Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርስ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  ፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርስ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  ቀን:

  – በምትኩ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሊቋቋም ነው

  – ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥነ ምግባር ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይገደዳል

  – ፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሆን ነው

  የፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርስ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡ በምትኩ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋምን ለመመሥረት የሚያስችል ሌላ ረቂቅ አዋጅም ለፓርላማ ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡

  ፓርላማው ከቀረቡለት በርካታ ረቂቅ አዋጆች መካከል በቅድሚያ የተወያየው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) አስፈጻሚ አካላትን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 916/2008 ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

  ይህ አዋጅ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት ወቅት በፓርላማው የፀደቀ ሲሆን፣ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀረበበት ረቂቅ ማሻሻያም ሦስት አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡

  የመጀመሪያው ረቂቅ ማሻሻያ የአዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 16 መሰረዙን የሚገልጽ ነው፡፡ አንቀጽ 16 ማለት የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባርን ሙሉ በሙሉ የሚዘረዝር ነው፡፡

  ሌሎች ረቂቅ ማሻሻያዎቹ የሚመለከቱት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት አሁን ከሚገኝበት የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ወጥቶ፣ ተጠሪነቱ ለጊዜው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡

  በሌላ በኩል ደግሞ የፍትሕና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩትና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነት በቅርቡ ይቋቋማል ተብሎ ለሚጠበቀው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲዘዋወር የሚያደርጉ ማሻሻያዎች ናቸው፡፡

  ፓርላማው ረቂቅ ማሻሻያውን ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ ይህ ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡትን ማሻሻያዎች ተቀብሎ ለፓርላማው የውሳኔ ሐሳቡን የሚያቀርብ ከሆነ፣ በዚህ መሠረትም ፓርላማው ካፀደቀው በሥራ ላይ የሚገኘው ፍትሕ ሚኒስቴር ይፈርሳል፡፡

  በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ በስልክ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ ‹‹›ፓርላማው ማሻሻያውን ካፀደቀው ፍትሕ ሚኒስቴር ምን ይዞ ይቆማል?›› በማለት እንደሚፈርስ አረጋግጠዋል፡፡

  ይሁን እንጂ በምትኩ የፍትሕ ሚኒስቴርን ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችን በኃላፊነት የሚረከብ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚቋቋም ገልጸዋል፡፡

  ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ ይህንኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ በተመሳሳይ ዕለት ለፓርላማው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ጋር አባሪ የተደረገው ማብራሪያ የሕግ ማስከበር ተግባር በዓቃቤ ሕግ የሚከናወን መሆኑን፣ ነገር ግን ይህ የዓቃቤ ሕግነት ሥራ በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ እየተሠራ የሚገኝ በመሆኑ የሕግ ማስከበር ሥራውን ውጤታማና ቀልጣፋ እንዳይሆን ማድረጉን ይገልጻል፡፡

  እስካሁን ባለው አፈጻጸም የዓቃቤ ሕግነት ሥራ በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ማለትም በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንዲሁም በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ተበትኖ የሚገኝ መሆኑን ያስረዳል፡፡

  ‹‹ይህ አፈጻጸም ወጥነት የሌለውና የሕዝብን ጥቅም በአግባቡ የማያስከብር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም የተበተነውን የዓቃቤ ሕግነት ሥራ በአንድ ተቋም በማሰባሰብ በወጥነትና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ መፈጸም እንዲያስችል፣ የመመርመር ሥራ ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲሰበሰብ ማድረግና የመክሰስ ሥልጣን የሚኖረው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈልጓል፤›› ይላል የረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ ማብራሪያ፡፡

  የሚቋቋመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ዋና አማካሪና ተወካይ ሆኖ እንደሚሠራ ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል፡፡

  የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ፌዴራል ፖሊስን ማዘዝ፣ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ላይ የክትትል ሪፖርት እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ምርመራው በአግባቡ ተከናውኖ እንዲጠናቀቅ፣ በሕዝብ ጥቅም መነሻ ወይም በወንጀል የማያስጠይቅ ሁኔታ መኖሩ በግልጽ ሲታወቅ እንዲቋረጥ፣ ወይም የተቋረጠው እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑን ረቂቁ ያስረዳል፡፡

  ፖሊስ በራሱ የጀመረው ምርመራ ካለ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማሳወቅ ግዴታ ሲኖርበት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በምርመራ መዝገብ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ወይም ፍርድ ቤት በመዝገቡ ላይ ስለተሰጠው ውሳኔ ለፖሊስ እንደሚያሳውቅ ረቂቁ ይገልጻል፡፡

  ምርመራ የማድረግ፣ ማስረጃ የማሰባሰብ፣ ኤግዚቢት የመያዝ፣ ተጠርጣሪን የማቅረብና የመሳሰሉት ተግባራት የፖሊስ መሆናቸውን የረቂቁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ምርመራውን የመምራት ሥልጣን እንደሚኖረው፣ በተጨማሪም የማኅበረሰብ አገልግሎት ቅጣቶችን የሚያስፈጽም አደረጃጀትን ማመቻቸት፣ ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና ትዕዛዞች መፈጸምና መከበራቸውን መከታተል፣ ሳይፈጸሙ ከቀሩ ወይም አፈጻጸማቸው ሕግን ያልተከተለ ከሆነ ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት በማመልከት የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖረው በረቂቅ አዋጁ ተገልጿል፡፡

  የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚሆን፣ የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፓርላማው እንደሚሾም ረቂቁ ይገልጻል፡፡

  የረቂቁ አንቀጽ 26 ደግሞ ስለ ዓቃቢያነ ሕግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 74/1986 የሚሻር መሆኑን፣ እንዲሁም ከረቂቅ አዋጁ ጋር የሚቃረኑ ማናቸውም ሕጐች በረቂቅ አዋጁ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ይገልጻል፡፡

  በመሆኑም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ረቂቅ አዋጅ የሚፀድቅ ከሆነ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የመክሰስ ሥልጣኑ ተቀንሶ፣ መልካም ሥነ ምግባርን በማስረፅ ተግባር ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይገደዳል፡፡

  ፓርላማው ከአንድ ወር በፊት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን በሥነ ምግባር ትምህርት ላይ ብቻ ጊዜውን እያጠፋ እንደሆነ በመግለጽ እንደተቸው ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

  በረቂቅ አዋጁ አንቀጾች ዙሪያ በስልክ አጭር ማብራሪያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ ‹‹የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቀድሞም ቢሆን በዋናነት የተቋቋመው ሙስናን የማይሸከም ዜጋን ለመፍጠር እንዲሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹በሙስና ወንጀሎች ላይ ክስ መመሥረት ተጨማሪ ኃላፊነቱ ነበር፡፡ ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ ጐልቶ የሚታወቀው የመክሰስ ኃላፊነቱ ነው፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

  ፓርላማው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅንም ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

  አንዳንድ የፓርላማው አባላት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መሆኑ የሚፈለገውን የሙያ ነፃነት ሊነፍገው አይችልም ወይ? የፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነት በጊዜያዊነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠበትንና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያልሆነበት ምክንያትና ሌሎችንም የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲመለከትላቸው ጠይቀዋል፡፡

     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...