Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  መቋጫ አልባው የመደብና የብሔር ጥያቄ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ‹‹የብሔርና የመደብ ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

  በመድረኩ ሦስት ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ጽሑፎቹ ከቀረቡ በኋላ ደግሞ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ምንም እንኳን የአገሪቱ መሠረታዊና ማዕከላዊ የፖለቲካ ሒደትና አወቃቀር ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ቢሆንም፣ በዕለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች ቁጥር ግን በእጅጉ አነስተኛ ነበር፡፡

  ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መሠረታዊ ጉዳይ ሆነው በመጉላት እስካሁን ድረስ ሁነኛ መፍትሔ ያልተበጀላቸው እነዚህ ጥያቄዎች፣ በየዘመናቱ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የትጥቅ ትግልን እንደ ሥልት በሚከተሉ ቡድኖች መካከል ያሠላለፍና የአብሮ መሥራት መነሻ ነጥቦች ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በርካታዎቹ የፖለቲካ ተዋናዮች በዚህ ጉዳይ ላይ ባላቸው የተለያየ አረዳድና አቋም የተነሳም ተለያይተዋል፡፡

  የብሔርና የመደብ ጥያቄ በተለይ ከተማሪዎች እንቅስቀሴ መፋፋምና ከዘውዳዊው ሥርዓተ ሥልጣን መልቀቅ ወዲህ ባለችው ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ፖለቲካዊ ቡድኖች የመመሥረቻና የትግል መሠረታዊ ጥያቄ በመሆን እስካሁን ድረስ ዘልቋል፡፡ በቅርብ ጊዜም ቁርጥ ያለና ሁሉንም ፖለቲካዊ ቡድኖች በሚያስማማ መልኩ መቋጫ የሚያገኝ አይመስልም፡፡

  በርካታ ጽሑፎችና በወቅቱ የፖለቲካ ተዋናይ የነበሩ ግለሰቦች እንደሚገልጹትና በግልጽም እስካሁን ድረስ እንደሚታየው፣ የብሔርና የመደብ ጥያቄ በኢትዮጵያ መሠረታዊ ነገር ግን በተለያዩ አውታሮች የተቃኘ የትግል ሥልት ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል በፖለቲከኞችም ሆነ በምሁራን መካከል ጉዳዩን አስመልክቶ ወጥና ተከታታይነት ያለው አቋም ወይም አተያይ የሌለው፡፡

  የብሔርና የመደብ መብትን ለተመለከተ በተለይ በ1960ዎቹ የነበረው የጉዳዩ አረዳድ በወቅቱ በነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በተለያየ መንገድ እንዲዋቀሩና እንዲደራጁ አስገዳጅ እንደነበር፣ የተለያዩ ጸሐፍት በተለያዩ ጽሑፎች አስታውቀዋል፡፡

  በዚህ በመደብና በብሔር ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ ስማቸው ጎልተው በሚወጡ የአገሪቱ ፖለቲከኞች አንዱና ዋነኛው የቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  በዕለቱ ተጋብዘው የመወያያ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ አንዱ ሲሆኑ፣ ‹‹የመደብና የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የመነሻ ሐሳብ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለኢትጵያዊያን ተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

  ጽሑፉን ከማቅረባቸው በፊት ለምን ጽሑፉን በእንግሊዝኛ እንደሚያቀርቡ ያስረዱት አቶ ሌንጮ፣ ዋነኛ ምክንያታቸውን የገለጹት የአማርኛ ችሎታቸው የሚቀርበውን ውስብስብ ሐሳብ ለማቅረብ ውስን መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

  ሐሳባቸውን በእንግሊዝኛ በማቅረባቸው ይቅርታ የጠየቁት አቶ ሌንጮ፣ በእርሳቸው የፖለቲካ ጅማሮ ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ሻዕቢያና ሕወሓት በመደብና በብሔር ጥያቄ ላይ ያላቸውን አተያይ በመግለጽ ነበር፡፡

