Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የአገር ሀብት ለመጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ዋና ኦዲተር ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል የአገር ሀብትና ንብረት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን፣ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ወጪዎች በአግባቡ መከናወናቸውን፣ ገንዘብ ነክ ከሆኑት በተጨማሪ የእያንዳንዱን መንግሥታዊ ተቋም የዕቅድ ክንውን ከአገሪቱ የተለያዩ ሕጎች ጋር ተጣጥሞ ተግባራዊ መደረጉን መቆጣጠርና ማረጋገጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአሠራር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲስተካከሉ፣ የወንጀል ፍሬ ነገር ያለባቸውን ደግሞ ለፓርላማው በማቅረብ ውሳኔ እንዲተላለፍ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተጠሪነቱ ለፓርላማው ሲሆን፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥትን ለመቆጣጠር እንደ ፓርላማው የቀኝ እጅ ይቆጠራል፡፡ ይህንን ተቋም ከማናቸውም ዓይነት ጉንተላና ማስፈራራት ለመከላከል አለመቻል በአገሪቱ ላይ ግዙፍ የሆነ በደል ያደርሳል፡፡

  የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ ማክበር ማለት መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ የራስ ምታት የሆነውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግር ለመቅረፍ ከሚያግዙ መካከል ይህ ተቋም ልዩ ግምት ይሰጠዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው ንቅናቄም አጋዥ ይሆናል፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ጋር ተጣጥሞ ሥራውን በአግባቡ ሲያካሂድ፣ ተጠሪ የሆነለት ፓርላማም ከሕዝብ በተሰጠው ውክልና መሠረት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግለት ይገባል፡፡ ለሥራው መሰናክል ሊሆኑ የሚችሉ የአስፈጻሚውን አካላት መቆጣጠር አለበት፡፡ ከማናቸውም ዓይነት ዘለፋ፣ ማስፈራራትና ጥቃትም ሊከላከለው ኃላፊነት አለበት፡፡

  በተለያዩ ጊዜያት እንደተስተዋለው በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አካላት ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እያሳዩ ያሉት አዝማሚያ እንደ ማንቂያ ደወል ካልታየ፣ ንቀትና ማናለብኝነት የሚፈጥሩት መታበይ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፡፡ ምልክቶቹም በተደጋጋሚ እየታዩ ነው፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኦዲት ግኝቶቹ አማካይነት ያቀረባቸው ችግሮችን ከማስተካከል ይልቅ፣ ሰሞኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት ሲቀርብ የታየው ዓይነት አዝማሚያ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የመቆጣጠርና መስመር የማስያዝ ኃላፊነት የፓርላማው ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶች ላይ የእቢተኝነት አስተያየቶችን ከሰጡት መካከል ማዕድን ሚኒስቴርና የመሳሰሉት ይታወሳሉ፡፡ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም አይዘነጋም፡፡ የፓርላማውን የመከታተልና የመቆጣጠር አቅም የበለጠ እንዲፈረጥም ማድረግ የሚችለውን ዋና ኦዲተር ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጉሸማ መከላከል የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡

  በጣም የሚገርመው ጉዳይ ደግሞ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝቶቹ ያቀረባቸውን ችግሮች ከማስተካከል ይልቅ፣ እንቢተኝነታቸውን በግልጽ የሚያንፀባርቁት በፓርላማ ተገኝተው ነው፡፡ ፓርላማውም ይህንን ሁሉ እንቢተኝነት እያየ መረጃ የሚያቀርብለትን ዋና ኦዲተር በተቋም ደረጃ ሲከላከል አይስተዋልም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ጥቂት የምክር ቤት አባላት ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ፣ ፓርላማው እንደ ተቋምና እንደ መጨረሻው የአገሪቱ የሥልጣን አካልነቱ ዋና ኦዲተርን ሲከላከል አይታይም፡፡ ፓርላማው ይህንን ትልቅ ኃላፊነት በተቋም ደረጃ ካልተወጣ የማን ኃላፊነት ሊሆን ነው? አስፈጻሚው አካል ችላ በተባለ ቁጥር የዋና ኦዲተር ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የሕዝብን ሀብትና ንብረት የማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅም ይሸረሸራል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ስለመልካም አስተዳደር መነጋገር ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡

  ዋና ኦዲተር መተቸት ወይም መወቀስ ካለበት ሥራውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ብቻ ነው፡፡ ከተቋቋመበት ዓላማ ወጥቶ ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ሲሰማራ ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በኦዲት ግኝቶችም ሆነ በዕቅድ ክንውን ላይ በቀረቡ ሪፖርቶች አቀራረብ ላይ አቤቱታ ያላቸው በአግባቡ ለፓርላማ በማቅረብ መሞገት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዋና ኦዲተር ያቀረባቸውን የማስተካከያ አስተያየቶች ለመቀበል ይቸግረኛል ማለት አይቻልም፡፡ በሕግም ያስጠይቃል፡፡ ፓርላማው ከዋና ኦዲተር በቀረቡለት ሪፖርቶችና አስተያየቶች መሠረት በርካታ መንግሥታዊ ተቋማትን በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴው አማካይነት መከታተሉና መቆጣጠሩ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በኦዲት ግኝቶች ላይ የታዩባቸውን ግድፈቶች እንዲያስተካክሉ የተነገራቸው ተቋማት ኃላፊዎች እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ፣ እንደ ተቋም አቋም ይዞ ሊሞግታቸውና ሊገስጻቸው ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርምጃ እንዲወስዱ ማድረግም አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ስላለበት፡፡

  ይህ እንደ ማሳያ ሆኖ ሌሎች ተቋማት ማለትም ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ምርጫ ቦርድም ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ መላቀቅ አለባቸው፡፡ ነፃነታቸውም ሊከበር ይገባል፡፡ እነዚህ ተቋማት ከተቋቋሙባቸው መሠረታዊ ዓላማዎች ጋር ተጣጥመው በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ በስተቀር ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ስለአገር ዕድገት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፓርላማው እነዚህን ተቋማት ከማናቸውም ዓይነት የሥራ አስፈጻሚው ተፅዕኖ የማላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ተቋማቱ በአግባቡ ሥራቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ብቻ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተዓማኒነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና መንሰራፋትና የፍትሕ መስተጓጎል የአገር ችግሮች የሚፈቱት ዴሞክራቲክ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ ፓርላማው ዋና ኦዲተርን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ የአገር ሀብት የሚጠበቀውና የሕግ የበላይነት የሚከበረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የአገር ሀብት ለመጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ዋና ኦዲተር ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...

  የቅጥፈት እንጀራ!

  የዛሬው ጉዞ ከሲኤምሲ ወደ መገናኛ ነው። በዚህ በከባዱ የኑሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...