Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትየእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ‹‹ለሁለንተናዊ ለውጥ›› እያሠራ ያለው ጥናት መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

  የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ‹‹ለሁለንተናዊ ለውጥ›› እያሠራ ያለው ጥናት መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

  ቀን:

  ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተቋም አደረጃጀት ክፍተት ጋር ተያይዞ ብዙ ተብሏል፣ አሁንም እየተባለ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም የእግር ኳሱ ጉዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘቱ ሳያንስ፣ ለዜጎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ጠንቅ ሆኖ ለሕይወትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡ በየአራት ዓመቱ በምርጫ ወደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚመጡ አመራሮች በቅድመ ምርጫና በድኅረ ምርጫ ወቅት ቃል ለሚገቧቸው ዕቅዶች ከአቅም ውስንነት ወይም በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ተግባራዊ ስለማያደርጓቸው የችግሮቹ ስፋትና ጥልቀት እንዲሰፋ ምክንያት ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ በቅርቡ ከዓመት ያህል የውዝግብ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ኃላፊነት የመጣው አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ገና ከጅምሩ ሲንከባለል በመጣው ተመሳሳይ ችግር ሰለባ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው ችግሩን ለማስወገድ የፌዴሬሽኑን አጠቃላይ መዋቅራዊ ቅርፅና ይዘት የሚያጠና አካል አቋቁሜያለሁ ይላሉ፡፡ በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ፍጻሜ ያገኘውን የፕሪሚየር ሊግ ጨምሮ በየደረጃው ሊጎች የፍትሕ ያለህ በሚሉ አቤቱታዎች ፌዴሬሽኑን በማጨናነቅ ላይ መሆናቸው ይሰማል፡፡ ለነዚህም ቢሆን ተቋሙ አሁንም የጠራ ነገር እንደሌለው ነው የሚናገሩት፡፡ ለወራት ያለ ዋና አሠልጣኝ የቆየው ብሔራዊ ቡድን አዲስ አሠልጣኝ ቅጥር ተፈጽሞለታል፡፡ የምርጫው አካሄድስ እንዴት ነበር? በሚሉና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

  ሪፖርተር፡- በእርሶ የሚመራው የፌዴሬሽኑ አዲሱ አመራር በዚህ ወቅት ምን እየሠራ ነው? ክለቦች በተለይም በአሁኑ ሰዓት በርካታ የፍትሕ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ስለመሆኑ ይሰማልና፡፡

  አቶ ኢሳያስ፡- ሥራ አንድ ብለን የጀመረው በቀድሞ አመራር ተጀምሮ ያልተጠናቀቀውን የዓመቱን የውድድር መርሐ ግብር በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም አዲሱ አመራር በእንጥልጥል ላይ ያሉት እነዚህ ጉዳዮች እልባት ሳያገኙ ወደ ሌሎች ዕርምጃዎች መሄድ አልፈለገም፡፡ እርግጥ ነው ብዙኃኑ የስፖርት ቤተሰብ እግር ኳስ ላይ የሚያቀርባቸው በጣም ብዙ ብዙ ጉድለቶች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ ይህ ነገር ከመሠረቱ መቀየር እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ይህን ለመቀየር ደግሞ ግብታዊነት ይጠቅማል የሚል እምነትም የለኝም፣ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ከፍተኛ ባለሙያተኞች ያሉበት፣ በፒኤችዲ ደረጃ ሁለትና ሦስት ምሁራን ብዙ ጊዜ የተለያዩ የጥናት ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቁ ሰዎች፣ ከፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ጀምሮ በአጠቃላይ የተቋሙን ሁለንተናዊ ቁመና ሊለውጥ የሚችል ጥናት በበሻሌ ሆቴል ሆነው በማጥናት ላይ ይገኛሉ፡፡ ያ ሲጠናቀቅ ሙያተኛውንና ሙያውን ማጣጣምና ማገናኘት እንጀምራለን፡፡ በእኔ እምነት ለውጥ ማምጣት የሚቻለው እነዚህ ነገሮች ተጠናቀው ወደ ተግባር ሲለወጡ ነው፡፡ ተቋሙን ለመለወጥ መጀመር ያለብን ካደረጃጀት ነው፡፡ ተቋሙ ብዙ ነገር የለውም፣ ሲሄድ የነበረው በዘልማድ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድን ተቋም ተቋም ነው ከሚያስብሉት ነገሮች የአመራር ብቃትና የአሠራር ሥርዓት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ በዚህ መነሻነት ነው ሥራችንን ለመሥራት የምናስበው፡፡ ይሁንና በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ለውጥ ከመሻት የተነሳ ችኮላዎች ይታያሉ፣ ትክክልም ነው፡፡ ግን ደግሞ ችግሩን ከመሠረቱ ለማስወገድ መሠረታዊ የሚባሉ የጥናት ቅደም ተከተሎች የማያዳግም ሥራ መሥራት እንደሚገባ መረሳት የለበትም የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ምክንያቱም የቤቱ አደረጃጀት ብዙ ክፍተት አለበት፡፡ ተቋሙ እንደ ተቋም እየተንቀሳቀሰ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ የሥራ አስፈጻሚውና የማኔጅመንት ቡድኑ የሥራ ድርሻ በውል አይታወቅም፡፡ ኃላፊነታቸው የተቀላቀለ ነው፡፡ የኃላፊነት ወሰንም የለውም፡፡ ስለዚህ ይህን ጉዳይ በውል ለይቶ ለማስቀመጥ የአንድና የሁለት ወር ጊዜ ወስዶ በደንብ መለየትና ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ሲወርድ ቋሚ ኮሚቴዎች እንዴትና በምን አግባብ መቋቋምና መደራጀት እንዳለባቸው አይታወቅም፡፡ እነዚህን አጥርቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