  ከዚህም በመነሳት በተለይ ኢሕአፓና መኢሶን ምንም እንኳን የፖለቲካ አተያይና የሶሻሊዝም ትንታኔና አረዳዳቸው የተለያየ ቢሆንም፣ ሁለቱም ግን በጭቆና ሥር የሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው እንዲከበር ይወተውቱ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ በተቃራኒው ሻዕቢያና ኦነግ ደግሞ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ካለው የቅኝ ግዛት ትንታኔ በመነሳት ይሁን በሌላ ምክንያት፣ ጥያቄያቸው የቅኝ ግዛት እንደሆነና ቅኝ ተገዥ የሆነውን ሕዝባቸውን ነፃ ለማውጣት እንደሚታገሉ አስታውቀው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የመኢሶንም ሆነ የኢሕአፓ ጥያቄም ፍላጎትም አልነበረም፡፡

  ከዚህ በተቃራኒ የቆመው ሕወሓት ደግሞ እንደ አቶ ሌንጮ ገለጻ የተለየ መስመር የያዘ ኃይል ነበር፡፡ ሕወሓት ከላይ ከተጠቀሱት ፖለቲካዊ ቡድኖች በተለየ መሪዎቹ የተለየ መስመር እንደተከተሉ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ሕወሓት ይከራከርና ፖለቲካዊ መስመሩን ይገነባ የነበረው በብሔራዊ ጭቆናና ነፃነት ላይ በመመሥረት ነው እንጂ በመደብ ላይ እንዳልነበር ያብራራሉ፡፡

  በዚህም መሠረት በብሔራዊ ጭቆናና ነፃነት ትግል ላይ ትንታኔውን ያደረገው ሕወሓት፣ በሒደት አገር አቀፍ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) በመፍጠር አገሪቱን ለመስተዳደር መብቃቱን ያወሳሉ፡፡

  የዘውዳዊውን ሥርዓት መገለል ተከትሎ የብሔርና የመደብ ጥያቄ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር የተቆጣጠረው ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ የተሰበሰቡ የተለያዩ ኃያሎች ጉዳዩን በተለያየ መነጽር ቢመለከቱትም አሁንም ጥያቄው እንዴት ይፈታ የሚለው፣ እንዲሁም በተጨባጭ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጥያቄ የመደብ ወይም የብሔር የሚለው ግን መንቀዋለል ላይ ያለ ጥያቄ ነው፡፡

  የመደብ ነው ከተባለ የትኛው መደብ ነው የትኛውን የጨቆነው? ግልጽ የሆነ የመደበ ልዩነትስ አለ ወይ? የሚለው፣ እንዲሁም የብሔር ጥያቄ ነው ከተባለ ደግሞ የትኛው ብሔር ጨቋኝ? የትኛው ብሔር ተጨቋኝ ነበር? የሚለው ጥያቄ በግልጽ እስካልተመለሰ ድረስ እንደህ ካለው የፖለቲካ አተካራ በቅርቡ ስለመውጣት አልያም ስለመላቀቅ ምንም መረጋገጫ የለም በማለት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡

  በአገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ በስፋት የሚታወቁት አቶ ሌንጮም ቢሆኑ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት ያከናወኑትን ንባብና ጥናት ሲቋጩ የደረሱበት መደምደሚያ አስገራሚ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  የመደብንና የብሔርን ጥያቄ ከተለያዩ አገሮችና ከማርክሲዝም ዓለም አቀፋዊነት አንፃር፣ እንዲሁም ሌኒንና ሮዛ ፓርክን መሠረት አድርገው ጉዳዩን ተንትነው ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ከተጠቀሱት ትንታኔዎችና አረዳድ በመቀጠል ባደረጉት ጥናትና ምርምር በመጨረሻ የደረሱበት መደምደሚያ፣ በጣም አስፈላጊው ነገር ራስን በራስ ማስተዳደር (Self Determination) ሳይሆን ራስን በራስ የመግለጽ/የራስ ማንነት (Self Identification) መሆኑን አውስተዋል፡፡

  በዚህም መሠረት የራስን በራስ የመግለጽ መብት የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንደ ምክንያት ሲያቀርቡም ይህ መብት ሰብዓዊም ፖለቲካዊም ይዘት ያለው መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

  ሰብዓዊ መብት የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ አንድን ሰው ማንነቱን ነጥቆ አንተ እንዲህ ነህ ማለት፣ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ቁስ አካልነት መቁጠር ነው ብለው፣ ፖለቲካዊ መብት የሚሆነው ደግሞ በአንድ ቡድን ውስጥ ሆኖ በተለያዩ ጉዳዮች ለመሰባሰብ መጀመርያ ራስን በመግለጽ የሚጀምር በመሆኑ ነው ሲሉ፣ ራስን በራስ የመግለጽ መብት መሠረታዊነትን አብራርተዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አንዱ ራስን የመግለጽ መብት አካል ነው በማለት፣ ራስን በራስ የመግለጽ መብት ፈርጀ ብዙ መገለጫዎች ያሉት በመሆኑ ዋናው የመብት ጥያቄ ሊሆን እንደሚገባው ሞግተዋል፡፡

  እንዲህ ያሉ መብቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ ግን ከምንም በላይ የተቋማት መገንባትና መጠናከር መሠረታዊና አስፈላጊ ሁኔታዎች ናቸው ሲሉም፣ በርካቶች የሚሟገቱለትን የተቋማትን መገንባትና መጠናከር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

  ሌላው በዕለቱ የመነሻ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት መምህር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ እሳቸውም ‹‹የህዳጣን ብሔሮችና ማኅበረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

  ወደ ዋነኛው ጉዳይ ከመግባታቸው በፊት በቃሉ ብያኔ ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማንሳት፣ ቃሉ ምን ያህል ለመበየን አስቸጋሪና አጨቃጫቂ እንደሆነ በመጥቀስ ነው፡፡

  ህዳጣን የሚለው ቃል ሕገ መንግሥቱ አናሳ የሚለው ሲሆን፣ ‹‹አናሳ የሚለው ፖለቲካዊ ትክክል ነውን? ተገቢ አይደለም የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ ህዳጣን የሚለውንም የማይቀበሉ አሉ፡፡ በአማርኛ ሁነኛ የሆነና ብዙዎችን የሚያስማማ ቃል ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ ቃሉ አንድና ወጥ የሆነ ብያኔ አልባ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

  በቃሉ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም ጽሑፍ አቅራቢው ግን የህዳጣን መብቶችን አስመልክቶ አሁን ባለው ተጨባጭ የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ ምን ይመስላል? ከዚህ በተጨማሪም የህዳጣን መብት ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ መርሆዎች አንፃር በተግባርና በተጨባጭ የታየው ነገር ምን ይመስላል? እንዲሁም ህዳጣን ሲባል ምን ማለት ነው? ማንስ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክረዋል፡፡

  ምንም እንኳን የቃሉ ብያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ አናሳ ወይም ህዳጣን የሚለው አጨቃጫቂ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን አናሳ (Minority) ለሚለው ቃል በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አንድ ብያኔ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡     ነገር ግን በብዙዎች ጽሑፎች የሚጠቀሰውን የፍራንቺስኮ ኮፓሮቶሪ ብያኔን እንደ መነሻ በመውሰድ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አተያይ አስቀምጠዋል፡፡

  ፍራንቺስኮ ካፓርቶሪ የሕዳጣን መብትን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ሪፖርተር በመሆን ያገለገለ ባለሙያ ሲሆን፣ በእሱ ከያኔ መሠረት ሕዳጣን አራት መሠረታዊ መገለጫዎች አላቸው፡፡

  እነዚህም በቁጥር አናሳ መሆን፣ በበላይነት ሥርዓት ውስጥ የበላይ ያልሆነ፣ በአገረ ማኅበረሰብ ውስጥ ከቀረው ሕዝብ የተለየ ቋንቋ፣ የብሔር ወይም የሃይማኖት ማንነት ያለው ቡድን መሆን፣ እንዲሁም ይህን የተለየ ማንነቱን ለማስቀጠልና ለማስጠበቅ ፍላጎት ያለው ወይም የአብሮነት ስሜት ያለው ቡድን መሆን የሚሉት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  በዚህ መሥፈርት መሠረት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ማነው ህዳጣን? የሚለው አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹት፣ (ዶ/ር) ጌድዮን ‹‹ምክንያቱም ሃይማኖትን ወይም ብሔርን መሠረት አድርገን ከፍራንቺስኮ ካፓሪቶሪ ብያኔ ጋር አያይዘን ብናይ በሚያከራክር ሁኔታ ትልቅ ቁጥር አላቸው የሚባሉትን ጨምሮ፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች በህዳጣን ማዕቀፍ ውስጥ ማየት ይቻላል፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

  ከዚህ ጋር አያይዘውም አንድ ቡድን እንደ ህዳጣን ከተቆጠረ በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች መሠረት ምን ዓይነት መብቶች ሊጎናፀፍ ሊገባ እንደሚችል፣ ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡

  በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች መሠረት ህዳጣንን በተመለከተ በመሠረታዊነት አራት መርሆዎችን ማንሳት እንደሚቻል የሕግ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም ለህልውና ጥበቃና ከለላ የማግኘት የተለየ ማንነትን የማስቀጠልና የማሳደግ፣ እኩልነትን የማረጋገጥና ከአድሏዊነት አሠራር ከለላ የማግኘት፣ እንዲሁም ትርጉም ያለውና ውጤታማ ተሳትፎ የሚሉ መብቶች ናቸው፡፡

  ይህ ዓለም አቀፍ መርህ ሲሆን፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ግን አናሳ ብሔሮች/ቡድኖች በተለየ ሁኔታ ዝርዝር መብቶች እንዳልተቀመጡ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አናሳ የሚለውን ሐረግ የምናገኘው አንድ ንዑስ አንቀጽ ላይ ብቻ ነው፡፡ ምናልባትም ከጀርባ ያለው አስተሳሰብ ሁላችንም በዚያ ጀልባ ላይ ተሳፋሪ ከሆንን፣ ለሁሉም የጋራ የሆኑ የቡድን መብቶችን በተለይም ደግሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ስለተሰጠ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

  በዚህም መሠረት ከላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡት የህዳጣን መብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ባለ ደረጃ እንደሚገኙ ለመግለጽ መምህር ከመሆናቸው አንፃር በግሬድ (በውጤት) ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡

  በመሆኑም ለህልውና በቂ ጥበቃና ከለላ መስጠትን በተመለከተ፣ ‹‹ባለፉት ሦስት ዓመታት የሆነውን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በፊት የነበረውን ስንመለከት ጥቃት እየደረሰብን እየተፈናቀልን ነው፣ ህልውናችን አደጋ ላይ እየወደቀ ነው በሚል ከተለያዩ ብሔሮች በተለያዩ ጊዜያት ሰፋ ያለ አቤቱታ ይሰማ ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹D›› ወይም ‹‹F›› እሰጠዋለሁ፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

  የተለየ ማንነትን ማስቀጠልና ማሳደግን በተመለከተ ግን የብርሃን ጭላንጭል ያለበት እንደሆነ የገለጹ ሰሆን ለዚህም ውጤት ‹‹B›› ሰጥተው አልፈውታል፡፡

  ሌላው ‹‹C›› ወይም ‹‹D›› ያገኘው መለኪያ ደግሞ እኩልትና ከአድሎዊነት ከለላ ማግኘት መብት፣ እንዲሁም ትርጉም ያለው ውጤታማ ተሳትፎ የማድረግ መብትን የተመለከቱት መርሆች ናቸው፡፡

  ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ዋነኛ ማጠንጠኛዎች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ መብቶችን ለማስከበር ሁነኛ መንገድ አለማበጀቱ፣ ሕገ መንግሥቱ የዘረጋው መዋቅር ከመደብ፣ ከፆታና ከሌለች የፍትሕ ጥያቄዎች ይልቅ ለብሔርና ለፍትሕ ይበልጥ ትኩረት መስጠቱንና የመሳሰሉትን እንደ ምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

  በተመሳሳይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በሪሁ ተወልደ ብርሃን፣ ‹‹የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከብሔርና ከመደብ አንፃር›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

  በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ያመጣቸው መሠረታዊ ለውጦች ምንድን ናቸው? የብሔር ጥያቄ ለምንድነው የሕገ መንግሥቱ ማጠንጠኛ የሆነው? በሚሉ ጉዳች ላይ ምልክታቸውን አጋርተዋል፡፡

  የጽሑፎቹ አቅራቢዎች ማብራሪያ ከተሰማ በኋላ በዕለቱ ተሳታፊ የነበሩትን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጨምሮ ሌሎችም ተሳታፊዎች በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ያላቸውን አስተያየትና ጥያቄዎች የሰነዘሩ ሲሆን፣ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡

  - Advertisement -
  - Advertisement -spot_img

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -