Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ፌርማታ ፅሁፎች

  ‹‹አንተንም ያፈርሱ ይሆን?››

  ትኩስ ፅሁፎች

  የ130 ዓመት ፈሪ ዕድሜ (129 ዓመት) ባላት አዲስ አበባ፣ በአገር በቀል የጭቃ ኪነ ሕንፃ ግንባታ ፒያሳ ሠራተኛ ሰፈር አካባቢ የቆመው ጥንታዊ ፎቅ፡፡ በርካቶች የሚኖሩበትን ይህን ባለ ሦስት ፎቅ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ የአዲስ አበቤዎች የቤት አሠራር ጥበብን እያሳያ ይዘልቅ ይሆን? ኦማር ኻያም ምግብ ቤት አካባቢ የቆዩ አንድ አዛውንት ወደ እሪ በከንቱ እየዘለቁ ሳለ የተናገሩትም፣ ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡ ‹‹አንተንም ያፈርሱ  ይሆን?››

  (ሔኖክ መደብር)

  ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን

  * * *

  ደንበኞችን ያስቆጣው የጉግል ኤፕሪል ዘ ፉል

  ኤፕሪል አንድ በአውሮፓውያን ባህል ልዩ ቦታ የሚሰጠው ቀን ነው፡፡ ሰዎች አስደንጋጭ መልዕክቶች የሚለዋወጡበት ኤፕሪል ዘ ፉል፣ ከግለሰቦች በዘለለ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ደንበኞቻቸውን የሚሸውዱበት ቀን ሆኗል፡፡ በዘንድሮው ኤፕሪል ዘ ፉል የጉግል ካምፓኒ ተሳትፏል፡፡ ድርጅቱ ለዕለቱ በጂሜይል አካውንት ላይ ያደረገው ለውጥ ግን ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ ጉግል ሰዎች ኢሜይል የሚልኩበት በተን አጠገብ ‹‹ሚክ ድሮፕ›› የሚል በተን ጨመረ፡፡ በተኑን የሚጫኑ ሰዎች ኢሜይል የሚልኩለት ግለሰብ የሚሰጣቸውን መልስ እንዳያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ በተኑ በታዋቂው የአኒሜሽን ፊልም ‹‹ሚኒየንስ›› ላይ ያሉትን ቢጫ ድንክዬ ገፀ ባህሪያትም ያሳያል፡፡ ‹‹ሚክ ድሮፕ››ን መጠቀም አለመጠቀምም የጂሜይል ደንበኞች ፍላጐት ቢሆንም፣ ብዙዎች በስህተት በተኑን ተጭነዋል፡፡

  ለላኩት ኢሜይል ምላሽ ሳያገኙ ሲቀሩና ስለጉዳዩ ለጉግል አቤት ሲሉ፣ ድርጅቱ ለኤፕሪል ዘ ፉል የወጠነው ቀልድ እንደሆነ አሳወቀ፡፡ ብዙዎች ብስጭታቸውን በድርጅቱ ቅሬታ ማሰሚያ ድረ ገጽ ላይ ገለጹ፡፡ ድርጅቱም አስቂኝ ይሆናል ብሎ ያሰበው ነገር የተጠቃሚዎቹን ሥራ እንዳስተጓጐለ ተገንዝቦ ‹‹ሚክ ድሮፕ››ን አጠፋ፡፡ ‹‹ያስቃል ብለን ያሰብነው ነገር የብዙዎች ራስ ምታት በመሆኑ በጣም አዝነናል፤›› የሚል የይቅርታ መልዕክት ጉግል አስተላልፏል፡፡

  በተኑ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት በስህተት ተጠቅመው ለተጐዱ ሰዎች ግን በተኑ መወገዱ መፍትሔ አልሆነም፡፡ ጸሐፊው አላን ፓሽኪ በበተኑ ከተጎዱ አንዱ ነው፡፡ ጽሑፉን በስህተት ለአርታኢው በ‹‹ሚክ ድሮፕ›› በተን ላከ፡፡ ለጽሑፉ ማስተካከያ ሲላክለት ግን ማየት አልቻለም፡፡ አርታኢዋ አስተያየቷን እንዳልተቀበለ በመገመትና ኢሜይሉ ላይ ባየችው ቢጫ ድንክዬ ሚኒየን ተበሳጭታ ከሥራ አስወጥታዋለች፡፡

