Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለከባቢ አየር ሙቀት መጨመር አዋጭና ፈጣን መፍትሔ ያስፈልጋል!

  በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ደረጃ የከባቢ አየር ሙቀት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ነው፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተቆራኝቶ የምድርን ሙቀት መጠን እያናረ ያለው ክስተት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚቋቋሙት በላይ እየሆነ ነው፡፡ የደን መራቆት፣ የውኃና የመሬት በአግባቡ አለመያዝ፣ የአካባቢ ብክለት፣ ለአረንጓዴ ሥፍራዎች ትኩረት አለመስጠት፣ ከመጠን በላይ በካይ ጋዞችን መልቀቅና የመሳሰሉት ለሙቀት መጨመር ምክንያት ናቸው፡፡ ከከተሞች መስፋፋትና ከሕዝብ ቁጥር መጨመር አንፃርም ሲታይ፣ የተወሰኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም በሚደረገው ርብርብ ደኖች ይራቆታሉ፡፡ የውኃ አካላት ይደርቃሉ፡፡ መሬት በሚደርስበት ከፍተኛ ጫና አፈር ይሸረሸራል፡፡ በከተሞች ለቁሳዊ ዕድገት ብቻ ከፍተኛ ርብርብ ስለሚደረግ ፓርኮችና አረንጓዴ ሥፍራዎች ይዘነጋሉ፡፡

  ምንም እንኳ የቁጥር ጉዳይ አስተማማኝ ባይሆንም፣ የአገሪቱ ከሦስት በመቶ በታች እንደሆነ የሚነገርለት የደን ሽፋን 15 በመቶ መድረሱ ይነገራል፡፡ በአፈር ጥበቃና በደን ላይ እየታዩ ያሉ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፣ በመላ አገሪቱ በጣም በመጨመር ላይ ያለው ሙቀት በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ያሳያል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በአገሪቱ ግብርና ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በችግሩ ፅኑነት ምክንያት ‹‹የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት›› የሚባል ፖሊሲ ተቀርጿል፡፡ በዚህም ፖሊሲ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2025 ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያለው ኢኮኖሚ ለማስፈን ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች በተጀመሩበት በዚህ ወቅት ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአስከፊው ድርቅ ሰለባ ሆነው፣ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊነት ተዳርገዋል፡፡ ከድርቁ ጫና በተጨማሪ የከባቢ አየር ሙቀቱ እየጨመረ በመሆኑ ሕይወታቸውን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡

  የአየር ንብረት ለውጡ በአርሶ አደሮችና በአርብቶ አደሮች ላይ በሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት፣ የኢኮኖሚው ምሰሶ የሆነው ግብርና ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የሥራ ሥር ምግቦችን ጨምሮ የብርዕ ሰብሎች ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ በአገሪቱ የእንስሳት ሀብት ላይም እንዲሁ ከፍተኛ ኪሳራ ያጋጥማል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የወጣው ‹‹የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት›› ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚደረገውን መላመድ ከፍተኛ በጀትና ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ከመጠቀም ጀምሮ፣ ዝናብ ጠባቂ የሆነውን የአገሪቱን እርሻ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ መስኖ ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በዘመኑ ምርምር በመታገዝም ዝርያቸው የተሻሻሉ ዘሮችን መጠቀም ግድ ይሆናል፡፡ የእንስሳት ሀብት አያያዙንም ማዘመን የግድ ይላል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥና የከባቢ አየር ሙቀት ተፅዕኖዎችን በሚገባ መክቶ ሕዝብን ከችግር የሚታደግ ዘመናዊ አሠራር ማስፈን የጊዜው ጥሪ ነው፡፡ የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ሕዝብ ሕይወት ሊያሳስብ ይገባል፡፡

  በሌላ በኩል በከተሞች የሚታየው ሙቀት ከፍተኛ ወበቅ በማመንጨት በዜጎች የዕለት ተዕለት ሥራ፣ ጤናና የአኗኗር ዘይቤ ላይ አሉታዊ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ከተሞች ከመጠን በላይ እየሆነ የመጣው የከባቢ አየር ሙቀት እንዲሁ ችላ የሚባል አይደለም፡፡ በተለይ ሕፃናት፣ እርጉዞች፣ አራሶች፣ ሕመምተኞችና አረጋውያንን ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በከተሞች ውስጥ ለመኖሪያ፣ ለንግድ፣ ለማምረቻ፣ ለአገልግሎት መስጫና ለመሳሰሉት ሕንፃዎችና የተለያዩ ግንባታዎች ሲከናወኑ ለፓርኮችና ለአረንጓዴ ሥፍራዎች የሚሰጠው ትኩረት አሳዛኝ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ሕንፃዎች ሲገነቡ፣ አንድም ቦታ አዲስ ፓርክ ወይም አረንጓዴ ሥፍራ ሲገነባ አይታይም፡፡ ከታላቁ ቤተ መንግሥት እስከ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ድረስ የተንጣለለውና በአንድ ወቅት የሕዝብ መናፈሻ የነበረው ሥፍራ፣ ዛሬ በግለሰብ ቁጥጥር ሥር ውሎ ተቆልፎበታል፡፡ ኮንዶሚኒየሞች በተገነቡባቸው በርካታ ሳይቶች አንድም ፓርክ የለም፡፡ ክፍት ሥፍራዎችም ካሉ የመኪና ማቆሚያ ሆነዋል፡፡ በየመንደሩ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተሸንሽነው ተሸጠው ሕንፃዎች ተገትረውባቸዋል፡፡ ከተማዋ በዚህ ምክንያት መተንፈሻ ሳንባ የላትም፡፡

