[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲል ልጃቸው አኩርፎ አገኙት]
- ምን ሆነሃል?
- ምን እዚህ ዳዲ …
- ፊትህን እኮ ዘፍዝፈኸዋል፡፡
- ኢሜሉ ነዋ ዳዲ፡፡
- ኔትወርኩ አስቸገረህ?
- የትኛው ኔትወርክ?
- ስንት ዓይነት ኔትወርክ አለ?
- ያው የሙስናው ኔትወርክ…
- እ…
- የደላላው ኔትወርክ …
- ምን አልክ?
- ይኼ ቃል እኮ ስለሚያደናግረኝ ነው፡፡
- እኔ ያልኩህ የቴሌውን ነው?
- ዛሬ እንኳን ደህና ነው፡፡
- ታዲያ ምን ሆነህ ነው ያኮረፍከው?
- ለስኮላርሽፕ አፕላይ አድርጌ አልነበር?
- ምን አሉህ?
- አልተቀበሉኝም፡፡
- ለምን ሲባል?
- እኔንጃ ዳዲ፡፡
- እኔ ሪኮመንዴሽን ጽፌልህ?
- ምን ታደርገዋለህ ዳዲ?
- በጣም ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
- ከማን ጋር?
- ከኒዮሊብራሎቹ ጋር!
[ክቡር ሚኒስትሩ የኒዮሊብራሎቹ ኤምባሲ ደወሉ]
- ጤና ይስጥልኝ፡፡
- አለቃሽን አገናኚኝ፡፡
- ማን ልበል ጌታዬ?
- ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አለቃሽን አገናኚኝ አልኩሽ እኮ?
- ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡
- እናንተም ትገማገማላችሁ እንዴ?
- ግምገማ ላይ ሳይሆን ስብሰባ ላይ ናቸው ነው ያልኩዎት፡፡
- ስብሰባማ ካልተገማገምሽበት የምን ስብሰባ ነው?
- ምን ልርዳዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ልጄ ለስኮላርሽፕ አፕላይ አድርጐ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- ግን አልተቀበሉትም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዩኒቨርሲቲዎቹ እኮ ነፃ ተቋማት ናቸው፡፡
- እኔ ተወረዋል አልኩኝ እንዴ?
- ያው ልጁን ስላልተቀበሉት ኤምባሲው ምንም ማድረግ አይችልም ልልዎት ነው፡፡
- የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ እኮ ነው?
- ቢሆንም ኤምባሲው ምንም ማድረግ አይችልም፡፡
- ለማንኛውም አለቃሽ ግምገማውን ሲጨርስ ይደውልልኝ፡፡
- እሺ፡፡
[አምባሳደሩ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወሉላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተም ትገማገማላችሁ እንዴ?
- ኧረ ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡
- እኛም ተገማግመን ስብሰባ ብለን ነው የምንሸውደው፡፡
- ለማንኛውም ምን ልርዳዎት?
- እናንተም ጋ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት ነው?
- የምን የመልካም አስተዳደር ችግር?
- ልጄ እናንተ አገር ያለ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አመልክቶ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- ዩኒቨርሲቲው ግን አልተቀበለውም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ አገር ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት ዓለም ላይ ያሉ ተማሪዎች እኮ ነው የሚያመለክቱት፡፡
- እና እነሱ አመለከቱ ተብለው የእኔ ልጅ መውደቅ አለበት?
- ማለቴ ውድድሩ ከባድ ነው ልልዎት ነው፡፡
- ይኸው የእናንተ ኢንቨስተሮች አገራችን ላይ እንደፈለጉ እየተንቀሳቀሱ አይደል እንዴ?
- እሱ ከዚህ ጋር ምን ያገናኘዋል?
- በደንብ ነው እንጂ የሚያገናኘው፡፡
- እኮ እንዴት ሆኖ?
- የእኔን ልጅ ነካችሁ ማለት አገሪቷን ነካችሁ ማለት ነው፡፡
- አገሪቷ የእርስዎ ናት ማለት ነው?
- እና የእናንተ ናት፡፡
- ይቅርታ አላወቅኩም ነበር፡፡
- ለማንኛውም ጠብቁ፡፡
- ምን እንጠብቅ?