  * * *

  አውሮፕላን ውስጥ ዮጋ ካልሠራሁ ያሉ መንገደኛ ጉዞ አስተጓጐሉ

  ከሐዋይ ወደ ጃፓን ይጓዝ በነበረው አውሮፕላን አንድ ተሳፋሪ በአውሮፕላኑ ጋለሪ ውስጥ ዮጋ ካልሠራሁ ብለው አምባጓሮ በመፍጠራቸው አውሮፕላኑ ወደ ሐዋይ ለመመለስ መገደዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

  ዮጋ ካልሠራሁ በሚል የበረራ ሥርዓቱን ለማስተጓጐል የሞከሩት የ72 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ በመጨረሻም ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ዘገባው እንደሚያመለክተው ልክ ምሳ እንደተጠናቀቀ አዛውንቱ ከአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል ወደሚገኘው ጋለሪ አመሩ፡፡ ለምን ሲባሉ ዮጋ እየሠሩ ሜዲቴት ማድረግ እንደሚፈልጉም ገለጹ፡፡ ይህ የበረራ ሥነ ሥርዓቱን የሚጻረር ተግባር እንደሆነ ቢገለጽላቸውም አሻፈረኝ አሉ፡፡ አብረዋቸው ይጓዙ የነበሩት ባለቤታቸው የበረራ አስተናጋጆቹን እንዲሰሙ ቢመክሯቸውም የሚሆን አልሆነም፡፡ ይልቁንም በኃይል መንቀሳቀስና መጮህ ጀመሩ፡፡ እንግዲህ የአዛውንቱ ሁኔታ ምን ያህል ከባድ ቢሆን የአውሮፕላኑን ጉዞ እንዳስተጓጐለ መገመት ይቻላል ይላል ዘገባው፡፡

  * * *

  …ሀገሬ ኢትዮጵያ
  ሃያ አንድ የባሕር በር ÷ የነበረሽ ሀገር
  የእመ አምላክ አሥራት ÷ የቃል ኪዳን ማኅደር
  በሥነ ጥበብ ቅርፅ ÷ በሥልጣኔ ድር
  ካዋቀርሽው አጥር ÷ መውጫ መግቢያሽ በር
  አንድ እንኳ ቋሚ አጥተሽ ÷ የሚያስተናብር
  ሀገሬ ኢትዮጵያ ÷ ያ ዓለም ምስክር።
  የቆምሽበት ዓለም ዳሩ ቢሸረሸር
  ዕድልሽ ተቀብሮ ÷ ዕድያሽ ቢሠወር
  ሀገሬ ኢትዮጵያ መቼም መኖር አይቀር!
  እመ አምላክ ከጎንሽ ÷ ቆማ ለዘወትር።
  በአኵሱም ሥልጣኔ ÷ በኢትዮጲስ ኃይል
  በሳባ በሕንደኬ ÷ በምን ይልክ ዓይን
  ዓርማሽ ከፍ ብሎ ከሰንደቅሽ ጋር
  አዶሊስን ጥጌ ÷ ምፅዋን በራስጌ
  አሰብን በጎኔ ÷ በርበራን አንዳርጌ
  ቆሞ ያሳየኝ ነበር ÷ ያላንዳች ችግር
  ዳህላክ ባሕር ማዶ ሳለሽ ሰፊ ግብር።
  ከሳባ ዛር ውላጅ ÷ ከሒማር ሕዝብ ዘር
  ከቤጃ አዋይ ÷ ከካሡ አኅዋል
  በሰሜን ምሥራቅ እስከ የመን ዳር
  እስከ ኖቢያ ምድር ሰሜናዊ ክፍል
  እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ካድማስ ባሻገር
  ሃያ አንድ የባሕር በር ÷ ሃያ አንድ አጥር
  ሃያ አንድ በረኛ ÷ ሃያ አንድ ቃፊር
  የነበረው ጎንሽ ቢከዳውም ምዕር
  ሀገሬ አይሻለሁ! ቆመሽ በሁለት እግር
  በእመ አምላክ ቃል ኪዳን ÷ ወበእግዚአብሔር።

  • ኃይለ ልዑል ካሣ፣ አዲስ አበባ (መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.)

