Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትክፍልፋይ ወገንተኝነትና አፈናቃይነት የፖሊሲ ችግር አይደለምን?

  ክፍልፋይ ወገንተኝነትና አፈናቃይነት የፖሊሲ ችግር አይደለምን?

  ቀን:

  በታደሰ ሻንቆ

  ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አለኝ የምትለው ኢትዮጵያ ብሔረሰብ ነክ ንቁሪያዎች፣ መጤ እያሉ መበደልና መግፋት ሲያንቀረቅቡን  ቆይተው ድንገት ዘግናኝ ግድያዎች የሚታዩባትና በሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብን ያፈናቀለ ቀውስ የሚገዝፍባት አገር ሆናለች፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ‹‹የግጭት ቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሔ ዳይሬክቶሬት›› በሰየመች አገር ውስጥ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የአንድ መቶ ቀናት የሥልጣን ዘመን ራሱ እየተከበረ ያለው ደም ማፋሰሱን፣ ማፈናቀሉን፣ በመብት ማንጓለሉንና በቀጠለ የግጭት ዜና ጭምር ነው፡፡ እስካሁንም ቀውሱ የሚያዛልቅ መፍትሔ ገና አላገኘም፡፡

  ለብሔር ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ካለ የኢሕዴግ የፖለቲካ ተግባር የተወለዱትን ችግሮች ባጭሩ ብናስቀምጣቸው በጎጆኛነት የኔ የሆነና ያልሆነ ሕዝብ ብሎ መለየት፣ ከዚሁ ጋር የኔ ብሔረሰብ የሚሉትን መሬት በመተሳሰብ ውስጥ መጠመድ፣ የእኔ የተባለ ሕዝብና መሬት ለይቶ ገዥነትንና በሊታነትን መቆጣጠር፣ በዚህም አማካይነት ጎጆኛ አዕምሮን ማስፋፋት (ከወጥንቅጥ ከተሜ አደግነትና ከአማራነት ጋር የተዛመደ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረን ዕይታ በብሔር ማንነት በማፈርና ሌላውን በመዋጥ ትምህክታዊነት እየቀጠቀጡ ወደ ጎጆኛነት መበጣጠስ)፣ የአካባቢን ኅብረተሰብ በቤተኛነትና በባይተዋርነት ማንጓለል፣ ከዚህም  ባስ ሲል ማፈናቀል፣ ብሔረሰብ ወይም አካባቢ የለዩ የንግድ ተቀቋማትን ፈጥሮ አካባቢ አለፍ የሀብት ሽሚያ ውስጥ መግባት፣ ምድሬ በሚሉት ሥፍራ ውስጥ ግን በባይተዋርነት በዝባዥነት በፈረጁት ላይ አትነግድብን የሚል ቅዋሜና ውድመት ማድረስ ተብለው መጠቃለል ይችላሉ፡፡

  እነዚህ ጣጣዎች ሥርዓቱ ያመጣቸው ሳይሆኑ ከአፈጻጸም ወይም ከአያያዝ የፈለቁ ናቸው ባይነት እውነት መናገር ወይስ በእውነታ ላይ ዓይን ጨፍኖ ምኞታዊነትን ሙጥኝ ማለትና ሕመምን መደበቅ? አዕምሯቸውን ያልዘጉት የራሳቸውን መደምደሚያ መቅረፅ እንዲችሉ ጥቂት ነገሮችን እናክል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ አወቃቀሩ ጎጇዊ ብሔረተኛነትንና የኢትዮጵያን እውነታ የማስተናገድ ዲቃላ ውጤቶች እንደ መሆናቸው፣ የችግር ምንጭነታቸው ድርሻ ከፊል ነው፡፡ እነሱ ራሳቸው የብሔርተኝነት ከፊል ውጤት እንደ መሆናቸው የችግር እናትነቱን ሥፍራ የሚወስደው ጎጇዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡

  ብሔርተኝነት “ሀ” ብሎ የሚጀምረው ሕዝቤ፣ ብሔሬ ወይም ብሔረሰቤ ብሎ ነው፡፡ ይኼንን ብሎ ሲነሳ ሌላውን የእኔ ያልሆነ ሌላ ሕዝብ የእነሱ ብሎ መለየቱ ነው፡፡ በብሔረሰብ ማንነት አለማፈርና መብትን አስከብሮ ከሌላው ጋር መኖር ከብሔረተኝነት ጋር በጣም የተለያየ ነገር ነው፡፡ ብሔረተኝነት ብሔረሰባዊ መብትን አስከብሮ ከመኗኗር ያለፈ፣ ፕሮግራምን ነድፎ የያዘ ፖለቲካ ነው፡፡ በንቅናቄ መልክም ሆነ በፓርቲ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥልጣን ሲሄድም ሆነ በሥልጣን ላይ ሆኖ ፕሮግራሙን እያናፈሰ ይቀሰቅሳል፣ ይመለምላል፡፡ ሻዕቢያ፣ ኦነግም ሆነ ሕወሓት ሕዝቤ መሬቴ ማለት የጀመሩት ገና በጎረቤት አገር ውስጥም ሆነ በበረሃ ውስጥ ሲላወሱ ነው፡፡ የይዞታ ካርታ የሠሩት ለሥልጣን ከመብቃታቸው በፊት ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ሻዕቢያ ድል መታሁ ሲል ከያዘው ውጭ ቀረኝ የሚለውን መሬት በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ነበር የተጠመደው፡፡ የኦነግ ዋና ሩጫም በአካልም በርዕዮተ ዓለምም የኦሮሞ ያለውን መሬት መቆጣጠር ነበር፡፡ ትግራይን ከመቆጣጠር አልፎ አዲስ አበባ የገባውና ኢሕአዴጋዊ የኢትዮጵያ ገዢነትን ያቀደው ሕወሓት ግን ከየብሔረሰቡ ብሔረተኞች በመብራት እየፈለጉ የመሻረክ፣ የማደራጀትና የማራባት አብሮም እነ ኦነግን ከመሳሰሉ ተቀናቃኞች ጋር የመሽቀዳዳም ሥራ ነበረበት፡፡ በቤተኛነትና በመጤነት፣ በባለቤትነትና በባዳነት፣ በባላገርነትና በባይተዋርነት ማጥመድና ማፈናቀል በተግባር የተጀመረውም ገና በጧቱ ከ1983 ዓ.ም. ማክተሚያ ጀምሮ አማራን በነፍጠኝነት ከማዋከብ ጋር ነው፡፡  በ1983 ዓ.ም. የነሐሴው ቻርተር መሠረት በተካሄደው ሽንሸናም ሆነ በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በፀደቀው አወቃቀር ውስጥ ሚዛን ያጡ እንደ ሐረርና ጋምቤላ ያሉ ሚጢጢዎችና ኦሮሚያና አማራ የሚባሉ ግዙፎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነውም፣ ከአጠራር አንስቶ ድርሻህ ቤትህ ይህ ነው የሚል መልዕክት የሚረጭን የ“ክልል” ስያሜን ያመጣውም ጎጆኛ ብሔረተኝነት ነው፡፡

  የሐምሌ 15 1983 ዓ.ም. ቻርተር በአንቀጽ 2(ለ) ላይ “እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ … በራሱ የተወሰነ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ” ቁልጭ አድርጎ ድርሻን ይናገራል፡፡ የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 (1-3) “የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች”ን  መብት ሲያስቀምጥ የቀነሰው ነገር ቢኖር “በራሱ” የምትለዋን የባለቤትነት ገላጭ ነው፡፡ አንቀጽ (47) ላይ ባለው የክልሎች ዝርዝር በመጀመርያዎቹ አምስት ተራዎች ውስጥ የትግራይ ክልል፣ የአፋር ክልል፣ ወዘተ በማለት ዓይነት የአካባቢውን ስም ተከትሎ “ክልል” የሚለው ቃል ይመጣል፡፡ ከስድስተኛው እስከ ስምንተኛው ተራ ውስጥ ላይ ዓይነተ ብዙነት ይጠቆማል፡፡ በተለይም  ስምንተኛው ተራ ላይ “የጋምቤላ ሕዝቦች” ሲባል እስከ አምስተኛ ተራ ቁጥር “ሕዝቦች”  አለመታከሉ፣ ሌሎቹ ከግዙፉ ብሔረሰብ እኩል ባለመብት እንዳልሆኑ ታስቦ ይሆን የሚል ጥያቄ የሚጭር ነው፡፡ ዘጠነኛው ላይ ደግሞ በነጠላ “የሐረሪ ሕዝብ ክልል” መባሉ ቁርጥ ባለ አነጋገር የሐረሪ ድርሻ ለማለት የተፈለገ ያህል ያስገርማል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በዚህ መልክ ይቀመጥ እንጂ፣ ክልሎቹን የሚገዙት ብሔረተኛ ፓርቲዎች ሰዎች ሲናገሩም ሲጽፉም “ብሔራዊ ክልል” ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ የመለመዱ ብዛት እኔ ራሴን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ “ብሔራ ክልል” ተብሎ የተጻፈ እስኪመስለኝ ህሊናዬን ተጭኖኝ ነበር፣ ሕገ መንግሥቱን እስከማመሳክር ድረስ፡፡

  “የትግራይ ብሔራዊ ክልል”፣ “የሶማሌ ብሔራዊ ክልል”፣ “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል”፣ ወዘተ እየተባለ ሲነገር ቁልጭ ባለ መልክ ስለይዞታ መወራቱ ነው፡፡ እነዚህን ይዞታዎች የሚገዙት ብሔረተኛ ቡድኖች አጠራርም ባለ “ይዞታው”ን ሕዝብ የሚያሳውቅ ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ “ብሔራዊ ክልል” የተሰኘው አጠራር በደቡብ ሕዝቦች ክልልም ላይ የተለመደ መሆኑ ነው፡፡

  ሌላም የሚደንቅ ነገር አለ፡፡ በኢሕዴን ውስጥ የነበሩ አማራ ፖለቲከኞች ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄነት (ብአዴን) ወርደው በዚያው መቅለጣቸው፣ ነባር የብሔር ጭቆና ቁስልና እህህታ የሌለባቸው መሆኑ ብርታት እንኳ ሆኗቸው የሚገዙት ክልል ኅብረ ብሔራዊ ግቢ የመሆኑን እውነታ ውስጣዊ የብሔረሰቦች አስተዳደሮች በመፍጠርና ከአማርኛ ውጪ በአገውኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ሥርጭት በማካሄድ እንደገለጹ ሁሉ፣ የክልልሉንም የፓርቲያቸውንም መጠሪያ አርመው በአስተዳደር ግቢያቸው ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን ኦሮሞ ነሽ ትግሬ ብሎ ያላስቀረ ሁሉንም አካታች የፓርቲ ባህርይ በመያዝ፣ ለቀሪዎቹ ብሔረተኛ ፓርቲዎች አርዓያ ሳይሆኑ መቅረታቸው ለምን የሚያሰኝ ይመስለኛል፡፡

