Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ተወደደም ተጠላም ሻዕቢያ እንቅስቃሴውን የሚያቆመው የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን ሲያውቅ ነው››

  አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር

  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው 25ኛውን የግንቦት ሃያ አከባበር፣ በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት ተጠልፈው ስለተወሰዱ ሕፃናትና ስላሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ መግለጫውን የተከታተለው ነአምን አሸናፊ በወቅቱ የተነሱትን ጥያቄዎችና ምላሾች እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

  ጥያቄ፡- አይኤስ የተባለው አሸባሪ ድርጅት 16 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ገድያለሁ በማለት አስታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ምን መረጃ አለው? ምንስ እየተሠራ ነው?

  መልስ፡- አሸባሪው አይኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ ዕርምጃ ወስጃለሁ ብሎ መግለጫ እንደሰጠ በመገናኛ ብዙኃን ተከታትለናል፡፡ በጉዳዩ ላይ በሚዲያ ከሰማነው ውጪ ዝርዝር መረጃ የለንም፡፡ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ይሞከራል፡፡ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ የማግኘትና ያለማግኘት አይደለም፡፡ አይኤስ ኢትዮጵያውያንን ገድያለሁ ማለቱ ብቻውን በቂ ነው፡፡ አሳዛኝ ነው፡፡ ከአሁን በፊትም የተፈጸመ ድርጊት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ በአስቀያሚ የሽብር ድርጊት ውስጥ የተሰማራ ድርጅት የፈለገውን ያህል ምክንያት ቢደረደር፣ ሽብር በማንም ዜጋ ላይ ቢፈጸም ሽብር ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጸም ደግሞ የበለጠ ያሳዝነናል፡፡ ስለዚህ የምንከታተለው ነው የሚሆነው፡፡ ያገኘነው መረጃ ምንም ይሁን ግን አይኤስ ኢትዮጵያውያንን ገደልኩ ብሎ መግለጫ ማውጣቱ ብቻውን ለኢትዮጵያውያን ልብን የሚሰብርና እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡

  ስለዚህ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተቻለ መጠን እንዲህ ዓይነቶቹን ጉዞዎች ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር፡፡ መንግሥት አልባ በሆነ በአሸባሪዎች ተፅዕኖ ሥር ያለ አካባቢ ውስጥ ዞሮ ዞሮ እንዲህ ዓይነት ነገር መከሰቱ የማይቀር እንደሆነ ታውቆ የተለየ ጥንቃቄ ቢደረግ፡፡ መንግሥት አሸባሪዎች በየትኛውም አካባቢ በሚፈጽሙት ድርጊት በማንኛውም የሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ድርጊት እንደሆነ ያምናል፡፡ በሽብርና በአሸባሪዎች ላይ በራሳችን መንገድ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ከሌሎች አጋሮቻችንም ጋር ሆነን በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

  ጥያቄ፡- በአገሪቱ እየዘነበ ካለው የበልግ ዝናብ ከፍተኛነት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ነው፡፡ አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የጎርፍ የጉዳት መጠንስ ምን ያህል ነው?

  መልስ፡- መንግሥት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተለይ በስፋት በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎች አሁን ባለው ሁኔታ ለጎርፍ በስፋት የሚጋለጡት እነርሱ ናቸው፡፡ የግድ ዝናብ እዚያ አካባቢ መዝነብ አይጠበቅበትም፡፡ በተለይ በጅግጅጋና በድሬዳዋ ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ከማስጠንቀቂያ በዘለለ ግን በየአካባቢው ሊደረጉ የሚችሉ በርካታ ጥንቃቄዎች መደረግ እንዳለባቸው፣ በተለይ ከተሞች አካባቢ የተደፈኑ የተፋሰስ ጉድጓዶችን ለመክፈት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው፡፡ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ሰው ተንቀሳቅሶ ወደ ተሻሉ አካባቢዎች ሊሄድ የሚችልበት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በተወሰነ ደረጃ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ጎርፍ ከድርቅ የከፋና የቱንም ያህል ዝግጅት ቢደረግ የማይቀሩ አደጋዎች ይኖሩታል፡፡ ከድንገተኛነት ጋር የተያያዘ የሚፈጠር አደጋ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች፣ ከምሥራቁ የአገራችን ክፍል ድሬዳዋና ጅግጅጋ በተጨማሪ አሁን በደቡብ ምሥራቅ አካባቢ ከፍተኛ አደጋ ደርሷል፡፡ በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ በሰው፣ በንብረት፣ በእንስሳትና በማሳ ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡

