Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ክቡር ሚኒስትር

  [ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

  • እየተከታተልክ ነው ለመሆኑ?
  • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
  • ቴሌቪዥን ነዋ፡፡
  • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን አሰብክ ታዲያ?
  • በጣም አስፈሪ ነገር ነው፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
  • ትራምፕ ነዋ፡፡
  • ትራኩ ነው ያልከኝ?
  • የአሜሪካኑ ትራምፕ ነው ያስጨነቀኝ ስልዎት፡፡
  • እኔ ደግሞ የዩሮ ትራኩ ጉዳይ ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡
  • እኔ እኮ ወሬ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡
  • ምኑ?
  • ክቡር ሚኒስትሩ ዩሮ ትራከር አላቸው ሲባል፡፡
  • ቢኖረኝ ምን ችግር አለው?
  • ያው ከየት ያመጡታል ብዬ ነው?
  • ከብዙ ቦታ ላመጣው እችላለሁ፡፡
  • ለነገሩ እርስዎ ብዙ ቦታ እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • ማለቴ ሊያመጡበት የሚችሉበት ብዙ አቅም አለዎት ብዬ ነው፡፡
  • ዛሬ የፈለኩህ እንዴት አየኸው ልልህ ነው?
  • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
  • የሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር፡፡
  • በቴሌቪዥን ነዋ፡፡
  • ቀልዱን ተውና ቁምነገሩን አስቀድም፡፡
  • ሰው በጣም ተገርሟል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በምኑ ነው የተገረመው?
  • ኢሕአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን በማመኑ ነዋ፡፡
  • ይኼ ምኑ ነው የሚያስገርመው?
  • ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን ማመኑ ነዋ፡፡
  • እስከዛሬ አምኖ አያውቅም?
  • አዎና ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምን አምኖ እንደማያውቅ ታውቃለህ?
  • አላውቅም፡፡
  • አጥፍቶ ስለማያውቅ ነዋ፡፡
  • ምን አሉኝ?
  • አጥፍቶ አያውቅም፡፡
  • ለነገሩ አጥፍቶ የሚያውቀው ሌላ ነገር ነው፡፡
  • ምን?
  • መብራት፡፡
  • እ…
  • ውኃ፡፡
  • እ…
  • ኔትወርክ፡፡
  • ሌላስ?
  • አንዳንዴም የሰው ሕይወት፡፡
  • በል በል ሌላ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ፡፡
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለማንኛውም አሠራራችንን መለወጥ አለብን፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሁሉን ነገር በአዲስ መልኩ መጀመር አለብን፡፡
  • በአዲስ ሲሉ?
  • ሕዝቡ በጣም ተማሮብናል፡፡
  • እርሱማ ግልጽ ነው፡፡
  • ስለዚህ ሕዝቡን ማስደሰት አለብን፡፡
  • እኮ በምን እናስደስተው?
  • አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን፡፡
  • ለምን ሲባል?
  • ሕዝቡ በደል በደል በሚሸት ሕንፃ ውስጥ ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
  • እና ምን ይደረግ?
  • አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን ስልህ፡፡
  • የትኛው ሕንፃ ውስጥ ነው የምንገባው?
  • የምንገባበትን ሕንፃ እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
  • የመንግሥት ሕንፃ ነው?
  • የግል ነው እንጂ፡፡
  • በኪራይ ክቡር ሚኒስትር?
  • አዎና የግል ሴክተሩን እኮ ማበረታታት አለብን፡፡
  • እና ከመንግሥት ሕንፃ ወጥተን ወደ ኪራይ እንግባ እያሉ ነው?
  • ለሕዝቡ ሲባል የማይደረግ ምንም ነገር የለም፡፡
  • ለማን አሉኝ?
  • ለሕዝቡ፡፡
  • ለእርስዎ ማለትዎ ነው?

  [ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤታቸው ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]