  የኢትዮጵያ መላ ሕዝቦች የዴሞክራሲ አገዛዝ ግንባታ ዕድል የተጓለለው በብሔር የተደራጀው ኢሕአዴግ ሠራዊቱን የአገሪቱ የታጠቀ ኃይል ማደራጃ ሲያደርግ ነበር፡፡ ከዴሞክራሲ በመለስም፣ አገሪቱ ባላት የሙያና የዕውቀት አቅም ሙስናን እየታገሉ ዕድገትን የማራመድ አቅሞች ክፉኛ የመጎሳቆልና የመባከን ቀውስ ውስጥ የገቡትም፣ የከተማ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ ይቅርና የረባ ትምህርት ቀመስ እንኳ ያልፈጠሩ ብሔረሰቦች ራሳቸውን የቻሉ ክልል ሲደረጉ፣ በሌሎች ሻል ያለ አቅም ባላባቸው አካባቢዎችም ቢሆን አድርጉ የተባሉትን ለማድረግ የሚመቹ እበላ ባዮችን እያግበሰበሱ በ”አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ማጥመቅ ሲካሄድና ከበረሃ የመጡ ታጋዮችን ከአቋራጭና ከሩጫ ሥልጠና ትምህርት ጋር ወታዳራዊ ባልሆኑ አውታራትም ውስጥ መሰግሰግ ሲመጣ ነበር፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ከደርግ ጊዜ በበለጠ በሩ ወለል ያለለት፣ የአቋራጭና የጥድፊያ ትምህርት ሲጀመርና ለወራት ሳይማሩ ለፈተና መቅረብና የይስሙላ ማሟያ ፈተና ወስዶ ማለፍ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹ፍትሐዊ መብት›› ሲደረግ ነበር፡፡

  ብሔረተኛ ቡድኖች በቻርተራዊ/ሕገ መንግሥታዊ የክልል ይዞታዎች ገዥ ሲሆኑና ክልሎች ውስጥ ክፍልፋይ ብሔረተኝነት እየተስፋፋ ሲሄድ፣ በዚያው ልክ የዕውቀትና የሙያ ብቃት የለሽነት ጎሰኛ አድሏዊነትን ተገን አድርጎ መሹለክለክ ቻለ፡፡ “ትምክህተኞች”ን ከጥቅምና ከእኩል መብት በመግፋትና የጭቁን ብሔረሰቦችን ያለፈ ተበዳይነትን በማካካስ ሽፋን ውስጥ ተጠያቂነት የሌለበት ዘረፋም እየተባዛ ሄደ፡፡ በአማራ የተጀመረው መጤ እየተባሉ እስከ መፈናቀል የሄደ መገፋትም በስተኋላ ለትግራዩ፣ ለኦሮሞው፣ ለጉራጌው፣ ለወላይታው፣ ለሶማሌው፣ ለኑዌሩ፣ ለአኙዋኩ፣ ወዘተ ሁሉ የሚደርሰውና ሁሉም አካባቢ የሚፈጽመው ለመሆን በቃ፡፡ በአጭሩ የጎጆ ብሔረተኛ ፖለቲካና ገዢነትን ስሙን “ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኛነት” አልነው አላልነው፣ በኢትዮጵያ የ27 ዓመታት ልምድ እንደታየው ጎሰኛ አድሏዊነትን በአስተሳሰብም በተግባርም የሚያራባ፣ ለብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ዋስትና የማይሆን፣ የሙያ ሥነ ምግባርንም ሆነ የሰውነትና የዜግነት መብቶችን ለፍርድ አቅርቦ የሚያንገላታ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በኢትዮጵያ እውነታ የብሔረሰቦች መብቶች መከበርና እኩልነት የሚገኘው ከብሔረተኛ ገዢነትና ከብሔረተኝነት ሳይሆን፣ ከዴሞክራሲና ከዴሞክራትነት መሆኑ ቁልጭ እያለ ወጥቷል፡፡ ይህ ማጠቃለያ የኢትዮጵያን እውነታ ጠልቆ ከመመርመር የተገኘ ንድፈ ሐሳብ ሳይሆን፣ በሩብ ምዕት ዓመት ልምድ ጎጆኛ ብሔረተኛነት ያሳያቸውን ፀባያት ከማስተዋልና ይኸው ልምድ እንደ ዕጣን ዛፍ ያፈጨጨልንን ትምህርት ከመውሰድ ያላለፈ ነው፡፡

  የኢትዮጵያን ልምድ ማንበብ ይህን ያህል የቀለለ ሆኖ ሳለ፣ ችግሮቻችንን በጥልቀት መርምረን ተረዳን የሚሉት የኢሕአዴግ መሪዎች ምላሳቸውን ሳያደናቅፋቸው የአፈጻጸምና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ካልሆነ በቀር፣ የብሔረሰቦች መከባበርና እኩልነት ተረጋግጧል ይሉናል፡፡ ሥልጣን ላይ ከሌሉ ኢሕአዴጋውያንም በኩል ቢሆን ‹‹በዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ኢትዮጵያ ታብባለች! እኩልነትና ሰላም ይደረጃል!›› እንባላለን፡፡ በተቃዋሚነት ያሉ ብሔረተኞችም ብሔረተኛ ፖለቲካን መጣል እንደሚያሻ (ማብለጥና ማድላት ለብሔረተኝነት ውስጣዊ ባህርይ እንደሆነ) ገና አልተከሰተላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ የተግባር ትምህርት ተገሽሮ እያለ፣ የዴሞክራሲያዊ ብሔረተኛነት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተማሪ የሆኑት ሕወሓቶች ከመጀመርያም በጎጆኛ አመለካከት ተሰንክለው፣ ምርኮ ለምዬ ጎጆ ከማሰባሰብና ጎጇዊ ኩባንያዎች ከማደራጀት ያላመለጡ ሆነው፣ ጎጇዊ ሩጫና ብልጠት ጎጇዊ ተፀናዋችን ወልዶ ክልሌ አትግባ እስከማለት ሲተናኮል እየታየ፣ ምኞት ዓይንን ካላወረ በቀር እንደምን የብሔረተኝነትን ጠንቀኛነት ማየት ይከብዳል?

  “ችግሩ የአፈጻጸም ነው” የሚሉንም ሆኑ “በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት አገር ታብባለች” የሚሉን ሰዎች ለመሆኑ “ኤፈርት” ኢኮኖሚያዊ መረብንና በዚህ ዓይነት ሌሎቹ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ከየወገናዊ ብሔረተኞች ጋር ሆነው የፈጠሯቸውንና እየፈጠሯቸው ያሉትን የኢኮኖሚ መረቦች እንዴት ሊያስተናብሯቸው ነው? ሁሉም ዛሬ ያሉ ክልሎች እነ ሐረርና ጋምቤላም በየፊናቸው የየራሳቸውን የግብርና፣ የፋብሪካ፣ የፋይናንስና የንግድ መረቦች ፈጥረው በየክልላቸው እንዲወሰኑ፣ ከክልል ቢያልፉ ወደ ውጭ እንዲነግዱ ሊያደርጉ ነው? ወይስ ለየትኛውም ክልል ጎጇዊ ኩባንያዎች ማደራጀት መብቱ መሆኑንና ሁሉም የየበኩሉን እስኪያቋቋም ድረስ የቀደሙ አይነግዱ ብሎ መቃወም ‹ጥገኛ አመለካከት› መሆኑን አስተምረው፣ በ‹ነፃ ውድድር› ላይ የሚደርስ ቅዋሜንና ጥቃትን ሊያፀዱ ነው? የዚህ ዓይነት ጉዞ የሚያደርሰው የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ወደ መገንባት? ወይስ ተነገደብን የሚል ቅሬታና ቁርሾን አራብቶ ወደ መባላት?

  ነገሩን ከሌላ ጥግ እንቅረበው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በእኩል ዓይን ማክበርና ማስተናገድ ጎጇዊ ወገንን ከሚያበልጥ ዕይታ የወጣ ዴሞክራሲያዊ ህሊናንና አንድ ወጥ አካታችነትን በተከተለ አገር አቀፍም ሆነ አካባቢያዊ የፓርቲ አስተሳሰብና አደረጃጀት ውስጥ መግባትንና ለማንጓለል የማይመች የነባራዊ ሁኔታ አጋዥነትን ይሻል፡፡ የጎጆኛ ብሔረተኞች ህሊናዎችና ፓርቲዎች ድምር ከመሆን ፈንታ ኅብረ ብሔራዊ ህሊናና ፖለቲካዊ ስብስቦሽ ባለበት አኳኋን የተጋገዘ የልማት አቅም ሊሠሩ የሚችሉ ብሔረሰቦች ወይም ክፍሎቻቸው የተቃቀፈ አስተዳደራዊ ምድር ቢፈጥሩ ለምሳሌ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ምሥራቅ ኦሮሚያ አንድ አስተዳደራዊ ግቢ ቢሠሩ የብሔረሰብ መሬቴ እዚህ ጋ ቀረ በማለት የሚነሳ ውዝግብና ደም መፋሰስ ትርጉም ያጣል፡፡ ቤተኛና ባይተዋር ብሎ ለማበላለጥና ለማፈናቀል የማይመች ነባራዊ እውነታ ይፈጠራል፡፡ በአስተዳደራዊው ምድር የሚደራጀው የፖሊስ ጥንቅርም ብሔረ ብዙ (ዋና ባለቤት ነኝ በሚል አንድ ብሔረሰብ ያልተዋጠ) ስለሚሆን፣ በማንም ብሔረተኛ ቅስቀሳ አማካይነት የተወሰነ ዓይነተኛ ሕዝብን ለይቶ ማጥቂያ መሣሪያ ለማድረግ አይመችም፡፡ ትቅቅፍ ያስገኛቸው የኢፌዴሪ ኅብረ ብሔራዊ ግቢዎች ሁሉ ተፎካክሮ የመነጋገድ፣ የማትረፍና የመመንደግ አቅም ያላቸው ይሆናሉ፡፡ በአካባቢ ውስጥም ሆነ በአገር ደረጃ ኅብረ ብሔራዊ የንግድና የፋብሪካ ትስስር ለመፍጠር፣ አዲሱ ማኅበራዊ የአዕምሮ ሙሽት የሚስማማ (በሰፊ ዕይታ የታሰሰ) ይሆናል፡፡ የወሎና የጎንደር መሬት ወደ ትግራይ ገባ የሚል ብግነትም በሦስቱ አካባቢዎች ወይም ከሦስቱ በተውጣጣ ጉድኝት ውስጥ ባለቅሬታዎችን በሚሹት ውስጣዊ አስተዳደር ውስጥ በማካተት ሊቃለል ይችላል፡፡

  አገራችን ውስጥ የተፈለፈሉት ችግሮች ይህን መሰል ነባራዊ የቅንብር ማስተካከያ ይሻሉ፡፡ አማራጩ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የትኛውም ነባራዊ ማሻሻያ ቢሆን ግን ሥራ ላይ ለመዋል የሕዝቦችን ተቀባይነት ማግኘት የግድ ይሻል፡፡ ጎጆኛ ፖለቲከኛነትን አልፎ በመሄድና የአስተዳደር አወቃቀር ላይ ማሻሻያ በማድረግ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ፍላጎትና እምቢተኝነት አለ? ይህ ሁሉ እየተጎለጎለና የአሳማኝነት ውጤት እያፈራ ወደ መፍትሔ መሄድ የሚቻለው በርጋታ በመወያየት ነው፡፡ 

  ለሰላማዊ ልማት የሚስማሙ ኅብረ ብሔራዊ ግቢዎች የማደራጀት ሥራ በተወሰነ ደረጃ አማራ ክልልን፣ ይበልጡን ደግሞ ኦሮሚያን በአራቱም ማዕዘን ማቀፊያ የሚያደርግ እንደ መሆኑ ከአንድ አካባቢነት ወደ ብዙ አካባቢነት መሄድ አሁን ባለንበት ደረጃ በቶሎ ለመቀበል የሚከብድ ውሳኔ መሆኑ አይታበልም፡፡ የብሔር ጭቆና ባልደረሰበትና በብሔር መካለል እጅግም የማይዋጥለት በነበረው አማራ ውስጥ ዛሬ የአማራ ጥቅም የሚከበርለት በአማራነት እስከተደራጀ ነው የሚሉ ኃይሎች እንደ መፈጠራቸው፣ ወደ ሁለት ሦስት አካባቢ መፈንከት አማሮችን እንኳ ማከራከሩ አይቀርም፡፡ ከዚህ ተነስተን በብሔር ጭቆና ውስጥ ለኖረው ኦሮሞ ምን ያህል ከባድ ውሳኔ እንደሚሆንበት መገመት ይቻላል፡፡

  ጥቅሜንም መብቴንም አጣ ይሆን ብሎ መሥጋትና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የሥጋቱ ተገቢነት ግን  ለብቻ መሰባሰብን አማራጭ የለሽ የመብት ቤት፣ በተለያዩ የአስተደደር ግቢዎች ውስጥ መግባትን ደግሞ መብት መገፈፊያ አያደርገውም፡፡ አንድ ክልል ውስጥ ተሁኖ መብት ሊረገጥ እንደሚችል ሁሉ በተለያዩ ግቢዎች ውስጥ ተሁኖም መብት ሊሟላ ይችላል፡፡ ምኞታዊያን ግን ይህ እውነት እንዳይጤንና የእስካሁኑ የአገዛዝ አወቃቀር እንዳይነካ ሲሉ የማያመጡት ውልግድግ ማደናገሪያ የለም፡፡

  የኢትዮጵያ ችግሮች እነዚህ ናቸው፣ የለም ሌሎች ናቸው እያሉ በየጠበል ከማተት ታልፎ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን በቴሌቪዥን መድረክ ላይ ያገናኘ ውይይት (በኢቢሲ፣ በፋና፣ በኢኤንኤን፣ በዋልታ) ላመል ይሞካከር እንጂ አደባባይ ለአደባባይ ከሚንቀዋለሉ ፕሮፓጋንዳዊ አስተሳሰቦችና ከእውነታ ቆዳዎች ዘልቀው ነገሮችን በጥልቀት የሚበረብሩ ውይይቶች ገና አልመጡም፡፡ የምናገኛቸውም ውይይቶች ከሰው አመራረጥ አንስቶ እስከ ውይይት ማስተናበር ድረስ ጥንቃቄ የሚደረግባቸው (የተቀዳደደ መንግሥታዊ ፖለቲካንና ፖሊሲን ከመጣፍ ከመንግሥት ፖለቲካ ያፈገነገጠ ሕዝብ ገብ አመለካከትን ከማለዘብ ሽርጉድ ያልራቁ) ናቸው፡፡ ለረዥም ጊዜያት እየተሸፋፈነና እየተካደ ሲበስልና ሲሰራጭ የኖረ ብሔረሰብ ነክ መሸካከር ተማሪን ከተማሪ፣ እግር ኳስ ደጋፊን ከእግር ኳስ ደጋፊ ባፋለጠበት፣ ጠመንጃ የያዘ ጠመንጃ የለሾችን በረፈረፈበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በተፈናቀለበት መልክ ሲከሰት ችግሩን የአንድ የሁለት ዓመት ችግር፣ የታጣቂና የአመራር፣ የፀረ ሕዝቦች ቅስቀሳ ውጤት አድርጎ ለማሳነስ (“በጠባቦች” የተጀመረ ጣጣ ወደ ሕዝብ የማይገባ አድርጎ ራስን ለማታለል) ተሞክሯል፡፡

