Monday, August 15, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የስኳር ፕሮጀክቶች ለገጠማቸው ፈተና የመንግሥት ማብራሪያ ይጠበቃል!

  ሰሞኑን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ ተስፋ በመቁረጥና ሕመም እየተሰማቸው ሪፖርት ማቅረባቸውን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት ተጠቃሽ ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው ዕቅድ መሠረት 77 ቢሊዮን ብር በማንቀሳቀስ አሥር የስኳር ፋብሪካዎችን ገንብቶ ሥራ ለማስጀመር ለስድስት ዓመታት ቢውተረተርም እየተሰማ ያለው ግን አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰበት ይህ የልማት ዘርፍ አንድ ፋብሪካ ሥራ ማስጀመር ተስኖት፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ዕዳ የመክፈል አደጋ ጋር ተፋጧል፡፡ በአገሪቱ የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው የስኳር ፕሮጀክቶች እንዲህ ዓይነት ፈተና ውስጥ ሲወድቁ፣ ሕዝብ የመንግሥትን ፈጣን ምላሽ ይጠብቃል፡፡

  መንግሥት የአገርን አጠቃላይ ጉዳዮች እንዲመራ በሕዝብ የተሾመ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ በየትም አገር ቢሆን የአገርን ውሎና አዳር የማስታወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ከኃላፊነቶቹ መካከል የአገርን ፀጥታ ማረጋገጥ፣ የሕዝቡን ማኅበራዊ ደኅንነት መጠበቅ፣ የአገር ኢኮኖሚን በአግባቡ መምራት፣ ሕግ ማስከበርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ከተሰጣቸው የልማት ውጥኖች መካከል የስኳር ልማት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ፣ ከሞላ ጎደል ተጠናቀው ሥራ መጀመር የነበረባቸው ፋብሪካዎች አፈጻጸማቸው ተስፋ አስቆራጭ ነው ሲባል ያስደነግጣል፡፡

  አገሪቱ ለስኳር ልማት ባላት ምቹነት ምክንያት አሥር አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት፣ በዓመት ከ4.07 ሚሊዮን ቶን በላይ ስኳር አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የተለጠጠ ዕቅድ በመከለስ ሰባት ፋብሪካዎችን ለማጠናቀቅ ሥራ ለማስጀመር ቢታሰብም፣ ፕሮጀክቶቹ ሳይጠናቀቁ በውጭ ምንዛሪ ዕዳ የሚከፈልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ የችግሩን ሥረ መሠረት ለሕዝብ የማስረዳት ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡

  መንግሥት የኢኮኖሚው ዕድገት ጤናማ ሆኖ ወደፊት እንዲራመድ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝብን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን ማበረታታት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በአግባቡ መያዝ፣ የክፍያ ሚዛን ጉድለትን መቀልበስና በከፍተኛ ደረጃ ሥራ መፍጠርን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም ያግዛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት አሠራር በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች የተገለጹትን ችግሮች ስንመረምር ግን የአሠራሮች ግልጽ አለመሆን፣ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መጓደሎች በግልጽ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ግልጽነት የጎደላቸው አሠራሮች ደግሞ የአገር ሀብት እያወደሙና ሕዝብን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየከተቱ በመሆናቸው የመንግሥት ማብራሪያ የግድ ይላል፡፡

  በስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች በቀረበው ማብራሪያ መሠረት፣ የስኳር ፋብሪካዎቹን ግንባታ እንዲያከናውን ስምምነት የፈጸመው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በተባለው ጊዜ ካለማጠናቀቁም በላይ፣ የሥራ አፈጻጸሙና የሚፈጸምለት ክፍያ ግን ፈጽሞ የማይደራረሱ ናቸው፡፡ ይህ ከአገሪቱ የግዥና የጨረታ ሕግ ጋር የሚጣረስ ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስምምነቶች ላይ የውል ማሻሻያዎች እየተደረጉ የአፈጻጸም ጊዜ ቢራዘምም፣ የፋብሪካዎቹ ግንባታ እንደተጓተተ በሪፖርቱ በአኃዞች ተደግፎ ቀርቧል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የአገሪቱን የግዥና የኮንትራት ሕግ የሚጥስ ተግባር ሲፈጸም መንግሥት የት ነው ያለው? ሃያ ሦስት በመቶ ግንባታ ለተፈጸመለት የስኳር ፋብሪካ 94 በመቶ ክፍያ የሚፈጸመው በየትኛው ሕግ ነው? የስኳር ኮርፖሬሽን ከአገር ውስጥና ከውጭ 77 ቢሊዮን ብር ተበድሯል፡፡ አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ሳይገባ ከሚቀጥለው በጀት ዓመት (ሐምሌ) ጀምሮ 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈተና በአገሪቱ ላይ ተጋርጦ ተጠያቂው ማነው? መንግሥት ወጣ ብሎ ለሕዝቡ ይንገር፡፡

  ሜቴክ በእጁ ከነበሩት አሥር ፋብሪካዎች መካከል ሰባቱ ተወስደው ለሌሎች ገንዘብ ይዘው ለመጡ ኮንትራክተሮች ተሰጥተዋል፡፡ አሁን በእጅ የቀሩት ሦስቱ ፋብሪካዎች ግንባታ መቼ እንደሚጠናቀቅ እንማይታወቅ ተገልጿል፡፡ ሌላው በጣም የሚያስገርመው ጉዳይ፣ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ከሜቴክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቢዝነስ ኮንትራት ሕግ የማይመራ መሆኑን መግለጻቸው ነው፡፡ ይህ ማለት የተደረጉት ስምምነቶች በውል ያልታሰሩና ልቅ ናቸው ማለት ነው፡፡ በሜቴክ ላይ እንደማንኛውም የቢዝነስ ድርጅት ቅጣት መጣል እንደማይቻል ይታወቃል መባሉ ደግሞ ይደንቃል፡፡ ሜቴክ እንደማንኛውም በሕግ የተቋቋመ ድርጅት በአገሪቱ ሕግ አይመራም ነው? ወይስ የማይታወቅ ሌላ ችግር አለ? በስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች የተለያዩ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ የአገሪቱን ሕጎች ለማስከበርና የሕዝብን ሀብት ለመጠበቅ ባለበት ኃላፊነት ችግሮቹን ማጣራትና ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

  ስኳር ኮርፖሬሽን እንደ ማንኛውም መንግሥታዊ የልማት ድርጅት የራሱ ችግሮች ይኖሩበታል፡፡ ውስጣዊ ችግሮቹን ከማፅዳት በተጨማሪ በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት አገርን ዋጋ የሚያስከፍል ፈተና ሲገጥመው ግን ሊታደገው የሚገባው መንግሥት ነው፡፡ ‹‹… የማይችሉትን ሁሉ እንችላለን እያሉ አገርን ዋጋ እያስከፈሉ ነው …. እንቢ ብለን እንኳን እንዳንታገል አመራሮች ያሸማቅቁናል …›› እየተባለ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ሲደረግለት፣ ጉዳዩ ከአገር ህልውናና ከሕግ ማስከበር ጋር የተያያዘ መሆኑን አውቆ መነሳት የመንግሥት ኃላፊነት መሆን ሲገባው፣ ጣት ከመቀሳሰር ይልቅ መፍትሔ ላይ ማተኮር ይሻላል ማለት አይቻልም፡፡ አሁን ግልጽ የተደረገው ችግር ከአገር ሀብት ውድመትና ከሕዝብ ህልውና ጋር ጭምር የተያያዘ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት ኃላፊነቱን ያጓደለ ወገን በሕግ ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ከሕግ በላይ መሆን አይቻልምና፡፡ መንግሥት ሕግ ያስከብር፡፡

  የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጎድል ተጠያቂ ይሆናል፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ማንሳት እንደሚችልና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን ያስረዳል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው አስታውቋል፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራትና ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው በአንቀጽ 9 ላይ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት አገሪቷን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕግ እያከበረና እያስከበረ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን ለገጠመው ፈተና በምክንያትነት የተጠቀሰው ሜቴክም ስለተፈጠረው ችግር ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ስለገጠመው ፈተና ለሕዝብ በግልጽ የማብራራት ኃላፊነት ግን አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ነው!     

      

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...