  ሪፖርተር፡- የጥናት ቡድኑ ኃላፊነቱን ሲወስድ የጠየቀው ጊዜ ምን ያህል ነው?

  አቶ ኢሳያስ፡- በአጠቃላይ ከ50 ቀናት በላይ ነው የጠየቁት፡፡ ይሁንና እኛም ጥናቱ ቶሎ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ካለን ጉጉት በመነሳት በ50 ቀናት እንዲያጠናቅቁ ባደረግነው ጥረት እነሱም ተስማምተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወደ ሃያ ቀናት ያህል ሠርተዋል፡፡ ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም በሌላ በኩል ይህን የአሠራር ክፍተት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ለሚያስችለው የዕቅድ አካል መሆናችን ሊያስደስተን ይገባል፡፡ በእርግጥም አንድ ጭብጥ ላይ እንደርሳለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጥናቱ ሲጠናቀቅ ከሙያተኛ ቅጥር ጀምሮ ማን ምን ዓይነት ቦታ ላይ ቢመጣ ይጠቅማል? ከሚለው ጀምሮ ክፍተቱ በአጠቃላይ መልስ እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተቋምን ተቋም የሚያደርገው ባለሙያ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በግሌ የፌዴሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ የሚለውጥ ሥራ መሥራት ካልቻልኩ ቀደም እንዳሉት ዓመታት የዕለት ዕለት ሥራ ለመሥራት ከሆነ ሥራውን ባልጀምረው እመርጣለሁ፡፡ እያንዳንዱ ሥራ ባለቤት ኖሮት እንዲሄድ እፈልጋለሁ፡፡ የስፖርት ቤተሰቡን አደራ የምለው ትዕግሥት ኖሮት፣ ከዚያም ምን ሠራችሁ ብሎ እንዲጠይቀን ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ዕቅዱ ሰፋ ያለ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንከር ያለ የፋይናንስ አቅም ይጠይቃል፣ ያለው ነገር ደግሞ ለዚህ የሚሆን አይመስልም፣ እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

  አቶ ኢሳያስ፡- ይኼ ጉዳይ ለብዙዎቻችን ያስፈራል፣ ግን ደግሞ ወጪዎች ከዚህም ላነሰ ጉዳይ ሲወጡ ይታያል፡፡ እንደተባለው የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ አቅም ከዜሮ በታች ነው፡፡ ይህንኑ በሚመጣው ጠቅላላ ጉባዔ ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡ ይሁንና ቤቱን መለወጥና ማሻሻል ካለብን ሌሎች ወጪዎችን ቀንሰን የሚቀድመውን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ ችግራችን መቅደም ያለበት የቱ እንደሆነ ማወቁ ላይ ስለሆነ፣ በዚህ ረገድ ምንም እንኳ ፋይናንስ ማነቆ ቢሆንብንም በግሌ ይህን ኃላፊነት እስከተቀበልኩ ድረስ ወደ ኋላ የምልበት አንዳች ሊኖር አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት የሙያተኛው እጥረት ነው ፋይናንሱ በበቂ ሁኔታ እንዳይኖር ያደረገው፡፡ አሁንም በዚህ እሳቤ የማንሠራ ከሆነ እጥረቱ እየባሰ እንጂ አይቀንስም፡፡ ሌላው እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ምንም እንኳ ግንባታው ቢዘገይም ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘው የካፍ ቴክኒካል የልህቀት ማዕከል ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም ይህን ቃለ መጠይቅ በሰጠሁበት ሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ከካፍ የሚመጣ ቡድን አለ፡፡ የልህቀት ማዕከሉን እንረከባለን፡፡ በዚያ ላይ ፊፋ የልማት ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ላይ ከፍቷል፤ ይኼ ራሱ ይዞት የሚመጣው ነገር ይኖራል፡፡

  ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ የልህቀት ማዕከሉን ቢረከብ አሁን ካለበት ቀውስ አኳያ ሊያቃልልለት የሚችለው ነገር ይኖራል?

  አቶ ኢሳያስ፡- ፌዴሬሽኑ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት የሚያወጣውን ወጪ ሙሉ በሙሉ  እንኳ ባይሆን ሆቴልና መሰል ወጪዎችን ይቀንስለታል፡፡ ምክንያቱም ማዕከሉ ባስገነባቸው አምስት ቪላዎች ውስጥ 40 ደረጃቸውን የጠበቁ አልጋዎች አሉ፡፡ ለልምምድ የሚሆን የተሟላ ሜዳ አለው፡፡ ታዲያ ይህን ማዕከል ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንዳንጠቀምበት የሚከለክለን ምንድነው? እንደሚታወቀው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ትልቁ ወጪ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ለሆቴል የሚያወጣው ነው፡፡ በዚያ ላይ አዲሱ ጥናት ከሚመልሰው ለምሳሌ ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት አንዱ ነው፡፡ አሁን ባለው ፌዴሬሽኑ ገንዘብ ሊያመነጭ የሚችል ጠንካራ ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት የለውም፡፡ የተቋሙ አንዱና ትልቁ የድህነት ምንጭ የዚህ ክፍል መድከም ነው፡፡ ሌላው ብሔራዊ ቡድኑ ከእንግዲህ የተሟላ ነው ብለን ባንወስድም የራሱ የሆነ የልምምድ ሜዳ ይኖረዋል፣ ትልቅ ሀብትም ነው፡፡ በቅርቡ ከካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ጋር በአካል ተገናኝተን በብዙ ጉዳዮች ተነጋግረናል፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ሀብት የምናመነጭባቸው ዕቅዶች እንዳሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡

  ሪፖርተር፡- የክለቦችና የስፖርት የቤተሰቡ ስሜት ከፍተኛ በመሆኑ እርስዎ የሚመሩት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከወዲሁ ከፍተኛ ወቀሳና ውግዘት እያስተናገደ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ለዕቅዶቻችሁ መሳካት እንቅፋት ሊሆኑ አይችሉም?

  አቶ ኢሳያስ፡- እንደተባለው በተለይ የስፖርት ቤተሰቡ ፍላጎት እግር ኳሱ ከሚገኝበት ደረጃ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን አጣጥሞ ለመሄድ እኮ ነው ጊዜ ወስደን የምንሠራው፤ ሥራ ወሳኝ ነው የምንለው፡፡ ለዚህ ሰሞኑን ከተነሳው ቅሬታና አቤቱታ ብጀምርልህ፣ አብዛኛው ጥርጣሬ የወለዳቸው ናቸው፡፡ በግሌ ምንም ዓይነት አሴት የሚጨምሩ ነገሮች እንዳልሆኑ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም የመጨረሻዎቹን ጨዋታዎች ብንመለከት ፌዴሬሽኑ አዲስ አበባ ላይም ሆነ ጅማ ላይ ዋንጫም ሆነ ሜዳሊያ እንዲኖር አድርጓል፡፡ ይሁንና ለአንዳንዶቹ ጥርጣሬዎች መነሻ ተብለው የተወሰዱት በተለይ አዲስ አበባ ላይ በነበረው ጨዋታ እነዚያ ሜዳሊያዎች ለምን እንግዳው ፊት አልተቀመጡም? የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ቢሮ ውስጥ ነበሩ፣ ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ይኼ ቅሬታ ሊያስነሳ የሚችለው? ይኼ ጥቃቅን የፕሮቶኮል ስህተት እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ በእኔ ላይ የደረሰው ያ ሁሉ ውርጅብኝ ለምን እንደሆነ ባስብም ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ድርጊቱ በእርግጥ ክብረ ነክ ነው፡፡ መደረግም አልነበረበትም፤ እኔ ስለሆንኩ ሳይሆን ተቋሙ መከበር ነበረበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም የስፖርት ቤተሰቡ ከእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ካልወጣ በተለይ ለእግር ኳሱ ትልቅ ችግር አድርጌ ነው የምወስደው፡፡

  ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣትዎ በፊት የውድድር ዓመቱ ዋንጫ በአሸናፊነት ያጠናቀቀው ጅማ አባ ጅፋር ክለብ ሥራ አስኪያጅ ስለነበሩ ነገሩን የሚያያይዙት አሉ?

  አቶ ኢሳያስ፡- ይኼ ኃላፊነት እኔም ባልሆን ዞሮ ዞሮ የሚመራው አንድ ሰው ነው፡፡  ከዚህ ውጪ ከሰማይ አይመጣም፡፡ ተመርጨ ነው የመጣሁት፣ ታዲያ የመረጠህ አካል ለምን ይጠረጥርሃል? በግሌ ይህን ኃላፊነት ስረከብ በቅን ለማገልገል ዝግጁ ሆኜ ነው የመጣሁት፤ የጅማውን ጉዳይ እዚያው ጅማ ላይ ነው ትቼ የመጣሁት፡፡ አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነኝ የማውቀውም ይህንኑ ነው፡፡ ክለቦቻችን ዓመቱን ሙሉ የሚጫወቱት ለዋንጫ ሊሆን ይገባል፡፡ የቤት ሥራቸውን ሳይወጡ ጣት ወደ ሌሎች መቀሰር ተገቢ ነው ብዬ አልወስድም፡፡ ወደፊትም ሊታረም የሚገባው ይኸው ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ይህን ጉዳይ በጥንቃቄ ማስታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ እነዚህ ሁሉ የተለምዶ አሠራር ውጤቶች ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- ለወራት ያለ አሠልጣኝ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቅጥር ፈጽማችኋል?

  አቶ ኢሳያስ፡- እውነት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከምርጫው ጋር ተያይዞ አድሏዊነት እንዳለ የሚናገሩ አሉ?

  አቶ ኢሳያስ፡- እንደሚታወቀው መጀመርያ የተደረገው ማስታወቂያ ማውጣት ነው፡፡  ይሁንና በማስታወቂያው መሠረት የቀረቡት ተወዳዳሪዎች በብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ግምገማ የሚመጥኑ ሆኖ አልተገኙም፡፡ አሁንም ኮሚቴው በተሰጠው ኃላፈነት መሠረት አምስት ሰዎችን እንዲያቀርብ ሆኖ ከአምስቱ ሁለቱ በራሳቸው ፈቃድ ከምርጫ ውጪ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሦስቱ ሰዎች መረጃ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ የተሻለ መረጃ ያለው ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ በመሆኑ ሊመረጥ ችሏል፡፡ አድሏዊነት ስለሚባለው እኛም አንስተን ተከራክረንበታል፡፡ እንደተባለው ክፍተት ሊኖር አንደሚችል እንወስዳለን፡፡ ምክንያቱም ሙሉ የሚባል ነገር የለም፣ ዝርዝሩን ለጊዜው ማንሳት ባያስፈልግም ቴክኒክ ኮሚቴውም ማብራሪያ ሰጥቶበታል፡፡ በተቻለ መጠን በቀጣይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ሥራ ለመሥራት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ጥርጣሬ የሚዳርገንን አሠራር ለማስቀረት እንደምንሠራ ግን ቃል መግባት እፈልጋለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል እርስዎ በተገኙበት ፌዴሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ክለቦች ከአንድ ዓመት በኋላ ሊጉን በኃላፊነት እንዲያስተዳድሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ባለው ሁኔታ ይሳካል?

  አቶ ኢሳያስ፡- ብዙ ጊዜ አዲስ ነገር እንፈራለን፣ አሁንም አስረግጨ የምነግርህ ክለቦች ሊጉን ለማስተዳደር አቅሙም ብቃቱም አላቸው፡፡ ትልቁ ነገር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ብቻ ነው፡፡ ችግሩ አላስፈላጊ ጥርጣሬዎች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚያን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ክለቦቻችን ለአንድ የውድድር ዓመት በትንሹ የሚይዙት በጀት ከ30 ሚሊዮን ብር አያንስም፡፡ ግን ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ከሜዳ ገቢ አንድ ሚሊዮን ብር እንኳን አያገኙም፡፡ እውነታው ይኼ ከሆነ ቆም ብሎ በማሰብ አካሄዱን በሚገባ መመርመርና መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...