Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜና​የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

  ​የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

  ቀን:

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስና ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በቂ ባለመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ዕርምጃ ሊወስድ ነው፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተንሰራፋው ሙስና የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ነዋሪዎችን ለምሬት እየዳረገ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማው ሲያቀርቡ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙሰኞች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ዕርምጃው በቂ ስላልሆነ የፌዴራል መንግሥት በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ዕርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በመሬት ዘርፍ መዋቅር ውስጥ በሙስና የተጠረጠሩ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ አስተዳደሩ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኙት ላይ እንጂ በከፍተኛ ሥልጣን እርከን የሚገኙት ላይ አይደለም በማለት አሁንም ከነዋሪዎች ቅሬታ እየቀረበ ይገኛል፡፡ የሚወሰደው ዕርምጃ ጥፋተኞች የሚባሉትን ያልነካ፣ አልፎ አልፎም መልካም ስም ያላቸውን የጎዳ ነው ሲሉ የሚተቹ አሉ፡፡

  የፌዴራል መንገሥት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ከሚነሱት ችግሮች አንፃር ጠንከር ያለ ግምገማ ተካሂዶ ዕርምጃ እንዲወሰድ መመርያ ቢሰጥም፣ ከአንድ ሳምንት በፊት የተካሄደው ግምገማ ያመጣው ለውጥና የወሰደው ዕርምጃ የለም ተብሏል፡፡

  በዚህ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተቋቋመው ንቅናቄና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራልና በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቶች ላይ ካሰባሰቡት መረጃ በመነሳት፣ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል፡፡

  የፌዴራል መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ ለጊዜው ባይገለጽም፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

  የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የአዲስ አበባን ጉዳዮች ብቻ የሚመለከት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡

  ‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሠራ ጠንካራ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው፤›› ሲሉ አቶ ወዶ ገልጸዋል፡፡

  የመንግሥት ዕርምጃ ትኩረት የሚያደርገው ሙስና በብዛትና በውስብስብ ኔትወርክ ተተብትቦ በሚገኝባቸው በመሬት ልማትና ማኔጅመንት፣ በንግድ፣ በገቢ ግብርና በአጠቃላይ የታክስና የጉምሩክ ሥራዎች፣ የመንግሥት ዕቃና አገልግሎት ግዢ፣ በኮንትራት አስተዳደር፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድም ተጠቁሟል፡፡

  በእነዚህና በሌሎችም ዘርፎች ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ የቆዩ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የዕርምጃው ሰለባ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

  የፌዴራል መንግሥት በ1995 ዓ.ም. በአቶ ዓሊ አብዶ ይመራ የነበረውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማፍረሱና በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር መተካቱ ይታወሳል፡፡

  በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 መሠረት፣ የአዲስ አበባ አስተዳዳር ለፌዴራል መንግሥቱና ለነዋሪዎቹ ጭምር ተጠያቂነት አለበት፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...