  መንግሥት በመጀመሪያ ግምት እስከ 500 ሺሕ ሕዝብ ድረስ ሊፈናቀል ይችላል የሚል ግምት ነበረው፡፡ ይህም ግምት በየጊዜው መረጃዎችን በመሰብሰብ የሚከለስ ነው፡፡ አስቀድሞ ከኤልኒኖ ክስተት መዳከም በኋላ የአየር ሁኔታ ተንባዮች እንደሚገልጹት የላኒና ክስተት እንደሚመጣ፣ በተለይ በድርቅ የተጐዱት አካባቢዎች ላይ ደራሽ ጎርፍ እንደሚያስከትል አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ የተፈናቀሉና የተጐዱ ወገኖችን ለመርዳት መንግሥት ዝግጅት አድርጓል፡፡ ግን የቱንም ያህል ዝግጅት ቢደረግ የጎርፉን አቅጣጫና ጎርፍ የሚያጠቃቸውን አካባቢዎች መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ መተንበይ አይቻልም፡፡ በሁሉም ለዚህ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ አካባቢዎች ውስጥ ሕዝቡ፣ የመንግሥት አካላትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው፣ ጉዳቱ ሲከሰት ደግሞ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ የሚሆኑ መሰል ድጋፎች በመንግሥት በኩል በተጠናከረ መንገድ እንደሚሰጥ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በተግባር እየሆነ የለውም ይኸው ነው፡፡

  ነገር ግን አሁን ባለን ግምት ዝናቡ የሚቀጥል ነው፡፡ ስለዚህ ለአደጋዎቹ መዘጋጀት፣ አደጋዎቹ ቢከሰቱ በሰው ሕይወት፣ በእንስሳት እንዲሁም በንብረት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገን እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ ሕዝቡም በዚህ ረገድ ከጀመረው ጠንካራ ርብርብ በተጨማሪ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በዚህም መሠረት ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በተለይ ምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ከበልግ ዝናብ መሻሻል ጋር ተያይዞ በሰብል ተሸፍነው የነበሩ አካባቢዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፡፡ ድርቁን በተወሰነ ደረጃ ተቋቁመን የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ጎርፍ ያመጣውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት የተጐዱ ወገኖችን ለማገዝ የተጀመረው ጥረት በተጠናከረ መንገድ ይቀጥላል፡፡

  ጥያቄ፡- በድርቅ ለተጐዱ ወገኖች በሚገባው የዕርዳታ እህል ምክንያት የጂቡቲ ወደብ መጨናነቁ ይታወቃል፡፡ በወደቡ ዕቃዎችን ቶሎ ባለማንሳት ምክንያት የዲመሬጅ ዋጋም እንዲሁ እየጨመረ ነው፡፡ መንግሥት በእዚህ ላይ ምን እየሠራ ነው?

