Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርጥምር ዜግነት ይፈቀድልን!

  ጥምር ዜግነት ይፈቀድልን!

  ቀን:

  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከበርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውን የውጭ ዜጎች ውስጥ አንዱና አድናቂዎ መሆኔን በቅድሚያ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ክቡርነትዎ ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን፤›› በማት የተናገሩትን ከሰማሁ ቀን ጀምሮ ይህ አስተሳሰብ እኔና መሰል ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ዜጎችን ይጨምር ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ በሐሳቤ ስለሚመላለስ ነው ይቺን ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡

  በኢትዮጵያ ተወልደን ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የውጭ አገር ዜግነትን ተቀብለን የምንኖር ሰዎች፣ ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ፤›› ለመሆን አልቻልንም፡፡ ይህንንም እንድል የተገደድኩት ሳንወድ በግድ የተለያዩ የሕግ ገደቦች የተጣሉብን በመሆኑ ነው፡፡ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እያለን፣ በእነዚህ ሕገ ደንቦች የተነሳ ኢትዮጵያዊ ከመባል ወደ ትውልደ ኢትዮጵያዊነት ዝቅ ተደርገናል፤ ወይም ደግሞ ዳያስፖራ የሚለው መጠሪያ ስማችን ሆኗል፡፡ በእርግጥ በ1994 ዓ.ም. በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ የወጣው አዋጅ ቁጥር 270/1994፣ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶችን ተጠቃሚ አደረገ እንጂ እንደ አንዳንድ ጎረቤት አፍሪካ አገሮች ጥምር ዜግነትን (Dual Citizenship) በመፍቀድ የኢትዮጵያዊነት መብቶችን አላጎናጸፈም፡፡

  በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለዜጎቻቸው ጥምር ዜግነትን በመፍቀድ ዜጎች ከትውልድ አገራቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲጠናክሩ፣ ለአገርና ለወገን ዕድገት ከፍፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ስለማድረጋቸው በሰፊው ይነገራል፡፡ በተለይም ጋና ትጠቀሳለች፡፡ ከአገሯ ተወላጅ የውጭ ዜጋ አልፎ ተርፎ ለአሜሪካ ዜጎች ጭምር የጥምር ዜግነት መብት በመስጠት በመልካም ምሳሌነት ከመታየቷም በላይ ተጠቃሚነቷም የጎላ ሆኗል፡፡  

  ‹‹ዳያስፖራ›› በሚባለው ስያሜ የምንታወቀው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ድጋፍ ባይኖረንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) እንዳሉት ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ፤›› መሆናችንን በተግባር ማሳየት አይከብደንም፡፡ ከዚህ ቀደም በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ወቅት ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል መፈክር ይዘን በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች ድምጻችንን ማስተጋባታችን ይታወሳል፡፡ በደርግ መንግሥት ወቅትም ቀይ ሽብርንና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ሲካሔዱ፣ ከውጭ ሆነን በመቃወም ከወገኖቻችን ጎን አልተለየንም፡፡

  በኢሕዴግም መንግሥት የተጀመረውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ ለማድረስም ቦንድ በመግዛት፣ ከግል ኩባንያዎችም የተለያዩ አክሲዮኖችን በመግዛት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊነታችንን አስመስክረናል ማለት እንችላለን፡፡ በመሆኑም እኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንደ ኬንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም አገሮች የጥምር ዜግነት መብት አያገባንም ወይ?

  በአሁኑ ጊዜ በእርሶ መሪነት በሚካሔደው መሠረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥና የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለፍርኃትና ማወላወል እንዲሳተፉ ለማስቻል የጥምር ዜግነት መብት ሕግ ማውጣትና መተግበር አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት አለ፡፡

  አዋጅ ቁጥር 270/2002 የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ከሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ለይቶ ስድስት ሰፋፊ መብቶችን ቢሰጥም ሁለት መሠረታዊ ገደቦችን ግን ያስቀምጣል፡፡

  በአንቀጽ 6 ቁጥር 1 እና 2 ላይ የተቀመጡት ገደቦች ‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመንግሥት ደረጃ በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንደማይኖራቸውና በአገር መከላከያ፣ በአገር ደኅንነት፣ ወይም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥሮ መሥራት እንደማይችሉ ይገድባል፡፡ አንቀጽ 15 ግን ይህን አዋጅ የሚቃረኑ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመርያዎችና ውሳኔዎች ይህን አዋጅ በሚመለከት ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፤›› በማለት የአዋጁን ጠንካራነት አስፍሯል፡፡

  በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጠንካራ አዋጅ ላይ ተመሥርተውና ተማምነው ከመንግሥት ቦንድ፣ ከግል ድርጅቶች፣ በተለይም ከግል የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን በመግዛት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በጋራ በመሥራት ለዓመታት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ አዋጅ ቁጥር 592/2000ን በመጥቀስ የውጭ አገር ዜጋ ከፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን መግዛት አይችልም በማለት በአዋጅ ቁጥር 270/1994 ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ለይቶ የተሰጣቸውን መብት አንስቶ በቀጭን ትዕዛዝ የብዙ ሺሕ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የፋይናንስ አክሲዮን ድርሻ እንዲሰረዝ ከማድረጉም በላይ በጉዳዩ ክርክር ለመፍጠር የሞከረውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተቋማቱ የሕግ አካላትን በማስጠራት በቁጥጥር ሥር በማዋልና በማስፈራራት ያነሱትን የመብት ጥያቄ እንዲተዉ አስገድደዋቸዋል፡፡

  በማስፈራሪያው የተነሳ በርካቶች ጉዳዩን በሕግ ከመጠየቅ ይልቅ ከ20 ዓመታት በላይ ያካበቱት የአክሲዮን ድርሻ በሃራጅ ተሸጦ፣ የገዙበትን ዋጋ ብቻ ተቀብለው ትርፉ ለብሔራዊ ባንክ ሲገባ በዝምታ አልፈዋል፡፡ ይህ ድርጊት በአደባባይ የተፈጸመና ማስረጃውም በይፋ ስላለ፣ ብሔራዊ ባንክም ሆነ የግል የፋይናንስ ተቋማት አይክዱትም፡፡

  በብሔራዊ ባንክና በግል ፋይናንስ ተቋማት ዕርምጃ ምክንያት አገር ወዳዱ ዳያስፖራ ኪሳራ ላይ ወድቋል፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ባንክ የግል የፋይናንስ ተቋማት የበላይ ተቆጣጣሪ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ከተቋቋሙ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ታዲያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ አገር ዜጎች በሕገወጥነት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ሰርገው መግባታቸውን ለማወቅ እንዴት ይኼን ያህል ዓመት ወሰደበት? አክሲዮን ሻጮቹ ሕጋዊ የአክሲዮን ባለቤት መሆን የሚችለውንና የማይችለውን ለመለየት እንዴት ከ20 ዓመታት በላይ ወሰደባቸው? የአክሲዮን ባለቤት ለመሆን የቻሉት በማጭበርበር ነው ወይስ በአክሲዮን ሻጮች ልመና ነው? ለዚህ ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው፡፡  የፋይናንስ ተቋማቱም ሆኑ ሌሎች አካላት የተጣለባቸውን የካፒታል ጣሪያ ለመሙላት አቋራጩ መንገድ የዳያስፖራውን ሀብት መጠቀም አማራጫቸው እንደነበር የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

  ነገር ግን ሁሉም ዳያስፖራ የደረሰበትን ኪሳራ ዝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡ የብሔራዊ ባንክን ማስፈራሪያ ወደ ጎን በማለት አሥር የማይሞሉ ተበዳዮች ያለፍርድ ንብረት አይወረስብንም በማለት ብሔራዊ ባንክ ራሱ ከሳሽና ዳኛ ሆኖ ከሚቆጣጠራቸው የፋይናንስ ተቋማት ጋር በማበር የእነሱን ተጠቃሚነት፣ የዳያስፖራውን ተጎጂነት በመቃወም በፍርድ ቤት ክስ መሠርተው ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የከሰሱት የፋይናንስ ተቋማቱን ነው፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ በበላይነት በሚቆጣጠረን ብሔራዊ ባንክ ታዘን ነው በማለት ‹‹ከደሙ ንጹህ ነን›› ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ብሔራዊ ባንክም ተቋማቱም ከጉዳዩ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በፍርድ ሒደቱም አንድ ላይ ግፊት ሳያደርጉ እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ ዛሬም ድረስ ከሳሾች ተገቢውን ፍትሕ አላገኘንም በማለት በይግባኝ ላይ ይገኛሉ፡፡

  የዚህ ደብዳቤ ጸሐፊ ከላይ በተዘረዘረው ጉዳይ ውስጥ ለመግባት የተገደደው፣

  አንደኛ፤ በአዋጅ ቁጥር 2701994 መሠረት በሕግ አውጪው አካል ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከፍ ያለ መብት መስጠቱ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ግን ሕግ አስፈጻሚው፣ ብሔራዊ ባንክ፣ የውጭ ዜጎች የፋይናንስ ተቋማት ላይ መሳተፍ አይችሉም የሚለው አዋጅ ቁጥር 592/2000 ላይ ብቻ በማተኮር አዋጅ ቁጥር 270/1994 ትውልደ ኢትዮጵያንን ከሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ለይቶ ከፍ ያለ መብት እንደሰጠ ጨርሶ በመዘንጋት ወይም የዚህን ሕግ ተቀዳሚነት (Supremacy) ባለማጤን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ለብዙ ሚሊዮን ብር ኪሳራ ዳርጓል::

  ሁለተኛ፤ ቦንድና አክሲዮን ሁለቱም የፋይናንስ መሣሪያ ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 592/200 ላይ ብቻ በማተኮር የቦንድ ባለቤት የሆኑትን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩትን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለምን እንደ አክሲዮን እንዳልተሰረዘባቸው ግልጽ አይደለም፣ ወይም ነገ እንደ አክሲዮኑ የማይሰረዝበት ምን ዋስና አለ?

  ሦስተኛ፤ ሕግ አውጪው አካል ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣው ሕግ እያለ በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኪሳራ ላይ መውደቃቸውን እያየና እስከዛሬ ድረስም በጉዳዩ ላይ በተደረገው ሙግት የሕግ ተርጓሚው አካል አንድ ለከሳሽ አንድ ደግሞ ለተከሳሽ ተፈርዶ ሁለቱም ዛሬ በይገባኝ ላይ እንደሚገኙ ተገንዝቦ ነገሩን በማጤን መፍትሔ ቢሰጠው መልካም ነበር፡፡

   የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑት የውጭ አገር ዜጎች በተፈጸመው ተግባር ከማዘናቸውም በላይ፣ ወደፊትም በሚደረገው ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ጥርጣሬ ላይ ሳይወድቁ እንደማይቀሩ ይታመናል፡፡፡ ማንም ዜጋ ንብረቱን ላለማጣት ሲል በፍትሕ አባባይ፣ በፍርድ ቤት ቆሞ የመከራከር ዕድል ማግኘት አለበት፡፡ ዜጎች ከሃያ ዓመታት በላይ የገነቡትን የአገሪቱን መልካም ስም በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ ማሳጣት ፍትሐዊ አይደለም፡፡ የግለሰብ ሀብትን የውርስ ዕርምጃ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተው በሕግ የበላይነት ጉዳያችን እንዲታይ ያደርጉ ዘንድ ይህች ግልጽ ደብዳቤ ትማጸናለች፡፡

  ዋነኛው፣ ለተከሰተውና ወደፊትም ሊከሰት የሚችለው ሌላው የትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትልቁ ችግር የዜግነት ችግር ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የተሠራጩት ኢትዮጵያዊያን በምን ዓይነት ጠንካራ ሰንሰለት ከአገራቸው ጋር እንደተቆራኙ መግለጽ ያዳግታል፡፡ ሁሉም በያሉበት በልቡ ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ›› ብለው የሚዘምሩ መሆናቸው አያከራክርም፡፡

  የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችና ልጆቻቸው ዜግነት ቢያገኙ ኢትዮጵያዊነት ይደመራል፣ ያበዛል እንጂ አይቀንስም፡፡ አገሪቱም ትጠቀማለች እንጂ አትጎዳም፡፡ ስለሆነም ይህች ግልጽ ደብዳቤ በጥምር ዜግነት ኢትዮጵያዊነት እንዲበዛ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጣልቃ እንዲገቡ ደጋግማ ትማጸናለች፡፡

  (ፍቅረንዋይ በዛብህ)

  * * *

  የቦምብ ጥቃቱ በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ነው!

  ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተቃጣ ወንጀል ነው፡፡

  ላለፉት ለ27 ዓመታት የደበዘዘው ኢትጵያዊነት ቀድሞ ወደነበረበት ፍቅርና አንድነት በተመለሰበት ወቅት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ ሰላማዊው የድጋፍ ሠልፍ ላይ አንድነትና ፍቅርን የጠሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ እየተጋጨ እንዲኖር የፈለጉ፣ ከአገር ጥቅም በላይ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድሙ የሕዝብ ጠላቶች ባቀነባበሩት ጥቃት የደረሰው የቦምብ ጥቃት እጅጉን የሚወገዝ ነው፡፡

  ይህ ጥቃት በሠልፉ ላይ በተገኙ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው፡፡ ጥቃቱ የኢትዮጵያን አንድነት የበለጠ የሚጠናከር እንጂ በተጀመረው የለውጥ አካሄድ ላይ መሰናክል እንደማይሆን ነገር ግን ለውጥን መቀበል ያልቻሉ፣ አሮጌ አመለካከት የተሸከሙ ሙሰኞችን ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያበሳጭ ነው፡፡ የድጋፍ ሠልፉ አንድነትና ፍቅር የተሰበከበት ልዩ መድረክ በመሆኑ፣ አሸናፊውና ባለድሉም አንድነትና ዴሞክራሲን የተጠማው ኢትዮጵያዊ በሙሉ፣ የዴሞክራሲና የአንድነት ጠላቶችና ሙሰኞች የተጋለጡበት፤ የተሸነፉበት ኢትዮጵያዊነት ያበበበት ዕለት ስለሆነ፣ እየታየ ያለው የለውጥ ሒደት ግቡን እንዲመታ ዴሞክራሲ ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ጎን በመሆን የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

  በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መመኪያና ኩራታችን በሆነችው አገራችን የተጀመሩና እየታዩ ያሉትን የለውጥ ሒደቶች እንዲጎለምሱ፣ ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ በሚቻላቸው ሁሉ ድጋፋቸውን በአንድነት መንፈስ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኢኮኖሚ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ በጥሩ የኑሮ ምቾትና ድሎት ውስጥ ቢሆኑም ከደስታቸው በላይ አገራቸውን እያሰቡ በአገራቸው ውስጥ ካሉት የለውጥ ኃይሎች ጋር በመተባበር ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በሚቻላቸው ነገር ሁሉ መደገፍና መተባበር አለባቸው፡፡

  በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ምክንያት ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ ቀድምት አይሁዶች ‹‹በማንኛውም ምቾት ውስጥ ሆነን ስለአገራችን ስለጽዮን እናስባለን፣ ከተድላችን በላይ ስለ ጽዮን ባናስብ . . . ይህ ነገር ይድረስብን፣ ያኛው ነገር ይሁንብን፤›› በማለት ቃለ መሃላ ይፈጽሙ ነበር፡፡ ዛሬ እንደምናየው የታላቋ የእስራኤል መንግሥት ጠንካራ  ሆኖ እንዲመሠረት ያስቻሉትና የደገፉት በያሉበት አንድነትና ትብብር ፈጥረው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  

  እኛም በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ታላቅ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የጠላት ኃይል ያሸነፍነው በተባበረ ክንድ ነውና ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡ ይህንን የለውጥ መንገድ የማይፈልጉ የሕዝብ ጠላቶችና ሙሰኞች ብቻ ናቸው፡፡ የለውጥ ሒደቱ ያልተዋጠላቸው ሙሰኞችን ለማጋለጥና ለማሳፈር በአንድነት እንተባበር፡፡ ስለፍቅር፣ ስለመቻቻልና ስለአንድነት በየአካባቢያችን፣ በማኅበራዊና በመጓጓዣ ቦታዎችና በሌላውም ውሏችን ሁሉ እንነጋገር፡፡

  በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ይህንን ሴራ ያቀነባበሩ ወይም ከዚህ ድርጊት ጀርባ ያሉ ቡድኖችና ግለሰቦች፣ በሁሉም አካባቢ ሰላም እንዳይኖር ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጩ የለውጥ ሒደቱን ለማጨናገፍ የጥፋት መረብ የሚዘረጉትን ሴረኞች ማንነት በፍጥነት በመመርመርና በመለየት ለሕዝብ ይፋ በማውጣት ያጠፉትን ለሕግ ማቅረብ ይገባል፡፡ ለሕዝብ የማይጠቅም አመለካከት ይዘው በሥልጣን ላይ የሚገኙ ተሿሚዎችም እንዲወርዱ እንፈልጋለን፡፡

  (ዓለሙ ደንጊሶ ዋዬ፣ ከሐዋሳ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...