  **************

  ተጓዡ

  በአንድ ወቅት በጣም፣ በጣም ረጅም መንገድ የተጓዘ መንገደኛ ነበር፡፡ ለብዙ ቀናት ከተጓዘ በኋላ ውኃ በጣም ጠማው፡፡

  እናም ከአንዲት ጎጆ አጠገብ ሲደርስ ቆም ብሎ ጎጆዋ ውስጥ ያለችውን ሴት ሰላምታ እንኳን ሳይሰጣት “ውኃው እንዴት ነው? ውኃ አለሽ?’’ ብሎ ጠየቃት፡፡

  አሮጊቷም ሴት “እንደምንድነህ? ደህና ነህ? ሰላምታ እንኳን ሳትሰጠኝ ውኃ መጠየቅህ በጣም ቢጠማህ ነው፤” ብላ መለሰችለት፡፡

  መንገደኛውም “እንግዲያው ይህንን ካልሽና ምን ያህል እንደተጠማሁ ካወቅሽ በጣም አስተዋይ ሰው ነሽ ማለት ነው፤” አላት፡፡

  እርሷም “አዎ ነኝ፤ ነገር ግን ውኃውን ልሰጥህ አልችልም ምክንያቱም ባለቤቴ አህዮችን የሚያኮላሽ ሰው ስለሆነ ብዙ ውኃ ያስፈልገዋል፡፡ እጆቹን በየቀኑ ባይታጠባቸውም እንኳን ሲሞት የሚታጠብበት ውኃ እያጠራቀምን ነው፤” አለችው፡፡

  ተጓዡም ሰው እንዲህ አለ “ለተጠማ ተጓዥ ጠብታ ውኃ መከልከልሽ ክፉ ሰው ያሰኝሻል፡፡”

  እርሷም “አንተ ሰው ሆይ፣ ማንም ብሎኝ የማያውቀውን እንዴት ክፉ ብለህ ደፍረህ ትናገረኛለህ? ልጆች ሁሉ፣ ከብቶችና ፍየሎች እንኳን ክፉ ብለውኝ አያውቁም፤” አለችው፡፡

  መንገደኛውም “ምናልባት ፍየሎቹ በሰላም እየኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ ግን አንቺም ሆንሽ አነጋገርሽ ክፉ መሆናችሁን ነው የማውቀው፤” አላት፡፡

  ሴትየዋም “ስለ ክፋት ካነሳህ ተግባቢ ሰዎች ብቻ ናቸው እርስ በርሳቸው የሚሞጋገሱት፡፡ ክፉ የሆኑ እንግዳ ሰዎች ግን ከጎጆው ደጃፍ ላይ ይቆማሉ፡፡ ለምን አትገባም?” ብላ ወደ ውስጥ ጋበዘችው፡፡

  እርሱም “ያንቺ እዚህ መኖር ለእኔ ትርጉም አለው፡፡ ሁሉም ሰው የተለያየ ነገሮችን ማሞጋገስ ይወዳል፡፡ እኔ ደግሞ ገብቼ አንቺን ላወድስሽ እፈልጋለሁ፤” ብሏት ወደ ጎጆው በመግባት አብረው በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡

  • በዶዮ ሁካ የተተረከ የኦሮሞ ተረት

  * * *

  ሚሊዮን ዶላሮች ያላስቆሙት ወርቅ ቆፋሪ

  ብዙዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሎተሪ አልያም ዕጣ ሲደርሳቸው፣ ገንዘብ ለማግኘት መኳተናቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፣ ያገኙትን ገንዘብ ላሰኛቸው ነገር ማዋልን ይመርጣሉ፡፡ የትውልደ ሜክሲኳዊው ኤፍረን አግዊሬ ውሳኔ ግን ከብዙዎች የተለየ ነው፡፡ ኤፍረን የወርቅ ቁፋሮ ሠራተኛ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ከሥራ በኋላ ጎራ ያለበት መዝናኛ ውስጥ በሳንቲም በሚሠራ ማሽን ተጫውቶ 12.5 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሄደው ይህ ሜክሲኳዊ 64 ዓመቱ ሲሆን፣ አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፣ ሥራውን በጣም ስለሚወድ ለ16 ዓመታት የዘለቀበትን ወርቅ ቁፋሮ እንደሚገፋበት ተናግሯል፡፡ ካገኘው ገንዘብ በጥቂቱ ቀንሶ ከባለቤቱ ጋር ቤት የገዙ ሲሆን፣ የተቀረውን ለክፉ ቀን ይሆናል በሚል ባንክ አስቀምጠው ወደ ሥራው ተመልሷል፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ተጨማሪ ለማንበብ

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች