Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማያገናዝቡ ዕቅዶች የመንግሥትን ተዓማኒነት እየሸረሸሩ ነው!

  አገር የምትመራው በአግባቡ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ በሚውል መሪ ዕቅድ ነው፡፡ በርካታ ዕቅዶች ተጨባጭ ሁኔታዎችን ባለማገናዘባቸው ምክንያት አፈጻጸማቸው ከታሰበው በታች ሲሆን ይታያል፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት በማንቀሳቀስ ሥራ ላይ ለማዋል ምክንያታዊና በተግባር ሊታይ የሚችል ዕቅድ መኖር አለበት፡፡ በአግባቡ የማይሳካ ዕቅድ የውድቀት ማሳያ ነው፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚታየው የዕቅዶች በአግባቡ አለመሳካት ነው፡፡ በእርግጥ ዕቅድን መቶ በመቶ ማሳካት የማይቻል ቢሆንም፣ ከሚፈለገው ደረጃ በታች መውረድ ግን ጤናማ አይደለም፡፡ ዕቅዶች ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማገናዘብ እየተሳናቸው ነው፡፡ በዚህም የመንግሥትን ተዓማኒነት እየሸረሸሩ ናቸው፡፡

  ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የንግድ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የኤክስፖርት ዘርፍ ሪፖርት ለምንነጋገርበት ጉዳይ ዋቢ መሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተጀመረበት በዚህ በጀት ዓመት፣ አገሪቱ ከኤክስፖርት ዘርፍ ትጠብቀው የነበረው ገቢ በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ሪፖርቱ ያወሳል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪና ከማዕድን ዘርፎች አገሪቱ 2.91 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ቢታቀድም፣ የተገኘው 2.05 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ከሸቀጣ ሸቀጥ የኤክስፖርት ንግድ ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ 5.01 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በዘጠኝ ወራት የተገኘው 2.05 ቢሊዮን ዶላር ብቻ በመሆኑ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሦስት ወራት እየቀሩ አፈጻጸሙ ከ50 በመቶ በታች ነው፡፡ የታቀደውና አፈጻጸሙ ለንፅፅር የሚመች አይመስልም፡፡

  ዕቅድ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣምና በተግባር ሊረጋገጥ የሚገባው መሆን ሲገባው፣ የዕቅድ ትርጉሙ እየጠፋ ነው ያለው፡፡ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መነሻ ጀምሮ በብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ‘ዕቅድ መለጠጥ’ የሚባል ጽንሰ ሐሳብ የተለመደ ሆኗል፡፡ ዕቅድ ምክንያታዊና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል መሆን ሲገባው፣ የተለጠጠ የሚል ታርጋ ተለጥፎለት የተሳሳተ ጽንሰ ሐሳብ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ የተለጠጠ የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት የዕቅዶች አፈጻጸም ሲበላሽ፣ ለስህተት የሚዳርጉ ሰበቦች ይደረደራሉ፡፡ የዕቅድ ችግር ካልሆነ በስተቀር ዓለም አቀፉን ገበያ ማሳበቢያ ማድረግ ተቀባይነት የለውም፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ በጥራት፣ በዋጋና በአቅርቦት ፍጥነት ተወዳዳሪ መሆን ከተቻለ ዓለም አቀፉ ገበያ አዋጭ ነው፡፡ ይህም በተግባር የተረጋገጠ ነው፡፡

  እንደ ምሳሌ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳን እንይ፡፡ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ጀምሮ ለእነዚህ የኤክስፖርት ንዑሳን ዘርፎች የተለጠጠ ዕቅድ ቢያዝም፣ የተገኘው ውጤት ግን ከሚጠበቀው በታች ያሽቆለቆለ ነው፡፡ በዕቅድ ዘመኑ መጀመርያ ላይ ጨርቃ ጨርቅ አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያስገኛሉ ተብሎ ይታቀዳል፡፡ በተግባር የተገኘው ግን በጣም ትንሽ ነው፡፡ የንዑሳን ዘርፉ ባለቤቶች የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሊጠናቀቅ የወራት ዕድሜ እየቀረው እንኳን፣ ዕቅዱን እናሳካለን በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ውጤቱ ግን ከተጠበቀው በታች ነበር፡፡ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ሲጠናቀቅ ከጨርቃ ጨርቅ ከፍተኛ ገቢ ቢጠበቅም፣ አፈጻጸሙ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች ያነሰ ነበር፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ ይዘት ሲኖረው፣ የመጀመሪያው ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የሚያሳየው በተመሳሳይ ማሽቆልቆልን ነው፡፡ በዘጠኝ ወራት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 508.06 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም፣ የተገኘው ግን 258.58 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የተሳካው የዕቅዱ 51 በመቶ ብቻ ነው፡፡

  ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይፋ ከተደረገ በኋላ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አፈጻጸማቸውን ከዕውነታው ጋር ለማቀራረብ ዕቅዳቸውን መከለሳቸው ቢሰማም፣ ዕቅዶቻቸው የተለጠጡ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ባለማገናዘብ በአካዴሚያዊ መንገድ ብቻ ማቀድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እየከፋ ነው፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ዕቅዶች፣ ሕጎች፣ ወዘተ. በጥንቃቄ ታይተው የማይወጡ ከሆነ ተዓማኒነቱን ያጠፉበታል፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸውን ዕቅዶች መነሻ በማድረግ የሚያቅዱ ኢንቨስተሮች ተግባራዊ መሆን ባልቻሉ ዕቅዶች ምክንያት ብቻ ሥራቸው ስለሚጎዳ በመንግሥት ላይ ያላቸው ዕምነት ይጠፋል፡፡ የዕቅዶች አፈጻጸም ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ ሲሄድ የመንግሥት ተዓማኒነት አብሮ እየወረደ ነው፡፡

  የአገሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች እስካሁን ካጋጠሙ ልምዶች መማር አለመቻላቸውን ዋነኛ ማሳያ እየሆነ ያለው፣ ከዓመት ወደ ዓመት ግቡን አልመታ ያለው የኤክስፖርት ዘርፍ ገቢ ነው፡፡ በየዓመቱ ከፍተኛ የሰው ኃይል፣ የአገር ሀብትና ጊዜ ፈሶባቸው አፈጻጸማቸው የወረደ ዕቅዶችን በአግባቡ ለይቶ መፍትሔ ለማምጣት ከመሞከር ይልቅ፣ ምክንያቶችን በመደርደር እንደ ቀልድ ለማለፍ የሚደረገው ሙከራ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ የኤክስፖርት አፈጻጸም ያሽቆለቆለበት ምክንያት በዓለም ገበያ ዋጋ ማነስ፣ በፍላጎት መቀነስ፣ በጥራትም ሆነ በመጠን አለመጨመርና በሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ቢሳበብም፣ መፍትሔ መፈለግ ግን ዋነኛው የቤት ሥራ ነው፡፡ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ይኼንን ችግር ለማስወገድ ካልተጋ አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ትገባለች፡፡

  በአጠቃላይ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የሚወጡ ዕቅዶች ችግሮች ይስተዋሉባቸዋል፡፡ የአገር ሀብት የሚወጣባቸውን ዕቅዶች በአግባቡ መፈጸም ካልተቻለ ጉዳቱ የአገር ነው፡፡ ዕቅድና አፈጻጸም ካልተጣጣሙ አገር እንዴት ታድጋለች? የዜጎች ሕይወት እንዴት ይለወጣል? የአገሪቱ የንግድ ሚዛን እየተዛባ በቀጠለ መጠን ሸክሙ ሕዝብ ላይ ነው የሚወድቀው፡፡ ዕቅዶች ሲወጡ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ካልታዩ ዕድገትን ማሰብ ይከብዳል፡፡ በተለይ ፖሊሲ አውጪዎች በተደጋጋሚ ከታዩ ተሞክሮዎች ልምድ በመቅሰም መፍትሔ የመፈለግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የግብርና ምርቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ችግሮች በመፍታት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የግድ ነው፡፡ በዘርፉ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች በአግባቡ ከተፈቱ ውጤቱ አመርቂ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመስኩ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችና አመራሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ከመነሻው ለተግባር የማይመች ዕቅድ እያወጡ ችግር ከመፍጠር፣ ከዕውነታው ጋር የሚጣጣምና በባለሙያዎች የሚታገዝ አሠራር ማስፈን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ በመሆኑም ዕቅዶቹ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ካልተጣጣሙ የመንግሥትን ተዓማኒነት ይሸረሽራሉ! አሁንም እየሸረሸሩ ነው!           

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...

  የቅጥፈት እንጀራ!

  የዛሬው ጉዞ ከሲኤምሲ ወደ መገናኛ ነው። በዚህ በከባዱ የኑሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...