Sunday, August 14, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ዓቃቤ ሕግ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ ምስክሮቹን ማሰማት ጀመረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖራቸው ቼክ ማውጣት (መጻፍ) ወንጀል ክስ በመሠረተባቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ ግንቦት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ምስክሮቹን ማሰማት ጀመረ፡፡

  ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል በሚል ከቆጠራቸው ስምንት ምስክሮች መካከል አራቱን ያቀረበ ቢሆንም፣ ሦስቱን አሰምቶ አንደኛውን እንደማይፈልጋቸው ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ አሰናብቶ ለቀሪዎቹ ምስክሮች ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

  የአቶ ኤርሚያስን ክስ እየመረመረው በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መጀመርያ ቀርበው ምስክርነታቸውን ያሰሙት፣ አሜሪካ የሚኖሩ ወንድማቸው ውክልና ሰጥተዋቸው ለሁለት ቤቶች በድምሩ ሦስት ሚሊዮን ብር መክፈላቸውን የገለጹ ግለሰብ ናቸው፡፡

  ምስክሩ በ18 ወራት ገንብቶ ማስረከብ እንደሚጀምር አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር በገባው ቃል መሠረት፣ ወንድማቸው ከማኅበሩ ጋር ውል እንዲዋዋሉና ክፍያ እንዲፈጽሙ ነግረዋቸው መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡

  በውሉ መሠረት ሊፈጸምላቸው ባለመቻሉ ወደ አክሰስ ሪል ስቴት በመመላለስ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ፣ ከነወለዱ የአንደኛውን አፓርትማ ክፍያ እንደመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡

  የአቶ ኤርሚያስ ፊርማ ያረፈበት የ500 ሺሕ ብር ቼክ ተጽፎላቸው እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 4 ቀን 2012 ማውጣት እንደሚችሉ በተነገራቸው መሠረት ቢመላለሱም ገንዘባቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ የተናገሩት ምስክሩ፣ እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 13 ቀን 2013 እንዳስመቱበት ተናግረዋል፡፡ ወንድማቸው ሠርተውት የነበረን ቤት ሸጠው ሁለት አፓርታማዎች እንዲገዙላቸው ያደረጉት አንዱን እየኖሩበት ሌላውን አከራይተው ለመጠቀም በማሰብ እንደበር ገልጸዋል፡፡

  የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች አቶ ሞላ ዘገዬና አቶ መኮንን አራጋው ምስክሩ ውል የፈጸሙት ከማን ጋር እንደሆነ ሲጠይቋቸው፣ ከአክሰስ ሪል ስቴት ጋር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቼኩንም የተቀበሉት ከማኅበሩ ፋይናንስ ኃላፊ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሕጋዊ ሙሉ ውክልና ስላላቸው ቼክ የመቀበልም መብት እንደተሰጣቸውም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ሌላው ሁለተኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ከአቶ ኤርሚያስ ጋር ከ18 ዓመታት በላይ ከሃይላንድ ውኃ ጀምሮ አብረው መሥራታቸውን የገለጹት፣ በአክሰስ ካፒታል ኩባንያ ውስጥ የሚሠሩ ግለሰብ ናቸው፡፡

  ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ አገር ውስጥ ገቢ አክሰስ ሪል ስቴትን ገንዘብ እንደጠየቀው፣ ነገር ግን 500 ሺሕ ብር ስለጎደለው መክፈል ባለመቻሉ የድርጅቱን ጠቃሚ የሆነ ንብረት ሊወስድበት እንደሆነ ነግረዋቸው 500 ሺሕ ብር እንዲሰጧቸው ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ 500 ሺሕ ብር ሲሰጧቸው የ500 ሺሕ ብር ቼክ እንደሰጧቸውና ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ማውጣት እንደሚችሉ አቶ ኤርሚያስ የነገሯቸው ቢሆንም፣ ቼኩን ለመመንዘር ወደ ዘመን ባንክ ሲሄዱ በቂ ገንዘብ እንደሌለ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ መጋቢት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. አቶ ኤርሚያስ ከአገር መውጣታቸውን በማወቃቸው አስመትተውበት ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ለጠበቃቸው መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ ቼኩን የጻፈላቸው የማኅበሩ ፋይናንስ ኃላፊ መሆኑንና ፊርማው ግን የአቶ ኤርሚያስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች ምስክሩ ገንዘቡን ከየት አምጥተው እንደከፈሉ ሲጠይቋቸው፣ ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቼኩን የሰጣቸው የፋይናንስ ክፍሉ በመሆኑ ምክንያት እንዴት ሊሆን እንደቻለ ተጠይቀው፣ አቶ ኤርሚያስ ወደ ውጭ አገር ስለሚሄዱ አንድ ሙሉ ፓድ ቼክ ፈርመው ለፋይናንስ ይሰጡና ፋይናንስ ለሚመለከተው ወጪ እየጻፈ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ ሁለት የሙያ ምስክሮችን ከዘመን ባንክ ያቀረበ ሲሆን፣ ቼክን በሚመለከት ሙያዊ ማብራሪያ የሚሰጡ መሆኑን ጭብጥ አስይዞ የመጀመርያው ባለሙያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

  ሁሉንም ንግድ ባንኮች የሚያስተዳድርና የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሆኑን ጠቁመው ቼክ የሚይዝ ደንበኛ ቼኩን በአግባቡ መያዝ እንዳለበት፣ በቂ ገንዘብ በባንክ ከሌለው ቼክ መጻፍ እንደሌለበት በመመርያ መደንጋጉን አስረድተዋል፡፡ አንድ ደንበኛ በቂ ገንዘብ በባንክ ሳይኖረው ቼክ ከጻፈ ባንኩ የመጀመርያ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደሚጽፍለት፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከጻፈ በጻፈው ገንዘብ መጠን የአምስት በመቶ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጥልበትና ለሦስተኛ ጊዜ ከጻፈ በባንኩ የከፈተውን ሒሳብ እንደሚዘጋው በመመርያው መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

  አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር የዘመን ባንክ ደንበኛ መሆኑን ያስረዱት ባለሙያው፣ ከባንኩ ጋር ያለው ደንበኝነት መሰረዙን አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሦስት ደንበኞች እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 15 ቀን 2013 ማኅበሩ በባንኩ ካለው የገንዘብ መጠን በላይ የያዙ ቼኮችን ይዘው በመምጣታቸው ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመርያ ባይከተልም ሦስት ቼኮች በአንድ ጊዜ በመምጣታቸው ሊዘጋ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

  በባንክ ደንበኛ ሒሳብ ውስጥ በቂ ስንቅ የለም ማለትና ሒሳቡ ተዘግቷል ማለት ልዩነት እንዳለውና እንደሌለው እንዲያስረዱ የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ምስክሩ፣ ‹‹ልዩነት አለው›› በማለት ጀምረዋል፡፡

  አንድ የባንክ ደንበኛ በተለያየ ምክንያት ሒሳቡን ሊዘጋ እንደሚችል ጠቁመው፣ በቂ ስንቅ የለውም የሚባለው ግን ደንበኛው በባንክ ያስቀመጠው ገንዘብ በቼክ እንዲመነዘር ለሰጠው ደንበኛው ከጻፈው ገንዘብ አንሶ መገኘት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  በቂ ስንቅ ሳይኖር ተጻፉ የተባሉት ቼኮች ሒሳቡ ከመዘጋቱ በፊት ስለመሆኑ የተጠየቁት ባለሙያው፣ ቼክ በቀኑ ወይም የመክፈያ ጊዜውን ወደፊት አድርጎ የሚጻፍ ቢሆንም፣ የመክፈያ ጊዜው ሳይደርስ ግን ሒሳቡ ሊዘጋ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ሒሳብ ከመዘጋቱ በፊት ገንዘብ ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ ተጠይቀው፣ ምክንያቱን ባያውቁትም በፍርድ ቤት የታገደ 1.6 ሚሊዮን ብር እንደነበረው ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ገንዘቡ የእከሌ ነው ብሎ እስካልገለጸ ወይም እስካላዘዘ ድረስ የዚህ አካል ነው ማለት ስለማይቻል ብሩ እንደታገደ መሆኑን አክለዋል፡፡

  ዓቃቤ ሕግ ሌላው የሙያ ምስክር ተመሳሳይ ነገር ላይ እንደሚመሰክሩ በመግለጽ እንደማይፈልጓቸው ለፍርድ ቤቱ በማሳወቅ ትቷቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሌሎች ምስክሮችን ፖሊስ በስልክ ሳይሆን መጥሪያ በማድረስ እንዲጠራ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች