አምስተኛውን መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ያስተናገደው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 124 ቀን ለሚቀረው የሪዮ ኦሊምፒክ እየተዘጋጀ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገባ፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ 43 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀደም ሲል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በደቡብ ክልል መናገሻ በሆነችው ሐዋሳ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የተከናወነው አምስተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች መዝጊያ ላይ የተገኙት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት በቀለ አማካይነት የቀረበላቸውን የሪዮ ኦሊምፒክ እቅድ ከተመለከቱ በኋላ ነው ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ቃል መግባታቸው የተሰማው፡፡
የወጣትና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፣ ለዚህ የሁላችንም ለሆነው አገራዊ አጀንዳ ተነሳሽነቱን በመውሰድ ረገድ የደቡብ ክልል የመጀመሪያ እንደሆነ መግለጻቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ሳይወሰን የኦሊምፒክ መርህን በተከተለ መልኩ አዘጋጅቶ እንዲጠናቀቅ ያስቻለው አምስተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አምሮና ደምቆ እንዲፈጸም ትልቁን ድርሻ ለተወጣው ለክልሉ ሕዝብና መንግሥት ምስጋና እንዳቀረቡም ታውቋል፡፡