Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት ምክንያት የሰዎች ሕይወት አለፈ

  በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት ምክንያት የሰዎች ሕይወት አለፈ

  ቀን:

  በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር መተማ ወረዳ በእርሻ መሬት ይገባኛል ምክንያት ተከስቶ በነበረው ግጭት የሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ ግጭቱ በመከላከያ ኃይል ጣልቃ ገብነት ቢቆምም፣ ግጭቱን ለዘለቄታው ለመፍታት እንዲያስችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር የላኩትን መልዕክት አድርሰዋል፡፡

  ረቡዕ ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለቱን አገሮች በሚያዋስነው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች የ13 ወታደሮችና ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ግጭቱ በመተማና በቋራ ነብስ ገበያ በተባለ አካባቢ ነው የተከሰተው፡፡

  ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በሥፍራው የመሬት ባለይዞታነት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ቢሆንም፣ በሥፍራው በጋራ ድንበር ለመጠበቅ በሚል የሰፈሩ የሱዳን ወታደሮች በተደጋጋሚ ትንኮሳ ስለሚያደርሱ በቋሚነት በእርሻ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚቸገሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡

  የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር እንዲህ ዓይነት ግጭት የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንደማይጎዳው፣ ግንኙነቱን ለማጠናከር ግን አገራቸው እንደምትሠራ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ከሱዳኑ አቻቸው አል ዲርዲሪ መሐመድ አህመድ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡ ለሱዳን ፕሬዚዳንት የተላከውም መልዕክት ይህ ይዘት ያለው እንደሆነም ታውቋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሰሞኑን በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አከባቢ በአርሶ አደሮች የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነና ክረምት በመጣ ቁጥር የሚከሰት መሆኑን ገልጸው፣ የሁለቱም አገሮች መሪዎች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

  ይኼንንም ችግር ለመፍታት ሁለቱ አገሮች ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸውም ተወስቷል፡፡

  ከአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያዊያኑ የእርሻ መሬታቸውን እንዳያርሱ በመከልከላቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለበርካታ ዓመታት የሚጠቀሙበትን የእርሻ መሬት ሱዳናውያኑ የእኛ ነው በማለታቸው፣ ትክክል አለመሆናቸው ቢነገራቸውም ሊቀበሉ ባለመፈለጋቸው ግጭቱ መቀስቀሱ ታውቋል፡፡

  በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ደላሎ ቁጥር አራት የእርሻ የኢንቨስትመንት ሥፍራ፣ እንዲሁም በሱዳን በሳንዶ በተባለው አካባቢ ግጭቱ ተቀስቅሶ ከሁለቱም በኩል ሰዎች ሲሞቱ ጉዳትም ደርሷል፡፡ የሟቾችና የተጎጂዎች ቁጥር በውል አልታወቀም ቢባልም፣ በወቅቱ 13 ሰዎች ከሁለቱም ወገን መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡

  የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው እንዲሰማራ ተደርጎ ግጭቱ የበረደ መሆኑንና በሁለቱ አገሮች በመሪዎች ደረጃ የመልዕክት ልውውጥ እየተደረገ እንደሆነ፣ ግጭቱንም በዘላቂነት ለማስወገድ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌዴሬሽኑ ቀጣይ ምርጫና የሊጉ አክሲዮን ማኅበር መግለጫ

  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...

  በጉራጌ ዞን በርካታ አካባቢዎች የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

  የክልሉ ፖሊስ በኢ-መደበኛ ኃይሎች የተጠራ አድማ ነው ብሎታል በደቡብ ብሔሮች...

  ኩባንያዎች ከአክሲዮን ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ከግብር ነፃ ተደረገ

  ከተቋቋሙ በኋላ ካፒታላቸውን ለማሳደግ አዲስ አክሲዮኖችን የሚሸጡ ኩባንያዎች፣ በአክሲዮን...