Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትኢትዮጵያ በ2018 የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች 56 አትሌቶችን ታሳትፋለች

  ኢትዮጵያ በ2018 የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች 56 አትሌቶችን ታሳትፋለች

  ቀን:

  ኢትዮጵያ በአልጄሪያ መዲና አልጀርስ በሚከናወነው 3ኛው የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች በስድስት ስፖርቶች 56 አትሌቶችን ታሳትፋለች፡፡ ጨዋታዎቹ በ20 ስፖርቶች በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች የሚካሄዱት ከሐምሌ 11 ቀን እስከ 21፣ 2010 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ልዑካን በሦስት ዙር ወደ አልጀርስ እንደሚያመሩ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ለልዑካኑ ሐምሌ 7 ቀን በኢትዮጵያ ሆቴል አሸኛኘት የተደረገለት ሲሆን፣ የመጀመርያው ልዑክ ሰኞ ሐምሌ 9 ቀን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀና ታውቋል፡፡

  ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በቦክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በወርልድ ቴኳንዶና በካራቴ ትሳተፋለች፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ከተለያዩ ፕሮጅክቶች ተመልምለው ከግንቦት 27 ቀን ጀምሮ በሆቴል ተቀምጠው ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቡድኑን አጠቃላይ ወጪ መሸፈን ብቻ ሳይሆን፣ አትሌቶቹ በሆቴል መሰባሰብ ከጀመሩበት ጀምሮ ሥልጠና በሚያደርጉባቸው ሁሉ በመገኘት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን  የአትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ ተሾመ ከበደ ተናግረዋል፡፡

  አሠልጣኙ የቡድናቸው ዝግጅት ለሦስተኛው የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ለሚዘጋጀው የ2018 የወጣቶች ኦሊምፒክ የሚወዳደሩ ምርጥ ስፖርተኞች ለማፍራት ጭምር ነው፡፡

  የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 የሚሆኑ የሚሳተፉበት በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡ የመጀመርያው ጨዋታ በሐምሌ 2002 ዓ.ም. የሞሮኮ መዲና ራባት ስታስተናግድ፣ ሁለተኛውን በግንቦት 2006 ዓ.ም. የቦትስዋና መዲና ጋቦሮኔ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡

  በሌላ በኩል በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ወጣት ብላ የምታሠልፋቸው አትሌቶች ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሲሆን ቆይቷል፡፡ ለዚህም በማሳያነት በፊንላንድ አስተናጋጅነት ሲካሄድ ሰንብቶ እሑድ ሐምሌ 8 ቀን ፍጻሜውን ባገኘው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ3,000 ሜትር ተሳትፋ የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው የ16 ዓመቷ ታዳጊ ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር ዕድሜ ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡

  የዕድሜ ጉዳይ አትሌቲክሱን ለዓመታት ለወቀሳና ለትችት ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ አሁንም ለሦስተኛው የአፍሪካ ወጣት ጨዋታዎች እየተዘጋጀ በሚገኘው ቡድን ላይ ተመሳሳይ ትችት ይደመጣል፡፡ በተለይ የአትሌቲክስ ቡድኑ አሠልጣኝ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ችግሩን ለማስወገድ በጋራ ምልመላና ዝግጅቱን ከታች ከፕሮጀክት ጀምሮ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ያደረጉበት በመሆኑ እንደማያሠጋቸው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ረቡዕ ሐምሌ 4 ቀን አትሌቶቹ ዝግጅት በሚያደርጉባቸው በአዲስ አበባ ስታዲየምና በብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከሆነ፣ አመራሩ እንዳለፉት ዓመታት አኅጉራዊውን ጨምሮ ለትልልቅ ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎች ከሚደረጉ የይድረስ ይድረስ ዝግጅት መውጣት ይኖርበታል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ቦርድ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ኃላፊነት ከተረከበ ጀምሮ የመስክ ልምምዶችን ጨምሮ በርካታ ተደጋጋሚ ግምገማና ክትትሎችን ሲያደርግ መቆየቱንና ይህም ለ2020 ኦሊምፒክ የሚደረገውን ዝግጅት ጭምር እንደሚመለከትም አውስተዋል፡፡

  በመስክ ጉብኝቱ ያገኘናት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ‹‹በአትሌቲክሱም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች ‹ሠርገኛ መጣ. . .› ከሚመስል አሠራር በመውጣት በተለይም ይመለከተናል የምንል አካላት ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን አቅደን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፤›› በማለት ለዓመታት ሲሠራበት የቆየው የይድረስ ይድረስ አካሄድና አሠራር እንደማያዋጣ ተናግራለች፡፡      

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...