Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ፀደቀ

  የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ፀደቀ

  ቀን:

  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሕግ ምሁራን ካቀረቡዋቸው የማሻሻያ አስተያየቶች አብዛኞቹን ሳያካትት ፀደቀ፡፡

  ፓርላማው ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ከሰማ በኋላ ነው የማቋቋሚያ አዋጁን ያፀደቀው፡፡

  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ የወጡ ሕጐች በሥራ ላይ በሚተረጎሙበት ጊዜ በአግባቡ ተግባራዊ መሆናቸውን ለመከታተል፣ ለሕዝብና ለመንግሥት ያስገኙትን ፋይዳ የማረጋገጥ ሥራዎች እንዲከናወኑ፣ ቀደም ሲል ተበታትነው የነበሩ ሥራዎች ወደ አንድ ተቋም በማሰባሰብ ወጥነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍና የሕግ የበላይነትን በማስከበር በፍትሕ ሥርዓቱ የመልካም አስተዳደር ከማሰፈን አንፃር ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው፣ ቋሚ ኮሚቴው እንዳመነበት የውሳኔ ሐሳቡ ይገልጻል፡፡

  ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቡን ከማቅረቡ በፊት ባካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፉ የሕግ ባለሙያዎች የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋማያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተካተቱት፣ ከዓቃቤ ሕግ ሙያ ውጪ የሆኑ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣኖች እንዲወጡና ፍትሕ ሚኒስቴር ሳይፈርስ እነዚህን ኃላፊነቶች ይዞ እንዲቀጥል ያቀረቡት አስተያየት በቋሚ ኮሚቴው ተቀባይነት አላገኘም፡፡

  በተመሳሳይም የዓቃቤ ሕግ ሙያ ነፃነትን የሚጠይቅ መሆኑንና የአስፈጻሚው መንግሥትን የበላይ አካል ጭምር በሕግ የመጠየቅ ኃላፊነት የሚኖረው በመሆኑ በረቂቅ ሕጉ ላይ የተቋሙ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲሆን መደረጉ ተገቢ አለመሆኑንና ነፃነቱንም የሚጋፉ ስለሆነ እንዲሻሻል ጠይቀው ነበር፡፡

  ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ በምሁራኑ የቀረቡት የማሻሻያ ጥያቄዎች አልተካተቱም፡፡

  ምሁራኑ በረቂቅ ሕጉ ላይ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመማከር ክስ እንደሚያነሳና እንደሚያስቀጥል መጠቀሱ የተቋሙን ነፃነት የሚጋፋ መሆኑን በማስረዳት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚማከርባቸው ጉዳዮች በግልጽ እንዲወሰኑ በማለት ያቀረቡት የማሻሻያ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

  በዚህም መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥትን በመወከል የወንጀል ጉዳዮች ክስ ይመሠርታል፣ ይከራከራል፣ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ አገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚነሳበት አግባብ መመርያ ያወጣል፤›› ተብሎ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

  በዚሁ ዕለት ፓርላማው ካፀደቃቸው ሕጐች መካከል፣ የፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያቋቁመው አንቀጽ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 13/2008 እንዲሰረዝ የቀረበው ማሻሻያ አዋጅ ይገኝበታል፡፡

  በዚህም መሠረት ማሻሻያው በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚባል ተቋም አይኖርም፡፡

  በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነት ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ተነስቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን የቀረበውን ማሻሻያ አዋጅንም አፅድቆታል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...