Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናሰሞኑን በተቀሰቀሱ ግጭቶች በኢንቨስተሮች የቡና ማሳዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

  ሰሞኑን በተቀሰቀሱ ግጭቶች በኢንቨስተሮች የቡና ማሳዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

  ቀን:

  ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ በሚገኙ ግጭቶች የሰው ሕይወት በአሰቃቂ መንገድ እየጠፋ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ትልቁን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገባው ቡና በከፍተኛ ደረጃ ሰለባ ሆኗል፡፡

  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በተለይ በደቡብ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በደቦ በሚንቀሳቀሱ ወጣቶች የበርካታ ኢንቨስተሮች ቡና ማሳዎች መውደማቸው ታውቋል፡፡

  ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ቤአኤካ፣ አፍሮ ጽዮንና ኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናል ተጠቃሽ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

  ቤአኤክ ቢዝነስ ግሩፕ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን 2‚700 ሔክታር መሬት ተረክቦ ቡና በማልማት ላይ ነው፡፡ ኩባንያው ዘመናዊ የቡና ማሳዎች ማዘጋጀቱንና የቡና ማጣሪያ ጣቢያ መገንባቱ፣ እንዲሁም 26 ኪሎ ሜትር መንገድ መሥራቱን ይናገራል፡፡ የኩባንያው ባለቤት አቶ ምሥጋና ካሳሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሰሞኑን ከየት እንደመጡ ያልታወቁ ወጣቶች አሥር ሔክታር መሬት ላይ የለማ ቡና ጨፍጭፈውባቸዋል፡፡

  ‹‹የቡና ማጣሪያው ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለት ስለነበረ ተርፏል፡፡ ማሳውን ያወደሙት የአካባቢው ሰዎች ሳይሆኑ ከሌላ ቦታ የመጡ ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

   የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል በኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚታወቀው አፍሮ ጽዮን ኩባንያ ተጠቃሽ ነው፡፡ አፍሮ ጽዮን ኩባንያ የሸካ ዞን አጎራባች በሆነው ጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ አካባቢ ካለማው መሬት ውስጥ 130 ሔክታር የሚሆነውን የአካባቢው ወጣቶች የእኛ ነው በማለት ወረው እንደያዙት አስታውቋል፡፡

  የአፍሮ ጽዮን ኩባንያ ባለቤት አቶ ሲሳይ ደስታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ያለሙትን የቡና ማሳ ወጣቶች በኃይል የእኛ ነው በሚል ይዘውታል፡፡

  ‹‹ለጋምቤላ ክልል መንግሥት ጉዳዩን አመልክተናል፡፡ ክልሉ ጉዳዩን የሚያጠና ቡድን እየላከ ነው፤›› በማለት አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

  ሌላው የተፈጠረው ችግር ተጠቂ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ማሳ ነው፡፡ ሻለቃ ኃይሌ በሸካ ዞን አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ቡና ያለማ መሆኑን፣ ከቡና ምርት ጎን ለጎንም ማር በማምረት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ቡና ኢንቨስትመንት የገባው ሻለቃ ኃይሌ፣ 18 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱንና  አስቸጋሪውን የኢንቨስትመንት ጊዜ አልፎ ቡና ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን አስረድቷል፡፡

  ነገር ግን ሰሞኑን በተነሳው ችግር የኃይሌ ኢንቨስትመንት በተለይም ማሻ ከተማ የሚገኘው ንብረት የተሰባበረበት መሆኑንና 600 ሠራተኞች እንደተበተኑበት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

  ሻለቃ ኃይሌ እንደሚለው፣ 270 ሠራተኞችን ከአካባቢው ማስወጣት አስቸጋሪ ሆኖበታል፡፡

  ‹‹እኔ የማጣው ገንዘብ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሕይወት ግን አደጋ ውስጥ ይገኛል፤›› ሲል የገለጸው ኃይሌ፣ ‹‹አንድ ኢንቨስትመንት ለአካባቢው ማኅበረሰብ መጥቀም ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር እንደመሆኑ ወጣቶች ረጋ ብለው ማሰብ አለባቸው፤›› በማለት ጥሪውን ለወጣቶች አስተላልፏል፡፡

  ለማሳያ ከቀረቡት ከእነዚህ ኢንቨስተሮች በተጨማሪ በሌሎችም አካባቢዎች እየደረሱ ያሉት ችግሮች ያሳሰባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የቡና ዘርፍ ዋና ተሳታፊዎችን ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ሰብስበው አነጋግረዋል፡፡

  ስብሰባው ላይ የተገኙ የቡና ኢንቨስተሮች እንደገለጹት፣ እያጋጠሙ ባሉ ግጭቶች ሥራ መሥራት እንዳልቻሉና ንብረትም እየወደመ  መሆኑን በመግለጽ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሰጡት ምላሽም ሰላምና ፀጥታን በሚመለከት መንግሥት የሚያከናውነው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢንቨስተሮችም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

  ‹‹ኢንቨስትመንቱ በብዙ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ተሰራጭቶ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ፖሊሲ ማውጣት አይቻልም፡፡ መንግሥት መከላከል አለበት፡፡ እናንተ ኢንቨስተሮችም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ችግሩን መፍታት አለባችሁ፤››  ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  ግጭቱ የተነሳው በሾካ ዞን በሚገኙ ሦስት ከተሞች ነው፡፡ እነሱም በማሻ ወረዳ ማሻ ከተማ፣ በአንደራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማና በየኪ ወረዳ ቴፒ ከተማ ነው፡፡

  የችግሩ መነሻ ከዚህ ቀደም የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. የከፋ ዞንና የቤንች ማጂ ዞን፣ የሸካ ዞን ነዋሪዎችን አነጋግረው ከተመለሱ በኃላ ነው፡፡

  በወቅቱ በተካሄደው ስብሰባ የሸካ ብሔረሰቦች አባላት ‹‹ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ዘላፊዎች ከተሰብሳቢዎች ደርሰውብናል፣ የመልካም አስተዳደር ችግር አለብን፣ መሠረተ ልማት አልተሟላልንም፤›› የሚሉ ጥያቄዎችን አሰምተዋል፡፡

  ከዚህ በኋላ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ መንገድ ተዘግቷል፣ በሰው ላይም ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡ በዚሁ ችግር የተነሳ ኢንቨስትመንቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...