Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አገር ሌብነትን የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም!

  ሙስናም ተባለ ኪራይ ሰብሳቢነት ውጤቱ ሌብነት ነው፡፡ ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት መከራ በምታይ አገር ውስጥ ሌብነት ሲስፋፋ የሕዝቡ አኗኗር ይናጋል፡፡ በአገር ሰላምና ደኅንነት ላይ አደጋ ይጋረጣል፡፡ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ገና ከጅምሩ ‹‹ሙስናን የማይሸከም ኅብረተሰብ እንፈጥራለን›› ቢልም፣ ከብልሹ አሠራር ጋር ሰምና ወርቅ የሆነው ሌብነት የአገር አደጋ እየሆነ ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ የመጣው ይህ አስከፊ ተግባር፣ በተለያዩ ገጽታዎች አስፈሪነቱን እያሳየ ነው፡፡ አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አገር በአሁኑ ጊዜ ሌብነትን ለመሸከም የሚችል ጫንቃ ስለሌላት፣ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ ይመለከተኛል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለጉዳዩ ትልቅ ክብደት መስጠት አለባቸው፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮችን እያነሳን እንነጋገራለን፡፡

  ሰሞኑን የዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2007 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት ትልቅ አጽንኦት የተሰጠው፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ አስደንጋጭ የሚባል የሕግ ጥሰት መታየቱ ነው፡፡ ይህ ከዓመት ዓመት አልሻሻል እያለ የመጣ ችግር ቁጣን የሚቀሰቅስ ሲሆን፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት አገርን ምን ያህል አደጋ ውስጥ እንደሚከት ማሳያ ነው፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ ከተጠቀሱት መካከል ዋና ዋናዎቹ በበርካታ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ መገኘት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ከ629 ሚሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰብ፣ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ ከ221 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ፣ ከደንብና መመርያ ውጪ ያላግባብ ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚከናወኑ ግንባታዎች የአማካሪነት ፈቃድ በሌላቸው ለግንባታ አፈጻጸም ማረጋገጫ እየተሰጠ ከ834 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ፣ ወዘተ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት ሙሉ በመሉ ሌብነት ተፈጽሞባቸዋል ለማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በእንዲህ ዓይነቶቹ የተዝረከረኩ አሠራሮች ምን ያህል የአገር ሀብት የሌቦች ሲሳይ ሆኗል? የሚለው ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

  በተጨማሪ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ለአርሶ አደሮች በይፋ መሸጣቸው፣ ከ570 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች መጋዘን ውስጥ ተከማችተው የመጠቀሚያ ጊዜያቸው እንዲያልፍ መደረጉ፣ በንብረትነት ተመዝግበው ሊብሬ ያላቸው ተሽከርካሪዎች የት እንደደረሱ አለመታወቁና የመሳሰሉት የብልሹ አሠራር ውጤቶች ይህችን ደሃ አገር የሚያሳቅቁ ናቸው፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ በሚያቀርባቸው ሪፖርቶቹ በፋይናንስም ሆነ በክንዋኔ ኦዲት ግኝቶቹ፣ የችግሮቹን መጠን ከማሳየቱም በላይ ለዕርምት የሚረዱ ማሳሰቢያዎችንም ይለግሳል፡፡ ነገር ግን በየዓመቱ ምን ጉድ ነው የሚሰማው የሚያስብሉ ሪፖርቶች መቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተዝረከረኩ አሠራሮች የሠፈኑባቸው ተቋማት መብዛት ለፅድቅ ሳይሆን ለኩነኔ ይመስላል፡፡ ባይሆን ኖሮማ የመንግሥት የፋይናንስና የግዢ ሥርዓትን አክብሮ መሥራት ማንን ይገዳል? የኮንትራት ውሎችን በሕጉ መሠረት ማከናወን እያለ ጥሰት መፈጸም ለምን ያስፈልጋል? እንደተባለውም ለሌብነት የሚያመቻቹትን እነዚህ ዝርክርክ አሠራሮች የሚመሩ ሹማምንት ተጠያቂ ቢሆኑ ኖሮ የአገር ሀብት ለአደጋ አይጋለጥም ነበር፡፡ አገር በሌላት አቅምም አትሰቅይም ነበር፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

  ‹‹ሙስናን የማይሸከም…›› ወይም ‹‹ሙስናን የሚፀየፍ…›› ኅብረተሰብ የሚገነባው የአገር ፍቅር ከውስጣቸው የሚነዝራቸው ዜጎች በአንድነት ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን ጠረኑ የማያስጠጋና ክፋት የተፀናወተው የሌብነት ኃይል አገር በመቦጥበጥ ላይ ነው፡፡ ሐሳዊ መሲህ የሆኑ የቀበሮ ባህታውያንን ተገን ያደረገ የጥፋት ኃይል፣ ከሚወድመው የዚህች ደሃ አገር ውስን ሀብት ይልቅ የተንጠለጠለባትን የሌብነት ምሰሶ እንዳይወድቅ ለመታደግ ይውተረተራል፡፡ ‘ልማቱ የፈጠረው ሀብት ቀልብ እየሳበ ስለሆነ በመጠኑም ቢሆን ሙስና ቢኖር አይገርምም’ እየተባለ ከሰሜን አሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከአፍሪካ እስከ እስያ ትንታኔ ይሰጣል፡፡ ይህች አገር እንዲህ ዓይነት መላ ቅጡ የጠፋበት የሌብነት አጀንዳ ለማስተናገድ አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ የላትም፡፡ ከተጠያቂነት በመሸሽ አገርን ለማውደም የሚደረገው ግልብ አስተያየት መቆም አለበት፡፡

  በአገሪቱ የተጀመሩ ልማቶች በታቀደላቸው ጊዜ ተጠናቀው በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በቴሌኮም፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሳሰሉት ዘርፎች መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው ከሌብነት የፀዱ እጆች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ሙስናን የማይሸከሙ›› እና ‹‹ሙስናን የሚፀየፉ›› ዜጎች በእርግጥም የበላይነትን ሲይዙ ነው፡፡ የአገሪቱ ውስን ሀብት ሌቦች ሲመዘብሩት በመኖሪያ ቤት ዕጦት የሚንገላቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ለትምህርት የደረሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ከብት ጠባቂ ሆነው ይቀራሉ፡፡ መዳን በሚችሉ ሕመሞች የሚሰቃዩ ሚሊዮን ወገኖች ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ይደፈርሳል፡፡ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የሚደረገው ትንቅንቅ  በሽንፈት ይጠናቀቃል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይውል የነበረ አዕምሮ ባክኖ ይቀራል፡፡ ከሌብነት የሚገኘው የአገር ውርደትና የሕዝብ መደህየት ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻም የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  አገሪቱ በዓለም አቀፍ ሚዲያው ጭምር አድናቆት የተቸረው ዕድገት በማስመዝገብ የተስፋውን ጎዳና ጀምራለች፡፡ ነገር ግን ይህንን የተስፋ ጉዞ የሚያጨናግፉ የአስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሠራሮች በየቦታው በብዛት ይታያሉ፡፡ እሴት ሳይጨምሩ ሚሊዮኖችን የሚያፍሱ ዘመናዊዎቹ ኮንትሮባንዲስቶችና የአየር በአየር ተዋናዮች ሲበዙ፣ እንኳን የተጀመሩት መሠረተ ልማቶች ሊጠናቀቁ የነበሩትም ይወድማሉ፡፡ ልማቱ ፍትሐዊና ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን የሚፈለግ ከሆነ፣ በኔትወርክ ተሳስረው አገር የሚበጠብጡ ወገኖች በሕግ ሊቆሙ ይገባል፡፡ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በአገልግሎት መስጫዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ የጥፋት ኃይሎች አገር ሲበዘብዙ ዝም ብሎ መመልከት የጥፋቱ ተባባሪ መሆን ነው፡፡ ‘ተጠያቂነት ስለሌለባቸው ከዓመት ዓመት የሕግ ጥሰት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል’ ተብሎ በምሬት ሪፖርት ሲቀርብ መልሱ ዝምታ ከሆነ፣ ራስን በራስ ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም፡፡

  በአጠቃላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት የምንሰማቸው የመንግሥት ጨረታዎች፣ ግዢዎች፣ ኮንትራቶች በፋይናንስ ሕግ ጥሰቶችና በብልሹ አሠራሮች ሲተበተቡ አገር የሚያስደነግጡ ናቸው፡፡ የደሃ አገር ሀብት በማናለብኝ ባዮች ሲዘረፍ ኧረ በሕግ ማለት ከአገር ወግና ልማድነት በላይ ባህል መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ የሥልጣን የመጨረሻ አካል የሆነው ፓርላማ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የፓርላማ አባላት ታማኝነት ለአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ ለወከላቸው ሕዝብና ለህሊናቸው እስከሆነ ድረስ ፓርላማው ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ ሚዲያውን ከጎኑ ማሠለፍ ይኖርበታል፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተግባሩን በሕጉ መሠረት ብቻ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው፣ ቁጥጥሩ ጠበቅ ሲልበትና በሚዲያው ዕይታ ውስጥ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም የታወቀ አሠራር ነው፡፡ የሙስና ምንጭ የሚደርቀው በቁርጠኝነት የሚጠይቅ አካል ሲኖርና ከሙስና በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች ሲጋለጡ ብቻ ነው፡፡ አገሪቱም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሙስናን የምትሸከምበት ጫንቃ እንደሌላት ሊታወቅ ይገባል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጭራ አናድርጋት!

  ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የልማት መስኮች አንገቷን ቀና የምታደርግባቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆናቸው ያበረታታል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...