በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል የዕርቀ ሰላም ሒደት በአሜሪካ እንደሚጀመር ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ሒደት ፍጻሜ የሚያገኝበት፣ በውጭ የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት፣ ፍፁም የቤተ ክርስቲያናቷ አንድነት የሚመለስበት እንዲሆን የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
በ1984 ዓ.ም. የነበሩት 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተወሰኑ አባቶች ጋራ ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ ለ26 ዓመታት ተከታዮቿ ምእመናን እያዘኑ በከፍተኛ የሰላም ዕጦት ውስጥ አሳልፋለች፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ከችግሩ መፈጠር መነሻ ማግሥትና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በአራት የተለያዩ የስብሰባ ጊዜያት ዕርቀ ሰላሙን ለማምጣት ሊቃነ ጳጳሳትን መድቦ አሜሪካ ድረስ በመላክ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን፣ ከዚህ በተጨማሪ በዓመት ሁለት ጊዜያት በሚያደርጋቸው ጉባዔያት የሰላሙ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ መቆየቱን በመግለጫው አስታውሷል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ዘመናት የተፈራረቁባትን የውጭና የውስጥ ፈተናዎች በመቋቋም እምነቷን፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን አፅንታ መቆየቷን ያወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ በቤተ ክርስቲያኗ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ዓመታትም ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶሱ በዓመት ሁለት ጊዜያት በሚያደርጓቸው ጉባዔዎች የሰላሙ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
‹‹ይህ የምእመናን ልጆቻቸውን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ሰላማዊ መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ የ2010 ዓ.ም. የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ተዋቅሯል፤›› ሲሉም ፓትርያርኩ ገልጸዋል።
ኮሚቴው ያቀረበውን የእርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የእርቅ ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ ዕልባት እንዲያገኝ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን መሰየሙንም አስታውቀዋል።
በዚሁ መሠረትም ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ሒደት ፍፃሜ የሚያገኝበት እንዲሆንም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል። ይህ ጥረት የሰመረ እንዲሆን መላው የቤተ ክርስቲያኗ ገዳማትና አድባራት ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንዲተጉም ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም አሁን በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተጀመረው እርቀ ሰላም ያለምንም መሰናከል ለውጤት ይበቃ ዘንድ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ፈቃድ ከተሰጠው አካል በስተቀር ማንም መግለጫ መስጠት እንደማይገባውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሳስበዋል።
በዕርቀ ሰላሙ ሒደት በሚደረገው ማንኛውም ውይይት የነበረውንና ቤተ ክርስቲያኒቱ ይዛው የቆየችውን ቀኖና በተመለከተ፣ ውይይቱም ሆነ እይታው በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ብቻ የሚታይ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