- ተመጣጣኝ ዕርምጃ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ ጸሐፊያቸውን አስጠሯት]
- ተቃጠልኩ እኮ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት እንደሚሞቅ አታይም?
- የሙቀቱን ነገርማ ተውት፡፡
- ተንገበገብን እኮ ባክሽ፡፡
- በዚህ ላይ ደግሞ ኑሮ ውድነቱ ሲጨመር ያስቡት፡፡
- እ…
- ለነገሩ እርስዎ እሱ ብዙም አይገባዎትም፡፡
- ስሚ አሁን ኖት ያዥልኝ፡፡
- የምን ኖት ክቡር ሚኒስትር?
- የአየር ንብረታችን እየተለወጠ ነው፡፡
- ይኼማ ግልጽ ነው፡፡
- ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ማን ነው? ተፈጥሮ ናት?
- የለም የለም፣ ኒዮ ሊብራሎቹ ናቸው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር አውለው ይኸው በሙቀት እያነደዱን ነው፡፡
- እና ምን ይደረግ?
- አሁን በአስቸኳይ ይገዛ፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ኤሲ ለሁሉም ሠራተኛ ይገዛ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አየሽ ሙቀቱን መቋቋም የምንችለው ቢሯችን ውስጥ ኤሲ በመክፈት ነው፡፡
- የኑሮ ውድነቱንስ በምን እንቋቋመው?
- ለእሱም መክፈት ነዋ፡፡
- ምን?
- ኤልሲ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን እየተደረገ ነው?
- ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ነጋዴው እኮ እየተንጫጫ ነው፡፡
- ምን ቢንጫጫ አሉ?
- ከፍተኛ ምሬት ነው እኮ ያለው፡፡
- እኮ በምኑ?
- ዕቃው ሁሉ ወደብ ደርሶ መምጣት አልቻለም፡፡
- ምን ይደረግ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው እኮ፡፡
- ወደቡ እኮ የእኛ አይደለም፡፡
- የማን ነው ወደቡ?
- የጂቡቲ ነዋ፡፡
- የራሳችንን ገንብተናል አይደል እንዴ?
- እሱማ ደረቅ ወደብ ነው፡፡
- እንዲረጥብ ማጠጣት ነዋ፡፡
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቢገባኝ ባይገባኝ ኪሴ ካልገባልኝ ምን ያደርግልኛል?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- መንግሥት እንኳን ይችለዋል እኔ ግን በምን አቅሜ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ዲሜሬጁን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- ጨዋታውን ተመለከቱት እንዴ?
- የምን ጨዋታ?
- እግር ኳሱን ማለቴ ነው፡፡
- ዌኬንድ ላይ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነበረ እንዴ?
- ኧረ የአገርዎትን ነው ያልኩዎት?
- እንግሊዝም ብትሆን አገራችን ናት፡፡
- ለነገሩ ፓስፖርት እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡
- የምን ፓስፖርት?
- ያው በዜግነት ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም…
- እ…
- በኢንቨስትመንትዎ እንግሊዛዊ ነዎት፡፡
- እንዴት ማለት?
- እዚህ ካለዎት ሀብት እዚያ ያለው ይበልጣል ብዬ ነዋ፡፡
- ይኼን ነው ስታወራ የምትውለው አይደል?
- ብቻ ሕዝቡ አፍሯል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆኖ?
- በቡድናችን ውጤት፡፡
- ተሸነፍን እንዴ?
- ሽንፈት ቢሉ ሽንፈት ነው፡፡
- በማን ነው የተሸነፍነው?
- በአልጄሪያ፡፡
- ስንት ለስንት?
- 7ለ1
- ቀኑን ሙሉ ነው እንዴ የተጫወቱት?
- እነሱማ የሚሉት ሌላ ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- ውጤቱን አጥብበነው ነው የመጣነው፡፡
- ጭራሽ?
- እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዚህ ሽንፈት ግን እኔም የተማርኩት ነገር አለ፡፡
- ምን ተማሩ?
- የጥርነፋ ስትራቴጂያችንን መቀየር እንዳለብን፡፡
- አንድ ለአምስቱን?
- አዎና፡፡
- በምን?
- በአንድ ለሰባት!