  በዚህ ረገድ የታየው ምኞታዊነት በመከላከያና በባንዲራ ጉዳይም ታይቷል፡፡ የመከላከያ ኃይሉና የኢትዮጵያ ባንዲራ የኢሕአዴግ ተደርጎ የሚታየው ምን እንከን ተሠርቶ እንደሆነ በመመርመርና ማረሚያውን በመፈለግ ፋንታ፣ ከፀረ ሰላምነትና ሕገ መንግሥት ከመጣስ ጋር እያያዙ ላይ ላዩን በመብከንከን ውይይት ባክኗል፡፡

  እንዲህ ያለው የእውነታና የውይይት አለመገጣጠም የኢትዮጵያን የፌዴራልነት ዘይቤ በመገምገም ረገድም ውስጥ ይመላለሳል፡፡ እስካሁን በመገናኛ ብዙኃን ሲሰራጩ በሰማናቸው ውይይቶች ውስጥ የተንፀባረቁት ጎላ ጎላ ያሉ መከራከሪያዎች ‹‹ብሔር ተኮሩ (ቋንቋን የተከተለው) ፌዴራላዊ አወቃቀር እንከን የለሽ ነው… እሱን ለመቀየር መሞከር ብሔር ብሔረሰቦችን መካድ፣ ብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ ማስተዳደር ይቅርባቸው እንደ ማለት ነው… አንድ አገር አንድ ሕዝብ አንድ ማዕከላዊ መንግሥት የሚል ዘይቤ ተመልሶ መጣ ማለት ነው፡፡ … የፌዴራሊዝም መሠረቱ ብሔር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም … ራስን በራስ ማስተዳደር በራስ (ባንድ) ቋንቋ እንጂ በሌላ ሊሆን አይችልም፤›› የሚሉ ናቸው፡፡

  የራስ አስተዳዳር የሚባለውን ነገር በመልኩ ወይም በቆዳው ብቻ እናሳብና የእነዚህን መከራከሪያዎች ውልቃቶች እንመልከት፡፡

  እንኳን በሰዎች ሥራ ውስጥ በተፈጥሮ ሥራም ውስጥ ስህተት መኖሩ፣ ከጊዜያትና ከሁኔታዎች መቀየር ጋር የሚያረጅና ወደ እንከንት የሚለውጥ ነገር መኖሩ አይቀርምና ለአወቃቀርም ሆነ ለሕገ መንግሥት “እንከን የለሽ” የሚል መከላከያ መደቀን፣ አትንኩብን እንደ ሃይማኖት እዩልን ከማለት የማይሻል ነው፡፡ እንዲህ ያለው እምቢታ ጆሮ የለውምና በሎጂክ አይረታም፡፡

  በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር ላይ ለውጥ ለማድረግ መሞከርን ብሔረሰቦችን ከመካድና አንድ ማዕከላዊ አስተዳደርን መልሶ ከማምጣት ጋር ያስተካከለውን መከራከሪያ ደግሞ፣ ምን ያህል ቁም ነገር እንዳዘለ ከመጨረሻው ጀምረን እንየው፡፡ አካባቢያዊ ራስ ገዝነት ይቅርና ሁሉም አካባቢዎች ከአንድ ማዕከል ይተዳደሩ እስካልተባለ ድረስ፣ ኢትዮጵያ የራስ ገዝ አካባቢዎች ፌዴራላዊ ቅንብር ሆና መቀጠሏ ያለቀለት ጉዳይ (ፌዴራላዊነት በኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል አጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘ አደረጃጀት) ሆኖ ሳለ፣ አሁንም ፌዴራላዊ አወቃቀራችንን እርማት እናድርግለት እንጂ እንሻረው ሳይባል አሃዳዊ አስተዳደር ዞሮ መጣብን የሚሉ ጩኸት በፍሬ ነጥብ መከራከር ሳይሆን ባዶ ማምታት ነው፡፡

  የፌዴራል አወቃቀር እርማትን፣ ብሔረሰቦችን ከመካድና ዕውቅና ከመንሳት ጋር ወዳስተካከለው መከራከሪያ እንምጣ፡፡ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ በተናጠል መታወቅ የለባችሁም፣ እንደ አንድ ብሔረሰብ ነው መታየት ያለባችሁ የሚል ውሳኔ እንጫንባችሁ ቢባል፣ ወልቃይትና ራያ ከአንድ ቋንቋ በላይ ተናጋሪዎች ናችሁና ዓይነተኛ ማኅበረሰባዊ ህልውና የላችሁም፣ በየቋንቋ መዘርዘርና መበተን አለባችሁ ቢባል፣ ወይም አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ማኅበረሰቦች ማንነታቸው እንዳይታወቅና በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙ ቢሞከር፣ ማንነትን ስለመካድ ዕውቅና ስለመንፈግ ማውራት ልክ ይሆናል፡፡ እየተባለ ያለው ግን ማንነት ይደፍጠጥ ሳይሆን ባለቤት እኔ ነኝ፣ አንተ ባይተዋር ነህ ለሚል በጥባጭነት የማይመቹና የተመጣጠነ የልማት አቅምን የሚያስገኙ ኅብረ ብሔራዊ ግቢዎችን እንፍጠር ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት እውነታ ውስጥ ይኼንን ሐሳብ ማቅረብ ደግሞ ፈጽሞ ዱብ ዕዳ ነገር ማምጣት አይደለም፡፡ ባለቤትና መጤ ባይነት የአገራችንን ሰላም እየነሳና ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶችን እያደፈረሰ ያለ መሆኑ ሁላችንንም ያሳሰሰበ ችግር ይመስለኛል፡፡ ፌዴራላዊ አሸናሸኑን የማስተካከል አንዱ ዋና ምክንያት ይኼንኑ ችግር ማቅለል ነው፡፡ በመፍትሔነት የተጠቆመው ነገር መሬት ላይ የሌለን ነገር እንፍጠር ያለ (ለምሳሌ ከየብሔረሰቦች እየዘገነንን አሁን ባሉ ክልሎች ውስጥ እንነስንስ የሚል ዓይነት ጉድ ያመጣ) አይደለም፡፡ አሁን ባሉ ክልሎች ውስጥ ማኅበረሰባዊ ዥንጉርጉርነት አለ፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ ትግራይ ውስጥ ትግሬ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ አማራም ውስጥ እንዲሁ፡፡ አማራ የሚባለው ግቢ ውስጥ አካባቢያዊ ክምችት ያላቸው አማራ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች ማንነታቸው ታውቆ፣ በቋንቋቸውና በባህላቸው ውስጥ የመኖር መብት ሳይጎድልባቸው ሊኖር እንደሚችሉ ሁሉ በሌላው አካባቢም እንዲያ ዓይነቱ መብት ዕውን መሆን ይችላል፡፡

  ብሔር ብሔረሰብነትን መሠረት ማድረግና እያንዳንዱን ብሔረሰብ ክልላዊ የራስ አስተዳደር ማድረግ የተጨነቅንበትን ችግር የሚፈታ ቢሆን እሰየው በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ መንገድ ለመሄድ ብንሞክር ከ70 እስከ 80 ያህል ክልሎች ይወለዳሉ፡፡ ከብዛታቸው በላይ ደግሞ ብዙዎቹ ቁንጥርጣሪ፣ እጅግ ጥቂቶች ደግሞ ግዙፍና ሰፊ ይሆኑና የልማት አቅምን የማመጣጠን ነገር ጭራሽ በፍትሐዊነት የማይለካ አለመኳኋን ይሆናል፡፡ ባለቤትና መጤ መባባልን የማስወገድ ነገርም፣ ከየብረሔሰባዊ ክልል ውስጥ የሌላ ብሔረሰብ አባላትን እየለቀምን በየአድራሻቸው ካልከተትንና ከዚያም በኋላ ከአድራሻቸው ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ ማገጃ ካላበጀን አይፈታም፡፡ በሌላ አነጋገር ከታሪክና ከሰዎች ተፈጥሯዊ ተላዋሽነት ጋር የሚቃረን የዕብደት ሥራ የሚሆነው ብሔር ብሔረሰብነትን መሠረት ያደረገ ክልል ፈጠራ ነው፡፡

  ዥንጉርጉርነት በሁሉም አካባቢዎች ከሞላ ጎደል በስብጥርም ሆነ በክምችት የሚገኝ ከሆነ፣ አሁን ካሉት ክልሎች ውስጥም ቢሆን በአንድ ዋና ብሔረሰብ ቁጥር ያልተዋጡና ኅብረ ብሔራዊ ግቢነታቸው ቁልጭ ያለ ክልሎች (ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉልና የደቡብ ሕዝቦች) ያሉን ከሆነ፣ የእነሱ ዓይነት አቀነባበር ችግሮቻችንን ለማቃለል የሚረዳን ከሆነና በዚያ መንገድ መሄድ ብሔረሰባዊ ማንትንና መብቶች የማይነካ ከሆነ ስለምን ምሰሶ የተነቃነቀ ያህል ኡኡ ይባላል!? ብዙ ብሔረሰቦች ያቀፉት ጋምቤላና ቤንሻንጉል ከምዕራባዊ ኦሮሞና አማራ ጋር ተጎዳኝተው የማናቸውም ማንነትና ብሔረሰባዊ መብት መስዋዕት ሳይሆን፣ ተለቅለቅ ያለ ኅብረ ብሔራዊ ግቢ (አቅም) ቢፈጥሩ ጥቅም እንጂ ምን ጉዳት አለው? ሶማሌ ክልል ውስጥ ኦሮሞ እንዳለ ሁሉ ኦሮሚያ ውስጥ ሶማሌ ካለ፣ ሶማሌንና ምሥራቃዊ ኦሮሞን ከሐረር ጭምር ያቀናጀ የኦሮሞውም የሶማሌውም ውስጣዊ የራስ አስተዳደርና የማንነት መጠሪያ ያልተሰረዘበት፣ ግን ብሔራዊ ክልሌ ለማለትና ለማንጓለል የማይመች ኅብረ ብሔራዊ ግቢ ቢፈጠር፣ በዚያው ዓይነት ኦሮሞው ከአፋርም ከአማራም ጋር የተቀናጀባቸው የዳርና የመሀል ኅብረ ብሔራዊ ግቢዎች ቢደራጁ ቀድሞም ለነበረ መላላስና መስተጋብር እንቅፋት ከማስወገድ በቀር ምን ችግር ይመጣል? ከኦሮሞ በኩል ተቆራረስን የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ወገኖች ከብሔረተኛ ስሜታዊነት ውጪ የአደረጃጀት ለውጡን ካስተዋሉት የኦሮሞ አስተቃቃፊነት ፊት የነበረ እንጂ አዲስ የመጣ አይደለም፡፡ ወደዚያም ሆነ ወደዚህ አስተዳደር ውስጥ ያለ ኦሮሞ ማኅበራዊ ፍሰቱ በአስተዳደር መስመር ሊታጠርና ሊለያይ የማይችል እንደ መሆኑ፣ በየአስተደደሩ ውስጥ ኦሮሞ ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ወዘተ እያለ ውስጣዊ የአስተዳደር አካባቢውን መግለጽ እንደመቻሉ፣ እንዲሁም ከገዳ ጋር በተያያዙ የትድድርና የባህል ዓውዶቹ በኩል ብሔረሰብ አቀፍ ተራክቦዎችን ማካሄድ እንደ መቀጠሉ የመቆራረስ ኪሳራ አይገጥመውም፡፡ እንዲያውም ሌሎች ብሔረሰቦችን ማቀፉ ከኦሮሚኛ የፌዴራል ቋንቋ መሆን ጋር ሲገናኝ ውጤቱ የኦሮሞ መቆራረስ ሳይሆን ትልቅ ኦሮሟዊ ኅብረተሰብ መገንባት ይሆናል፡፡