  • ምነው ደስ ያለህ ትመስላለህ?
  • እንዴት አልደሰት?
  • እኮ ምን ተገኘ?
  • ያው አፉን ከፍቶ የነበረው ሕንፃችን ተከራይ ተገኘለት፡፡
  • ማን ሊከራየው ነው?
  • እኛ ነና፡፡
  • እናንተ ማን ናችሁ?
  • የእኛ መሥሪያ ቤት፡፡
  • ምን?
  • አዎን ሁሉን ነገር ጨርሼዋለሁ፡፡
  • ለምንድን ነው ቢሮ የምትቀይሩት?
  • በአዲስ መንፈስ ሥራ መጀመር አለብና፡፡
  • ያላችሁበት የመንግሥት ሕንፃ አይደል እንዴ?
  • ቢሆንስ?
  • ታዲያ ከዛ ወጥታችሁ ወደ ግለሰብ ሕንፃ ልትገቡ?
  • ምን አለበት?
  • ለነገሩ ከመንግሥት ሕንፃ ወደ መንግሥት ባለሥልጣን ሕንፃ ነው የገባችሁት፡፡
  • አመጣሽው ጨዋታውን፡፡
  • ያን ያህል ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡
  • ያው ነው ስልሽ፡፡
  • የእኔ ሥራ ብቻ ተቀዛቅዟል፡፡
  • የትኛው ሥራሽ?
  • የፈርኒቸሩ ሥራ ነዋ፡፡
  • ለእሱም ቢዝነስ ሥራ አግቼልሻለሁ፡፡
  • ምን ተገኘ?
  • አዲሱ ሕንፃ ውስጥ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር ያስፈልገናል፡፡
  • የድሮዎቹ ምን ሆኑ?
  • ወንበሮቹ ራሳቸው ግፍ ግፍ ይሸታሉ፡፡
  • ታዲያ ወንበሮቹ ሳይሆኑ ወንበሮቹ ላይ የተቀመጡት እኮ ናቸው ግፈኞቹ፡፡
  • ቢሆንም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
  • እኔማ ደስ ነው የሚለኝ፤ ቢዝነስ አገኘሁ፡፡
  • ስለዚህ ተዘጋጂ፡፡
  • ስለእሱ አታስብ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

  • አቤት ክቡር ሚኒስትት፡፡
  • አንድ ሐሳብ መጥቶልኝ ነው፡፡
  • የምን ሐሳብ?
  • አዲሱ ቢሮ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር መግዛት አለብን፡፡
  • ምን?
  • ሁሉን ነገር በአዲስ መንፈስ መጀመር አለብን ስልህ፡፡
  • ፈርኒቸሮቹ ከተገዙ እኮ ስድስት ወራቸው ነው፡፡
  • ስማ ቢሆኑም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች መገልገል የለበትም፤ መቀየር አለባቸው፡፡
  • መቀየርማ ያለባቸው ሰዎቹ ናቸው፡፡
  • ሰዎቹን መቀየር ከባድ ስለሆነ ወንበሮቹን ብንቀይራቸው ይሻላል፡፡
  • ሕዝቡ እኮ የተማረረው በወንበሮቹ ሳይሆን በሰዎቹ ነው፡፡
  • አየህ በወንበሮቹ ጀምረን በሰዎቹ እንቀጥላለን፡፡
  • ለማንኛውም የሰዎቹን ቅያሬ ስንጠብቅ ቀኑ እንዳይደርስብን፡፡
  • የምኑ ቀን?
  • የምፅዓት ቀን!

  [የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]

  • ጠዋት የት ሄደሽ ነው?
  • አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ታዲያ አታስፈቅጂም እንዴ?
  • ስልክዎትን ብለው ብለው አልሠራ አለኝ፡፡
  • ሞክረሽልኝ ነበር?
  • በጣም ብዙ ጊዜ ነው የሞከርኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አየሽ ሌላም ሰው ቢፈልገኝ አልገኝም ማለት ነው፡፡
  • ለእኔ አልሠራልኝም ነበር፡፡
  • ሕዝቡ የሚማረረው እኮ እንደዚህ እየሆነ ነው፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ስልኬ በአዲስ መቀየር እንዳለበት ገብቶኛል፡፡
  • እ…
  • አዲስ አይፎን ያስፈልገኛል፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ የአይቲ ክፍል ኃላፊውን አስጠሩት]

  • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሕዝቡ ምን ያህል እየተማረረ እንደሆነ ታውቃለህ አይደል?
  • በጣም ተማሯል፡፡
  • ሕዝቡን እኔን ሊያገኘኝ አልቻለም፡፡
  • ቢሮ መቼ ተቀምጠው ያውቃሉ?
  • ቢሮ ባልቀመጥም ቢያንስ በስልክ ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
  • ስልክዎትን የሚያውቀውማ ይደውልልዎታል፡፡
  • የማያውቀውም ቢሆን ቢያንስ በኢሜይል ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
  • ታዲያ ለምን አያገኝዎትም?
  • አየህ ኮምፒዩተሮቻችን አሮጌ ናቸው፡፡
  • እ…
  • አሁን አዲስ ሕንፃ ውስጥ ስለምንገባ ሁሉንም በአዲስ ኮምፒዩተር መተካት አለብን፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር አሁን ያሉት ኮምፒውተሮች እኮ ከተገዙ ገና ስድስት ወራቸው ነው፡፡
  • ስማ ቴክኖሎጂው እኮ በየጊዜው ነው የሚቀያየረው፡፡
  • እ…
  • ስልኮቻችንም በአዲስ መቀየር አለባቸው፡፡
  • ጨረታ ይውጣ?
  • ቢሮክራሲ አያስፈልግም፡፡
  • ምን?
  • እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ የኮምፒዩተር ቢዝነስ የሚሠራው ወንድማቸው ጋ ደወሉ]

