Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የአገር ሰላም እየደፈረሰ ሕዝብ ላይ አይቆመር!

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ሰላም፣ ዕድገትና ህልውና ሥጋት የሚሆኑ አጓጉል ድርጊቶችን ይፀየፋል፡፡ በገዛ ወገኑ ላይ ቀርቶ በባዕድ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጸም ከልቡ ይፈልጋል፡፡ ይህ የዘመናት አኩሪ ቅርስና እሴት እየተጣሰ ግን አስከፊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ ከመኖሪያ ቀዬው እየተፈናቀለ እንደ አውሬ ይገደላል፡፡ መጤ እየተባለ ንብረቱ እየተዘረፈ እንደ ጉድፍ ይጣላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት እየተራከሰና አካባቢያዊ ማንነት እየነገሠ፣ በገዛ አገር መድረሻ ማጣት የተለመደ ትዕይንት እየሆነ ነው፡፡ በአንድ በኩል በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በአንድነት እንኑር እየተባለ በየአደባባዩ ይለፈፋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከክልሌ፣ ከዞኔ፣ ከወረዳዬ፣ ከቀበሌዬ፣ ወዘተ. ውጣልኝ እየተባለ ወገን ይሰቃያል፡፡ በትዕቢት የተሞሉ ዓይኖች፣ በሐሰት የደነደኑ ምላሶች፣ ክፉ ሐሳብ የሚጠነስሱ ልቦችና የቆሸሹ እጆች የንፁኃንን ደም ያፈሳሉ፡፡ የአገራዊ ማንነት ክብርን ያዋርዳሉ፡፡ በአፋቸው ስለአንድነት ቢዘምሩም ልባቸው በጭካኔ ተሞልቷልና የአገር ሰላም እያደፈረሱ ነው፡፡

  ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የማይመጥን ጭካኔ የተላበሱ ወገኖች፣ ለዘመናት አብሯቸው የኖረውን ወገናቸውን ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ የሚቆጣና የሚገስፃቸው እየጠፋ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም እየደፈረሰ ነው፡፡ በብዙ ሥፍራዎች አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ባለመቻላቸው ንፁኃን የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው፡፡ አንድ ዜጋ በፈለገው ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብቱ በአደባባይ እየተገፈፈ ሲባረር ዝም እየተባለ ነው፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እየተባባሰ ያለውን ቀውስ እያስታመሙት ነው፡፡ አገር አለኝ፣ ወገን አለኝ ብሎ ክፉና ደጉን ችሎ የሚኖር ባተሌ ሰው ሳይቀር የጥቃት ሰለባ ሲሆን ማቆሚያው የት ነው ማለት ካልተቻለ አደጋ አለ፡፡ የመሰንበቻዎቹን ዋና ዋናዎቹን ጥፋቶች ብናነሳ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ተወላጆች መካከል የተከሰተው ግጭት በርካቶችን ለዕልቂት ዳርጎ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን አፈናቅሏል፡፡ በደቡብ ክልል በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በወልቂጤና በመሳሰሉት የደረሰው ጥፋት፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዜጎችን ከማፈናቀል ታልፎ የተፈጸመው ግድያ፣ በደቡብ ወሎ በከሚሴና በባቲ የተፈጸሙ አሳዛኝ ድርጊቶች ያሳስባሉ፡፡ የአገር ሰላም በሚያስፈራ ሁኔታ እየደፈረሰ ነው፡፡ በአገር ህልውና ላይ የተቃጣ አደጋ ነው፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሥልጣን መንበሩን ከተቆናጠጡ ወዲህ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እየታየ የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸው በተለያዩ ሥፍራዎች ስለሰላምና ፍቅር የማነቃቂያ ንግግሮች ቢያደርጉም፣ ግጭቶች በተቀሰቀሱባቸው ሥፍራዎች እየተገኙ ሰላም ለማስፈን ቢተጉም፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን መልዕክተኛ በማድረግ መሆን ያለበትን ለማድረግ ቢጥሩም የሚፈለገው ሰላም እየጠፋ ግጭቶች እያገረሹ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ያልተለመዱ ጥፋቶች እየታዩ ነው፡፡ የግለሰቦች ዕለታዊ ግጭት የብሔር ሰሌዳ  እየተለጠፈለት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በከንቱ እየጠፋ ነው፡፡ አራስ ሕፃን የታቀፈች እናት ከጎጆዋ ተባራ ሜዳ ላይ ስትጣል፣ አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶች ከሕፃናት ጋር ተወርውረው ሲጣሉ፣ አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች እየተደበደቡ ሲባረሩ፣ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ጥሪት ያፈሩ እየተነጠቁ ሲሳደዱና ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሲዳረጉ የአዞ እንባ ከማፍሰስ ውጪ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ከወገን ሰቆቃ ይልቅ ክልልነት፣ ዞንነት፣ ልዩ ወረዳነትና የመሳሰሉት የጠበቡ ፍላጎቶች እስኪያሳፍሩ ድረስ ተሰምተዋል፡፡ ሰብዓዊነት ዘቅጦ ቁሳቁስ እየገነነ የሰው ልጅ ረክሷል፡፡ የሚያስከብረው ኢትዮጵያዊነት እየተናቀ አካባቢያዊ ማንነት ላይ የተሠራው ፍሬ አፍርቶ አገር እያተራመሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እከሌ ከእከሌ ሳይባባሉ ካልፈጠኑ እየታየ ያለው አደጋ ከቁጥጥር ውጪ መሆኑ አይቀርም፡፡

