Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በሞጆ ከተማ በ100 ሚሊዮን ዶላር የቆዳ ኢንዱስትሪ ዞን ሊገነባ ነው

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከአዲስ አበባ ከተማ 76 ኪሎ ሜትር ርቀት በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ አቅራቢያ በ100 ሚሊዮን ዶላር የቆዳ ኢንዱስትሪ ዞን ሊገነባ ነው፡፡

  ለአካባቢያዊ ብክለት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን የቆዳ ፋብሪካዎች አንድ ቦታ ለማሰባሰብ የታቀደው ከዓመታት በፊት ቢሆንም ዕቅዱ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፕሮጀክቱ ጥናት ከሦስት ዓመት በፊት ቢጠናቀቅም ገንዘብ  ባለመገኘቱ ዘግይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድር በመፍቀዱ ወደ ሥራ እየተገባ ነው ብለዋል፡፡

  ከኢትዮጵያ መንግሥት ግምጃ ቤትና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በሚገኝ 100 ሚሊዮን ዶላር የኢንዱስትሪ ዞኑ ይገነባል ተብሏል፡፡

  የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ከተማ በብዛት ተከማችተው የሚገኙ ሲሆን፣ ፋብሪካዎቹ በአብዛኛው ዘመናዊ የፍሳሽ ማጠራቀሚያ የሌላቸው በመሆኑ ለአዋሽ ተፋሰስ አደጋ ሆነው ቆይተዋል፡፡

  አቶ ወንዱ እንዳስታወቁት በሞጆ አካባቢ 14፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ስድስት ቆዳ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙት ፋብሪካዎች የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብተው ባሉበት የማያመርቱ ካልሆነ ወደ ሞጆ ይዘዋወራሉ፡፡ አሁን የሚገነባው የኢንዱስትሪ ዞን በማዕከል ደረጃ የፍሳሽ ማጣሪያ የሚያካትት በመሆኑ የኢንዱስትሪ ብክለትን ከመቅረፍ ባሻገር፣ ለጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የመንግሥት ድጋፍ በተሟላ መንገድ ለማግኘት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

  በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የቆዳ ኢንዱስትሪ ዞን ለ40 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ለምትጠብቀው ኢትዮጵያ ትልቅ የምሥራች ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡

  የኢንዱስትሪ ዞኑ በአጠቃላይ 200 ሔክታር መሬት የተያዘለት ሲሆን፣ ግዙፉ ጆርጅ ሹ ኩባንያ 75 ሔክታር መሬት በመጠቀም ፋብሪካዎች ይገነባል፡፡ በተቀረው 125 ሔክታር መሬት ላይ በአጠቃላይ የቆዳ ፋብሪካዎችን የፍሳሽ ማጣሪያ ያማከለና ላብራቶሪዎችን ያካተተ 20 ኩባንያዎችን ያሳትፋል ተብሏል፡፡

  ይህ ፕሮጀክት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን አሟልቶ ከመያዙ በተጨማሪ ከቦታቸው የሚነሱ የሞጆ ነዋሪዎችን የሚያቅፍ፣ እንደ አትራፊ ተቋም ሳይሆን ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከግምት የሚያስገባ መሆኑን አቶ ወንዱ አብራርተዋል፡፡

  የፕሮጀክት ጥናቱ የተጠናቀቀው እ.ኤ.አ በ2015 በመሆኑ፣ የግንባታ ወጪው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል አቶ ወንዱ ጠቁመዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች