በለሷን እስቲ እዩዋት ÷ እስኪ ተመልከቱአት፤
እስቲ አስተውሉአት ÷ በሩቁ ሳትቀርቡአት።
ማነው የጠበቃት? ማነው የቀጠራት?
ማነው የተከላት? ማነው ያፀደቃት?
ትናንትን ደግፎ ÷ ዛሬን እንደ ያዛት።
እናንት ባለ ጊዜ!
ክረምትና በጋ ÷ ሳላችሁ ከጥንት
የየግል ፍላጎት ÷ ለየቅል ስሜት፤
በለሷን እስቲ እዩዋት! ምን የተረፋት?
ያ መልካም ውበቷ ÷ ረግፎ ባንድ ክረምት።
ክረምት ዓምና አቻምና ÷ አልፈህ እንደ ዘበት
በጋም ደርሰኽላት ÷ እግሩ በወጣበት፤
እንግዲህ ፍሬዋ ÷ ብትኾን መድኃኒት
ለሆድ ቁርጠትና ÷ ለመንፈስ ጭንቀት።
በለስ ወረት አታውቅ ÷ ትኖር በነፃነት
ኀድራው ተሟሙቆ ÷ ሁሉ በሞላበት።
ያቺ የንጋት ፀሐይ ÷ ያቺ የቀን ኀድራ
እግሮቿ ሲወጣ ÷ ካ‘ዘን ከመከራ፤
በለሷን እስቲ እዩዋት! እስኪ ተመልከቷት፤
እስቲ አስተውሏት ÷ ዞራችሁ በስቷላ።
የተፈጥሮ መብቷ ÷ ተራክቦቷ ጎላ
ተከልላ አትኖር ÷ ዛሬማ መሀሏ።
ቦኦቦ ለማ ሴራ ÷ በፍቅር ተቀጥራ
ባ‘ቢይ ቃለ መኃላ ÷ በየውኃው ታጥራ
እጅጉን ጠንክራ፤
በየቅርንጫፉ ÷ በየግንዱ አፈራ
የሰላሟ ዛላ።
ካ‘ገር በስተ ጀርባ ÷ በተዘረፈ ሀብት
መዋዕለ ነዋይ የሚፈስባት
ሁሉን ቻይ መሬት፣
ምሽቱን ከበሮ ÷ ሲደለቅባት
ጭፈራው ሲቀልጥ ÷ ሌቱን ያለ ዕረፍት፤
ያንድ ጎኑ ጥጋብ ÷ ‘ሚቈረቍራት
ያንድ ጎኑ ረሃብ ÷ እንደ ጠናባት፤
አገር በጀርባዋ ÷ ሸክመ ብዙ ናት
ዞሮ ማን አያት።
( ኃይለ ልዑል ካሳ፣ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም.)