  የአገር ህልውና ከግለሰቦችና ከቡድኖች ህልውና በላይ ነው፡፡ ትውልድ ያልፋል ሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ መንግሥት በሌላ መንግሥት ይቀየራል፡፡ አንድ መሪ ሄዶ ሌላው ይመጣል፡፡ አገር ግን ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን እንዴት ትኖራለች የሚለው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብሔርተኝነትን ከመጠን በላይ እየለጠጡ በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት የሚያራግቡ ወገኖች እየበዙ ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ተሰደው በሰው አገር ጥረው ግረው እየኖሩ ካሉ ጽንፈኞች ጀምሮ፣ በአገር ቤት የሥልጣን ግብግብ ውስጥ እየተሻኮቱ ያሉ ኃይሎች ድረስ የተጠላለፉ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው አንድነትና ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ በኅብረት መቆማቸውን እያሳዩ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ አጠያያቂ እያደረጉ ያሉ ድርጊቶች በየቦታው መከሰታቸው ያሳዝናል፡፡ አንዱ ሥፍራ የተቀሰቀሰ ግጭት በስንት እግዚኦታ ጊዜያዊ መፍትሔ አገኘ ሲባል፣ ሌላ ቦታ ይፈነዳና ኢትዮጵያውያን ይሳቀቃሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜማ እያገረሸባቸው ያሉ ግጭቶች ምክንያታቸው ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ እዚህ ግባ የሚባል ምላሽ የለም፡፡ መንግሥት የሌለ ይመስል የአካባቢ ሹማምንትና የፀጥታ አካላት ድምፅ አይሰማም፡፡ አልፎ አልፎ ቢሰማም ተዓማኒነት የለውም፡፡ በዚህ መሀል ግን አገር ትሸበራለች፡፡ ሕዝብ ይተራመሳል፡፡

  ኢትዮጵያዊነት የሚከበረው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መቆም ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን እያንጓጠጠ፣ እየፈረጀና እያሳደደ የጋራ አገር ይኖራል ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው፡፡ ከአገሩ ወጥቶ በተለያዩ አገሮች ተሠራጭቶ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ቢያንስ በአገሩ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ብጥብጥና ትርምስ ውስጥ እንዳይገቡ ማገዝ አለበት፡፡ በአገር ውስጥ ያለው ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቪስት ለአገር ህልውና የማይጠቅም ጠባብ ዓላማ ውስጥ ተሰንቅሮ ሕዝብን ከማመስ ይልቅ፣ ለአገራዊ አንድነትና ሰላም አስተዋጽኦ ያበርክት፡፡ ኢትዮጵያ ከአስፈሪው ቀውስ ውስጥ ወጥታ አንፃራዊ ሰላም ስታገኝና አዲስ ምዕራፍ ሊጀመር ተስፋ ሲኖር፣ የነበረችበት አዘቅት ውስጥ መልሰን ካልከተትን ብሎ ግርግር መፍጠር ለማንም አይበጅም፡፡ በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ እየቆመሩ አገርን በማተራመስ የፖለቲካ ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ ሕዝብን እርስ በርስ እያባሉ በኋላ ሲታወቅ በይቅርታ ስም አለባብሶ ለማለፍ የሚደረገው መሯሯጥም ትዝብት ውስጥ ከመጣል አልፎ ያስጠይቃል፡፡ ወንጀል ነውና፡፡ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይሉት ጥፋት ለጊዜው እንጂ የትም አያደርስም፡፡

  አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ነገሮችን እየታዘበ ነው፡፡ በየቦታው የሚፈጸሙ በደሎችና ኃጢያቶች ለጊዜው የተሸፋፈኑ ቢመስሉም፣ ከሕዝብ ዓይን የተሰወሩ አይደሉም፡፡ በሴራና በአሻጥር ፖለቲካ ልክፍት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሕዝብን ቢያከብሩ ጥሩ ነው፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ እየተናቀ የሚፈጸሙ በደሎችና ግፎች በፍጥነት ሊቆሙ ይገባል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግጭቶችን መቀስቀስና የንፁኃንን ሕይወት መቅጠፍ የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚገመተው በላይ እንደሚሆን ማሰብ ይገባል፡፡ በአገራችንም ሆነ በመላው ዓለም በሕዝብ ላይ የዘመቱም ሆነ ጥፋት ያደረሱ ምን እንደገጠማቸው የታሪክ ድርሳናት ብቻ ሳይሆኑ፣ በየዕለቱ የሚወጡ ዘገባዎች ከበቂ በላይ ያስረዳሉ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን አንድ ላይ ስንቆም ነው፡፡ ሥልጣን፣ ክብር፣ ዝና፣ ጥቅምና ቁሳቁስ ጊዜያዊና ኃላፊ ናቸው፡፡ አገር ግን ለትውልድ የምትቀጥል የጋራ ቤት ናት፡፡ ይህችን የጋራ ቤት ለማፍረስ ወይም ለማተራመስ የሚደረጉ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ይቁሙ፡፡ የአገር ህልውና ከምንም ነገር በላይ ነውና፡፡ የአገር ሰላም እየደፈረሰ ሕዝብ ላይ አይቆመር!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...