግ) ግድ ይሁን የሚለው ነው፡፡ አሁን በቀንዱ አካባቢ የተጀመረው የመያያዝ ሒደትም ይህንኑ የቅኝ ገዥዎች ካቴና የመበጠስ ዕድል ደቅኖላቸዋል፡፡ ሁለቱም ከጠብና ከጦርነት ነፃ የሚወጡት የታሰሩበትን የቅኝ ጣጣ በጣጥሰው ሲጥሉ አሮጌ ታሪክን ከመኖር አዲስ ታሪክን ወደ ማነፅ ሲሸጋገሩ ነው፡፡  

  ይህንን እውነታዊ ዕድል አስተውለው ፊት ለፊት የሚያወጡ አዲስ ፖለቲከኞች ከሁለቱም አገሮች (በተለይም ከኤርትራ) (በዚህ አቅጣጫ ውስጥ ማሰብ ፈተና የሚሆንባቸው ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የኤርትራ ነባር ፖለቲከኞች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ይህ ግን ኤርትራ ባለ ብዙ አማራጭ ሆና ሳይሆን ከእውነታ ጋር አድሮ ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ፣ የሕዝብን ጥቅም ጎድቶ ከምን ይሉኝና ከባዶ መታበይ ጋር ማደርን የመምረጥ ጉዳይ ነው፡፡ የኤርትራንም የኢትዮጵያንም ተጠቃሚነት ዜሮ ባደረገ ሁኔታ ውስጥ ሥራ ያጣ ወደብ መታቀፍና ሌሎች ብዙ ዕድሎችን ማምከን ነፃነትም ልባምነትም ሊሆን አይችልም፡፡ የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ ወደብ የማግኛ ንድፍ አድርገው የሚተረጉሙት አይታጡም፡፡ ለእነዚህ ዓይነቶቹ ኢትዮጵያ በሌሎች ወደቦች እየተጠቀመች ማደግ እንደቻለችና በአጥፊ በቀል የተጠመደችው (ከኢትዮጵያ ይልቅ ኤርትራ መሆኗን እንዲያስታውሱ እንመክራለን) በቅለው የጠብና የበቀል ዓምዶችን እስኪገረስሱ ድረስ የፈለገውን ያህል “ሰላም አወረድን/ተፋቀርን” ሊባል ቢችል እንኳ፣ ሁለቱም አገሮች በአሮጌ (ቅኝ አመጣሽ) ችግር መቋሰላቸው ይቀጥላል፡፡ ይህንን መቋሰል በማያዳግም አቅጣጫ የሚታገል አዲስ ፖለቲካ ዛሬ ብቅ ይል ይሆን? እየተደራረበ ያለው የኢትዮጵያና የኤርትራ ትውልዶች የመስዋዕትነት ዕዳ በዴሞክራሲ፣ በዘላቂ ሰላምና በዕድገት የሚካሰውስ መቼ ይሆን? በጣሊያን ቅኝ ገዥነት ጊዜ እንኳ ሊነጣጠሉ ያልቻሉት ወደ ፊትም የተያያዘ ዕጣ ያላቸው የአንድ ቤተሰብ ልጆች በፀብ ተጠፍረው የሚቆዩት እስከ መቼ ነው? ፀረ ፋሽስት ትግሉ እንደአቢቹ ያለ (የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይና የኤርትራ ጎበዞችን በአንድ ላይ የመራ) ወጣት ጀግናን እንዳሳየን ሁሉ፣ የዛሬው ጠመንጃ አልባ የፖለቲካ ትግልም ከሁለቱም ሥፍራዎች የወጡ ወጣት ጀግኖችን እንዲያሳየን እንጓጓለን፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...