  የሚገነቡት ሕንፃዎች ከመሠረታዊው የኪነ ሕንፃ መሥፈርት ውጪ አብዛኞቹ ተመሳሳይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በአሉሚኒየምና በመስታወት በመታጠራቸው ሙቀት እያመቁ ወበቅ ሕዝቡ ላይ ይረጫሉ፡፡ መስታወቶቻቸው እያንፀባረቁ የእግረኛንም ሆነ የአሽከርካሪን ዕይታ ይጋርዳሉ፡፡ ሕንፃዎቹ ተደጋግፈው ወደ ላይ ስለሚመዘዙ ንፋስ በአግባቡ እንዳይንቀሳቀስ አግደዋል፡፡ ብዙዎቹ እንኳን መጠነኛ አረንጓዴ ሥፍራ ሊኖራቸው የረባ የመኪና ማቆሚያ የላቸውም፡፡ መንግሥት ያወጣው የሕንፃ ግንባታ ሕግ ተግባራዊ የሚያደርገው በመጥፋቱ፣ ተገንብተው ሳይጠናቀቁና የብቃት ማረጋገጫ ሳያገኙ ይከራያሉ፡፡ ሕንፃዎች ብቻ የተደረደሩበት ከተማ ለአረንጓዴ ሥፍራዎችና ለፓርኮች ትኩረት ሳይሰጥ እያደግኩ ነው ቢል ከማዘን በስተቀር ምን ማለት ይቻላል? ሕንፃዎቹ የሚገነቡባቸው ግብዓቶች ቢያንስ ከከባቢ አየርና ከተስማሚነት አንፃር ለምን ትኩረት አይሰጣቸውም? የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች ንድፍ ከመሥራት በዘለለ ለውበትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያመቹ ሐሳቦችን በማፍለቅ እንዲያግዙ ለምን አይደረግም? ከሕዝብ ጤናና ደኅንነት አንፃር ቢታሰብበት ይበጃል፡፡

  የደረቅ ቆሻሻ ክምችት፣ የውኃ እጥረት፣ የወንዞች በድን መሆን፣ አገር በቀል ዕፅዋትን እያባዙ አለመትከል፣ ወዘተ የመሳሰሉት ችግሮች በጉልህ ይታያሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ተሽከርካሪዎች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት በካይ ጋዝና ከተለያዩ ማምረቻዎች የሚወጡ ጭሶችም እየበዙ ነው፡፡ በከተሞች ውስጥ የነዋሪዎች ቁጥር መጨመርና የተለያዩ አገልግሎቶች በበቂ መጠን አለመገኘት በራሱ የሚፈጥረው ጫና አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥራ በመስተጓጎሉ ከክምር ቆሻሻ ውስጥ የሚወጣው ሚቴን የተባለው በካይ ጋዝ በብዛት ወደ ከባቢ አየር እየገባ ከመሆኑም በላይ፣ በዜጎች ጤና ላይ አደጋ ደንቅሯል፡፡ የውኃ እጥረቱ ሲታከልበት ደግሞ የሥጋቱን መጠን ያንረዋል፡፡ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚፈሱት ወንዞች መበላሸት ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ ከተሞች በእንዲህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተከበው መፍትሔ መፈለግ ካልተቻለ ስለ አረንጓዴነትና ፅዱነት መነጋገር አይቻልም፡፡

  የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በሕዝብ ጤና ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የአካባቢ ተቆርቋሪዎችና የመላ ሕዝቡ የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የሚመለከታቸው አካላት በጥናት ላይ የተመሠረተ ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት አሠራር በማስፈን ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ፓርኮችና አረንጓዴ ሥፍራዎችን በብዛት መሥራት፣ ተክሎችና ዕፅዋትን ማብዛት፣ ሙቀትና በካይ ጋዝ ቀናሽ የሆኑ አዋጭ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ከንግግር በላይ ለተግባራዊ ክንውኖች ትኩረት መስጠትና የመሳሰሉት አስፈላጊ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ መጠኑ ለጨመረው የከባቢ አየር ሙቀት ተጨባጭ የሆነ አዋጭና ፈጣን መፍትሔ ያስፈልጋል!

    

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  ሰበበኞች!

  ዛሬ የምንጓዘው ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም...

  የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ተሳትፎ ለምን ደበዘዘ?

  በመታሰቢያ መላከ ሕይወት በዓለማችን የፖለቲካ ትግልና የአብዮት ታሪክ ሁሌም የፊተኛውን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...