  የአስተዳደር አካባቢዎችን የእኔ ለማለት የማይመቹ ኅብረ ብሔራዊ ግቢዎች አድርጎ ማደራጀትን ለመቃወም ከቀረቡ መከራከሪያዎች የቀረን ራስን በራስ ማስተዳደር ዕውን የሚሆነው፣ በብሔር ብሔረሰብ የራስ ቋንቋ ብቻ ነው ባይነት ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ በአንድ ክልል አመራር ውስጥ አባል በሆነ ሰው (የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በፋና ቲቪ ውይይት ላይ) የተነገረ ግን ውልቃቱን ለማሳየት አንድ ቀንበጥ ነጥብ የሚበቃው ቆሽቋሻ መከራከሪያ ነው፡፡ በዚህ መከራከሪያ መሠረት በክልል ደረጃ በአማርኛ ቋንቋ የሚተዳደሩት የደቡብ ሕዝቦች፣ የቤንሻንጉልና የጋምቤላ ክልሎች ገና ራስን በራስ የማስተዳደር ዓለም ውስጥ አልገቡም ማለት ነው፡፡ የራስ አስተዳደርን ለማሟላት፣ የደቡብ ሕዝቦች ክልል ከአማርኛ ባሻገር ሃምሳ ምናምን ቋንቋዎችን ክልላዊ የሥራ ቋንቋ ማድረግ ሊኖርበት ነው፡፡ የራያ ማኅበረሰብ ማንነቴ አንድ ራያ ነው፣ ግን በሦስት ቋንቋ እሠራለሁ ቢል፣ ጎንደር ውስጥ ያለው ቅማንት ማንነቴ ቅማንት ነው፣ ግን የማላውቀውን የተሰናበተ ቋንቋ እንደገና ማጥናት አይኖርብኝም በአማርኛ እተዳደራለሁ ቢል የዚህ መከራከሪ ባለቤት ምን ፍርድ ይሰጥ ይሆን? ራስን በራስ ማስተዳደርን ከየብሔረሰብ ጋር አጣብቆ የሚያይን አመለካት ጎጆኛ የምንለው ዕይታው ኅብረ ብሔራዊ ትቅቅፍን ራስን በራስ የማስተዳደር ሌላ ፈርጅ አድርጎ ማየት ስለሚቸግረው ነው፡፡

  ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ፣ በብሔረሰብም ሆነ በኅብረ ብሔራዊ ግቢ ውስጥ በአንድ ቋንቋም ሆነ ከአንድ በበለጠ ቋንቋ ትድድር ሲካሄድ ዋናው ቅርፁ ሳይሆን ትድድሩ ዴሞክራሲና ነፃነትን የሚተነፍስ መሆኑ (ሕዝብ ራሴን በራስ እያስተደደርኩ ነው፣ በመብት ውስጥ ተከብሬ እየኖርኩ ነው፣ በአግባቡ ማስተዳደር ያቃተውን፣ ግፍ የዋለና የዘረፈ ባለሥልጣንን በሕግ የመጠየቅ አቅም በተጨባጭ አለኝ የሚል ልበ ሙሉነት ያለው መሆኑ) ነው፡፡ ዕውን ዛሬ ይህ ዓይነቱ የሕዝብ ልበ ሙሉነት ከወረዳ እስከ ዞንና ክልል ድረስ፣ ከዚያም አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ አለ? ለዚህ ጥያቄ ‹‹መብቱ አለ ችግሩ ሕዝቦች በመብታቸው በአግባቡ እየተጠቀሙ አደለም›› የሚል መልስ ሰንዝረው የሚያስቁን አይታጡም፡፡ ለዚህ ዓይነት አስቂኞች ያለን ማስገንዘቢያ የሚከተለው ነው፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ›› እያሉ በማውራት ወይም ቴአትራዊ ምርጫ  በማካሄድ ወይም ያማሩ የመብቶች አንቀጾች በሕገ መንግሥትና በተዛማጅ የሕግ ሰነዶች ውስጥ በማስፈር ወግ አይለካም፡፡ ዴሞክራሲ የመብቶችና የተጠቃሚዎቻቸው በተግባር መገናኘት ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...