  • አቤት ጋሼ፡፡
  • የት ነው ያለኸው?
  • ካርታ እየተጫወትኩ ነው፡፡
  • አንተ ልጅ ይኼ ካርታ ሱስ ሆነብህ አይደል?
  • ያው በዘር እኮ ነው ሱስ የሆነብን ጋሼ፡፡
  • እኔ የት ነው ካርታ ስጫወት ያየኸው?
  • ያው አንተ በመሬት ካርታ ነዋ የምትጫወተው፡፡
  • ለማንኛውም አሁን ሥራ አግኝቼልሃለሁ፡፡
  • የምን ሥራ ጋሼ?
  • ለቢሯችን ሙሉ ኮምፒዩተር እንድታቀርብ፡፡
  • እየቀለድክ ነው ጋሼ?
  • የምን ቀልድ ነው? እውነቴን ነው፡፡
  • ከስድስት ወር በፊት ነው እኮ ለሙሉ ቢሮው ኮምፒዩተር ያቀረብኩት፡፡
  • እና ይኼኛውን አትፈልገውም?
  • ኧረ እንደሱ ማለቴ አይደለም፤ በጣም ደስ ብሎኝ ነው፡፡
  • ምኑ ነው ደስ ያለህ?
  • በቃ በዚህ ሥራ ሕንፃዬን እጨርሰዋለሁ ብዬ ነዋ፡፡
  • ሕንፃህንም ተጨማሪ ቦታ ስለሚያስፈልገን መከራየታችን አይቀርም፡፡
  • አንጀት አርስ ነህ ጋሼ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ተጠርተው ሄዱ፤ ሳያስቡት መገምገም ጀመሩ]

  • ክቡር ሚኒስትር ከብልሹ አሠራርዎት ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡
  • እናንተ ከእኔ ውጪ ሰው አይታያችሁም እንዴ?
  • ይኸው ባለፈው ተገምግመው አሁንም ያው ነዎት፡፡
  • ምን አደረግኩ?
  • ይኸው አዲስ ሕንፃ ውስጥ ካልገባን እያሉ ነው፡፡
  • በአዲስ መልክ ሥራ መጀመር ስላለብን ነዋ፡፡
  • ደግሞ ሕንፃው የእርስዎ ነው አሉ?
  • በተመጣጣኝ ዋጋ እስካከራየሁት ድረስ ምን ችግር አለው?
  • እ…
  • ፈርኒቸሮቹንም ቢሆን በአገር ዋጋ ነው የምናቀርበው፡፡
  • ሌላስ?
  • ኮምፒዩተሮቹም ቢሆኑ ሌተስት የሆኑት እኛ ጋ ስላሉ ነው፡፡
  • ወይ ቅሌት፡፡
  • ይህንንም ያደረግነው ሥራችንን በአዲስ መንፈስ ለመጀመር ነው፡፡
  • እርስዎም በአዲስ መልክ ጀምረውልኛላ፡፡
  • ምኑን?
  • ሌብነቱን!
    

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሥራ አጥነት ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም በዋና ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃና ቢሮዎች ላይ ያደረገውን ዕድሳት መርቀው በመክፈት ጉብኝት እያደረጉ ነው]

  እጅግ ውብ ዕድሳት ያደረጋችሁት! በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው፡፡ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በጣም ድንቅ ነው። ዕድሳቱን ያከናወነው ድርጅት ጥሩ ልምድ ያለው ይመስላል? ተቋራጩ ማን እንደሆነ አልነገርኩዎትም እንዴ? የትኛው ተቋራጭ...

  [ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ የተሸፈኑ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ከስንዴ ምርት ድጋፍና ክትትል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር እየመከሩ ነው] 

  ክቡር ሚኒስትር እንደነገርክዎት በሁሉም ስንዴ አብቃይ አካባቢዎቻችን ያሉ አርሶ አደሮች ጥሪያችንን ተቀብለው መሬታቸውን በኩታ ገጠም አርሰው በስንዴ ዘር ሸፍነዋል። በጣም ጥሩ ዜና ነው። በጣም እንጂ። የሚገርምዎት...

  [ክቡር ሚኒስትሩ የሚመሩት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ በያዘው ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ቢጀመርም በስተመጨረሻ አጀንዳውን ስቶ ስለ መዋደድ እየተጨቃጨቀ...

  በዛሬው መደበኛው መድረካችን አጀንዳ የተለመደው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ይሆናል። ሌላ አጀንዳ የምታስይዙት አጀንዳ ከሌለ በቀር ማለቴ ነው። ክቡር ሚኒስትር... እሺ ...ቀጥል አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። መደበኛ አጀንዳው እንደተጠበቀ...