  መልስ፡- የድርቁን ችግር ለመቋቋም መንግሥት ግዥ ፈጽሞ ያስገባው የዕርዳታ እህል አለ፡፡ እንደተባለው በጂቡቲ ወደብ መጨናነቅ አለ፡፡ የጂቡቲ ወደብ መጨናነቅን ያስከተለው የዕርዳታ እህል ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የዕርዳታ እህል የማምጣታችንን ያህል እያደገ ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያስፈልጉ የካፒታል ዕቃዎች፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እንደዚሁ በስፋት ስለመጡ ነው፡፡ ስለዚህ መጨናነቁ በቅርብ ጊዜ በምንፈልገው ደረጃ ይፈታል ተብሎ አይታመንም፡፡ ነገር ግን የሚያሳስበን የዲመሬጁ ክፍያ አይደለም፡፡ የሚያሳስቡን ዕርዳታው በትክክል በሰዓቱ ባለመድረሱ ምክንያት ሊጐዱ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር የሎጂስቲክስ አቅም ችግሮችን ለመፍታት ከወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡ በኋላ ደግሞ ወደየአካባቢው ለማድረስ ሁሉንም የትራንስፖርት አማራጮች እየተጠቀምን ነው ያለነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ የሚቻለው መከላከያ ካሉት ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹን ለዚህ ሥራ አሰማርቷል፡፡

  ጥያቄ፡- ከጋምቤላ ክልል በሙርሌ ጎሳ አባላት ታፍነው የተወሰዱ ሕፃናትን ለማስመለስ እየተሠራ ያለው ሥራ እንዴት እየተከናወነ ነው? በዘላቂነትስ ምንድነው የሚደረገው?

  መልስ፡- ከደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ግድያ ፈጽመው ሕፃናትን ጠልፈው ወስደዋል፡፡ ጉዳዩ እንደተፈጸመ ይህንን ነገር ዝም ብሎ መተው ስለሌለበት የታጠቀ ኃይል ድንበር ተሻግሮ ገብቶ እንዲህ ዓይነት ግድያ ሲፈጽም፣ ሕፃናትን ሲጠልፍና ንብረት ሲዘርፍ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ተብሎ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ሥራ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በጋራ ማከናወን ታምኖበት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በአስቸኳይ በመነጋገር የእኛ ሠራዊት አካባቢው እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በነገራችን ላይ ሁለት ነገር ነው ማየት ያለብን፡፡ አንደኛ የእኛ መከላከያ ኃይል የገባበት ምክንያት በዚህ ጉዳይ አደጋ ውስጥ የወደቁ ሕፃናትና ከብቶች መመለስ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ተብሎ ስለታመነ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት የፈጸሙ ወገኖች የሚገባቸውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው፡፡

  የመከላከያ ሠራዊታችን በተሠማራባቸው ተልዕኮዎች በሙሉ እንደ ሠፈር ጠበኛ ግጭት ተከስቷል በማለት ግጭቱ በተከሰተበት ዕለት የተገኘውን አሳዶ የሆነ ነገር አድርጌያለሁ ብሎ የሚረካ ተቋም አይደለም፡፡ ባህሪውም እንደዚያ አይደለም፡፡ ዋናው ትኩረት መደረግ የነበረበት ሕፃናቱ በሕይወት የሚመለሱበትን ማመቻቸት ነው፡፡ መተኮስ ችግር የለውም፡፡ አደጋ ያደረሰን ዘራፊ ኃይል ተከታትሎ ባሉን አቅሞች በሙሉ ዕርምጃ መውሰድ ከባድ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችለም፡፡ ዋናው ትኩረት ሕፃናቱ በሕይወት እንዲመለሱ ማመቻቸት ነው፡፡ ሕፃናቱን በሕይወት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተወደደም ተጠላም ድርድር ይጠይቃል፡፡ ለዚህ የሚደረገው ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ማሳተፍ ግዴታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የደቡብ ሱዳንን መንግሥት ማሳተፍ ግዴታ የሚሆነው ሕፃናቱን ለማስመለስ ብቻ አይደለም፡፡ በሰው ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ገብተን ዕርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ይነስም ይብዛ የመንግሥት ይሁንታ ቢኖር ይመረጣል በሚል በዚያ ላይ ተመሥርተን ያደረግነው እንቅስቃሴ አለ፡፡ ስለዚህ ሕፃናቱን በሕይወት ማስመለስ ካለብን ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር መነጋገር አለብን፡፡ በዚህ ምክንያት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ እኛ መጥተው ከእኛ ሠራዊት ጋር አንድ ላይ ሆነው ነው አሁን የድርድሩ ሒደት እየተካሄደ ያለው፡፡ ስለዚህ ይህ ድርድር መቼ ያልቃል የሚለው እንግዲህ ሕፃናቱ እስኪመለሱ ድረስ ይቀጥላል፡፡  ባለን እምነት ሕፃናቱ የሚመለሱበትን ማንኛውንም ዕድል አሟጠን እንጠቀማለን፡፡ የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ መገናኘት ስለሌለባቸው፣ የሕፃናቱን ሕይወት መጠበቅና ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎች የሚገባቸውን ቅጣት ያገኛሉ የሚለው ተለያይቶ መታየት አለበት፡፡

  ለማንኛውም ሁለተኛው የመከላከያ ሠራዊታችንም ሆነ የመንግሥት ትኩረት ወንጀሉን የፈጸሙ ወገኖች የሚገባቸውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው ነው፡፡ ስለዚህ የቅጣቱን ባህሪ እዚህ ሆነን ባንወስነው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም መሬት ላይ ያሉ ሰዎች የሚወስኑትና የሚያደርጉት ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ዋናው ነገር ትኩረት ማድረግ ያለብን ወንጀሉን የፈጸሙት ወገኖች የሚገባቸውን ቅጣት ያገኛሉ፣ ማግኘትም ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ብዥታ ሊኖር አይገባም፡፡ አሁን ዋናው ትኩረታችን ሕፃናቱ በሕይወት የሚመለሱበትን፣ እንዲሁም የተዘረፉ ከብቶች የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ አንደኛው ሌላኛውን አያስቀረውም፡፡

  ጉዳዩን በዘለቄታው ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ለሚለው በጣም ጥቅል የሆነውና የማያጣላው መልስ ልማት በአካባቢው ለሚጠናከርበት፣ አንዱ ለምቶ ሌላኛው ባለማበት ሁኔታ ወይም የልማት ጥያቄዎች በሚገባ ፍጥነት በሁለቱም ወገን ባልተረጋገጡበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት መዘራረፍ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ የተወሰኑ የባህል አላባውያን ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ምናልባት አንዳንድ አካባቢዎች ከብት መዝረፍ እንደ ቁም ነገር የሚቆጠርበት ልማድ ሊኖር ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ከብት መዝረፍ የሰው ሕይወትንም መቅጠፍ ስለሚያስከትል፣ መዝረፍ ብቻውንም ወንጀል ስለሆነ ይኼ ነገር ባህል ስለሆነ ተብሎ መተው ያለበት አይደለም፡፡ ይህ ነገር መቆም መቻል አለበት፡፡ ስለዚህ ቀጣይ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰቦች በጋራ መኖር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል በሚገነዘቡበት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል፡፡     

  ጥያቄ፡- የሻዕቢያ መንግሥት ከድንበር አካባቢ አፍኖ የወሰዳቸው 85 ኢትዮጵያውያንን አስመልክቶ መንግሥት ምን እየሠራ ነው?

  መልስ፡- በሻዕቢያ የታፈኑ ሰማንያ ምናምን ሰዎች ነበሩ፡፡ የተመለሱት 30 ናቸው፡፡ የሻዕቢያ ተላላኪዎች እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጽሙ አስፈቅደው አያደርጉም፡፡ ባለን ግምት ከሄዱት ሰዎች በሕይወት መመለስ የሚችሉት ተመልሰዋል፡፡ ሌሎች የት ገቡ የሚለውን ዝርዝር መረጃ በሒደት የምናየው ይሆናል፡፡ ቁጥሩ እርግጥ 85 ነበረ ወይ የሚለውንም ያው የጠለፉት ሰዎች ናቸው የሚያውቁት፡፡ የተጠለፉትና እንዲመለሱ የተደረጉት ሰዎችም የሚናገሩት በሕይወት የሌሉትን ሰዎች ዝርዝር ነው፡፡ ስለዚህ 85 ነበር 95 ነበር የሚለው አሁን ባለንበት ሁኔታ አካዴሚክ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ወንጀል ሻዕቢያ ተላላኪዎቹን ልኮ ዜጐቻችንን መጥለፉ ነው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ለእንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት ዋጋ መክፈል የግድ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ዋጋውን ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ ወገኖች ብቻ ናቸው ድርጊቱን መፈጸም የሚቀጥሉት፡፡ ከዚህ ውጪ በዚህ ጉዳይ ላይ መናገሩ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ ይህ ነገር ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሙከራዎች ይኖራሉ፡፡ ሙከራዎች ግን ዋጋ እንደሚያስከፍሉ መታወቅ አለበት፡፡ ያንን ዋጋ ለመክፈል እስከተዘጋጀ ድረስ ሻዕቢያ ተላላኪዎቹን መላክ ይችላል፡፡ ለዚህ ነው በደቡብ አቅጣጫ ሌላ ዙር የላከው፡፡ የሰሜኑ ክልል ብዙ አላዋጣውም፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎችም በተደጋጋሚ ባለፉት ሦስት ወራት ሙከራ አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ እንደደረሱ ይገደላሉ፡፡ አንዳንዶቹ እጅ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዳቹ አንድ ሁለት ሦስት ቀናት ተደብቀው ቆይተው እጅ ይሰጣሉ፡፡ ሻዕቢያ ችግር የለበትም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ወታሮች አይደለም እየላከ ያለው፡፡ የሚልከው የተደናበሩ አንዳንዴም የሚገደዱ ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ ስለዚህ በሰው ሀብት ነው ለመጠቀም እየሞከረ ያለው፡፡

  ጥያቄ፡- አሁን ባለው ሁኔታ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችና ክስተቶች ሲያጋጥሙ አደጋው ከደረሰ በኋላ ዕርዳታ እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የመተንበይ አቅማችን ምን ያህል ነው? እዚህ ቦታ ላይ አደጋ ሊከሰት ይችላልና ከአደጋው በፊት የሰዎች ሕይወት እንዳይጠፋ ለማድረግ መንግሥት ምን ዓይነት ሥራዎች እየሠራ ነው? በሌላ በኩል ደግሞ ጎረቤት አገሮች ተመሳሳይ አደጋዎችን ሲያደርሱ የእኛን ሉዓላዊነት በመድፈር ነው፡፡ እኛ ደግሞ የእነሱን ሉዓላዊነት በመጠበቅ ወደ ድርድር እየገባን ነው፡፡ በተለይ ከሙርሌ ጎሳ የሕፃናቱን ጠልፎ መውሰድ አንፃር በዚህ ሁኔታ የዜጐች ዋስትና ምንድነው?

  መልስ፡- የመተንበይ አቅም ምን ያህል ነው ለሚለው የሚተነብየው የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ነው፡፡ አሁን የሚቲዮሮሎጂ የመተንበይ አቅም ከአሁን በፊት ካለው በጣም የተሻለ ነው ብለን እናምናለን፡፡ እስካሁን ባለን ግምት ባለፉት ሦስት ወራት ይህንን ክስተት በሚመለከት በሚቲዮሮሎጂ እስካሁን የተሰጡት ትንበያዎች ከሞላ ጎደል የተሳኩ ናቸው፡፡ መተንበይ አንድ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ድሬዳዋ በጎርፍ ሊጠቃ እንደሚችል ትንበያ ሊኖር ይችላል፡፡ በጎርፍ ሊጐዱ የሚችሉ ቤቶች እነዚህ እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ሊተነበይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከተማ ውስጥ ውኃ ከገባ በኋላ እነማን የሚባሉ ሰዎችን ለአደጋ ያጋልጣል የሚለውን መተንበይ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የመተንበይ አቅም የራሱ ውስንነት አለው፡፡ ተንብየህ ስታበቃ ደግሞ የምትወስደው ዕርምጃም የዚያኑ ያህል እንደአቅሙ ውስንነት ይኖረዋል፡፡ አሁን በእርግጥ ምን ተንብየን ምን ደረሰ የሚለው አይደለም ጉዳዩ፡፡ ማስቀረት ስንችል ያልቀሩ አደጋዎች ካሉ ወደ እዚያ ነው መሄድ ያለብን፡፡

  እስካሁን ባለን መረጃ ማስቀረት ስንችል ያልቀሩ አደጋዎች አሉ ብለን አናምንም፡፡ ግን ባይሆኑ የምንመርጣቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ተተንብዮ ደረጃውን መረዳት የማይቻልበት ክስተት አጋጥሟል፡፡ ለምሳሌ የመሬት መደርመስ የተከሰተባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ እንደ ጎርፍ ዓይነቱ አደጋ በተለይም በእንደ እኛ ዓይነቱ ምላሽ የመስጠት አቅሙ ውስን በሆነ አገር ተንብየነውም ቢሆን የምንወስደው ነገር በራሱ በጣም ውስን ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ትኩረት ማድረግ የሚኖርብን በእኛ ጥረት መቅረት ያለባቸውን አደጋዎች እያስቀረን ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት የተቻለውን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በተደጋጋሚ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ ላይ ተመሥርተን ችግሩ ወደ ተባባሰ ደረጃ እንዳይሄድ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ችግሩ በደረሰባቸው አካባቢዎች ደግሞ አስፈላጊው ዕርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ በማመቻቸት ደግሞ መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሞላ ጎደል መልካም ሊባል የሚችል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

  እንግዲህ ሉዓላዊነት መድፈር የሚል ነገር አለ፡፡ የሙርሌ ታጣቂዎች ከብቶች ዘርፈው በሌሊት ሲሄዱ የአካባቢው የመረጃ ልውውጥ እንደሚያሳየው፣ ይህ ድርጊት በተደጋጋሚ የሚፈጸም ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል ያስፈልገናል የሚለው የመጣው ቁጥሩ ትልቅ መሆኑ ከታወቀ በኋላ ነው፡፡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው ስለገቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወዳጅ አገርን ድንበር በራስ ፍላጐት ዘልቆ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ይኼ የመንደር ልጆች ጠብ አይደለም፡፡ ተከትየው ሄጄ ሠፈር ውስጥ ብገባ ምን አገባው የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ሕግ የሚያከብር መንግሥት ነው ያለን፡፡ ዜጐቻችንን መከላከል አለብን ትክክል ነው፡፡ ዜጐቻችን ላይ ይኼ ነገር ደርሶ ግን ቢያንስ ማስታወቅ ነበረብን፡፡ አስታውቀን ነው የገባነው፡፡

  ስለሆነም እዚያ ከገባን በኋላ የት ቦታ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በሕፃናቱ ፈርደን መድፎች፣ ታንኮች አሉን፡፡ ከአየር እሳት የሚያዘንብ ኃይልም አለን፡፡ ነገር ግን እርሱ አይደለም ነገሩ፡፡ ከግል ስሜት በፀዳ መልኩ ነገሩን ማየት መቻል አለብን፡፡ የሉዓላዊነት መደፈር የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ ዝም ብሎ በዚህ መልኩ መረዳት ትንሽ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ዝርዝር ነገር ውስጥም ባንገባ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ሕፃናቱን ማስመለስ አለብኝ የሚል ኃይል ሕፃናቱ በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ መሆን መቻል አለበት፡፡ ሕፃናቱ በሕይወት መመለስ አለባቸው፡፡ ስለዚህ በስሜታዊነት ሳይሆን ዕርምጃ የሚወሰደው፣ ኃይል ካለ ዕርምጃ ይወሰድበታል፡፡ ግን ይህ ሠራዊት በኑዌሮችና በአኝዋኮች ላይ ጥቃት ስለተፈጸመ በሙርሌና በሹልኮች ላይ ጥቃት አይፈጽምም፡፡ በሕዝብ ላይ የደረሰን ጥፋት ሌላ ሕዝብ በማጥቃት ሊካስ አይችልም፡፡ ስለዚህ ዕርምጃ መወሰድ ካለበት ይህ ድርጊት በፍፁም በማይደገምበት፣ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የመጣውን ኃይል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ ተልዕኮዎችን ያሰቡ ወገኖች ጭምር ትምህርት ሊያገኙ በሚችሉበት መንገድ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

  ጥያቄ፡- በትግራይ ክልል በሻዕቢያ አማካይነት ኢትዮጵያውያን ታፍነው መወሰዳቸው ይታወቃል፡፡ የተወሰኑት ተመልሰዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል ከሻዕቢያ ተልከው የመጡ ግለሰቦችን የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል፡፡ አሁንም እንደገለጹት ሻዕቢያ ከዚህ ተግባሩ ላይቆጠብ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሉ ተናግረዋልና እስከ መቼ ነው እንደዚህ እያለ የሚቀጥለው? መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ የመውሰድ ዕቅድ አለው ወይ?

  መልስ፡- ሻዕቢያ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች የሚቆሙት መቼ ነው ለሚለው ሻዕቢያ ሲቆም ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ተመጣጣኝ ዕርምጃዎች ጠረጴዛ ላይ አሉ፡፡ መንግሥት ይህንን መደጋገም ያለበት አይመስለኝም፡፡ በየጊዜው ችግሩ በተከሰቱ ቁጥር ይህን ያህል ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስደን እየተባለ ሒሳብ ማወራረድ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ተወደደም ተጠላም ሻዕቢያ ይህን እንቅስቃሴውን የሚያቆመው የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ መሆኑን ሲያውቅ ነው፡፡ ያ ከባድ ዋጋ ሲሆን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ያ ከባድ ዋጋ ከገፋበት በምን ይገለጻል የሚለው በሒደት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ግን መንግሥት ለተተኮሰ ጥይት በሙሉ ተመሳሳይ ወይም እጥፍ ጥይት በመተኮስ ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ግን ዜጐቻችንን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን በሙሉ መሥራት ይቀጥላል፡፡  

  ጥያቄ፡- በክረምቱ የዘር አቅርቦት እንዴት ነው የሚሆነው? 1.7 ሚሊዮን ያህል ገበሬዎች የሚዘሩት የላቸውም የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ ነውና የዘር አቅርቦቱ ምን ይመስላል?

  መልስ፡- ከዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ መንግሥት ማዳበሪያና ዘር የማቅረብ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ነው፡፡ ምክንያቱም የዘንድሮው የዝናብ ወቅት እንዲያመልጠን አይጠበቅም፡፡ በብዙ አካባቢዎች ዘሩን ያጣ ብዙ ገበሬ አለ፡፡ ዘሩንም የበላ ገበሬ አለ፡፡ አንድ ገበሬ ዘሩን ለመብላት ሲገደድ የችግሩን ሥር መስደድ ነው የሚያሳየው፡፡ ግን ይህ ነገር በስፋት እንዳይከሰት የሚቻለው ጥረት ሁሉ ተደርጓል፡፡ አሁን ግን የበልግ አብቃይ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሚታየው ዝናብ ጥሩ ሰዓት ላይ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ ይህ ወቅት እንዳያልፍ በስፋት ዘር የማስገባት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህ ይቀጥላል፡፡ በሚቀጥለው ክረምት መደበኛና ከመደበኛ ከላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ነው ትንበያው የሚገልጸው፡፡ ስለዚህ የክረምቱ ሁኔታ ጥሩ ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ ነገር ግን ላሊና የሚባለው ክስተት ደግሞ ራሱን የቻለ ችግር ያስከትላል፡፡ በተለይ እንደተመለከትነው ደራሽ ጎርፍ በርካታ በድርቁ ተጠቅተው የነበሩ አካባቢዎችን ጨምሮ ሊያጠቃ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ግድቦች ሞልተዋል፡፡ ከሞላ ጐደል የውኃ አቅርቦት በተለይ ለእንስሳት ተቃሏል፡፡

  ጥያቄ፡- የስኳር ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ነገር አለ፡፡ ፕሮጀክቶቹ አሳሳቢ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

  መልስ፡- የስኳር ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ብዙዎቹ የስኳር ፕሮጀክቶች መጓተታቸው ይታመናል፡፡ የተጓተቱ አሉ፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ መግለጫዎች ሲሰጥባቸው ቆይቷል፡፡ አንዳንዶቹ አካባቢዎች ላይ እርግጥ አሳሳቢ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ አሁን ጥፋቱ የእገሌ ነው የእገሌ ነው የሚል ነገር ውስጥ የመግባት አዝማሚያን ብናስወግድ ጥሩ ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ፕሮጀክቶች ሲጀምር ታሳቢ ያደረጋቸው በርካታ ቁም ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዚያ ቁም ነገሮች አሁንም እንዳሉ ነው፡፡ ግን ፕሮጀክቶቹ በተለይ ሜጋ ፕሮጀክቶች በባህሪያቸው ዋጋ የመጨመርና የመዘግየት ነገር እንዳላቸው መናገር ይቻላል፡፡ ባህሪያቸው እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈቅዳል ስለተባለ ብቻ ደግሞ ያላግባብ ሲዘገዩ ይቅርታ መደረግ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ፓርላማው በትክክል እንዳስቀመጠው እነዚህ ነገሮች በአስቸኳይ ታርመው፣ በተለይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ መግባት የሚገባቸው ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ መካሰሱ የትም የሚያደርሰን አይሆንም፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚካሰሱት የመንግሥት ተቋማት ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ምክንያቱን ውጫዊ ለማድረግ የሞከረ አካል የለም፡፡ አሁን በመካሰስ ላይ ያሉት የመንግሥት ተቋማት ቤታቸውን አፅድተው ሙሉ ትኩረታቸውን ሥራውን ለማጠናቀቅ ማዋል እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ በዚህ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃም እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ የተወሰኑት ወደ ሥራ ለመግባት በጣም ጥቂት ጊዜ የቀራቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሚፈለገው በታች የተጓተቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት በሕዝብ ዘንድ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ መረዳት ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡ ከምንም በላይ ግን ብዙ የአገር ሀብት ነው ታጭቆ ያለው፡፡ በመሆኑም ይህንን በአስቸኳይ የማፅዳት የመንግሥት ሥራ ስለሆነ መንግሥት ይሠራል፡፡ እንግዲህ ውጤቱ ከሞላ ጐደል ጥሩ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡    

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

  ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ የግል ትምህርት...

  ከሱር ታክስ ነፃ የተደረጉ ምርቶች የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተጣለባቸው

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ያሉ አገሮችን ጫና የምትቋቋመው የማይቋረጥ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው›› ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ...

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ በጃፓን ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአፍሪካና በእስያ ጥናት ትምህርት...

  ‹‹ባንኮች በየዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘን ነው እያሉ ከሚከፋፈሉ ካፒታል ማሳደግ ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው›› አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር

  በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ምጣኔ እያደገ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የውስጥና የውጭ ችግሮች አሉ በሚባልባቸው ጊዜያት ሁሉ...

  ‹‹ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ይህች አገር አሁን በምናያት መንገድ አትኖርም›› ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሊቀመንበር

  ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢዜማ ምርጫም የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ጥናቶችን በማበርከት የሚታወቁም ሲሆን፣ በተለይ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ...